ውይይት ለመጀመር በትራክቶች ተጠቀሙ
1 ውጤታማ ምስክርነት መስጠትህ በአብዛኛው የተመካው ቀዳሚ ሆነህ ውይይት መጀመር በመቻልህ ላይ ነው ቢባል አትስማማም? ፈታኝ የሆነው ነገር የሰውዬውን ትኩረት ማርኮ ወደ ውይይት ሊያስገባ የሚችል ነገር መናገሩ ነው። ታዲያ ይህንን በተሳካ መንገድ ማከናወን የሚቻለው እንዴት ነው?
2 ብዙ አስፋፊዎች የታሰበባቸው ጥቂት ቃላት ተናግረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሠረቱት ትራክቶቻችን መካከል አንዱን እንዲወስድ በመጋበዝ ውይይት መጀመር ችለዋል። ርዕሶቻቸው ማራኪ ሲሆኑ ሥዕሎቻቸው ደግሞ በቀለማት ያጌጡና ቀልብ የሚስቡ ናቸው። ትራክቱ ብዙ የሚነበብ ነገር ስለሌለው ገና ከጅምሩ ሰውዬውን ተስፋ የሚያስቆርጠው አይሆንም። ቢሆንም እጥር ምጥን ያለው የትራክቶቹ መልእክት የሚመስጥ በመሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ሊያገለግል ይችላል።
3 አንዲት ምሥክር በግሏ የተሰማት ነገር ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው። “ጥድፊያ በተሞላበት በዚህ ዓለም ውስጥ ሰዎች በንባብ ብዙ ጊዜ ማጥፋት አይፈልጉም። ትራክቶች ግን ጠቃሚ የሆነውን መልእክት በሚገባ ለማብራራት ባያንሱም መጠናቸው ሰዎችን በሩቁ የሚያስፈራ አይደለም። ብዙዎቹን ትራክቶች በማንበቤ እውነትን መማር ችዬአለሁ።” እጥር ምጥን ባለ መንገድ በተዘጋጁት በእነዚህ ጽሑፎች ላይ የተብራራው የአምላክ ቃል ያለውን ኃይል አቅልለህ አትመልከት።—ዕብ. 4:12
4 አራት ቀላል ደረጃዎች፦ ብዙ አስፋፊዎች ቀላል አቀራረብ ተጠቅመው ውጤት አግኝተዋል። (1) ካሉን ትራክቶች መካከል ጥቂቶቹን አሳየውና የትኛውን መውሰድ እንደሚፈልግ ጠይቀው። (2) አንዱን ከመረጠ በኋላ የትራክቱን አንድ ዋና ነጥብ የሚያጎላ በደንብ የታሰበበት ጥያቄ ጠይቀው። (3) ጥያቄውን ለመመለስ ከትራክቱ ላይ ተስማሚ የሆነ አንድ አንቀጽ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አንብብ። (4) አዎንታዊ ምላሽ ካገኘህ በቀሪው የትራክቱ ፍሬ ነገር ላይ ውይይቱን ቀጥል። ወይም ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ከተባለው ብሮሹር አንድ ትምህርት ወይም ከእውቀት መጽሐፍ አንድ ምዕራፍ አሳየው። በዚህ መንገድ በቀጥታ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልትመራው ትችል ይሆናል። ቀጥሎ የቀረበው ሃሳብ ከትራክቶቹ አራቱን ለማበርከት ስትሞክር ምን ብለህ እንደምትጀምር ለመዘጋጀት ይረዳሃል።
5 “ዓለምን የሚገዛው ማን ነው?” የሚለውን የትራክቱን ርዕስ እንደ ጥያቄ አድርጎ ማቅረብ ይቻላል።
◼ እያነጋገርከው ያለኸው ሰው “አምላክ” ነው ብሎ ቢመልስ ወይም “እኔ አላውቅም” ቢል በገጽ 2 ላይ የሚገኙትን ሁለት የመግቢያ አረፍተ ነገሮችንና በገጽ 3 ላይ የሚገኘውን የመጀመሪያ አንቀጽ አንብብ። 1 ዮሐንስ 5:19ን እና ራእይ 12:9ን አብራራ። ሰውዬው የሰይጣን ዲያብሎስን ህልውና የሚጠራጠርም ሆነ ሰይጣን በዓለም ላይ ያለውን ኃይል አምኖ የሚቀበል፣ “የዓለም ሁኔታዎች የሚሰጡት ፍንጭ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር የሚገኘውን የማሳመኛ ነጥብ በመጠቀም ውይይቱን መቀጠል ትችላለህ። ፍላጎት ካሳየ ዲያብሎስ ከየት እንደመጣ ልታብራራለት እንደምትፈልግ ንገረው። በገጽ 3 እና ገጽ 4 ላይ የሚገኙትን ነጥቦች በመጠቀም ልታብራራለት ትችላለህ።
6 “እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?” የተባለው ትራክት ወዲያውኑ ፍላጎት የሚቀሰቅስ ሊሆን ይችላል። የሚከተለውን ጥያቄ በመጠየቅ ውይይት መጀመር ትችላለህ:-
◼ “እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታንን ዳግመኛ እናያቸዋለን ብለው ያስባሉ?” ሰውዬው መልስ ከሰጠ በኋላ ገጽ 4 ላይ ሁለተኛውን አንቀጽ አሳየውና ዮሐንስ 5:28, 29ን አንብብ። ከዚያ ቀጥለህ በትራክቱ የመጀመሪያ ንዑስ ርዕስ ሥር የተብራራውን ነጥብ መረዳቱ ጠቃሚ እንደሚሆን ግለጽ። አብራችሁ እንድትወያዩበት እንደምትፈልግ ግለጽለት።
7 “በቤተሰብ ኑሮ ተደሰት ” የተባለው ትራክት በመላው ዓለም ለሚገኙ ቤተሰቦች ሁሉ የሚሆን ነው። ይህንን ትራክት ተጠቅመህ እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
◼ “በዛሬ ጊዜ የቤተሰብ ተቋም ጥቃት እየደረሰበት ነው ቢባል ይስማሙ ይሆናል። የቤተሰብ ትስስር ጠንካራ እንዲሆን ምን መደረግ አለበት ብለው ያስባሉ?” ሰውዬው መልስ ከሰጠ በኋላ በገጽ 6 ላይ በሚገኘው የመጀመሪያ አንቀጽ ላይ እንዲያተኩር አድርግ። በገጽ 4 እና 5 ላይ ከሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መካከል አንዱን ምረጥና ምን ማለት እንደሆነ አብራራ። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ልታስጠናው እንደምትፈልግ ንገረው።
8 “መጽሐፍ ቅዱስን ማመን የሚችሉት ለምንድን ነው?” የሚለውን ትራክት ለማበርከት የሚከተለውን አቀራረብ ልትጠቀም ትችላለህ:-
◼ “ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መጽሐፍ ውስጥ ስለሚገኘው የቃየንና የአቤል ታሪክ ያውቃሉ። እንዲሁም የዘፍጥረት ዘገባ ስለ ቃየን ሚስት ይጠቅሳል። ይህች ሴት ከየት ተገኘች ብለው አስበው ያውቃሉ?” በገጽ 2 ላይ የሚገኘውን የመጨረሻ አንቀጽ በመጠቀም መልስ ስጥ። በተጨማሪም ትራክቱ የወደፊቱን ጊዜ በሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው መልእክትም እንደሚያብራራ አስረዳው። ከገጽ 5 ሦስተኛ አንቀጽ ጀምረህ ለማስረጃነት የቀረቡትን ጥቅሶች በመጠቀም ውይይቱን ቀጥል።
9 መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትራክቶችን በማሠራጨት ምሥራቹን ማዳረስ ውጤታማ ዘዴ መሆኑ በተሞክሮ የተረጋገጠ ነው። በማንኛውም ቦታ ስትሄድ ይዘኻቸው ለመሄድ የማያስቸግሩ በመሆናቸው ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ስትመሰክርና በመንገድ ላይ ስታገለግል ውጤታማ በሆነ መንገድ ልትጠቀምባቸው ትችላለህ። ትራክቶች ለአገልግሎታችን በጣም ጠቃሚ ናቸው። የተለያዩ ትራክቶችን መያዝህንና ውይይት ለመጀመር በሚገባ እየተጠቀምክባቸው መሆኑን እርግጠኛ ሁን።—ቆላ. 4:17