ልጆቻችሁን ለማስተማር ድረ ገጻችንን ተጠቀሙ
1. በድረ ገጻችን ላይ የሚገኘው “ልጆች” የሚለው ክፍል የተዘጋጀበት ዓላማ ምንድን ነው?
1 jw.org የተባለው ድረ ገጻችን በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎችን እንዲማርክ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው። በድረ ገጹ ላይ የሚገኘው “ልጆች” (“የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች” በሚለው ሥር “ልጆች” የሚለውን ክፈቱ።) የሚለው ክፍል ልጆች፣ ከወላጆቻቸውም ሆነ ከይሖዋ ጋር እንዲቀራረቡ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። (ዘዳ. 6:6, 7) ይህን ክፍል ልጆቻችሁን ለማስተማር ልትጠቀሙበት የምትችሉት እንዴት ነው?
2. ልጆቻችሁን ስታስጠኑ ዕድሜያቸውን ያማከለ ትምህርት መምረጥ የምትችሉት እንዴት ነው?
2 ዘዴኞች ሁኑ፦ እያንዳንዱ ልጅ የራሱ የሆነ ፍላጎት አለው። (1 ቆሮ. 13:11) ታዲያ ልጆቻችሁን ስታስተምሩ ዕድሜያቸውን ያማከለ ነገር መምረጥ የምትችሉት እንዴት ነው? ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘የልጆቼን ትኩረት የሚስበው ምንድን ነው? ምን ያህል ይረዱታል? ትኩረታቸው ሳይከፋፈል መቆየት የሚችሉት ለምን ያህል ጊዜ ነው?’ ሦስት ዓመት ወይም ከዚያ በታች የሆኑ ሕፃናትን “መጽሐፍ ቅዱስ መማሪያዬ” በተባለው ክፍል ሥር የሚገኙትን ነገሮች ማወያየት ይቻላል። አንዳንድ ቤተሰቦች ደግሞ “ልጆቻችሁን አስተምሩ” በሚለው ክፍል ውስጥ ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ ይወያያሉ። የሚከተሉት አማራጮችም አሉ።
3. ወላጆች “የቤተሰብ አምልኮ ፕሮጀክት” በሚለው ሥር ያሉ መልመጃዎችን በጥሩ መንገድ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
3 የቤተሰብ አምልኮ ፕሮጀክት፦ እነዚህ ፕሮጀክቶች የተዘጋጁት ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር እንዲያጠኗቸው ታስቦ ነው። እያንዳንዱን ታሪክና መልመጃ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ለማወቅ “ለወላጆች የተሰጠ መመሪያ” የሚለውን ፋይል አውርዳችሁ አንብቡ። ትናንሽ ልጆቻችሁን ለማስተማር “ቀለም የሚቀባ ሥዕል” እንደሚለው ያሉ የሥዕል ጨዋታዎችን መጠቀም ትችላላችሁ። ትላልቅ ልጆቻችሁ ደግሞ “ለጥናት የሚረዳ መልመጃ” የሚለውን እንዲሠሩ አድርጉ። በእያንዳንዱ ፕሮጀክት ላይ ያሉት መልመጃዎች በሙሉ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ወይም ትምህርት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፤ በመሆኑም በሁሉም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች በቤተሰብ አምልኮ ፕሮጀክቱ ላይ ሊካፈሉ ይችላሉ።
4. “የይሖዋ ወዳጅ ሁን” በሚለው ክፍል ሥር ምን ነገሮች ይገኛሉ?
4 የይሖዋ ወዳጅ ሁን፦ በድረ ገጻችን ላይ በሚገኘው በዚህ ክፍል ሥር የሚገኙ ቪዲዮዎች፣ መዝሙሮችና መልመጃዎች ወላጆች በትናንሽ ልጆቻቸው ልብ ውስጥ የአምላክን ቃል መቅረጽ እንዲችሉ ይረዷቸዋል። (ዘዳ. 31:12) እያንዳንዱ አጭር የአኒሜሽን ቪዲዮ ጠቃሚ ትምህርት ይዟል። የተደበቀን ነገር ፈልጎ እንደማግኘት ያሉ በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ጨዋታዎች የትምህርቶቹን ጠቃሚነት ያጎላሉ። ብዙውን ጊዜ ልጆች መዘመር ስለሚወዱ እንዲሁም መዝሙሮች የተማሩትን ነገር እንዲያስታውሱ ስለሚረዷቸው የመንግሥቱ መዝሙሮችና ለልጆች ተብለው የሚዘጋጁ መዝሙሮች በየጊዜው ኢንተርኔት ላይ ይወጣሉ።
5. ወላጆች፣ እውነትን ለልጆቻቸው ሲያስተምሩ ይሖዋ እንዲረዳቸው መጠየቅ ያለባቸው ለምንድን ነው?
5 ወላጆች፣ ይሖዋ ልጆቻችሁን በማሳደግ ረገድ እንዲሳካላችሁ ይፈልጋል። በመሆኑም ለልጆቻችሁ እውነትን ስታስተምሩ እንዲረዳችሁ በጸሎት ጠይቁት። (መሳ. 13:8) ይሖዋ በሚሰጣችሁ እርዳታ ታግዛችሁ ልጆቻችሁን “በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ” እንዲያገኙ ልታሠለጥኗቸው ትችላላችሁ።—2 ጢሞ. 3:15፤ ምሳሌ 4:1-4