የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w22 ሚያዝያ ገጽ 28-ገጽ 29 አን. 5
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአንባብያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • አምላክን በመታዘዝ በመሐላ ከገባው ቃል ተጠቃሚ ሁኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ይህን ያውቁ ኖሯል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • የገባኸውን ቃል ትጠብቃለህ?
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2017
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
w22 ሚያዝያ ገጽ 28-ገጽ 29 አን. 5

የአንባቢያን ጥያቄዎች

መጽሐፍ ቅዱስ ቃለ መሐላ መፈጸምን በተመለከተ ምን ይላል?

▪ ቃለ መሐላ እንዲህ የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል፦ “አንድ ሰው፣ አንድ ነገር ለማድረግ የሚገባው ቃል ነው፤ ቃሉ ክብደት የሚሰጠውና በሕግ የሚያስጠይቀው ነው። ብዙውን ጊዜ ግለሰቡ አምላክን . . . ምሥክሩ አድርጎ ይጠራል።” ቃለ መሐላው የቃል ወይም የጽሑፍ ሊሆን ይችላል።

አንዳንዶች ቃለ መሐላ መፈጸም ስህተት እንደሆነ ይሰማቸዋል፤ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት የተናገረውን ሐሳብ ነው፦ “ፈጽሞ አትማሉ . . . ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ግን ከክፉው ነው።” (ማቴ. 5:33-37) ኢየሱስ የሙሴ ሕግ ቃለ መሐላ መፈጸምን የሚጠይቅባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ያውቃል፤ አንዳንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ቃለ መሐላ እንደፈጸሙ ያውቅ እንደነበረም ግልጽ ነው። (ዘፍ. 14:22, 23፤ ዘፀ. 22:10, 11) ይሖዋ ራሱ በመሐላ ቃል እንደገባ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። (ዕብ. 6:13-17) በመሆኑም ኢየሱስ ‘ጨርሶ ቃለ መሐላ አትግቡ’ እያለ ሊሆን አይችልም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ በረባ ባልረባው ወይም ያለምንም ዓላማ እንዳንምል ማሳሰቡ ነበር። ቃላችንን መጠበቅ አምላክ የሚጠብቅብን ነገር እንደሆነ እንገነዘባለን። ቃል ከገባን ልንፈጽመው ይገባል።

ታዲያ ቃለ መሐላ እንድትፈጽም ብትጠየቅ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በመጀመሪያ ‘አደርገዋለሁ ብዬ ቃል የምገባውን ነገር ልፈጽመው እችላለሁ?’ የሚለውን ጉዳይ አስብበት። ይህን እርግጠኛ ካልሆንክ ቃል አለመግባትህ የተሻለ ይሆናል። የአምላክ ቃል “ስእለት ተስለህ ሳትፈጽም ከምትቀር ባትሳል ይሻላል” በማለት ያስጠነቅቀናል። (መክ. 5:5) ቀጥሎ ደግሞ ከምትፈጽመው ቃለ መሐላ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተመልከት፤ ከዚያም በመጽሐፍ ቅዱስ ከሠለጠነው ሕሊናህ ጋር የሚስማማ ውሳኔ አድርግ። ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።

አንድ ሰው ፍርድ ቤት ውስጥ ቃለ መሐላ ሲፈጽም፤ ቀኝ እጁን ወደ ላይ አንስቷል፤ ግራ እጁን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳርፏል።

ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ ቃለ መሐላዎች። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ምሥክሮች በትዳር ሲጣመሩ ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ። ሙሽራውና ሙሽሪት ‘በሕይወት አብረው እስከኖሩ ድረስ አንዳቸው ሌላውን ለመውደድ፣ ለመንከባከብና ለማክበር’ በአምላክና በምሥክሮች ፊት ቃል ይገባሉ። (አንዳንድ ጥንዶች ቃል ሲጋቡ እነዚህኑ ቃላት አይደግሙ ይሆናል፤ በአምላክ ፊት ግን ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።) ባልና ሚስት የሚባሉት ከዚህ በኋላ ነው፤ ትዳራቸው የዕድሜ ልክ ጥምረት ሊሆን ይገባል። (ዘፍ. 2:24፤ 1 ቆሮ. 7:39) የጋብቻ ቃለ መሐላ ተገቢና ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ነው።

ከአምላክ ፈቃድ ጋር የማይስማሙ ቃለ መሐላዎች። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ‘መሣሪያ ታጥቄ የአገሬን ዳር ድንበር አስከብራለሁ’ ወይም ‘በአምላክ ላይ ያለኝን እምነት እተዋለሁ’ ብሎ ቃለ መሐላ አይፈጽምም። ምክንያቱም እንዲህ ማድረግ ከአምላክ ሕግ ጋር ይጋጫል። ክርስቲያኖች ‘የዓለም ክፍል መሆን የለባቸውም’፤ በመሆኑም በዚህ ዓለም ውዝግቦችና ግጭቶች ውስጥ አይሳተፉም።—ዮሐ. 15:19፤ ኢሳ. 2:4፤ ያዕ. 1:27

ለሕሊና የተተዉ ቃለ መሐላዎች። አንዳንድ ቃለ መሐላዎችን ከመፈጸማችን በፊት ኢየሱስ “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” በማለት በሰጠው ምክር ላይ ማሰብ ሊያስፈልገን ይችላል።—ሉቃስ 20:25

አንድ ምሳሌ እንውሰድ፦ አንድ ክርስቲያን የአንድ አገር ዜጋ ለመሆን ወይም ፓስፖርት ለማውጣት ሲያመለክት የታማኝነት ቃለ መሐላ መፈጸም እንዳለበት አወቀ እንበል። የዚያ አገር የታማኝነት ቃለ መሐላ ከአምላክ ሕግ ጋር በግልጽ የሚጋጭ ነገር ለማድረግ ቃል እንዲገባ የሚጠይቀው ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናው ይህን ለማድረግ አይፈቅድለትም። ሆኖም የአገሩ መንግሥት፣ ከሕሊናው ጋር በሚስማማ መልኩ የቃለ መሐላውን ይዘት እንዲያስተካክል ይፈቅድለት ይሆናል።

በዚህ መንገድ የተስተካከለ ቃለ መሐላ መፈጸም በሮም 13:1 ላይ ከሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚስማማ ሊሆን ይችላል፤ ጥቅሱ “ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ” ይላል። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ቃለ መሐላ በመፈጸም መንግሥትን መታዘዙ ምንም ስህተት እንደሌለው ሊወስን ይችላል፤ ምክንያቱም አምላክም ቢሆን መንግሥትን እንዲታዘዝ እንደሚጠብቅበት ያውቃል።

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ቃለ መሐላ ስትፈጽም አንድ ዕቃ እንድትጠቀም ወይም የሆነ ዓይነት ምልክት እንድታሳይ ትጠየቅ ይሆናል፤ ይህም ቢሆን ለሕሊና የተተወ ጉዳይ ነው። የጥንቶቹ ሮማውያን እና እስኩቴሶች በሰይፋቸው ይምሉ ነበር፤ ይህን የሚያደርጉት፣ የተናገሩት ነገር እውነተኝነት በጦርነት አምላክ ፊት የተረጋገጠ መሆኑን ለማሳየት ነው። ግሪካውያን ደግሞ ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ እጃቸውን ወደ ሰማይ ያነሱ ነበር። ይህም የሚነገረውንና የሚደረገውን ነገር የሚያይ መለኮታዊ ኃይል እንዳለና የሰው ልጆች በፊቱ ተጠያቂ እንደሆኑ አምነው እንደሚቀበሉ የሚያሳይ ነበር።

አንድ የይሖዋ አገልጋይ ከሐሰት አምልኮ ጋር ግንኙነት ባለው ብሔራዊ አርማ እንደማይምል የታወቀ ነው። ሆኖም ፍርድ ቤት ምሥክርነት ለመስጠት ቀርበህ እጅህን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አድርገህ እውነቱን ለመናገር እንድትምል ብትጠየቅስ? እንዲህ ለማድረግ ልትወስን ትችላለህ፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ቃለ መሐላ ሲገቡ በእጃቸው ምልክት እንዳሳዩ የሚጠቅሱ ታሪኮች እናገኛለን። (ዘፍ. 24:2, 3, 9፤ 47:29-31) አንድ ነገር ግን ማስታወስ ይኖርብሃል፦ እንዲህ ዓይነቱን ቃለ መሐላ ስትፈጽም እውነቱን ለመናገር በአምላክ ፊት ቃል እየገባህ ነው። የሚቀርብልህን ማንኛውንም ጥያቄ በሐቀኝነት ለመመለስ ዝግጁ መሆን አለብህ።

ልናስብባቸው የሚገቡ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች

  • ማቴዎስ 5:37፦ “ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን።”

  • ዮሐንስ 15:19፦ “የዓለም ክፍል [አይደላችሁም]።”

  • ዘዳግም 5:9፦ “አምላክህ ይሖዋ እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግ . . . አምላክ ነኝ።”

  • ሮም 13:1፦ “ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ።”

  • ሉቃስ 20:25፦ “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ።”

  • 1 ጴጥሮስ 2:12፦ “መልካም ሥራችሁን በዓይናቸው ማየት እንዲችሉ . . . በዓለም ባሉ ሰዎች መካከል መልካም ምግባር ይኑራችሁ።”

ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ከፍ አድርገን ስለምንመለከተው ማንኛውንም ቃለ መሐላ ከመፈጸማችን በፊት ጉዳዩን በጸሎት ልናስብበት ይገባል። ቃለ መሐላው ከሕሊናችን ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ አለመሆኑን እርግጠኞች መሆን ይኖርብናል። ቃለ መሐላ ለመፈጸም ከወሰንን ደግሞ ቃላችንን መጠበቅ ይኖርብናል።—1 ጴጥ. 2:12

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ