ክርስቲያናዊ ሕይወት
የአምላክን ቃል ከፍ አድርጋችሁ ትመለከታላችሁ?
መጽሐፍ ቅዱስ የደራሲውን የይሖዋ አምላክን ሐሳብና እሱ የተናገራቸውን ነገሮች ይዟል። (2ጴጥ 1:20, 21) መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛ መሆኑ እንደሚረጋገጥ ያጎላል፤ እንዲሁም መላው የሰው ዘር በቅርቡ የተሻለ ሕይወት እንደሚጠብቀው ተስፋ ይሰጣል። በተጨማሪም የሰማዩ አባታችን ይሖዋ ምን ያህል አፍቃሪ አምላክ እንደሆነ ይገልጻል።—መዝ 86:15
ሁላችንም በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ የይሖዋን ቃል ከፍ አድርገን እንደምንመለከት የታወቀ ነው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብና ምክሩን በተግባር በማዋል ለዚህ ልዩ ስጦታ ያለንን አድናቆት እናሳያለን? ድርጊታችን “ሕግህን ምንኛ ወደድኩ!” በማለት የተናገረውን መዝሙራዊ ስሜት እንደምንጋራ የሚያሳይ ይሁን!—መዝ 119:97
ለመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ቦታ ይሰጡ ነበር—ተቀንጭቦ የተወሰደ (ዊልያም ቲንደል) የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት፤ ከዚያም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦
ዊልያም ቲንደል መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም የተነሳሳው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ያደረገው ጥረት በጣም አስደናቂ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
የቲንደል መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ወደ እንግሊዝ ይገቡ የነበረው እንዴት ነው?
እያንዳንዳችን የአምላክን ቃል ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?