አዲሶቹ ትራክቶች ያላቸው ማራኪ ገጽታ!
1. አዲስና ማራኪ ገጽታ እንዲኖራቸው ተደርገው የተዘጋጁት በአገልግሎት ላይ የምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች የትኞቹ ናቸው?
1 በ2013 ባደረግነው “የአምላክ ቃል እውነት ነው!” የተሰኘ የአውራጃ ስብሰባ ላይ አምስት አዳዲስ ትራክቶች አግኝተናል። “የሞቱ ሰዎች እንደገና በሕይወት መኖር ይችላሉ?” የሚል ርዕስ ያለው የመንግሥት ዜና ቁጥር 38ም በመደበኛነት ከምናበረክታቸው ትራክቶች መሃል ሆኗል። ስድስቱም ትራክቶች አዲስና ማራኪ ገጽታ አላቸው። በምንጠቀምባቸው ትራክቶች ገጽታ ላይ ለውጥ የተደረገው ለምንድን ነው? ከቤት ወደ ቤት በምናደርገው አገልግሎት ላይ ትራክቶቹ ያሏቸውን ገጽታዎች በጥሩ መንገድ ልንጠቀምባቸው የምንችለውስ እንዴት ነው?
2. የምንጠቀምባቸው ትራክቶች አዲስ ገጽታ እንዲኖራቸው የተደረገው ለምንድን ነው?
2 አዲስ ገጽታ እንዲኖራቸው የተደረገው ለምንድን ነው? ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል የምንጠቀምበት አቀራረብ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ ብዙውን ጊዜ የሚከተሉትን አራት ነገሮች ማድረግ አለብን፦ (1) ውይይት ለመጀመር የአመለካከት ጥያቄ መጠየቅ። (2) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማንበብ። (3) ጽሑፎችን ለምናነጋግረው ሰው ማበርከት። (4) በሚቀጥለው ጊዜ ልንወያይበት የምንችለውን አንድ ጥያቄ ካነሳን በኋላ ቀጥሮ መያዝ። ትራክቶቹ ያላቸው አዲስ ገጽታ እነዚህን አራት ነገሮች ቅደም ተከተላቸውን በጠበቀ መልኩ በቀላሉ ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳናል።
3. አዳዲሶቹን ትራክቶች ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?
3 እንዴት ልንጠቀምባቸው እንችላለን? (1) ሰላምታ ከሰጣችሁ በኋላ ለምታነጋግሩት ሰው በትራክቱ የፊት ገጽ ላይ ያለውን ትኩረት የሚስብ ጥያቄ ጠይቁት፤ ከዚያም የቀረቡትን አማራጭ መልሶች በማሳየት ሐሳብ እንዲሰጥ ጋብዙት። (2) ትራክቱን በመግለጥ “መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?” በሚለው ሥር ያለውን ጥቅስ ተወያዩበት። ሁኔታው አመቺ ከሆነ ጥቅሱን በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንብቡለት። የምታነጋግሩት ሰው ጊዜ ካለው “ይህን ማወቅህ ለአንተ ምን ጥቅም አለው?” በሚለው ላይ ተወያዩ። (3) ትራክቱን አበርክቱለትና የተቀረውን ሐሳብ በሚያመቸው ጊዜ እንዲያነብበው አበረታቱት። (4) ከመለያየታችሁ በፊት በጀርባ ገጹ ላይ በሚገኘው “ምን ይመስልሃል?” በሚለው ሥር ያለውን ጥያቄ አሳዩትና መጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄው በሚሰጠው መልስ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዙ።
4. አዳዲሶቹን ትራክቶች ተጠቅመን ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
4 ትራክቶቹን ተጠቅሞ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግም ቀላል ነው። ግለሰቡን መጀመሪያ ጊዜ ስታነጋግሩት በውይይታችሁ መደምደሚያ ላይ ላነሳችሁለት ጥያቄ መልስ ለመስጠት በትራክቱ የጀርባ ገጽ ላይ ያሉትን ጥቅሶች ተጠቀሙ። ከመለያየታችሁ በፊት ምሥራች የተባለውን ብሮሹር ፎቶግራፍ ከትራክቱ ላይ አሳዩት፤ ከዚያም ብሮሹሩን አውጥታችሁ፣ ስለተወያያችሁበት ጉዳይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሚሰጠውን ትምህርት አሳዩትና ብሮሹሩን አበርክቱለት። ብሮሹሩን ከወሰደ፣ በሚቀጥለው ጊዜ በብሮሹሩ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዙ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጀመራችሁ ማለት ነው! ወይም ደግሞ ብሮሹሩን ከመስጠት ይልቅ ሌላ ትራክት ልታበረክቱለት ትችላላችሁ፤ ከዚያም በትራክቱ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ያዙ።
5. ትራክቶች ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ ምን ድርሻ ያበረክታሉ?
5 ከ130 ለሚበልጡ ዓመታት ትራክቶችን በአገልግሎት ስንጠቀም ቆይተናል። መጠናቸውና ገጽታቸው የሚቀያየርበት ጊዜ ቢኖርም ምሥክርነት ለመስጠት ውጤታማ መሣሪያ ሆነው አገልግለዋል። እኛም የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት በዓለም ዙሪያ ማስፋፋታችንን ለመቀጠል ትራክቶቹ ያላቸውን አዲስ ገጽታ ጥሩ አድርገን እንጠቀም።—ምሳሌ 15:7ሀ