ይሖዋ እኔን የሚመለከተኝ እንዴት ነው?
1. መጽሐፍ ቅዱስ ከመስተዋት ጋር የተመሳሰለው እንዴት ነው?
1 ራሳችሁን በመስተዋት የመመልከት ልማድ አላችሁ? አብዛኞቻችን እንዲህ የማድረግ ልማድ አለን፤ ምክንያቱም መስተዋት መመልከታችን በመልካችን ወይም በአለባበሳችን ላይ መስተካከል ያለበት ነገር ይኖር እንደሆነ ለማወቅ ያስችለናል። መጽሐፍ ቅዱስ ከመስተዋት ጋር ተመሳስሏል። የአምላክን ቃል ማንበባችን ውስጣችንን ይኸውም ይሖዋ የሚመለከተውን ማንነታችንን ለማየት ያስችለናል። (1 ሳሙ. 16:7፤ ያዕ. 1:22-24) የአምላክ ቃል ‘የልብን ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።’ (ዕብ. 4:12) መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል ይበልጥ ውጤታማ ወንጌላዊ በመሆን ረገድ ማሻሻያ ልናደርግባቸው የሚገቡ ነገሮችን መመልከት እንድንችል የሚረዳን እንዴት ነው?—መዝ. 1:1-3
2. መጽሐፍ ቅዱስ ራሳችንን እንድንገመግም የሚረዳን እንዴት ነው?
2 መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መስተዋት ተጠቀሙበት፦ ስለ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች የሚናገሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ዘገባዎች ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸው ባሕርያት ምን እንደሆኑ ያስተምሩናል። ለምሳሌ ያህል ዳዊት ለአምላክ ስም ቅንዓት እንዳለው አሳይቷል። (1 ሳሙ. 17:45, 46) ኢሳይያስ አስቸጋሪ በሆነ ክልል ውስጥ በድፍረት ለመስበክ ራሱን አቅርቧል። (ኢሳ. 6:8, 9) ኢየሱስ በሰማይ ለሚኖረው አባቱ ጥልቅ ፍቅር ስላለው አገልግሎቱን እንደ ሸክም ሳይሆን የብርታትና የደስታ ምንጭ እንደሆነ አድርጎ ተመልክቶታል። (ዮሐ. 4:34) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች በቅንዓት ሰብከዋል፤ በይሖዋ ታምነዋል እንዲሁም ተስፋ ሳይቆርጡ ጸንተዋል። (ሥራ 5:41, 42፤ 2 ቆሮ. 4:1፤ 2 ጢሞ. 4:17) በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላችን ራሳችንን እንድንገመግምና የምናቀርበውን ቅዱስ አገልግሎት ጥራት በምን በኩል ማሻሻል እንዳለብን እንድንገነዘብ ይረዳናል።
3. አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ዛሬ ነገ ማለት የማይኖርብን ለምንድን ነው?
3 ማስተካከያ ለማድረግ እርምጃ ውሰዱ፦ መስተዋት ስንመለከት ማስተካከል ያለብን ነገር እንዳለ ብናስተውልና ያንን ለማስተካከል እርምጃ ባንወስድ መስተዋት መመልከታችን ምንም ጥቅም እንደማይኖረው የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ራሳችንን በሐቀኝነት መመልከትና አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ እንድንችል ይሖዋ እንዲረዳን ልንጠይቀው እንችላለን። (መዝ. 139:23, 24፤ ሉቃስ 11:13) የቀረው ጊዜ አጭር ከመሆኑም ሌላ የሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ነው፤ ከዚህ አንጻር አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ዛሬ ነገ ማለት አይኖርብንም።—1 ቆሮ. 7:29፤ 1 ጢሞ. 4:16
4. አንድ ሰው የአምላክን ቃል በትኩረት ከተመለከተ በኋላ ባየው ነገር ላይ ተመሥርቶ እርምጃ የሚወስድ ከሆነ ምን ጥቅም ያገኛል?
4 ይሖዋ ትኩረት የሚያደርግበት ውስጣዊ ማንነታችን ከውጫዊ ገጽታችን ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። (1 ጴጥ. 3:3, 4) አንድ ሰው የአምላክን ቃል በትኩረት ከተመለከተ በኋላ ባየው ነገር ላይ ተመሥርቶ እርምጃ የሚወስድ ከሆነ ምን ጥቅም ያገኛል? “ሰምቶ የሚረሳ ሳይሆን በሥራ ላይ የሚያውል ሰው ስለሆነ ይህን በማድረጉ ደስተኛ ይሆናል።” (ያዕ. 1:25) አዎ፣ ‘የይሖዋን ክብር እንደ መስተዋት እንድናንጸባርቅ’ ስለሚያደርገን ደስተኛና ውጤታማ ወንጌላውያን እንሆናለን።—2 ቆሮ. 3:18