የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w21 ሰኔ ገጽ 25
  • ይህን ያውቁ ኖሯል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይህን ያውቁ ኖሯል?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ግብር “የሠለጠነ ኅብረተሰብ” እንዲኖር ሲባል የሚከፈል ነው?
    ንቁ!—2004
  • “ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን ክፈሉ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ግብር መክፈል ይኖርብሃል?
    ንቁ!—2004
  • ግብርን በተመለከተ የሚሰማው ቅሬታ እየጨመረ መጥቷል
    ንቁ!—2004
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
w21 ሰኔ ገጽ 25
ኢየሱስ አንድ ዲናር ይዞ።

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በኢየሱስ ዘመን የኖሩ ሰዎች ምን ዓይነት ግብር መክፈል ይጠበቅባቸው ነበር?

ከጥንት ጀምሮ እስራኤላውያን ንጹሕ አምልኮን ለመደገፍ ገንዘብ የመስጠት ልማድ ነበራቸው። በኢየሱስ ዘመን ግን አይሁዳውያን የሚጠበቅባቸው ግብር እየበዛ ሄዶ ነበር፤ ይህም ከፍተኛ ጫና አሳድሮባቸው ነበር።

በአምላክ መቅደስ ውስጥ የሚከናወነውን አምልኮ ለመደገፍ፣ አዋቂ የሆኑ ሁሉም አይሁዳውያን ግማሽ ሰቅል (ሁለት ድራክማ) መክፈል ይጠበቅባቸው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይህ ገንዘብ፣ ሄሮድስ በገነባው ቤተ መቅደስ ውስጥ ለሚቀርቡት መሥዋዕቶችና ለሌሎች ወጪዎች ይውል ነበር። አንዳንድ አይሁዳውያን ወደ ጴጥሮስ ቀርበው ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ ያለውን አመለካከት ጠይቀውት ነበር። ኢየሱስ ይህ ግብር መከፈል የለበትም አላለም። እንዲያውም ኢየሱስ ይህን ግብር ለመክፈል የሚያስችል ሳንቲም ከየት እንደሚያገኝ ለጴጥሮስ ጠቁሞታል።—ማቴ. 17:24-27

በተጨማሪም በወቅቱ የነበሩ የአምላክ ሕዝቦች አሥራት ማውጣት ማለትም የሰብላቸውን አሊያም የገቢያቸውን አንድ አሥረኛ መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር። (ዘሌ. 27:30-32፤ ዘኁ. 18:26-28) የሃይማኖት መሪዎቹ ከእያንዳንዷ ነገር፣ ሌላው ቀርቶ “ከኮሰረት፣ ከእንስላልና ከከሙን” እንኳ አሥራት መውጣት እንዳለበት ያስተምሩ ነበር። ኢየሱስ አሥራት ማውጣትን አላወገዘም፤ ሆኖም የጸሐፍትንና የፈሪሳውያንን ግብዝነት አጋልጧል።—ማቴ. 23:23

በኢየሱስ ዘመን ሮማውያን አይሁዳውያንን ይገዙ ስለነበር ሕዝቡ ሌሎች የተለያዩ ግብሮችም ተጥለውበት ነበር። ለምሳሌ መሬት ያላቸው ሰዎች ግብር መክፈል ይጠበቅባቸው ነበር፤ ይህን ግብር በገንዘብ ወይም በዓይነት ሊከፍሉ ይችላሉ። ሕዝቡ ለመሬት ግብር የምርታቸውን ከ20 እስከ 25 በመቶ መክፈል ይጠበቅባቸው እንደነበር ይገመታል። በተጨማሪም እያንዳንዱ አይሁዳዊ በነፍስ ወከፍ ግብር መክፈል ይጠበቅበት ነበር። ፈሪሳውያን ኢየሱስን የጠየቁት ይሄኛውን ግብር በተመለከተ ነበር። ኢየሱስም ስለዚህ ግብር ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” አላቸው።—ማቴ. 22:15-22

በገቢ ወይም በወጪ ሸቀጦች ላይ የሚጣል ቀረጥም ነበር። እንዲህ ያለው ቀረጥ የሚሰበሰበው በወደቦች፣ በድልድዮች፣ በመስቀለኛ መንገዶች ወይም በከተማዎችና በገበያዎች መግቢያ ላይ ነበር።

በጥቅሉ ሲታይ በሮም አገዛዝ ሥር የነበሩ ሰዎች የተጣለባቸው ግብር ከአቅማቸው በላይ ነበር። የሮም ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ታሲተስ እንደገለጸው ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ይገዛ በነበረው በንጉሠ ነገሥት ጢባርዮስ ዘመን “ሶርያ እና ይሁዳ የተጣለባቸው ግብር በጣም ስለከበዳቸው ግብሩ እንዲቀነስላቸው ልመና አቅርበው ነበር።”

ግብር መክፈል ሸክም እንዲሆን ያደረገው ሌላው ነገር ደግሞ ግብሩ የሚሰበሰብበት መንገድ ነው። ግብር የሚሰበስቡት ሰዎች የሚመረጡት በጨረታ ነበር። ጨረታውን ያሸነፉት ሰዎች፣ ግብር ወይም ቀረጥ የሚሰበስቡላቸውን ሰዎች ይቀጥራሉ፤ ቀጣሪዎቹም ተቀጣሪዎቹም ትርፍ ለማግኘት ስለሚፈልጉ ሕዝቡን ተጨማሪ ገንዘብ ያስከፍሉታል። ዘኬዎስ እንዲህ ያሉ ቀረጥ ሰብሳቢዎችን ቀጥሮ ያሠራ የነበረ ይመስላል። (ሉቃስ 19:1, 2) ሕዝቡ ይህን አሠራር ይጠሉትና ቀረጥ ሰብሳቢዎቹን ይንቋቸው የነበረው ለዚህ ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ