የምናስተምራቸውን ሰዎች ልብ መንካት የምንችለው እንዴት ነው?
1. ኢየሱስ በሚያስተምርበት ወቅት በአድማጮቹ ላይ ምን ተጽዕኖ ማሳደር ችሏል?
1 ኢየሱስ ክርስቶስ የአድማጮቹን ልብ መንካት ችሎ ነበር። በአንድ ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በግልጽ ካብራራላቸው በኋላ ልባቸው ‘ይቃጠልባቸው’ እንደነበር ተገልጿል። (ሉቃስ 24:32) አምላክን የምንታዘዘው ከልባችን ተነሳስተን መሆን እንዳለበት እሙን ነው፤ ታዲያ የምናስተምራቸውን ሰዎች ስሜት በመቀስቀስ ለውጥ እንዲያደርጉ ልናነሳሳቸው የምንችለው እንዴት ነው?—ሮም 6:17
2. ዘዴኛና አስተዋይ መሆናችን የአንድን ሰው ልብ ለመንካት የሚረዳው እንዴት ነው?
2 ዘዴኛና አስተዋይ ሁኑ፦ ብዙ ሰዎች ትክክልና ስህተት የሆነውን ስለነገርናቸው ብቻ ለተግባር አይነሳሱም። እንዲያውም የሚያምኑበት ሃይማኖታዊ ትምህርት ትክክል እንዳልሆነ ለማስረዳት ጥቅስ ስናዥጎደጉድባቸው ጭራሹኑ ሊሸሹ ይችላሉ። አንድን ሰው ለተግባር ለማነሳሳት በቅድሚያ ግለሰቡ እንደዚያ ብሎ እንዲያምን ወይም እንዲያደርግ ያነሳሳውን ምክንያት ማስተዋል ይኖርብናል። በደንብ የታሰበባቸው የአመለካከት ጥያቄዎችን በዘዴ መጠየቃችን ግለሰቡ የልቡን አውጥቶ እንዲናገር ሊያበረታታው ይችላል። (ምሳሌ 20:5) እንዲህ ካደረግን ከአምላክ ቃል ውስጥ ልቡን የሚነካውን አንድ ነጥብ መምረጥ ቀላል ይሆንልናል። ስለዚህ ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ልናሳያቸውና ልንታገሣቸው ይገባል። (ምሳሌ 25:15) እያንዳንዱ ሰው መንፈሳዊ እድገት የሚያደርግበት ፍጥነት የተለያየ እንደሆነ አትዘንጉ። የይሖዋ መንፈስ በአስተሳሰቡና በድርጊቱ ላይ ተጽዕኖ የሚያደርግበት ጊዜ እንዲያገኝ ፍቀዱለት።—ማር. 4:26-29
3. የምናስተምራቸው ሰዎች ጥሩ ባሕርያት እንዲያዳብሩ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?
3 ጥሩ ባሕርያት እንዲያዳብሩ እርዷቸው፦ ስለ ይሖዋ ጥሩነትና ፍቅር የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የምናስተምራቸው ሰዎች ጥሩ ባሕርያት እንዲያዳብሩ ሊረዷቸው ይችላሉ። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ምን ያህል እንደሚያስብልን ለማስረዳት እንደ መዝሙር 139:1-4 ወይም ሉቃስ 12:6, 7 ያሉ ጥቅሶችን መጠቀም እንችላለን። ግለሰቦች ይሖዋ ላሳየን ጸጋ ያላቸው አድናቆት ሲጨምር ለእሱ ያላቸው ፍቅርና ታማኝነትም ያድጋል። (ሮም 5:6-8፤ 1 ዮሐ. 4:19) በተጨማሪም ምግባራቸው ይሖዋን እንደሚያስደስተው ወይም እንደሚያሳዝነው ሲረዱ እሱን በሚያስደስትና በሚያስከብር መንገድ ለመኖር ሊነሳሱ ይችላሉ።—መዝ. 78:40, 41፤ ምሳሌ 23:15
4. በአገልግሎት ላይ በምናስተምርበት ጊዜ የሰዎችን የመምረጥ ነፃነት እንደምናከብር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
4 ይሖዋ ማንም በግድ እንዲታዘዘው አያደርግም። ከዚህ ይልቅ ሰዎች ምክሩን መከተላቸው የጥበብ እርምጃ መሆኑን እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። (ኢሳ. 48:17, 18) እኛም ሰዎች ራሳቸው አንድ ዓይነት መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ በሚያስችል መንገድ በማስተማር የይሖዋን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ሰዎች በሕይወታቸው ላይ ለውጥ የማድረግን አስፈላጊነት አምነው ሲቀበሉ ውጤቱ ዘላቂ ይሆናል። (ሮም 12:2) ‘ልብን ወደሚመረምረው’ አምላክ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡም ያስችላቸዋል።—ምሳሌ 17:3