ትራክቶች በዛሬው ጊዜ ለምናደርገው አገልግሎት በጣም ጠቃሚ የሆኑት ለምንድን ነው?
1 በጥር 1, 1991 የመጠበቂያ ግንብ እትም በገጽ 30 ላይ “አንድ ትንሽ ጽሑፍ በመንገድ ላይ አገኘ” በሚል ርዕስ ሥር አንድ ተሞክሮ ወጥቶ ነበር። ተሞክሮው የባቡር ሃዲድ መስመር ጥገና ተቆጣጣሪ የሆነ አንድ ሰው ከትራክቶቻችን አንዱን በሃዲዱ መሀል ተጣብቆ እንዳገኘ ይናገራል። ትራክቱን ወዲያውኑ አነበበና ለልጁ ባል “ዛሬ እውነትን አገኘሁ!” አለው። ሁለቱም ሰዎች ተጨማሪ ጽሑፎችን አዘዙና አጠኑአቸው። አሁን ከአንድ መቶ በላይ የሆኑ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው በእውነት ውስጥ ናቸው። ይህ ተሞክሮ አንድ ትራክት ብቻ በማንበብ ምን ዓይነት ውጤት ሊገኝ እንደሚችል ያሳያል።
2 በአጋጣሚዎች ሁሉ መጠቀም፦ በየትም ቦታ የሚገኙ ወንድሞች ትራክት ለማበርከት በሚያስችሏቸው አጋጣሚዎች ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። አንዲት ወጣት ምስክር አስተማሪዋ የባልዋ እናት በመሞታቸው ምክንያት በጣም እንዳዘነች ተመለከተች። ወጣቷ እህት ለአስተማሪዋ የሚያጽናና ደብዳቤ ጻፈችላትና ከደብዳቤው ጋር እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ምን ተስፋ አላቸው? የሚለውን ትራክት ጨምራ ላከችላት። አስተማሪዋ አጭር የምስጋና ደብዳቤ ከጻፈችላት በኋላ ወጣቷን እህታችንን አነጋገረቻት። አሁን ይህች አስተማሪ አዘውትራ መጽሔቶችን ከእሷ ትወስዳለች።
3 አንዳንድ አስፋፊዎች ወደ መቃብር ቦታ በሚወስድ መንገድ ላይ ሲያገለግሉ መቃብሮችን የሚያሳምሩ ሰዎች ተመለከቱ። አስፋፊዎቹ አጋጣሚውን ትራክቶች ለማበርከት ተጠቀሙበት። የሚቀጥለው ቀን ብዙ ሰዎች የመቃብሩን ቦታ የሚጎበኙበት የበዓል ቀን ስለነበረ አስፋፊዎቹ ወደ መቃብሩ ቦታ በሚያስገባው በር ላይ ቆመው ትራክቶችን ለማበርከት ወሰኑ። ሦስት ሰዎች ብቻ አንፈልግም ሲሉ ከአምስት መቶ በላይ ትራክቶች ተበረከቱ። በሚቀጥለው ዓመት ከአንድ ሺህ በላይ ትራክቶች ሲያበረክቱ ስድስት ሰዎች ብቻ ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም። ብዙ ሰዎች የተሰማቸውን ጥልቅ አድናቆት ገልጸዋል። ከእነርሱም አንዱ እየሄደ ትራክቱን አነበበው። ጥቂት ቆይቶ ተመልሶ መጣና ትራክቱን ያበረከተችለትን እህት አነጋገራት። “ይህ ጽሑፍ የያዘውን መልእክት እንዲያነብ የምፈልገው ሰው አለ። ሌላ ተጨማሪ ማግኘት እችላለሁ?” አላት።
4 ትራክቶችን በቀላሉ የትም ቦታ ይዘናቸው ለመሄድ እንችላለን። ከማናውቃቸውም ይሁን ከምናውቃቸው ሰዎች ጋር መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስንነጋገር ከተዘጋጁት አራት ትራክቶች በአንዱ ወደ መወያየት የሚያመራ አጭር ሐሳብ ጣል ለማድረግ መጣር አለብን። ከጎረቤቶቻችን ጋር ስንነጋገር፣ ገበያ ስንሄድ ወይም ሰው ስንጠብቅ፣ ዘመዶቻችንን ስንጠይቅ ወይም በሌሎች ብዙ ሁኔታዎች ይህን ማድረግ እንችላለን።
5 ትራክቶች ውጤታማ የሆኑበት ምክንያት፦ ትራክቶቹ በማራኪ ቀለማት የተዋቡ ናቸው። አጠር ያለ አቀራረብ አላቸው። የቤት ባለቤቶችና መደበኛ ባልሆነ መንገድ የምናገኛቸው ሰዎች ብዙ እንዲያነቡ የሚያስገድዱ ባለመሆናቸው አይጨንቃቸውም። ይሁን እንጂ መልእክቱ ስሜት የሚስብና እውቀት የሚጨምር ነው። አንባቢው በትራክቱ ውስጥ ለተገለጸው ነጥብ ግልጽ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ አመለካከት ያገኛል። ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት የተባለውን ትራክት ከተቀበለና አብረው ከተወያዩበት በኋላ አንድ ወጣት እንዲህ በማለት አድናቆቱን ገለጸ:- “የዓለምን ሁኔታ በሚመለከት እንደዚህ ያለ የሚያበረታታ ትምህርት ሰምቼ አላውቅም።”
6 እነዚህን ትራክቶች በማንኛውም ተገቢ ወቅት ላይ ልንጠቀምባቸው እንፈልጋለን። ብዙ አስፋፊዎች ከቤት ወደ ቤት በሚያደርጉት የስብከት ሥራቸው ትራክቶቹ ውይይት ለመክፈት የሚረዱ ጠቃሚ መሣሪያዎች ሆነው አግኝተዋቸዋል። በአሁኑ ጊዜ በመመራት ላይ ያሉት ብዙ ጥናቶች የተጀመሩት በትራክት አማካኝነት ነው። በዚህኛው የመንግሥት አገልግሎታችን ዕትም በገጽ 4 ላይ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት በትራክቶች መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳዩ ተግባራዊ የሚሆኑ ሐሳቦች ተሰጥተዋል። አዎን፣ ትራክቶች ትንንሾች ቢሆኑም ለአገልግሎታችን ግን ጠቃሚ የሆኑ መሣሪያዎች ናቸው።