የማጫ ዋጋ እንስሳም ሊሆን ይችላል
ይህን ያውቁ ኖሯል?
የጥንቶቹ እስራኤላውያን የማጫ ዋጋ ይከፍሉ የነበረው ለምንድን ነው?
በጥንት ዘመን የማጫ ዋጋ፣ አንድ ወንድ አንዲትን ሴት ለማግባት ሲያስብ ለሙሽሪት ቤተሰብ የሚሰጠው ክፍያ ነው። ንብረት፣ እንስሳት ወይም ገንዘብ በመስጠት ክፍያው ይፈጸም ነበር። የማጫ ዋጋ የጉልበት ሥራ በማከናወንም ሊከፈል ይችላል፤ ለምሳሌ ያዕቆብ ራሔልን ለማግባት ሲል አባቷን ለሰባት ዓመታት ለማገልገል ተስማምቶ ነበር። (ዘፍ. 29:17, 18, 20) የዚህ ባሕል ዓላማ ምን ነበር?
የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ካሮል ማየርዝ እንዲህ ብለዋል፦ “[በግብርና በሚተዳደር] ቤተሰብ ውስጥ ሴት ልጅ የምታከናውነው ሥራ በጣም አስፈላጊ ነው፤ በመሆኑም የማጫ ዋጋ ሴት ልጃቸውን ለሰጡት የሙሽሪት ቤተሰብ ማካካሻ ይሆናል።” በተጨማሪም የማጫ ዋጋ በጋብቻ የተሳሰሩትን ቤተሰቦች ወዳጅነት ያጠናክራል። እንዲህ ያለው ወዳጅነት ደግሞ በችግር ጊዜ ለመረዳዳት ይጠቅማል። በተጨማሪም የማጫ ዋጋ፣ አንዲት ሴት እንደታጨች እንዲሁም እንክብካቤና ጥበቃ ተደርጎላት ካደገችበት የአባቷ ቤት ወጥታ ወደ ባሏ ቤት ልትሸኝ መሆኑን ያረጋግጣል።
የማጫ ዋጋ መክፈል፣ ሚስት የምትሸጥ ወይም የምትለወጥ ንብረት ተደርጋ እንደምትቆጠር የሚያሳይ አይደለም። ኤንሸንት ኢዝራኤል—ኢትስ ላይፍ ኤንድ ኢንስትቲውሽንስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ሙሽራው ለሙሽሪት ቤተሰብ ገንዘብ ወይም ሌላ ተመጣጣኝ ነገር እንዲከፍል መገደዱ ላይ ላዩን ሲታይ እስራኤላውያን ሴት ልጅን ንብረት አድርገው የሚቆጥሩ ሊያስመስል ይችላል። ሆኖም [የማጫ ዋጋ] ለቤተሰቧ የሚሰጥ ካሳ እንጂ ልጅቷን ለመግዛት የሚከፈል ዋጋ ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም።”
በዛሬው ጊዜም በአንዳንድ አገሮች የማጫ ዋጋ የመክፈል ባሕል አለ። ክርስቲያን ወላጆች ከሚገባው በላይ የማጫ ዋጋ መጠየቅ የለባቸውም፤ በዚህ መንገድ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት እንደሚከተሉ ያሳያሉ። (ፊልጵ. 4:5፤ 1 ቆሮ. 10:32, 33) ይህን ማድረጋቸው “ገንዘብ የሚወዱ” ወይም ስግብግቦች እንዳልሆኑም ያሳያል። (2 ጢሞ. 3:2) በተጨማሪም ባልየው የሙሽሪት ወላጆች የጠየቁትን የተጋነነ ዋጋ ሠርቶ እስኪያገኝ ድረስ የሠርጉን ቀን ለማራዘም አይገደድም። ባልየው አቅኚ ከሆነም የተጠየቀውን ከፍተኛ ዋጋ ለመክፈል ሲል ‘አቅኚነቴን አቁሜ የሙሉ ቀን ሥራ ልሥራ’ ብሎ አያስብም።
በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች የማጫ ዋጋን የሚተምን ሕግ አለ። በእነዚህ ቦታዎች የሚኖሩ ክርስቲያን ወላጆች ለእነዚህ ሕጎች ይታዘዛሉ። ለምን? ምክንያቱም ክርስቲያኖች “ለበላይ ባለሥልጣናት [እንድንገዛ]” እንዲሁም የሚያወጧቸው ሕጎች ከአምላክ ሕጎች ጋር የሚጋጩ እስካልሆኑ ድረስ እንድንታዘዛቸው የአምላክ ቃል ያዘናል።—ሮም 13:1፤ ሥራ 5:29