የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w22 ጥቅምት ገጽ 2-5
  • 1922—የዛሬ መቶ ዓመት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • 1922—የዛሬ መቶ ዓመት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “ድንቅ ሐሳብ”
  • በሺዎች የሚቆጠሩ አድማጮችን በሬዲዮ ማግኘት
  • “ADV”
  • አስፈላጊ ሥራ
  • 1919—የዛሬ መቶ ዓመት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
  • 1924—የዛሬ መቶ ዓመት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ዘወትር በሚያደርገው እድገት ተወዳዳሪ ከሌለው ድርጅት ጋር ማገልገል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • 1921—የዛሬ መቶ ዓመት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
w22 ጥቅምት ገጽ 2-5
በ1922 የተካሄደው ትልቅ ስብሰባ መድረክ። ከመድረኩ በላይ “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ” የሚል ማስታወቂያ ተሰቅሏል። ከመድረኩ በስተ ጀርባ “ADV” የሚሉት ፊደላት ይታያሉ።

መድረኩና ከላይ ያለው ማስታወቂያ በቅርበት ሲታይ

1922—የዛሬ መቶ ዓመት

“አምላክ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ድል [ያጎናጽፈናል]።” (1 ቆሮ. 15:57) የ1922 የዓመት ጥቅስ እንዲሆን የተመረጠው ይህ ጥቅስ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ታማኝ ከሆኑ በረከት እንደሚያገኙ አረጋግጦላቸዋል። በእርግጥም በዚያ ዓመት ይሖዋ እነዚህን ቀናተኛ ሰባኪዎች ባርኳቸዋል። መጽሐፎቻቸውን ራሳቸው ማተምና መጠረዝ እንዲሁም በሬዲዮ አማካኝነት የመንግሥቱን እውነት ማሰራጨት በጀመሩበት ጊዜ የይሖዋ በረከት አልተለያቸውም። ከዚያም በ1922 መገባደጃ ላይ ይሖዋ ሕዝቡን እየባረከ እንዳለ በድጋሚ ታየ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ታሪካዊ ስብሰባ አደረጉ። ያ ስብሰባ በይሖዋ ድርጅት እንቅስቃሴ ላይ ዛሬ ድረስ የሚታይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።

“ድንቅ ሐሳብ”

የስብከቱ ሥራ እየሰፋ ሲሄድ ተጨማሪ ጽሑፎች አስፈለጉ። በብሩክሊን ቤቴል የነበሩት ወንድሞች መጽሔቶችን ያትሙ የነበረ ቢሆንም ጠንካራ ሽፋን ያላቸውን መጻሕፍት የሚያሳትሙት በማተሚያ ቤቶች ነበር። ለወራት የዘለቀ የመጻሕፍት እጥረት መከሰቱ በስብከቱ ሥራ ላይ እንቅፋት ፈጥሮ ነበር። በዚህ ጊዜ ወንድም ራዘርፎርድ የማተሚያ ክፍሉ ኃላፊ የሆነውን ሮበርት ማርቲንን መጽሐፎቻችንን ራሳችን ማተም እንችል እንደሆነ ጠየቀው።

በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በኮንኮርድ አውራ ጎዳና ላይ የነበረው ፋብሪካ

ወንድም ማርቲን እንዲህ ብሏል፦ “ድንቅ ሐሳብ ነበር። ምክንያቱም መጻሕፍት ለማተምና ለመጠረዝ የሚያስችል አዲስ ፋብሪካ ልንከፍት ነው።” ወንድሞች ብሩክሊን ውስጥ በ18 ኮንኮርድ አውራ ጎዳና ላይ ሕንፃ ተከራዩ። ከዚያም የሚያስፈልጉትን መሣሪያዎች አሟሉ።

እርግጥ ይህ አዲስ ፋብሪካ በመከፈቱ የተደሰተው ሁሉም ሰው አልነበረም። ቀደም ሲል መጽሐፎቻችንን ያትምልን የነበረው ፋብሪካ ፕሬዚዳንት አዲሱን ፋብሪካ ጎብኝተው ነበር፤ እንዲህ ብለዋል፦ “ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው የሕትመት መሣሪያዎች በእጃችሁ ቢገኙም መሣሪያዎቹን ማንቀሳቀስ የሚችል ሰው በመካከላችሁ የለም። ምናለ በሉኝ፣ ይህን ማሽን በስድስት ወራት ውስጥ እንክትክቱን አውጥታችሁ ታስቀምጡታላችሁ።”

ወንድም ማርቲን እንዲህ ብሏል፦ “እኚህ ሰው የተናገሩት ነገር ምክንያታዊ ነበር፤ ይሁንና የሰጡት ሐሳብ ጌታን ከግምት ውስጥ ያስገባ አልነበረም፤ እሱ ደግሞ ዘወትር ከእኛ ጋር ነው።” ወንድም ማርቲን ትክክል ነበር። ብዙም ሳይቆይ በአዲሱ ፋብሪካ በቀን 2,000 መጻሕፍት ማተም ጀመርን።

ወንድሞች ፋብሪካ ውስጥ ከማተሚያ ማሽን አጠገብ ቆመው

በሺዎች የሚቆጠሩ አድማጮችን በሬዲዮ ማግኘት

የይሖዋ ሕዝቦች የራሳቸውን መጻሕፍት ከማተም በተጨማሪ ምሥራቹን ለማስፋፋት አዲስ ዘዴ ይኸውም የሬዲዮ ስርጭት መጠቀም ጀመሩ። እሁድ፣ የካቲት 26, 1922 ከሰዓት በኋላ ወንድም ራዘርፎርድ ለመጀመሪያ ጊዜ በሬዲዮ ቀረበ። በሎስ አንጅለስ፣ ካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ አንድ የሬዲዮ ጣቢያ “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚለውን ንግግር አቀረበ።

ፕሮግራሙን 25,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተከታትለውታል። አንዳንዶቹ ከንግግሩ በኋላ የአድናቆት ደብዳቤ ጽፈዋል። ደብዳቤ ከላኩት ሰዎች መካከል አንዱ በሳንታ አና፣ ካሊፎርኒያ የሚኖረው ዊላርድ አሽፎርድ ነው። ዊላርድ፣ ወንድም ራዘርፎርድ “አዝናኝና አስተማሪ” ንግግር በማቅረቡ አመስግኖታል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ቤታችን ውስጥ ሦስት የታመሙ ሰዎች አሉ። ስለዚህ በሬዲዮ ባይሆን ኖሮ እዚህ ሰፈር ድረስ ብትመጣ እንኳ ንግግርህን መስማት አንችልም ነበር።”

በቀጣዮቹ ሳምንታት የሬዲዮ ስርጭቱ ቀጠለ። መጠበቂያ ግንብ እንደገለጸው እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ቢያንስ 300,000 ሰዎች መልእክቱን በሬዲዮ አማካኝነት ሰምተዋል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በተገኘው ምላሽ ስለተበረታቱ ከብሩክሊን ቤቴል ብዙም ሳይርቅ በስታተን ደሴት ላይ የሬዲዮ ጣቢያ ለመገንባት ወሰኑ። በቀጣዮቹ ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ WBBR የተባለውን ይህን የሬዲዮ ጣቢያ የመንግሥቱን ምሥራች በስፋት ለማዳረስ ተጠቅመውበታል።

“ADV”

የሰኔ 15, 1922 መጠበቂያ ግንብ ከመስከረም 5 እስከ 13, 1922 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ ትልቅ ስብሰባ እንደሚካሄድ ገለጸ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ወደ ሴዳር ፖይንት ሲሄዱ ስብሰባውን ለመከታተል በጣም ጓጉተው ነበር።

ወንድም ራዘርፎርድ በመክፈቻ ንግግሩ ላይ እንዲህ አለ፦ “ጌታ . . . ይህንን ስብሰባ እንደሚባርከውና በምድር ላይ ታይቶ የማይታወቅ ምሥክርነት እንዲሰጥ እንደሚያደርግ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።” በዚያ ስብሰባ ላይ የነበሩት ተናጋሪዎች፣ ወንድሞችና እህቶች በስብከቱ ሥራ እንዲካፈሉ በተደጋጋሚ አበረታተዋል።

በ1922 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ በተደረገው ስብሰባ ላይ የተገኙ ታዳሚዎች

ከዚያም ዓርብ፣ መስከረም 8 ወንድም ራዘርፎርድ የሚሰጠውን ንግግር ለመስማት የጓጉ 8,000 ገደማ ሰዎች ወደ አዳራሹ ጎረፉ። ወንድም ራዘርፎርድ በመጋበዣ ወረቀቱ ላይ የሰፈሩትን “ADV” የሚሉትን የእንግሊዝኛ ፊደላት ትርጉም እንደሚያብራራ ተስፋ አድርገው ነበር። ተሰብሳቢዎቹ ቦታ ቦታቸውን ሲይዙ አንዳንዶቹ ከመድረኩ በላይ የተጠቀለለውን ሸራ አስተውለው መሆን አለበት። ከተልሳ፣ ኦክላሆማ የመጣው አርተር ካላውስ ስብሰባውን በደንብ ሊያዳምጥ የሚችልበት ቦታ አግኝቶ ነበር። በወቅቱ የድምፅ ማጉያ ስላልነበር እንዲህ ያለ ቦታ ማግኘት በጣም ጠቃሚ ነው።

“ከአፉ የሚወጣው እያንዳንዱ ቃል እንዳያመልጠን በጥሞና እናዳምጥ ነበር”

ስብሰባውን የሚረብሽ ምንም ነገር እንዳይኖር፣ ወንድም ራዘርፎርድ ንግግር እየሰጠ አርፍዶ የመጣ ሰው ወደ አዳራሹ መግባት እንደማይችል ሊቀ መንበሩ ተናገረ። ከጠዋቱ 3:30 ላይ ወንድም ራዘርፎርድ፣ ኢየሱስ በማቴዎስ 4:17 ላይ የተናገረውን ሐሳብ በመጥቀስ ንግግሩን ጀመረ፤ ጥቅሱ ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል’ ይላል። ወንድም ራዘርፎርድ ሰዎች ስለ መንግሥቱ የሚሰሙት እንዴት እንደሆነ ሲያብራራ እንዲህ አለ፦ “ኢየሱስ ራሱ በመገኘቱ ጊዜ የመከር ሥራ እንደሚያካሂድና እውነተኛና ታማኝ ሰዎችን ወደ ራሱ እንደሚሰበስብ ተናግሯል።”

በዋናው አዳራሽ ተቀምጦ የነበረው አርተር እንዲህ ብሏል፦ “ከአፉ የሚወጣው እያንዳንዱ ቃል እንዳያመልጠን በጥሞና እናዳምጥ ነበር።” ሆኖም አርተር በድንገት በመታመሙ ከአዳራሹ ለመውጣት ተገደደ። አርተር ተመልሶ መግባት እንደማይፈቀድለት ስላወቀ እያመነታ ወጣ።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ግን ተሻለው። ወደ አዳራሹ እየተመለሰ ሳለ ሞቅ ያለ ጭብጨባ ሰማ። በዚህ ጊዜ በጣም ጓጓ! ይህን ግሩም ንግግር ለመስማት ሲል ጣሪያው ላይ ለመውጣት ወሰነ። በወቅቱ የ23 ዓመት ወጣት የነበረው አርተር ወደ ጣሪያው የሚወስድ መወጣጫ አገኘ። ጣሪያው ላይ ያሉት የብርሃን ማስገቢያ መስኮቶች ክፍት ነበሩ። አርተር ወደ መስኮቶቹ ሲጠጋ ንግግሩ ‘ጥርት ብሎ ይሰማው’ ጀመር።

ሆኖም አርተር ብቻውን አልነበረም። አንዳንዶቹ ጓደኞቹም ጣሪያው ላይ ነበሩ። ከእነሱ መካከል አንዱ የሆነው ፍራንክ ጆንሰን ወደ አርተር ሮጦ በመምጣት “ሴንጢ ይዘሃል?” አለው።

አርተርም “አዎ ይዣለሁ” አለው።

ፍራንክ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ከሆነማ የጸሎታችን መልስ አንተ ነህ። ይሄ ትልቅ የተጠቀለለ ሸራ ይታይሃል? ማስታወቂያ ነው፤ ሚስማሩ ላይ ታስሯል። ዳኛውa የሚናገረውን በጥሞና አዳምጥ። ‘አስታውቁ፣ አስታውቁ’ ሲል እነዚህን አራት ገመዶች መቁረጥ አለብን።”

በመሆኑም አርተር ሴንጢውን ይዞ ወንድም ራዘርፎርድ ያንን ቃል እስኪናገር ከጓደኞቹ ጋር መጠበቅ ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ወንድም ራዘርፎርድ የንግግሩ ወሳኝ ክፍል ላይ ደረሰ። ወንድም ራዘርፎርድ በስሜትና በቅንዓት ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “ለጌታ ታማኝና እውነተኛ ምሥክር ሁኑ። የባቢሎን ርዝራዦች በሙሉ እስኪወገዱ ድረስ በውጊያው ወደፊት ግፉ። መልእክቱን በስፋት ብሎም ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች በመሄድ አውጁ። ይሖዋ፣ አምላክ እንደሆነና ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ እንደሆነ የዓለም ሕዝብ ማወቅ ይኖርበታል። ይህ የቀኖች ሁሉ ቀን ነው። እነሆ ንጉሡ በመግዛት ላይ ነው! እናንተ ደግሞ የእሱ አዋጅ ነጋሪዎች ናችሁ። ስለዚህ ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ!”

አርተር እንደገለጸው፣ እሱና ሌሎቹ ወንድሞች ገመዶቹን ሲቆርጡ ሸራው ያለምንም ችግር ተተረተረ። ማስታወቂያው “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ” የሚል ነበር። “ADV” የሚሉት ፊደላት የሚያመለክቱት “አስታውቁ” የሚል ትርጉም ያለውን የእንግሊዝኛ ቃል ነው።

አስፈላጊ ሥራ

በሴዳር ፖይንት የተደረገው ትልቅ ስብሰባ፣ ወንድሞች በጣም አስፈላጊ በሆነው የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩ ሥራ ላይ እንዲያተኩሩ ረድቷቸዋል። የፈቃደኝነት መንፈስ ያላቸው ሁሉ በዚህ ሥራ በደስታ ተካፍለዋል። በኦክላሆማ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚያገለግል አንድ ኮልፖርተር (በአሁኑ ጊዜ አቅኚ ተብሎ ይጠራል) እንዲህ ብሏል፦ “የምንሰብከው የድንጋይ ከሰል በሚወጣበት አካባቢ ሲሆን ብዙዎቹ ሰዎች ድሆች ነበሩ።” ይህ ወንድም ብዙውን ጊዜ ሰዎች ወርቃማው ዘመን በተባለው መጽሔት ላይ ያለውን መልእክት ሲሰሙ ‘ማልቀስ እንደሚጀምሩ’ ተናግሯል። “እነሱን ማጽናናት ልዩ መብት ነው” ብሏል።

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ኢየሱስ በሉቃስ 10:2 ላይ “አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው” በማለት የተናገረው ሐሳብ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንደሚጠይቅ ተገንዝበዋል። በዚያ ዓመት መገባደጃ ላይ መንግሥቱን ከዳር እስከ ዳር ለማስታወቅ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆርጠው ነበር።

a ወንድም ራዘርፎርድ በሚዙሪ፣ ዩናይትድ ስቴትስ አልፎ አልፎ ዳኛ ሆኖ ይሠራ ስለነበር አንዳንድ ጊዜ “ዳኛው” ተብሎ ይጠራል።

ለመላው ዓለም መመሥከር

የካቲት 26, 1922 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ “ዓለም አቀፍ የምሥክርነት ዘመቻ” አካሄዱ። በዓለም ዙሪያ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ልዩ ስብሰባዎችን በማካሄድ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚለውን ንግግር እንዲያዳምጡ አደረጉ።

ንግግሩ ቢያንስ በ33 ቋንቋዎች ተተርጉሟል፤ መጠበቂያ ግንብ እንደገለጸው፣ በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ብቃት ያላቸው የሕዝብ ተናጋሪዎች በሙሉ ማለት ይቻላል ይህን ንግግር ሰጥተዋል። በታላቋ ብሪታንያ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች 306 ስብሰባዎችን ያካሄዱ ሲሆን 67,010 ሰዎች በስብሰባዎቹ ላይ ተገኝተዋል። በስዊዘርላድ፣ በቤልጅየምና በፈረንሳይ የሚኖሩ ከ15,000 በላይ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች እነዚህ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ያገኙት አዎንታዊ ምላሽ ስላበረታታቸው በዚያው ዓመት ሰኔ 25፣ ጥቅምት 29 እና ታኅሣሥ 10 ላይ “ዓለም አቀፍ የምሥክርነት ዘመቻ” አካሄዱ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ