ለጥናት የሚረዱ ሐሳቦች
መስተዋቱን በደንብ ተጠቀሙበት
ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ መጽሐፍ ቅዱስን ከመስተዋት ጋር አመሳስሎታል፤ ውስጣዊ ማንነታችንን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። (ያዕ. 1:22-25) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ እንደ መስተዋት እንዲያገለግለን እንዴት አድርገን ልንጠቀምበት ይገባል?
በጥሞና አንብቡ። መስተዋት ላይ ራሳችንን የምናየው እንዲሁ ገረፍ አድርገን ከሆነ ጎልቶ የሚታይ እንከን እንኳ ሊያልፈን ይችላል። በተመሳሳይም ውስጣዊ ማንነታችን ላይ መታረም ያለበት ነገር እንዲታየን የአምላክን ቃል በጥሞና ማንበብ አለብን።
ከሌሎች ይልቅ ራሳችሁን ተመልከቱ። መስተዋቱን የያዝነው ከእኛ ትይዩ ሳይሆን ጋደል አድርገን ከሆነ የሌላ ሰው እንከን ሊታየን ይችላል። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ የሌሎችን እንከን ማሰብ ይቀናን ይሆናል። ይህ ግን እኛ ማስተካከል ያለብን ነገር ላይ እንዳናተኩር ያደርገናል።
ምክንያታዊ ሁኑ። መስተዋት ላይ የሚታየን እንከናችን ብቻ ከሆነ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል። በመሆኑም የአምላክን ቃል ስናነብ ምክንያታዊ መሆን አለብን፤ ይሖዋ ከእኛ ከሚጠብቀው በላይ ከራሳችን መጠበቅ አይኖርብንም።—ያዕ. 3:17