የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w24 ሐምሌ ገጽ 26-29
  • ከአዲስ ጉባኤ ጋር መላመድ የሚቻለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከአዲስ ጉባኤ ጋር መላመድ የሚቻለው እንዴት ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ቶሎ ለመላመድ የሚረዱ አራት መሠረታዊ ሥርዓቶች
  • “አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ”
  • እድገት ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ
  • የመኖሪያ ቦታ ልትቀይር ነውን?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1999
  • ከአዲሱ ጉባኤህ ጋር መላመድ የምትችለው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • ጉባኤው እየተጠናከረ ይሂድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ ቦታ አለህ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
w24 ሐምሌ ገጽ 26-29

ከአዲስ ጉባኤ ጋር መላመድ የሚቻለው እንዴት ነው?

ጉባኤ ቀይረህ ታውቃለህ? ከሆነ ዣን-ሻርል በሰጠው ሐሳብ ትስማማ ይሆናል፦ “የሁሉንም የቤተሰብ አባላት መንፈሳዊነት ጠብቆ ከአዲስ ጉባኤ ጋር መላመድ ተፈታታኝ ነው።” ወደ ሌላ አካባቢ የሚዛወሩ ሰዎች ሥራ፣ ቤትና አዲስ ትምህርት ቤት ከመፈለግ በተጨማሪ ከአዲስ የአየር ሁኔታ፣ ባሕልና የአገልግሎት ክልል ጋር መላመድ ይጠበቅባቸው ይሆናል።

ኒኮላ እና ሴሊን ደግሞ ለየት ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ የሰጣቸውን ምድብ ተቀብለው ወደ አዲስ ጉባኤ ተዛወሩ። እንዲህ ብለዋል፦ “መጀመሪያ ላይ በጣም ተደስተን ነበር። በኋላ ግን የጓደኞቻችን ናፍቆት አስቸገረን። በአዲሱ ጉባኤያችን ካሉት ወንድሞች ጋር ገና በደንብ አልተቀራረብንም ነበር።”a ታዲያ ጉባኤ መቀየር የሚያስከትላቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ተቋቁመህ ደስተኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ሌሎች እርዳታ ማበርከት የሚችሉት እንዴት ነው? እንዲሁም በአዲሱ ጉባኤህ ካሉት ክርስቲያኖች ጋር እርስ በርስ መበረታታት የምትችለው እንዴት ነው?

ቶሎ ለመላመድ የሚረዱ አራት መሠረታዊ ሥርዓቶች

አንዲት እህት ዕቃዎቿን እየፈታች ሳለ መሃል ላይ አረፍ ብላ መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብ።

በይሖዋ ታመን

1. በይሖዋ ታመን። (መዝ. 37:5) በጃፓን የምትኖረው ካዙሚ፣ ባለቤቷ የሥራ ቦታ በቀየረበት ወቅት ለ20 ዓመታት የኖረችበትን ጉባኤ ቀየረች። ታዲያ ‘መንገዷን ለይሖዋ አደራ የሰጠችው’ እንዴት ነው? እንዲህ ብላለች፦ “የተሰማኝን ፍርሃት፣ ብቸኝነትና ጭንቀት አስመልክቶ ወደ ይሖዋ በተደጋጋሚ ጸለይኩ። እንዲህ ባደረግኩ ቁጥር ይሖዋ የሚያስፈልገኝን ብርታት ሰጥቶኛል።”

በይሖዋ ይበልጥ መታመን የምትችለው እንዴት ነው? አንድ ተክል ለማደግ ከአፈር ውኃና ንጥረ ነገሮች ማግኘት እንደሚያስፈልገው ሁሉ እኛም እምነታችን እንዲያድግ ከፈለግን ልንመግበው ይገባል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኒኮላ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሲሉ ብዙ መሥዋዕቶችን በከፈሉት በአብርሃም፣ በኢየሱስና በጳውሎስ ምሳሌ ላይ ማሰላሰሉ ይሖዋ እንደሚደግፈው ያለውን እምነት እንዳጠናከረለት ገልጿል። ቋሚ የግል ጥናት ልማድ ማዳበርህ በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ለውጦች ለማስተናገድ ብቻ ሳይሆን በአዲሱ ጉባኤህ ውስጥ ላሉ ክርስቲያኖች ማካፈል የምትችለው መንፈሳዊ ስጦታ ለማግኘትም ይረዳሃል።

አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ሁለት ወጣት ወንድሞች የአዳራሹን የኦዲዮ/ቪዲዮ መሣሪያ እንዴት እንደሚጠቀሙ ሲያብራሩለት ሲያዳምጥ።

ከማወዳደር ተቆጠብ

2. ከማወዳደር ተቆጠብ። (መክ. 7:10) ዡል ከቤኒን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በተዛወረበት ወቅት ሰፊ የባሕል ልዩነት እንዳለ አስተውሏል። እንዲህ ብሏል፦ “አዲስ ሰው በተዋወቅኩ ቁጥር ሙሉውን የሕይወት ታሪኬን መናገር እንደሚጠበቅብኝ ተሰማኝ።” ሁኔታው ከለመደው የተለየ ስለሆነበት ራሱን ከጉባኤው ማግለል ጀመረ። ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር በደንብ ከተዋወቀ በኋላ ግን አመለካከቱን አስተካከለ። እንዲህ ብሏል፦ “የምንኖረው የትም ይሁን የት፣ ሁሉም የሰው ልጆች አንድ ዓይነት እንደሆኑ ተገንዝቤያለሁ። የሚለያየው ራሳቸውን የሚገልጹበት መንገድ ብቻ ነው። ሰዎችን በማንነታቸው መቀበል በጣም አስፈላጊ ነው።” ስለዚህ አዲሱን ጉባኤ ከቀድሞው ጉባኤህ ጋር ከማወዳደር ተቆጠብ። አን-ሊዝ የተባለች አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “ወደ ሌላ አካባቢ የተዛወርኩት ትቼ የመጣሁትን ነገር ለማግኘት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አዳዲስ ነገሮችን ለማግኘት ነው።”

ሽማግሌዎችም በአዲሱ ጉባኤያቸው ያለውን ሁኔታ ከቀድሞው ጉባኤያቸው ጋር ከማወዳደር መቆጠብ ይኖርባቸዋል። አንድ አሠራር የተለየ ነው ማለት የተሳሳተ ነው ማለት አይደለም። ሐሳብ ከመስጠትህ በፊት በጉባኤው ያለውን ሁኔታ በደንብ መረዳትህ ጥበብ ይሆናል። (መክ. 3:1, 7ለ) አመለካከትህን በጉባኤው ላይ ከመጫን ይልቅ ጥሩ ምሳሌ ሆነህ መገኘትህ የተሻለ ነው።—2 ቆሮ. 1:24

ሁለት ወንድሞች የስብሰባ አዳራሹን መስኮት ሲያጸዱ።

በጉባኤው እንቅስቃሴዎች ተካፈል

3. በጉባኤው እንቅስቃሴዎች ተካፈል። (ፊልጵ. 1:27) አካባቢ መቀየር ብዙ ጊዜና ጉልበት ይጠይቃል። ያም ቢሆን ከመነሻው አንስቶ ከተቻለ በአካል በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትህ በጣም አስፈላጊ ነው። ደግሞም በአዲሱ ጉባኤህ ውስጥ ያሉት ወንድሞችና እህቶች ብዙ ጊዜ የማያዩህ ከሆነ እንዴት ሊረዱህ ይችላሉ? ከሁለት ሴቶች ልጆቿ ጋር በደቡብ አፍሪካ ወደሚገኝ ትልቅ ከተማ የተዛወረችው ሉሲንዳ እንዲህ ብላለች፦ “በተቻለኝ መጠን በጉባኤው እንቅስቃሴዎች አዘውትሬ እንድካፈል ማለትም ከሌሎች ጋር አብሬ እንዳገለግልና በጉባኤ ስብሰባ እንድሳተፍ ምክር ተሰጥቶኝ ነበር። በተጨማሪም በቤታችን ውስጥ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ እንዲካሄድ ፈቃደኛ ሆንን።”

በአዲሱ ጉባኤህ ውስጥ ካሉት ወንድሞችና እህቶች ጋር “አንድ ላይ ሆናችሁ” በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች መካፈላችሁ “በምሥራቹ ላይ ያላችሁን እምነት ጠብቃችሁ ለመኖር” ይረዳችኋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አን-ሊዝ የጉባኤ ሽማግሌዎቿ ከሁሉም ሰው ጋር ለማገልገል ጥረት እንድታደርግ አበረታተዋት ነበር። ውጤቱስ ምን ሆነ? “ከጉባኤው ጋር ለመቀላቀል የሚረዳ ግሩም ዘዴ እንደሆነ ወዲያውኑ አስተዋልኩ” ብላለች። ከዚህም ሌላ የስብሰባ አዳራሹን እንደማጽዳትና እንደመጠገን ባሉ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ራስህን ማቅረብህ ጉባኤውን ጉባኤህ አድርገህ መመልከት እንደጀመርክ ይጠቁማል። በጉባኤው እንቅስቃሴዎች ይበልጥ መካፈልህ የጉባኤው ወንድሞችና እህቶች ቶሎ እንዲቀበሉህና ጉባኤው ቤተሰብህ እንደሆነ እንዲሰማህ ይረዳሃል።

ሁለት ጥንዶች አብረው ሲመገቡ።

አዳዲስ ጓደኞችን አፍራ

4. አዳዲስ ጓደኞችን አፍራ። (2 ቆሮ. 6:11-13) ጓደኛ ማፍራት የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ ትኩረት መስጠት ነው። ስለዚህ ከስብሰባዎች በፊትና በኋላ ከሌሎች ጋር ለመነጋገርና ለመተዋወቅ የሚያስችል በቂ ጊዜ አመቻች። ስማቸውን ለማወቅ የታሰበበት ጥረት አድርግ። የሰዎችን ስም ማስታወስህ እንዲሁም ሞቅ ያልክና በቀላሉ የምትቀረብ መሆንህ ሌሎች እንዲቀርቡህ ያነሳሳቸዋል። ይህ ደግሞ አዳዲስ ጓደኞችን ለማፍራት እንደሚረዳህ ምንም ጥያቄ የለውም።

በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ስለማግኘት ከመጨነቅ ይልቅ አዳዲሶቹ ወንድሞችህና እህቶችህ እውነተኛውን ማንነትህን እንዲያውቁ ፍቀድላቸው። የሉሲንዳን ምሳሌ ተከተል፤ እንዲህ ብላለች፦ “ቅድሚያውን ወስደን ሌሎችን ቤታችን በመጋበዛችን የቅርብ ወዳጆችን ማፍራት ችለናል።”

“አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ”

አንዳንዶች በማያውቋቸው ሰዎች ወደተሞላ የስብሰባ አዳራሽ መግባት ሊያስጨንቃቸው ይችላል። ታዲያ ወደ ጉባኤያችን የሚመጡ ወንድሞች ሁኔታው እንዲቀላቸው ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “ክርስቶስ እኛን እንደተቀበለን ሁሉ . . . እናንተም አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ” የሚል ማበረታቻ ሰጥቷል። (ሮም 15:7) ሽማግሌዎች የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል አዲሶችን ጥሩ አድርገው መቀበል ይችላሉ። (“ስኬታማ ለመሆን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ነገሮች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ይሁንና ልጆችን ጨምሮ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሁሉ አዲሶችን በመቀበል ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ።

ስኬታማ ለመሆን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ነገሮች

አንተ ማድረግ ያለብህ ነገር፦ ከሁለቱም ጉባኤዎች ሽማግሌዎች ጋር አስቀድመህ በመነጋገር አካባቢ ለመቀየር ያሰብክበትን ቀን፣ አዲሱን አድራሻህንና ስልክ ቁጥርህን አሳውቃቸው። የስብሰባ አዳራሹ የሚገኝበትን ቦታና ስብሰባ የሚካሄድበትን ሰዓት ለማወቅ ጥረት አድርግ። በአዲሱ ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ ላይ ስትገኝ ለሽማግሌዎችና ለሌሎች ወንድሞች ራስህን አስተዋውቅ።

ሽማግሌዎች ማድረግ ያለባቸው ነገር፦ የቀድሞው ጉባኤ ጸሐፊ የማስተዋወቂያ ደብዳቤውንና የጉባኤ የአስፋፊ መዝገብ ካርዱን (ካርዶቹን) ቶሎ ብሎ ወደ አዲሱ ጉባኤ መላክ አለበት። የአዲሱ ጉባኤ የአገልግሎት ኮሚቴ አዲስ የመጡትን አስፋፊዎች ወዲያውኑ በመስክ አገልግሎት ቡድን ውስጥ ሊመድባቸው ይገባል። የቡድን የበላይ ተመልካቹ አዲሶቹን አስፋፊዎች ሄዶ ቢጠይቃቸውና ቢያበረታታቸው ደስ እንደሚላቸው ምንም ጥያቄ የለውም።

ሌሎችን መቀበል ቤታችን መጋበዝን ይጨምራል፤ ሆኖም ለሌሎች ተግባራዊ እርዳታ መስጠትንም ሊያካትት ይችላል። ለምሳሌ አንዲት እህት ውድ ጊዜዋን በመሠዋት፣ ወደ አካባቢዋ ለተዛወረች እህት አካባቢውን አስጎበኘቻት፤ እንዲሁም የሕዝብ መጓጓዣ መጠቀም የምትችልበትን መንገድ አሳየቻት። እህታችን ያደረገችው ነገር አዲሷን እህት ልቧን የነካው ከመሆኑም ሌላ አካባቢውን ቶሎ እንድትለምድ ረድቷታል።

እድገት ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ

አንድ አንበጣ እድገት በሚያደርግበት ጊዜ ክንፎቹ መብረር ከመቻላቸው በፊት ቆዳውን ብዙ ጊዜ ይገለፍፋል። አንተም በተመሳሳይ ጉባኤ በምትቀይርበት ጊዜ ክንፎችህን ዘርግተህ በይሖዋ አገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ እንዳታደርግ የሚያግድህን ማንኛውንም የፍርሃት ስሜት ገልፍፈህ መጣል ይኖርብሃል። ኒኮላ እና ሴሊን እንዲህ ብለዋል፦ “ጉባኤ መቀየር ግሩም ሥልጠና ነው። ከአዳዲስ ሰዎችና ከአዲስ አካባቢ ጋር መላመዳችን አዳዲስ ባሕርያትን እንድናዳብር አጋጣሚ ፈጥሮልናል።” በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ዣን-ሻርል ቤተሰቡ ያገኘውን ጥቅም ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ለውጡ ልጆቻችን በአዲሱ ጉባኤ ውስጥ እድገት እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። ከጥቂት ወራት በኋላ ሴቷ ልጃችን በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ክፍል ማቅረብ ጀመረች፤ ወንዱ ልጃችን ደግሞ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆነ።”

ይሁንና ሁኔታህ ወደ ሌላ አካባቢ፣ ምናልባትም የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ለመዛወር የማይፈቅድልህ ከሆነስ? አሁን ያለህበትን ጉባኤ እንደ አዲስ አድርገህ በመቁጠር ከላይ ከተዘረዘሩት ሐሳቦች አንዳንዶቹን በሥራ ላይ ለማዋል ለምን አትሞክርም? በይሖዋ ታመን፤ ከተለያዩ ሰዎች ጋር አብረህ ለማገልገል ጥረት በማድረግ በጉባኤው እንቅስቃሴዎች የተሟላ ተሳትፎ አድርግ፤ እንዲሁም አዳዲስ ጓደኞችን ለማፍራት ወይም አሁን ካሉህ ጓደኞች ጋር ያለህን ወዳጅነት ለማጠናከር ጥረት አድርግ። ለአዲሶች ወይም ለተቸገሩ ወንድሞች ተግባራዊ እርዳታ መስጠት ትችል ይሆን? ፍቅር የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ስለሆነ እንዲህ ማድረግህ ለመንፈሳዊ እድገትህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ምንም ጥያቄ የለውም። (ዮሐ. 13:35) “አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ [እንደሚደሰት]” እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ዕብ. 13:16

ወደ አዲስ ጉባኤ መዛወር የተለያዩ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩትም በርካታ ክርስቲያኖች በዚህ ሂደት ደስተኛ መሆን ችለዋል፤ አንተም እንዲሁ ማድረግ ትችላለህ! አን-ሊዝ “ጉባኤ መቀየሬ ፍቅሬን እንዳሰፋ ረድቶኛል” ብላለች። ካዙሚ “ጉባኤ መቀየር የይሖዋን ድጋፍ ከዚህ በፊት አይተን በማናውቀው መንገድ ለማየት እንደሚረዳን” ተገንዝባለች። ዡል ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “አዳዲስ ጓደኞች ስላፈራሁ አሁን እንግድነት አይሰማኝም። እንዲያውም ከአዲሱ ጉባኤዬ ጋር በጣም ከመላመዴ የተነሳ ከእነሱ መለየት የሚከብደኝ ይመስለኛል።”

a ናፍቆትን መቋቋም ስለሚቻልበት መንገድ ጠቃሚ ምክር ለማግኘት በግንቦት 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “አምላክን ስታገለግል የሚያጋጥምህን ናፍቆት ታግሎ ማሸነፍ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ