የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ገጽታዎች ተጠቀሙባቸው
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ ትምህርት ሲማርና የተማረውን ተግባራዊ ሲያደርግ በመንፈሳዊ ያድጋል እንዲሁም ፍሬ ያፈራል። (መዝ. 1:1-3) የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ ያሉትን አንዳንድ ገጽታዎች በሚገባ በመጠቀም የምናስጠናው ሰው እድገት እንዲያደርግ ልንረዳው እንችላለን።
የመግቢያ ጥያቄዎች፦ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መግቢያ ላይ በምዕራፉ ውስጥ መልስ የሚያገኙ ጥያቄዎች አሉ። ተማሪው ለውይይቱ ጉጉት እንዲያድርበት እነዚህን ጥያቄዎች ልታነቡለት ትችላላችሁ። ወይም ደግሞ ለእያንዳንዱ ጥያቄ አጭር መልስ እንዲሰጥ አድርጉ። የተሳሳተ መልስ ቢሰጥም እንኳ በዚህ ጊዜ ልታርሙት አትሞክሩ። ተማሪው የሰጠውን መልስ ግምት ውስጥ በማስገባት የትኞቹ ነጥቦች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባችሁ ማወቅ ትችላላችሁ።—ምሳሌ 16:23፤ 18:13
ተጨማሪ ክፍል፦ ተማሪው በዋናው ጽሑፍ ላይ የሚገኘውን ትምህርት መረዳትና ማመን ከቻለ ተጨማሪ ክፍሉን በግሉ እንዲያየው ልታበረታቱት ትችላላችሁ። በቀጣዩ ጥናታችሁ ላይ ጥቂት ደቂቃዎችን ብቻ ወስዳችሁ በተጨማሪ ክፍሉ ላይ ያለውን ሐሳብ ተረድቶት እንደሆነ ጠይቁት። ይሁን እንጂ ተማሪውን ይጠቅመዋል ብላችሁ ካሰባችሁ ከጥናታችሁ ላይ ጊዜ ወስዳችሁ ተጨማሪ ክፍሉን ሙሉ በሙሉ ወይም የተወሰኑ አንቀጾችን መሸፈን ትችላላችሁ፤ አንቀጾቹን ካነበባችሁ በኋላ ለአንቀጾቹ አስቀድማችሁ ባዘጋጃችኋቸው ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ።
የክለሳ ሣጥን፦ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ የሚገኘው የክለሳ ሣጥን በመግቢያው ላይ ለሚገኙት ጥያቄዎች መልስ የሚሆኑ ሐሳቦችን ይዟል። ይህ ሣጥን፣ ተማሪህ ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች በሚገባ መረዳቱን እንዲሁም ነጥቦቹን ማብራራት መቻል አለመቻሉን ለማወቅ ይረዳሃል። በክለሳ ሣጥኑ ውስጥ የሚገኘውን እያንዳንዱን ነጥብ ብሎም የተጠቀሱትን ጥቅሶች አብራችሁ አንብቡ። ከዚያም ተማሪህ ጥቅሶቹን ተጠቅሞ የተጠቀሰው ነጥብ እውነት መሆኑን እንዲያስረዳ ጠይቀው።—ሥራ 17:2, 3