ነቢያትን አርዓያ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው—ሆሴዕ
1. የትኛውን ጥያቄ ራሳችሁን ጠይቃችሁ ሊሆን ይችላል?
1 ‘ለይሖዋ ስል እስከ ምን ድረስ መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ነኝ?’ ምናልባት ወደር ስለሌለው የይሖዋ ጥሩነትና ምሕረት በምታሰላስሉበት ጊዜ ይህን ጥያቄ ለራሳችሁ ጠይቃችሁ ሊሆን ይችላል። (መዝ. 103:2-4፤ 116:12) ሆሴዕ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ ቢጠይቅበትም እንኳ ይሖዋ ያዘዘውን በፈቃደኝነት ፈጽሟል። ታዲያ የሆሴዕን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
2. በስብከቱ ሥራ በመጽናት ረገድ የሆሴዕን ግሩም ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
2 በአስቸጋሪ ወቅት ስበኩ፦ ሆሴዕ በዋነኝነት መልእክቱን ያወጀው በእስራኤል መንግሥት ውስጥ ለሚገኙ አሥሩ ነገዶች ነው፤ በዚያም ንጹሑ አምልኮ ሊጠፋ ተቃርቦ ነበር። ንጉሥ ዳግማዊ ኢዮርብዓም በይሖዋ ፊት ክፉ ነገር ያደረገ ሲሆን ቀዳማዊ ኢዮርብዓም ያስጀመረውን የጥጃ አምልኮ አስፋፍቷል። (2 ነገ. 14:23, 24) ከዳግማዊ ኢዮርብዓም በኋላ የተነሱት ነገሥታትም ቢሆኑ አሥሩ ነገዶች በ740 ዓ.ዓ. እስከጠፉበት ጊዜ ድረስ ሕዝቡ በመንፈሳዊ እያዘቀጠ እንዲሄድ አድርገዋል። የሐሰት አምልኮ ይህን ያህል የተስፋፋ ቢሆንም እንኳ ሆሴዕ ቢያንስ ለ59 ዓመታት ታማኝ ነቢይ ሆኖ አገልግሏል። እኛስ የሰዎችን ግዴለሽነትና ተቃውሞ ተቋቁመን ከዓመት እስከ ዓመት በስብከቱ ሥራ ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል?—2 ጢሞ. 4:2
3. የሆሴዕ ሕይወት ይሖዋ ላሳየው ምሕረት ተምሳሌት የሚሆነው እንዴት ነው?
3 በይሖዋ ምሕረት ላይ አተኩሩ፦ ይሖዋ ሆሴዕን “አመንዝራ ሴት” እንዲያገባ አዝዞት ነበር። (ሆሴዕ 1:2) ሚስቱ ጎሜር ለሆሴዕ ወንድ ልጅ የወለደችለት ቢሆንም እንኳ ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው በኋላ ላይ ሁለት ልጆችን ከሌላ ሰው ሳትወልድ አልቀረችም። ሆሴዕ ይቅር ባይ ለመሆን ያሳየው ፈቃደኝነት ይሖዋ ከዳተኛይቱ እስራኤል ንስሐ ስትገባ ላሳየው ታላቅ ምሕረት ተምሳሌት ነበር። (ሆሴዕ 3:1፤ ሮም 9:22-26) እኛስ የይሖዋን ምሕረት ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ለማሳወቅ የግል ፍላጎታችንን ወይም ምርጫችንን ወደ ጎን ለማድረግ ፈቃደኞች ነን?—1 ቆሮ. 9:19-23
4. ለይሖዋ ስንል የምንከፍላቸው አንዳንድ መሥዋዕቶች የትኞቹ ናቸው?
4 አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች በአገልግሎት ሰፋ ያለ ጊዜ ለማሳለፍ ሲሉ ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ትተዋል። ሌሎች ደግሞ የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማራመድ ሲሉ በነጠላነት ለመኖር ወይም ልጆችን ላለመውለድ ወስነዋል። በሆሴዕ ሕይወት ላይ ስናሰላስል ‘እኔ መቼም እንዲህ ማድረግ አልችልም’ ብለን እናስብ ይሆናል። ይሁንና ለይሖዋ ጸጋ ያለን አድናቆት እያደገ ሲሄድና ኃይል ለማግኘት በቅዱስ መንፈሱ ስንታመን ልክ እንደ ሆሴዕ ጨርሶ ይሆናል ብለን ባላሰብነው መንገድ ይሖዋ ሊጠቀምብን ይችላል።—ማቴ. 19:26፤ ፊልጵ. 2:13