“እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ”
ወላጆች እንደ እረኛ ናቸው። በመሆኑም በቀላሉ መንገድ ሊስቱና ለአደጋ ሊጋለጡ የሚችሉትን ልጆቻቸውን በሚገባ መንከባከብ ይኖርባቸዋል። (ምሳሌ 27:23) ወላጆች ይህን ኃላፊነት መወጣት የሚችሉት እንዴት ነው? በልጆቻቸው አእምሮና ልብ ውስጥ ያለውን ለማወቅ በየቀኑ ጊዜ ሰጥተው ከእነሱ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ አለባቸው። (ምሳሌ 20:5) በተጨማሪም እሳትን መቋቋም የሚችሉ ነገሮችን በመጠቀም የልጆቻቸውን እምነት መገንባት ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮ. 3:10-15) “እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ” የተባለው ቪዲዮ በቋሚነት የቤተሰብ አምልኮ ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ያሳያል። ቪዲዮውን በቤተሰብ ሆናችሁ ተመልከቱትና በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ።
(1) የወንድም ሮማን ቤተሰብ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዳያተኩር ያደረገው ምንድን ነው? (2) ወንድም ሮማን የቤተሰብ አምልኮ ለማድረግ መጀመሪያ ላይ ያደረገው ሙከራ ያልተሳካው ለምንድን ነው? (3) ልጆችን በማሳደግ ረገድ ስኬታማ ለመሆን የሚረዳው የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ነው? (ዘዳ. 6:6, 7) (4) በቤተሰብ ውስጥ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንዲኖር ምን ሊረዳ ይችላል? (5) ልጆች ወላጆቻቸው ምን ዓይነት መሥዋዕቶችን ሲከፍሉ ማየት ይፈልጋሉ? (6) ወንድም ቤሮ እና ባለቤቱ በወንድም ሮማን ቤተሰብ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳደሩት እንዴት ነው? (ምሳሌ 27:17) (7) የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ስኬታማ እንዲሆን ከተፈለገ የቤተሰብ ራሶች አስቀድመው ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? (8) ወንድም ሮማን የቤተሰቡን ሁኔታ ለማሻሻል የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ ምንድን ነው? (9) የቤተሰብ አምልኮ ቋሚ መሆኑ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ኤፌ. 6:4) (10) በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ልናደርጋቸው የምንችላቸው አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? (11) ወንድም ሮማን፣ ማርከስ ትክክል የሆነውን ማድረጉ ያለውን ጠቀሜታ እንዲገነዘብ ረጋ ባለ መንፈስ ሆኖም ቁርጥ ያለ አቋም እንዳለው በሚያሳይ መንገድ የረዳው እንዴት ነው? (ኤር. 17:9) (12) ሪቤካ ከጀስቲን ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ እንድትችል አባትና እናቷ የረዷት እንዴት ነው? (ማር. 12:30፤ 2 ጢሞ. 2:22) (13) ወንድም ሮማንና ባለቤቱ በሕይወታቸው ውስጥ ማስተካከያ ሲያደርጉ እምነት እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው? (ማቴ. 6:33) (14) ይህ ቪዲዮ የቤተሰብ ራሶች የቤተሰባቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ጥረት ማድረጋቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የሚያጎላው እንዴት ነው? (1 ጢሞ. 5:8) (15) የቤተሰብ ራስ ከሆንክ ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?
ለቤተሰብ ራሶች የቀረበ ሐሳብ፦ ይህ ዘመናዊ ድራማ በ2011 በተደረገው የክልል ስብሰባ ላይ የቀረበ ነው። በዚያ ወቅት በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለባችሁ ተሰምቷችሁ ነበር? አሁንስ? አሁንም ተጨማሪ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለባችሁ ከተሰማችሁ እባካችሁ ጉዳዩን በጸሎት ካሰባችሁበት በኋላ አስፈላጊውን ለውጥ አድርጉ፤ እንዲህ ማድረጋችሁ ለቤተሰባችሁ የሚያስገኘው ጥቅም ዘላለማዊ ነው።—ኤፌ. 5:15-17