የአቀራረብ ናሙናዎች
በወሩ የመጀመሪያ ቅዳሜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚረዳ አቀራረብ
“ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል በሆነ ወቅት ላይ ጸሎት ያቀርባል። በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎችም እንኳ ችግር ሲያጋጥማቸው ይጸልያሉ። ታዲያ አምላክ ሁሉንም ጸሎቶች ይሰማል ብለው ያስባሉ?” ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው። የነሐሴ 1ን መጠበቂያ ግንብ ስጠውና በመጨረሻ ገጽ ላይ ያለውን ዓምድ አሳየው። ከዚያም በመጀመሪያው ጥያቄ ሥር ባለው ሐሳብ ላይ እና በዚያ ውስጥ ከተጠቀሱት ጥቅሶች መካከል ቢያንስ በአንዱ ላይ ተወያዩ። መጽሔቶቹን ካበረከትክለት በኋላ በሚቀጥለው ጥያቄ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።
ማሳሰቢያ፦ ይህ የመግቢያ ሐሳብ በወሩ የመጀመሪያ ቅዳሜ በሚደረገው የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ በሠርቶ ማሳያ መልክ መቅረብ ይኖርበታል።
መጠበቂያ ግንብ ነሐሴ 1
“እዚህ የመጣነው በአንድ ጉዳይ ላይ አጠር ያለ ውይይት ለማድረግ ነው። የብልግና ምስሎች መስፋፋት ብዙ ሰዎችን እያሳሰበ ነው፤ ሌሎች ደግሞ የብልግና ምስሎች ምንም ጉዳት የማያስከትሉ ጊዜ ማሳለፊያዎች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። እርስዎስ ስለዚህ ጉዳይ ያለዎት አመለካከት ምንድን ነው? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ኢየሱስ አንድ ነገር ጥሩነቱ የሚታወቀው በሚያፈራው ፍሬ እንደሆነ ተናግሯል። [ማቴዎስ 7:17ን አንብብ።] ይህ መጽሔት የብልግና ምስሎችን መመልከት ያስከተለውን ውጤት ያብራራል። በተጨማሪም የብልግና ምስሎችን ከመመልከት ልማድ ለመላቀቅ የሚረዱ ጠቃሚ ሐሳቦችን ይዟል።”
ንቁ! ነሐሴ
“ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል ረጅም ዕድሜ ቢኖር ደስ ይለዋል። በሳይንሱ መስክ የሚታየው እድገት ለዘላለም ለመኖር የሚያስችል መፍትሔ የሚያስገኝ ይመስልዎታል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] እስቲ ይህን ትኩረት የሚስብ ተስፋ ይመልከቱ። [1 ቆሮንቶስ 15:26ን አንብብ።] ታዲያ አምላክ ይህ ተስፋ ፍጻሜውን እንዲያገኝ የሚያደርገው እንዴት ነው? በሳይንሳዊ ምርምሮች አማካኝነት ነው ወይስ በሌላ መንገድ? የምናረጀውና የምንሞተውስ ለምንድን ነው? ይህ መጽሔት መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ ይዟል።”