የጥያቄ ሣጥን
◼ ልጆች በመንፈሳዊ የጎለመሱ እንዲሆኑ ምን መማር ይኖርባቸዋል?
ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን “በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ” ማሳደግ ከፈለጉ ብዙ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። (ኤፌ. 6:4) ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ወላጆች በየዕለቱ ማለዳ ላይ ከልጆቻቸው ጋር በዕለት ጥቅሱ ላይ መወያየት ያለውን ጥቅም ተመልክተዋል። በቤተሰብ አምልኮና በሌሎች ወቅቶች ቤተሰቡ ቪዲዮዎችን አብሮ በመመልከት መወያየት፣ የወጣቶች ጥያቄ በሚለው ዓምድ ሥር በሚወጡ ርዕሶች ላይ መወያየት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በድራማ መልክ ማቅረብ ወይም የልምምድ ክፍለ ጊዜ መመደብ ይችላሉ። ይሁንና ልጆች “ወደ ጉልምስና [እንዲገፉ]” ከተፈለገ ጥልቀት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችንም መማር ያስፈልጋቸዋል።—ዕብ. 6:1
እስቲ በክልላችን ውስጥ የምናገኛቸውን ሰዎች ምን እንደምናስተምራቸው ለአንድ አፍታ አስቡ። አብዛኛውን ጊዜ፣ አንድን ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ አግኝተን ስናነጋግረው አሊያም በሌላ ጊዜ ተመልሰን ስንጠይቀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅመን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ጥረት እንደምናደርግ የታወቀ ነው። ይህን መጽሐፍ አጥንቶ ከጨረሰ በኋላ ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ እናስጠናዋለን። እንዲህ የምናደርገው ለምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ ተማሪው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ የሆነ እውቀት እንዲያገኝ ይረዳዋል። “ከአምላክ ፍቅር” የተባለው መጽሐፍ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለት ተዕለት ሕይወት እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችል ያስተምረዋል። አንድ አዲስ ሰው ሁለቱንም መጻሕፍት ማጥናቱ በክርስቶስ ላይ ‘እንዲተከልና በእምነት ጸንቶ እንዲኖር’ ይረዳዋል። (ቆላ. 2:6, 7) ታዲያ ልጆቻችንስ እነዚህን መጻሕፍት ማጥናታቸው አይጠቅማቸውም? እነሱም ቢሆኑ ስለ ቤዛው፣ ስለ አምላክ መንግሥት እንዲሁም ሙታን ስላሉበት ሁኔታ መማር ያስፈልጋቸዋል። በተጨማሪም ልጆች፣ አምላክ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምን እንደሆነ እንዲሁም የምንኖረው በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ መሆኑን እንዴት ማወቅ እንደሚቻል መማር አለባቸው። ከዚህም ሌላ እውነት የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንደሆነ የሚያሳምን ነገር ማግኘት ይኖርባቸዋል። እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መረዳታቸውና “የማስተዋል ችሎታቸውን” ማሠልጠናቸው አስፈላጊ ነው። (ዕብ. 5:14) እርግጥ ነው፣ ወላጆች የልጆቻቸውን ዕድሜ እና የመረዳት ችሎታ ግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው። ያም ቢሆን ብዙ ልጆች ገና በለጋ ዕድሜያቸው ጥልቀት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መማር እንደሚችሉ ወላጆች ማስታወሳቸው ጠቃሚ ነው።—ሉቃስ 2:42, 46, 47
ወላጆችን ለመርዳት ሲባል የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተባለው መጽሐፍ ላይ የተመሠረቱ ለማጥናት የሚረዱ ርዕሶች በjw.org ላይ መውጣት ይጀምራሉ። ቤተሰቦች እነዚህን ርዕሶች በድረ ገጻችን ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > ወጣቶች በሚለው ሥር ማግኘት ይችላሉ። ወደፊት ደግሞ “ከአምላክ ፍቅር” በተባለው መጽሐፍ ላይ የተመሠረቱ ለማጥናት የሚረዱ ርዕሶች ይወጣሉ። እርግጥ ነው፣ በወረቀት የታተሙትን እነዚህን መጻሕፍትንም መጠቀም ይቻላል። ወላጆች በድረ ገጹ ላይ የሚወጡትን ርዕሶች በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ወይም ለልጆቻቸው ጥናት ሲመሩ አሊያም ልጃቸውን የግል ጥናት እንዲያደርግ ሲያሠለጥኑት ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ።