የደስታችሁ ምክንያት ምንድን ነው?
1. በእያንዳንዱ ወር መጨረሻ ላይ ለደስታችን ምክንያት የሚሆነው ምንድን ነው?
1 በወሩ መጨረሻ ላይ ሁላችንም የመስክ አገልግሎት ሪፖርታችንን እንድንመልስ እንጠየቃለን፤ በዚህ ጊዜ እያንዳንዳችን ለደስታ ምክንያት የሚሆነን ምንድን ነው? በአገልግሎት 130 ሰዓት የምናሳልፍ ልዩ አቅኚዎችም ሆንን የ15 ደቂቃ ድምሮችን ሪፖርት እንድናደርግ የተፈቀደልን አስፋፊዎች፣ ሁላችንም ለይሖዋ የሙሉ ነፍስ አገልግሎት በማቅረባችን መደሰት ይገባናል።—መዝ. 100:2
2. በይሖዋ አገልግሎት በትጋት መካፈል የሚኖርብን ለምንድን ነው?
2 ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ እንደመሆኑ መጠን ምርጣችንን ልንሰጠው ይገባል። (ሚል. 1:6) ፈቃዱን ለማድረግ ራሳችንን የወሰነው ለእሱ ካለን ፍቅር የተነሳ ነው። በመሆኑም ከጊዜያችን፣ ከችሎታችንና ከጉልበታችን ‘በኵራቱን’ ለይሖዋ አገልግሎት እንዳዋልነው እርግጠኞች ከሆን በእያንዳንዱ ቀን ወይም ወር መጨረሻ ላይ በግለሰብ ደረጃ ለደስታ ምክንያት የሚሆን ነገር እናገኛለን። (ምሳሌ 3:9) በሌላ በኩል ግን ሕሊናችን በዚህ ረገድ የተሻለ ማድረግ እንደምንችል የሚነግረን ከሆነ ሁኔታውን ለማስተካከል ምን ማድረግ እንደምንችል ቆም ብለን ማሰባችን አስፈላጊ ነው።—ሮም 2:15
3. ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደሩ ጥበብ ያልሆነው ለምንድን ነው?
3 “ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያነጻጽር”፦ ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማነጻጸሩም ሆነ የተሻለ አቅም የነበረንን ጊዜ በማስታወስ ራሳችንን መኮነኑ የጥበብ አካሄድ አይደለም። ሁኔታዎች ይለዋወጣሉ። ሰዎች ያላቸው አቅምም ቢሆን የተለያየ ነው። ራስን ከሌሎች አሊያም በፊት ከነበረን አቋም ጋር ማነጻጸር አብዛኛውን ጊዜ ወደ ፉክክር ሊያመራን አሊያም የዋጋ ቢስነት ስሜት እንዲያድርብን ሊያደርግ ይችላል። (ገላ. 5:26፤ 6:4) ኢየሱስ ሰዎችን አያወዳድርም ነበር። ከዚህ ይልቅ አቅማቸውን መሠረት በማድረግ ያመሰግናቸው ነበር።—ማር. 14:6-9
4. ኢየሱስ ስለ ታላንት ከተናገረው ምሳሌ ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?
4 ኢየሱስ ስለ ታላንት በተናገረው ምሳሌ ላይ እያንዳንዱ ሠራተኛ ታላንት የተሰጠው “እንደ ችሎታው” መጠን መሆኑን ተናግሯል። (ማቴ. 25:15) ጌታው ሲመለስ ሠራተኞቹ ስላከናወኑት ሥራ ሪፖርት እንዲያቀርቡ የጠየቃቸው ሲሆን አቅማቸውና ሁኔታቸው በፈቀደላቸው መጠን በትጋት የሠሩትን ሁሉ አመሰገናቸው፤ ወደ ጌታቸው ደስታ እንዲገቡም ጋበዛቸው። (ማቴ. 25:21, 23) እኛም በተመሳሳይ የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ በትጋት የምንካፈል ከሆነ የይሖዋን ሞገስ ብሎም ለመደሰት የሚያበቃ ምክንያት እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።