የመኖሪያ ቦታ ልትቀይር ነውን?
ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ አዎን፣ የሚል ከሆነ አንተም ሆንክ ሌሎች አስባችሁ ልታደርጓቸው የሚገቡ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። ቀጥሎ የቀረቡትን መሠረታዊ እርምጃዎች በመውሰድ አዲሱን ጉባኤህን ወዲያውኑ መላመድ ትችላለህ።
(1) መኖሪያ ለውጠህ የምትሄድበትን ቦታ ካወቅህ አሁን ያለህበት ጉባኤ ጸሐፊ የአዲሱ ጉባኤህን የመንግሥት አዳራሽ አድራሻ ሊያገኝልህ ይችል ይሆናል። እዚያ አካባቢ እንደደረስክ ወዲያውኑ አዳራሹን ፈልገህ የጉባኤ ስብሰባ የሚደረግበትን ሰዓት እወቅ። በመንግሥት አዳራሹ የሚጠቀመው ከአንድ በላይ ጉባኤ ከሆነ የአንተ መኖሪያ በየትኛው የጉባኤ ክልል ውስጥ እንደሚገኝ እንዲያሳውቁህ ሽማግሌዎቹን ጠይቅ። ስብሰባ ላይ መገኘት ለመጀመርና በጉባኤው ካሉ ሽማግሌዎች ጋር ለመተዋወቅ ጊዜ አትፍጅ።
(2) የአንተንም ሆነ የቤተሰብህን የጉባኤ የአስፋፊ ካርድ በማዘዋወር ረገድ የለቀቅኸው ጉባኤና የአዲሱ ጉባኤህ ጸሐፊዎች ይተባበራሉ። በተጨማሪም በአዲሱ ጉባኤህ ለሚገኙ ሽማግሌዎች የማስተዋወቂያ ደብዳቤ ይላክላቸዋል። (የመንግሥት አገልግሎታችን 2-19 ላይ የወጣውን የጥያቄ ሣጥን ተመልከት።) በዚያ የሚገኘው የጉባኤ የአገልግሎት ኮሚቴ ለአንተ አመቺ በሆነው ቡድን ለሚገኘው የመጽሐፍ ጥናት መሪ መምጣትህን ማሳወቅ አለበት። እርሱም የምትሄድበትን አዲስ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን መሰብሰቢያ ያሳይሃል።—ሮሜ 15:7
(3) በአዲሱ ጉባኤህ የሚገኙ አስፋፊዎች በሙሉ ካንተ ጋር የመተዋወቅና እንግድነት እንዳይሰማህ የማድረግ አስደሳች ድርሻ ማበርከት ይችላሉ። (ከ3 ዮሐንስ 8 ጋር አወዳድር።) ይህ ደግሞ ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር የሚያበረታታና የሚያንጽ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ እንድትችል ስብሰባ ላይ መገኘት አለብህ ማለት ነው።
(4) አንተም ከአዲሱ ጉባኤህ ጋር በመስክ አገልግሎት መሳተፍ ለመጀመር የመኖሪያ ቦታ ለውጥ ማድረግ የሚጠይቃቸው ሥራዎች በሙሉ እስኪጠናቀቁልህ መጠበቅ የለብህም። የመንግሥቱን ጥቅሞች በአንደኛ ደረጃ ባስቀመጥህ መጠን ሌሎች ነገሮች የሚሟሉ ሲሆን አንተም አዲሱን የመኖሪያ አካባቢህን በቶሎ ትላመዳለህ። (ማቴ. 6:33) አዲሱ ቤትህ ውስጥ ተረጋግተህ ስትቀመጥ በጉባኤ ካሉት አንዳንዶች መጥተው እንዲጠይቁህና የተሻለ ትውውቅ እንዲኖራችሁ መጋበዝ ትፈልግ ይሆናል።—ሮሜ 12:13
የመኖሪያ ቦታ መቀየር ትልቅ ሥራ ነው። ሆኖም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ መደረግ ያለበትን ነገር ካደረጉ መንፈሳዊ ኪሳራ ሊከሰት አይችልም። ሁሉም ለአፍቃሪ የክርስቲያን ወንድማማችነት ማኅበራችን ጥሩ አድናቆት ያድርባቸዋል።