‘ሕዝቡን ሰብስብ’
1. የአውራጃና ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች፣ እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆዩ ካደረጉት ታሪካዊ ስብሰባ ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?
1 እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ፣ በሲና ተራራ ‘ሕዝቡን እንዲሰበስብ’ ሙሴን አዞት ነበር፤ ይሖዋ ይህን ያደረገበት ምክንያት ሕዝቡ የእሱን ቃል በመስማት አምላክን እንዲፈሩና ለልጆቻቸውም የእሱን መንገድ እንዲያስተምሩ ነው። (ዘዳ. 4:10-13) ይህ ስብሰባ የማይረሳና እምነት የሚያጠናክር እንደነበር ጥርጥር የለውም! በቀጣዮቹ ወራት የይሖዋ ሕዝቦች ከእሱ ለመማር የአውራጃና ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ያደርጋሉ። ታዲያ ከእነዚህ ስብሰባዎች የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
2. በቅርቡ ለምናደርገው ትልቅ ስብሰባ ‘መዘጋጀት’ የምንችለው እንዴት ነው?
2 ‘ተዘጋጁ’፦ ይሖዋ፣ እስራኤላውያንን በሲና ተራራ ለሚያደርጉት ታሪካዊ ስብሰባ ‘እንዲዘጋጁ’ አዟቸው ነበር። (ዘፀ. 19:10, 11) በተመሳሳይም በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ክፍል እንዲያቀርቡ መብት የተሰጣቸው ብቻ ሳይሆኑ በስብሰባው ላይ የሚገኙ ሁሉ አስቀድመው በደንብ መዘጋጀታቸው አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙዎች ከሰብዓዊ ሥራቸው እረፍት መውሰድ ያስፈልጋቸዋል። ምናልባትም እናንተ ያላችሁበት ሁኔታ ከነህምያ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። የንጉሥ አርጤክስስ ጠጅ አሳላፊ የነበረው ነህምያ የኢየሩሳሌምን ግንብ እንደገና በመገንባቱ ሥራ ለመካፈል ሲል ከሥራው ፈቃድ መጠየቅ ነበረበት፤ ይሁን እንጂ ንጉሡ ላይፈቅድለት እንደሚችል ያውቅ ነበር። ነህምያ ከጸለየ በኋላ በድፍረት ሆኖም አክብሮት በሞላበት መንገድ ለንጉሡ ጥያቄውን አቀረበ። ንጉሡ እንዲሄድ የፈቀደለት ከመሆኑም በላይ ለግንባታ ሥራው ድጋፍ አድርጓል! (ነህ. 2:1-9) አሠሪያችሁን ፈቃድ ከመጠየቅ በተጨማሪ ከመጓጓዣና ከማረፊያ ቦታ ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጋችኋል? ሽማግሌዎች፣ በዚህ ረገድ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ለማገዝ ዝግጁዎች ናቸው። በሁሉም ቀናት ቀደም ብላችሁ ለመድረስ ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም ለምትሰሟቸው ነገሮች “ከወትሮው የተለየ ትኩረት” ስጡ።—ዕብ. 2:1
3. ለስብሰባው ልባችንን ለማዘጋጀት ምን ማድረግ እንችላለን?
3 ዝግጅት የምናደርግበት ሌላው አቅጣጫ ደግሞ ለማዳመጥና ለመማር ልባችንን ማዘጋጀት ነው። (ዕዝራ 7:10 የ1954 ትርጉም) የስብሰባው ፕሮግራም አስቀድሞ jw.org/am በተባለው ድረ ገጽ ላይ ይወጣል፤ በፕሮግራሙ ላይ የንግግሮቹ ርዕሶችና እያንዳንዱ ርዕስ የተመሠረተበት አንድ ወይም ሁለት ቁልፍ ጥቅስ ይገኛል። ስብሰባው ከመካሄዱ በፊት ባሉት የተወሰኑ ሳምንታት በቤተሰብ አምልኳችሁ ላይ በፕሮግራሙ ላይ ብትወያዩ ጥቅም እንደምታገኙ ጥርጥር የለውም። አንዳንድ አስፋፊዎች ፕሮግራሙን በማተም በስብሰባው ወቅት አጭር ማስታወሻ ለመያዝ ይጠቀሙበታል።
4. ወላጆች ስብሰባውን በመጠቀም ልጆቻቸውን ማስተማር የሚችሉት እንዴት ነው?
4 ‘ልጆቻችሁን አስተምሩ’፦ በሲና ተራራ የተደረገው ስብሰባ አንዱ ዓላማ እስራኤላውያን ወላጆች ‘ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ’ ነው። (ዘዳ. 4:10) መጪው ስብሰባ ወላጆች ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንዲችሉ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል። ስብሰባው በሚካሄድበት ወቅት ወላጆች፣ ልጆቻቸው አብረዋቸው እንዲቀመጡ ማድረግና በትኩረት እንዲከታተሉ መርዳት ይኖርባቸዋል። በእያንዳንዱ የስብሰባው ዕለት ማታ ላይ እንዲሁም በቤተሰብ አምልኳቸው ወቅት ትምህርቱን በቤተሰብ ሊወያዩበት ይችላሉ።
5. በመጪው ስብሰባ ላይ መገኘታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
5 በሲና ተራራ ላይ የተደረገው ታሪካዊ ስብሰባ፣ እስራኤላውያን የይሖዋ ሕዝብ የመሆን ልዩ መብታቸውን እንዲያደንቁ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። (ዘዳ. 4:7, 8) ከፊታችን ያለው ትልቅ ስብሰባም ተመሳሳይ ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ ይሆናል። በመንፈሳዊ ምድረ በዳ ከሆነው የሰይጣን ዓለም ለሦስት ቀናት በመራቅ በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ማበረታቻ እናገኛለን፤ እንዲሁም ከወንድሞችና እህቶች ጋር የሚያንጽ ጊዜ እናሳልፋለን። (ኢሳ. 35:7-9) የይሖዋ ቀን እየቀረበ እንደመሆኑ መጠን እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችለንን ይህን ስብሰባ ፈጽሞ ቸል ልንለው አይገባም።—ዕብ. 10:24, 25