ሰዓት አክባሪ የመሆንን ልማድ አዳብሩ
1. ይሖዋ ጊዜን በመጠበቅ ረገድ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?
ይሖዋ ሁሉንም ነገር የሚያከናውነው ጊዜውን ጠብቆ ነው። ለምሳሌ ያህል ለአገልጋዮቹ ‘በሚያስፈልጋቸው ጊዜ’ እርዳታ ይሰጣቸዋል። (ዕብ. 4:16) በተጨማሪም መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርበው “በተገቢው ጊዜ” ነው። (ማቴ. 24:45) በመሆኑም በፊታችን የምንጠብቀው ቁጣውን የሚገልጽበት ቀን ‘እንደማይዘገይ’ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዕን. 2:3) ይሖዋ ጊዜውን ጠብቆ ነገሮችን ማከናወኑ በእጅጉ ጠቅሞናል! (መዝ. 70:5) እኛ የሰው ልጆች ግን ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን እንዲሁም በሥራ ልንወጠር ስለምንችል ሰዓት ማክበር ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። ታዲያ ሰዓት የማክበር ልማድ ማዳበር ያለብን ለምንድን ነው?
2. ሰዓት ማክበር ለይሖዋ ክብር የሚያመጣው እንዴት ነው?
2 ብዙ ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱና ራሳቸውን የማይገዙ በሆኑበት በዚህ የመጨረሻ ዘመን ሰዓት አክባሪ መሆን ብርቅ እየሆነ መጥቷል። (2 ጢሞ. 3:1-3) በመሆኑም ክርስቲያኖች ሥራቸውን ሲያከናውኑ፣ በቀጠሮ እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ ሲገኙ ሰዓት የሚያከብሩ ከሆነ ሌሎች ይህን ማስተዋላቸው አይቀርም፤ ይህ ደግሞ ለይሖዋ ክብር ያመጣል። (2 ጴጥ. 2:12) በአብዛኛው ሰብዓዊ ሥራችንን በሰዓቱ እንጀምር ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የማርፈድ ልማድ አለን? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የመክፈቻው መዝሙርና ጸሎት ከመጀመሩ በፊት አስቀድመን መድረሳችን የሥርዓት አምላክ የሆነውን የሰማዩ አባታችንን የመምሰል ፍላጎት እንዳለን ያሳያል።—1 ቆሮ. 14:33, 40
3. ሰዓት አክባሪ መሆናችን ለሌሎች እንደምናስብ ያሳያል የምንለው ለምንድን ነው?
3 ሰዓት አክባሪ መሆናችን ለሌሎች እንደምናስብም ያሳያል። (ፊልጵ. 2:3, 4) ለምሳሌ ያህል፣ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን ጨምሮ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በሰዓቱ የምንገኝ ከሆነ የእምነት ባልንጀሮቻችን አይረበሹም። በሌላ በኩል ደግሞ የማርፈድ ልማድ ካለን ወንድሞቻችን ከእነሱ ጊዜ ይልቅ ለእኛ ጊዜ ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ ሊሰማቸው ይችላል። ሰዓት አክባሪ መሆናችን እምነት የሚጣልብን፣ ታታሪ እና ኃላፊነት የሚሰማን እንደሆንን ያሳያል፤ እነዚህ ደግሞ በብዙዎች ዘንድ የሚወደዱ ባሕርያት ናቸው።
4. የማርፈድ ልማድ ካለን መሻሻል የምንችለው እንዴት ነው?
4 የማርፈድ ልማድ ካላችሁ፣ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ሞክሩ። የተደራጃችሁ ሁኑ፤ ለዚህ እንዲረዳችሁ ሥራችሁን በጊዜው ለማከናወን የሚያስችላችሁን ሁኔታችሁን ያገናዘበ ፕሮግራም አውጡ። (መክ. 3:1፤ ፊልጵ. 1:10) ይሖዋ እንዲረዳችሁ በጸሎት ጠይቁት። (1 ዮሐ. 5:14) ሰዓት አክባሪ መሆናችን ሁለቱን ታላላቅ ትእዛዛት እንደምናከብር ይኸውም አምላክንና ባልንጀራችንን እንደምንወድ የምናሳይበት አንዱ መንገድ ነው።—ማቴ. 22:37-39