ነቢያትን አርዓያ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው—ኢዩኤል
1. በምንሰብክበት ወቅት የኢዩኤል ዓይነት ትሕትና እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
1 ነቢዩ ኢዩኤል ማን ነው? ኢዩኤል ስለ ራሱ የተናገረው ነገር ቢኖር ‘የባቱኤል ልጅ’ እንደሆነ ብቻ ነው። (ኢዩ. 1:1) የይሖዋ መልእክተኛ የሆነው ይህ ትሑት ነቢይ ትኩረት ያደረገው ባገኘው መብት ላይ ሳይሆን ከይሖዋ በመጣው መልእክት ላይ ነበር። እኛም በአገልግሎት ላይ ስንሆን ለራሳችን ውዳሴ ወይም እውቅና ለማግኘት ጥረት ከማድረግ ይልቅ የሰዎች ትኩረት በይሖዋና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲያርፍ እናደርጋለን። (1 ቆሮ. 9:16፤ 2 ቆሮ. 3:5) በተጨማሪም የምንሰብከው መልእክት የብርታት ምንጭ ይሆንልናል። ቅንዓታችን እንዲቀጣጠልና ተስፋችን ብሩሕ ሆኖ እንዲታየን የሚያደርገው የትኛው የኢዩኤል ትንቢት ገጽታ ነው?
2. የይሖዋ ቀን መቅረቡ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?
2 ‘የይሖዋ ቀን ቀርቦአል።’ (ኢዩ. 1:15)፦ እነዚህ ቃላት ከተጻፉ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ቢያልፉም እኛ የምንኖረው ይህ ትንቢት የመጨረሻውን ፍጻሜ በሚያገኝበት ጊዜ ላይ ነው። በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱና በክልላችን ያሉ ሰዎች ቸልተኞችና ፌዘኞች መሆናቸው የዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ እንደቀረበ የሚጠቁሙ ግልጽ ማስረጃዎች ናቸው። (2 ጢሞ. 3:1-5፤ 2 ጴጥ. 3:3, 4) መጨረሻው ምን ያህል እንደቀረበ ማሰላሰላችን ከምንም ነገር በላይ ለአገልግሎታችን ቅድሚያ እንድንሰጥ ያነሳሳናል።—2 ጴጥ. 3:11, 12
3. ወደ ታላቁ መከራ እየቀረብን ስንሄድ ለአገልግሎታችን ቅድሚያ መስጠታችን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
3 ‘ይሖዋ ለሕዝቡ መሸሸጊያ ይሆናል።’ (ኢዩ. 3:16)፦ እዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጸው መናወጥ ሊያመለክት የሚችለው ይሖዋ በታላቁ መከራ ወቅት የሚያስፈጽመውን የቅጣት ፍርድ መሆን ይኖርበታል። በዚያ ወቅት ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚያድናቸው ማወቃችን በጣም ያጽናናናል። (ራእይ 7:9, 14) በስብከቱ ሥራ ላይ መሳተፋችን ይሖዋ የሚደግፈንና ብርታት የሚሰጠን እንዴት እንደሆነ ለመመልከት ያስችለናል፤ ይህ ደግሞ በቅርቡ በሚመጣው በታላቁ መከራ ወቅት በጣም አስፈላጊ የሆኑትን ባሕርያት ማለትም እምነትንና ጽናትን እንድናዳብር ይረዳናል።
4. ደስተኛ የምንሆነውና የወደፊቱን ጊዜ በእምነት የምንጠባበቀው ለምንድን ነው?
4 የኢዩኤል መልእክት ለአንዳንዶች አስፈሪ መስሎ ቢታያቸውም ለአምላክ ሕዝቦች ግን አስደናቂ የመዳን ተስፋ የሚፈነጥቅ ነው። (ኢዩ. 2:32) እንግዲያው “ደስ ይበላችሁ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር፣ ሐሤት አድርጉ” የሚለውን በኢዩኤል 2:23 ላይ የተገለጸውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ በማድረግ የወደፊቱን ጊዜ በእምነት እንጠባበቅ፤ እንዲሁም ምሥራቹን በቅንዓት እናውጅ።