ነቢያትን አርዓያ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው—ናሆም
1. ከናሆም መጽሐፍ ምን ትምህርት እናገኛለን?
1 የጥንቷ ነነዌ ፍርስራሽ ልክ ናሆም እንደተነበየው ይሖዋ ጠላቶቹን የሚበቀል አምላክ እንደሆነና በጣም ኃያል የተባለው ጠላትም እንኳ እሱን መቋቋም እንደማይችል ያሳያል። (ናሆም 1:2, 6) የናሆምን ትንቢት በጥልቀት ስንመረምር ለአገልግሎታችን የሚጠቅም ብዙ ትምህርት እናገኛለን።
2. መልእክታችን አዎንታዊ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
2 ማጽናኛና ተስፋ መስጠት፦ የናሆምን መጽሐፍ ከላይ ከላይ ስናነበው ዝነኛ በሆነው በጥንቷ የአሦር ዋና ከተማ ማለትም በነነዌ ላይ የሚመጣውን ጥፋት የሚናገር ይመስለን ይሆናል። (ናሆም 1:1፤ 3:7) ይሁን እንጂ ይህ የጥፋት ፍርድ ለይሖዋ ሕዝቦች ምሥራች ነበር። ናሆም (“አጽናኝ” የሚል ትርጉም አለው) ወገኖቹ ለሆኑት አይሁዳውያን፣ ጠላታቸው በቅርቡ እንደሚጠፋ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። በተጨማሪም ናሆም ይሖዋ ‘በጭንቅ ጊዜ መሸሸጊያ’ እንደሆነ ገልጾላቸዋል። (ናሆም 1:7) እኛም ብንሆን በምንሰብክበት ጊዜ ለሰዎች ምሥራቹን መንገር እንዲሁም ይሖዋን መጠጊያቸው እንዲያደርጉት ማበረታታት ይኖርብናል።—ናሆም 1:15
3. ምሳሌዎችን በመጠቀም ረገድ ናሆምን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
3 ምሳሌዎችን መጠቀም፦ ናሆም፣ የነነዌን ጥፋት በራሳቸው በአሦራውያን እጅ ከጠፋችው ቴብስ (ኖእ አሞን) ከተባለችው የግብፅ ከተማ ጋር እያወዳደረ እንዲጽፍ ይሖዋ በመንፈሱ መርቶታል። (ናሆም 3:8-10) እኛም ስለዚህ ክፉ ሥርዓት መጨረሻ ለሰዎች በምንናገርበት ጊዜ ይሖዋ ቃሉን አንድም ሳይቀር እንደሚፈጽም የሚያረጋግጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ልንነግራቸው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል ባቢሎናውያንና ሜዶናውያን በ632 ዓ.ዓ. ነነዌን ለመውጋት ሲመጡ ከባድ ዝናብ በመዝነቡ ሳቢያ ሞልቶ ይፈስስ የነበረው የጤግሮስ ወንዝ የማይበገር ይመስል የነበረውን የከተማይቱን ቅጥር በከፊል አፈራርሶት ነበር። በዚህም የተነሳ ይሖዋ ልክ በትንቢት እንደተናገረው ነነዌ ወዲያውኑ በጠላቶቿ ቁጥጥር ሥር ዋለች።—ናሆም 1:8፤ 2:6
4. በአገልግሎት ላይ ግልጽ በሆነና በቀላሉ በሚገባ መንገድ መናገር የምንችለው እንዴት ነው?
4 ግልጽና በቀላሉ የሚገባ፦ የናሆም ትንቢት የተጻፈው ገላጭ በሆነና በሚመስጥ መንገድ ነው። ናሆም ያሰፈረው መልእክት ግልጽ ነበር። (ናሆም 1:14፤ 3:1) እኛም በተመሳሳይ ለሰዎች በቀላሉ የሚገባ አነጋገር መጠቀም ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 14:9) ሰዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ አግኝታችሁ ስታነጋግሩ የመጣችሁበትን ምክንያት ግልጽ በሆነ መንገድ አስረዱ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ስትመሩ ደግሞ ጥናቶቻችሁ በይሖዋና በቃሉ ላይ እምነት እንዲያሳድሩ እንዲሁም የቀረበው ትምህርት በግለሰብ ደረጃ እነሱን የሚነካቸው እንዴት እንደሆነ እንዲያገናዝቡ እርዷቸው።—ሮም 10:14
5. በናሆም ትንቢት ውስጥ ምን ማረጋገጫ እናገኛለን?
5 በስሙ የተሰየመው መጽሐፍ እንደሚያሳየው ናሆም የይሖዋ ቃል መፈጸሙ እንደማይቀር ጠንካራ እምነት ነበረው። የሰይጣን ሥርዓት የሚጠፋበት ጊዜ እየተቃረበ ባለበት በዚህ ወቅት “መከራም ዳግመኛ አይነሣም” የሚለው መለኮታዊ አዋጅ እንደሚያጽናናን ጥርጥር የለውም።—ናሆም 1:9