በመታሰቢያው በዓል ሰሞን የይሖዋና የኢየሱስ ዓይነት ቅንዓት ማሳየት ትችላላችሁ?
1. የይሖዋ ምሥክሮች በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ምን ልዩ ጥረት ያደርጋሉ?
1 ይሖዋ ዓላማውን ከዳር ለማድረስ የሚሠራው በቅንዓት ነው። የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸውን አንዳንድ በረከቶች አስመልክቶ ኢሳይያስ 9:7 “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል” ይላል። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስም ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ለእውነተኛው አምልኮ ከፍተኛ ቅንዓት እንደነበረው አሳይቷል። (ዮሐ. 2:13-17፤ 4:34) በዓለም ዙሪያ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አስፋፊዎች፣ የይሖዋና የኢየሱስ ዓይነት ቅንዓት ለማሳየት ሲሉ በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ከፍ ለማድረግ ልዩ ጥረት ያደርጋሉ። አንተስ እንዲህ ማድረግ ትችላለህ?
2. ከመጋቢት 7 ጀምሮ ምን ነገር በቅንዓት እናከናውናለን?
2 ለመታሰቢያው በዓል የሚደረግ ዘመቻ፦ በዚህ ዓመት ሰዎችን በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ መጋበዝ የምንጀምረው ቅዳሜ፣ መጋቢት 7, 2015 ነው። በዚህ ወቅት በአገልግሎት ላይ በቅንዓት ለመካፈል ከአሁኑ እቅድ አውጡ። ጉባኤዎች የአገልግሎት ክልላቸውን ለመሸፈን የተቻላቸውን ያህል ጥረት ያደርጋሉ። መጋበዣ ወረቀቱን ወይም jw.org/am የተባለውን ድረ ገጽ ተጠቅማችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁን፣ ተመላልሶ የምታደርጉላቸውን ሰዎች የሥራ ባልደረቦቻችሁን፣ ዘመዶቻችሁንና አብረዋችሁ የሚማሩትን ለመጋበዝ ከፍተኛ ጥረት አድርጉ።
3. በመጋቢትና በሚያዝያ ወር አገልግሎታችንን ማስፋት የምንችለው እንዴት ነው?
3 ረዳት አቅኚ፦ ቅንዓት አገልግሎታችንን ለማስፋትም ይረዳናል። በመጋቢትና በሚያዝያ ወር 30 ሰዓት በማገልገል ረዳት አቅኚ መሆን ስለሚቻል ብዙዎች ረዳት አቅኚ እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ረዳት አቅኚ ለመሆን ምን ማድረግ እንደምትችሉ በቤተሰብ አምልኳችሁ ወይም በግል ጥናታችሁ ወቅት በጸሎት አስቡበት። (ምሳሌ 15:22) በዘመቻው ወቅት የምታሳዩት ቅንዓት ሌሎችም በቅንዓት እንዲያገለግሉ ሊያነሳሳ ይችላል። በአገልግሎት ይበልጥ ለመካፈል በግለሰብ ደረጃ ማስተካከያዎችን የምታደርጉ ከሆነ የኢየሱስን ዓይነት ቅንዓት እያሳያችሁ ነው ማለት ይቻላል።—ማር. 6:31-34
4. የይሖዋና የኢየሱስ ዓይነት ቅንዓት ማሳየታችን ምን በረከት ያስገኝልናል?
4 በመታሰቢያው በዓል ሰሞን የይሖዋና የኢየሱስ ዓይነት ቅንዓት ማሳየታችን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝልናል። በክልላችን ለሚገኙ ብዙ ሰዎች መመሥከር እንችላለን። ይሖዋን ማገልገልና መስጠት የሚያስገኘውን ደስታና እርካታ እናጣጥማለን። (ሥራ 20:35) ከሁሉ በላይ ግን ቅንዓት በማሳየት ረገድ የላቀ ምሳሌ የሆኑትን አምላክንና ልጁን እናስደስታለን።