የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ስትጠቀሙ ታላቁን አስተማሪ ምሰሉ
1. ኢየሱስ ያስተማረው እንዴት ነበር?
1 ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ ሁልጊዜ ነገሮችን የሚያስረዳው ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ነበር። የሚያዳምጡት ሰዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ ለማድረግ ሲል በመጀመሪያ ለጉዳዩ ያላቸውን አመለካከት ይጠይቃቸዋል። (ማቴ. 17:24-27) ከዚያም ትኩረታቸውን ወደ አምላክ ቃል እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። (ማቴ. 26:31፤ ማር. 7:6) ደቀ መዛሙርቱ ወደፊትም መማራቸውን እንደሚቀጥሉ ስለሚያውቅ ብዙ ሐሳብ ላለማብዛት ይጠነቀቅ ነበር። (ዮሐ. 16:12) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እርሱ ያስተማራቸውን ነገር ያምኑበት እንደሆነና እንዳልሆነ እንዲሁም ሐሳቡ እንደገባቸውና እንዳልገባቸው ማወቅ ይፈልግ ነበር። (ማቴ. 13:51) የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ በዚህ መንገድ እንድናስተምር ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
2. በእያንዳንዱ ምዕራፍ መግቢያ ላይ የቀረቡትን ጥያቄዎች እንዴት ልንጠቀምባቸው እንችላለን?
2 የመግቢያ ጥያቄዎች:- አንድን ምዕራፍ ማጥናት ስትጀምሩ ከዋናው ርዕስ ሥር ባሉት ጥያቄዎች ላይ ትኩረት ብታደርጉ ጥሩ ነው። የተማሪውን የማወቅ ፍላጎት ለመቀስቀስ መልስ እንዲሰጥ ሳትጠብቁ ጥያቄዎቹን አንሱ። በጥያቄዎቹ ላይ አጠር ያለ ሐሳብ እንዲሰጥ መጋበዝም ትችላላችሁ። በሰጠው ሐሳብ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት ወይም የተሳሳተ መልስ ሰጥቶ ከሆነ ያንን ለማረም መሞከር አስፈላጊ አይደለም። ለሰጠው ሐሳብ ካመሰገናችሁት በኋላ በቀጥታ ጥናቱን ጀምሩ። በመግቢያ ጥያቄዎቹ ላይ የሰጠው ሐሳብ በየትኞቹ ነጥቦች ላይ ይበልጥ ማተኮር እንደሚያስፈልጋችሁ ለማወቅ ይረዳችኋል።
3. ጥናቱን ቀለል ባለ መንገድ መምራት የምንችለው እንዴት ነው?
3 ጥቅሶች:- ጥናቱ በጥቅሶች ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። (ዕብ. 4:12) ቢሆንም እያንዳንዱን ጥቅስ ማንበብ አስፈላጊ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለእምነታችን መሠረት ለሆኑት ጥቅሶች ትኩረት ስጡ። ተጨማሪ መረጃ የሚሰጡ ጥቅሶችን ማንበብ አያስፈልግ ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ እውነትን ባልተወሳሰበ መንገድ ያስተምራል። ጥናቱን ቀለል ባለ መንገድ ለመምራት ጥረት አድርጉ። በዋና ዋና ነጥቦች ላይ አተኩሩ፤ እንዲሁም ዝርዝር ሐሳቦችን አንስቶ ብዙ ከመናገር ወይም ሳያስፈልግ ስለ ርዕሱ የሚያብራራ ሌላ ጽሑፍ አምጥታችሁ ከማወያየት ተቆጠቡ።
4. በጥናቱ ወቅት በተጨማሪው ክፍል ላይ የሚገኙትን ሐሳቦች ጊዜ ወስዶ መወያየት ያስፈልግ እንደሆነና እንዳልሆነ የሚወስነው ምንድን ነው?
4 ተጨማሪ ክፍል:- ተጨማሪው ክፍል ዋናውን ነጥብ የሚደግፉ 14 ርዕሰ ጉዳዮችን ይዟል። በጥናቱ ወቅት በእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንደ አስፈላጊነቱ መወያየት ይቻላል። በተለይ ተማሪው በዋናው ጥናት ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እንደሚረዳውና እንደሚቀበለው ከተሰማችሁ በተጨማሪ ክፍሉ ላይ የቀረቡትን አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች በግሉ እንዲያነብ ልታበረታቱት ትችላላችሁ። ለምሳሌ፣ ተማሪው ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያምን ከሆነ “ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?” የሚለውን ምዕራፍ 4ን በምትወያዩበት ወቅት “ኢየሱስ ክርስቶስ—አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ” በሚለው ተጨማሪ ክፍል ላይ መወያየት ላያስፈልጋችሁ ይችላል። በሌሎች አጋጣሚዎች ደግሞ በጥናቱ ወቅት ተጨማሪ ክፍሉን ሙሉውን ወይም በከፊል መወያየቱ ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል።
5. በተጨማሪው ክፍል ላይ ለመወያየት ካሰብን ምን ማድረግ እንችላለን?
5 በተጨማሪው ክፍል ላይ ለመወያየት ካሰባችሁ ጥያቄዎችን ቀደም ብላችሁ በማዘጋጀት ዋናው ጥናት በሚመራበት መንገድ ልታጠኑ ትችላላችሁ። ወይም እንደ ተማሪው ሁኔታ ጥቂት ደቂቃዎችን ወስዳችሁ በዋናው ጥናት ወቅት ሐሳቦቹን አንድ ላይ ልትከልሱ ትችላላችሁ። እንደዚህ ማድረጋችሁ ተማሪው በግሉ ያነበበውን ሐሳብ ተረድቶት እንደሆነና እንዳልሆነ እርግጠኛ እንድትሆኑ ያስችላችኋል።
6. በእያንዳንዱ ጥናት መጨረሻ ላይ የሚገኘውን የክለሳ ሣጥን እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን?
6 የክለሳ ሣጥን:- በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ የሚገኘው ሣጥን ብዙውን ጊዜ መግቢያው ላይ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ የሚሆኑ ሐሳቦችን ይዟል። ጥናቱን ስትጨርሱ እነዚህን ሐሳቦች የምዕራፉን ዋና ዋና ነጥቦች ለመከለስ ልትጠቀሙባቸው ትችላላችሁ። አንዳንድ አስፋፊዎች እያንዳንዱን ሐሳብና ጥቅሶቹን ማንበብ ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። ከዚያም ጥቅሱ ሐሳቡን እንዴት እንደሚደግፍ ተማሪው በአጭሩ እንዲያብራራ ይጠይቁታል። አስጠኚው እንደዚህ ማድረጉ ተማሪው የትምህርቱ ዋና ዋና ነጥቦች የትኞቹ እንደሆኑና እነዚህን ትምህርቶች መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚደግፋቸው በግልጽ እንደገባው እንዲሁም ተማሪው ተስማምቶባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ያስችለዋል። በተጨማሪም ተማሪው እውነትን ለሌሎች ለመመሥከር መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት መጠቀም እንደሚችል ያሠለጥነዋል።
7. የተሰጠንን ተልእኮ ለመወጣት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን?
7 ሕዝቦችን እንድናስተምርና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠንን ተልእኮ መወጣት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው ውጤታማ መንገድ የኢየሱስን የማስተማሪያ ዘዴ መኮረጅ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ ይህንን እንድናደርግ ይረዳናል። ለሌሎች እውነትን ግልጽ፣ ቀላልና አስደሳች በሆነ መንገድ ለማስተማር ይህንን መጽሐፍ በጥሩ ሁኔታ ተጠቀሙበት።