ለማስተማር የምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች
1. ክርስቲያን ወንጌላውያን ከአንድ ባለሙያ ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?
1 አንድ የእጅ ባለሙያ የተለያዩ መሣሪያዎችን ይጠቀማል። በአንዳንዶቹ መሣሪያዎች የሚጠቀመው አልፎ አልፎ ለየት ያለ ሥራ ማከናወን ሲፈልግ ሲሆን ሌሎቹን ግን አዘውትሮ ይጠቀምባቸዋል። አንድ ልምድ ያለው ባለሙያ በተደጋጋሚ የሚጠቀምባቸውን መሣሪያዎች የያዘ ሣጥን አለው፤ ደግሞም እነዚህን መሣሪያዎች በመጠቀም ረገድ የተካነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የተቻለውን ሁሉ ጥረት እንዲያደርግና “ምንም የሚያፍርበት ነገር እንደሌለው ሠራተኛ” እንዲሆን ያበረታታል። (2 ጢሞ. 2:15) በአገልግሎት ላይ ይበልጥ የምንጠቀምበት መሣሪያ ምንድን ነው? ዋነኛው መሣሪያችን ሰዎችን “ደቀ መዛሙርት” ለማድረግ የምንጠቀምበት የአምላክ ቃል ነው። (ማቴ. 28:19, 20) በመሆኑም “የእውነትን ቃል በአግባቡ በመጠቀም” ረገድ የተካንን ለመሆን ጥረት ማድረግ አለብን። ይሁንና አዘውትረን የምንጠቀምባቸው ሌሎች መሣሪያዎችም አሉ፤ ሁሉም ክርስቲያኖች ሰዎችን ስለ እውነት ለማስተማር በእነዚህ መሣሪያዎች በሚገባ መጠቀም የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ማወቅ አለባቸው።—ምሳሌ 22:29
2. አዘውትረን የምንጠቀምባቸው የማስተማሪያ መሣሪያዎች የትኞቹ ናቸው?
2 አዘውትረን የምንጠቀምባቸው የማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን፦ ከመጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ የምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች የትኞቹ ናቸው? የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማስተማር አዘውትረን የምንጠቀምበት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ ነው። ተማሪው ይህን መጽሐፍ አጥንቶ ከጨረሰ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሕይወቱ ተግባራዊ እንዲያደርግ ለመርዳት ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ እንጠቀማለን። በመሆኑም እነዚህን ሁለት መጻሕፍት በመጠቀም ረገድ የተዋጣልን መሆን ይኖርብናል። ለማስጠናት ከምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች መካከል አንዳንድ ብሮሹሮችም ይገኙበታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር አዘውትረን ከምንጠቀምባቸው መሣሪያዎች መካከል ከአምላክ የተላከ ምሥራች! የተባለው ብሮሹር ይገኝበታል። በክልላችን ውስጥ የማንበብ ችሎታቸው ውስን የሆኑ ሰዎች ካሉ ወይም በቋንቋቸው የተዘጋጁት ጽሑፎች ጥቂት ከሆኑ ወይም ምንም ጽሑፎች ከሌሉ አምላክን ስማ አሊያም አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ የሚሉትን ብሮሹሮች መጠቀም እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ወደ ድርጅቱ ለመምራት የምንጠቀምበት ዋነኛው መሣሪያ በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው? የሚለው ብሮሹር ነው። መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው?፣ በመንግሥት አዳራሻችን ውስጥ ምን ይከናወናል? እንዲሁም አምላክ ስም አለው? የተባሉት ቪዲዮዎች ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ይረዳሉ፤ የእነዚህን ቪዲዮዎች አጠቃቀምም በሚገባ ማወቅ ይኖርብናል።
3. ወደፊት በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ ምን ዓይነት ርዕሶች ይወጣሉ?
3 ለማስተማር አዘውትረን የምንጠቀምባቸውን መሣሪያዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድንጠቀምባቸው የሚረዱ ርዕሶች ወደፊት በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ ይወጣሉ። በእነዚህ መሣሪያዎች አጠቃቀም ረገድ የተካንን ለመሆን ጥረት ስናደርግ የሚከተለውን በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን ምክር ተግባራዊ እናደርጋለን፦ “ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ። በእነዚህ ነገሮች ጽና፤ ይህን በማድረግ ራስህንም ሆነ የሚሰሙህን ታድናለህ።”—1 ጢሞ. 4:16