የጥናት ርዕስ 10
መዝሙር 31 ከአምላክ ጋር ሂድ!
የይሖዋንና የኢየሱስን አስተሳሰብ ኮርጁ
“ክርስቶስ በሥጋ መከራ ስለተቀበለ እናንተም ይህንኑ አስተሳሰብ ለማንጸባረቅ ዝግጁ ሁኑ።”—1 ጴጥ. 4:1
ዓላማ
ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ አስተሳሰብ ምን እንደተማረ እንዲሁም እኛ የምናገኘው ትምህርት።
1-2. ይሖዋን መውደድ ምን ይጠይቃል? ኢየሱስ በሙሉ አእምሮው ይሖዋን የወደደው እንዴት ነው?
“አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ ኃይልህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።” ኢየሱስ በሙሴ ሕግ ውስጥ ካሉ ትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው ይህ እንደሆነ አረጋግጧል። (ሉቃስ 10:27) ከዚህ ማየት እንደምንችለው ይሖዋን መውደድ ልባችንን ይኸውም ዝንባሌዎቻችንን፣ ምኞቶቻችንን እና ስሜቶቻችንን ያካትታል። ከዚህም ሌላ በሙሉ ነፍሳችን ለእሱ ማደርን እንዲሁም በሙሉ ኃይላችን ማለትም ጉልበታችን እሱን ማገልገልን ይጨምራል። ይሁንና ይሖዋን መውደድ አእምሯችንን ይኸውም የምናስብበትን መንገድም ያካትታል። እርግጥ ነው፣ መቼም ቢሆን የይሖዋን አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችልም። ይሁንና ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ በማጥናት ስለ አምላክ አስተሳሰብ ያለንን ግንዛቤ ማሳደግ እንችላለን፤ ምክንያቱም ኢየሱስ የአባቱን አስተሳሰብ ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል።—1 ቆሮ. 2:16
2 ኢየሱስ ይሖዋን በሙሉ አእምሮው ይወደዋል። አምላክ ለእሱ ያለው ፈቃድ ምን እንደሆነ ያውቅ ነበር፤ ይህን ፈቃዱን መፈጸም መከራ እንደሚያስከትልበት ቢያውቅም በዚያ መንገድ ለመኖር ቆርጧል። ሕይወቱ ሙሉ በሙሉ ያተኮረው የአባቱን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ነው፤ ምንም ነገር ትኩረቱን እንዲከፋፍልበት አልፈቀደም።
3. ሐዋርያው ጴጥሮስ ከኢየሱስ ምን ተምሯል? የእምነት ባልንጀሮቹንስ ምን እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል? (1 ጴጥሮስ 4:1)
3 ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ከኢየሱስ ጋር ጊዜ የማሳለፍ እንዲሁም ስለሚያስብበት መንገድ ከራሱ የመማር ልዩ አጋጣሚ አግኝተዋል። ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት ከጻፋቸው ደብዳቤዎች በመጀመሪያው ላይ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ለማንጸባረቅ ዝግጁ እንዲሆኑ አበረታቷል። (1 ጴጥሮስ 4:1ን አንብብ።) እዚህ ጥቅስ ላይ “ዝግጁ ሁኑ” ተብሎ የተተረጎመው አገላለጽ በኩረ ጽሑፉ ላይ ለውጊያ መታጠቅን የሚያመለክት ወታደራዊ አገላለጽ ነው። ስለዚህ የኢየሱስን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ፣ ክርስቲያኖች ከኃጢአትና በሰይጣን ከሚመራው ዓለም ጋር በሚያደርጉት ውጊያ ድል የሚያጎናጽፋቸው ሁነኛ ትጥቅ ይሆንላቸዋል።—2 ቆሮ. 10:3-5፤ ኤፌ. 6:12
4. ይህ ርዕስ የጴጥሮስን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳን እንዴት ነው?
4 በዚህ ርዕስ ላይ የኢየሱስን አስተሳሰብ እንዲሁም እንዴት ልንኮርጀው እንደምንችል እንመረምራለን። በሚከተሉት አቅጣጫዎች ጤናማ አስተሳሰብ ይዘን መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነም እንመለከታለን፦ (1) በሐሳብ ስምም ሆነን ለመኖር የሚረዳንን የይሖዋን አስተሳሰብ መኮረጅ፣ (2) ትሑት መሆን እንዲሁም (3) በጸሎት የይሖዋን እርዳታ መጠየቅ።
የይሖዋን አስተሳሰብ ኮርጁ
5. ጴጥሮስ የይሖዋን አስተሳሰብ ሳያንጸባርቅ የቀረበትን አንድ አጋጣሚ ጥቀስ።
5 ጴጥሮስ የይሖዋን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ ተስኖት የነበረበትን አንድ አጋጣሚ እንመልከት። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ እንዳለበት በዚያም ለሃይማኖት መሪዎች አልፎ እንደሚሰጥ፣ መከራ እንደሚደርስበትና በመጨረሻም እንደሚገደል ለሐዋርያቱ እየነገራቸው ነው። (ማቴ. 16:21) ጴጥሮስ ይህን ሲሰማ ከበደው፤ ይሖዋ፣ ተስፋ የተሰጠበትና እስራኤልን የሚያድነው መሲሕ እንዲገደል ይፈቅዳል ብሎ መቀበል ቸገረው። (ማቴ. 16:16) ስለዚህ ኢየሱስን ለብቻው በመውሰድ “ጌታ ሆይ፣ በራስህ ላይ እንዲህ አትጨክን፤ በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” አለው። (ማቴ. 16:22) ጴጥሮስ በዚህ ወቅት የይሖዋን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ ስለተሳነው ከኢየሱስ ጋር በሐሳብ መስማማት አልቻለም።
6. ኢየሱስ አስተሳሰቡ ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር ሙሉ በሙሉ እንደሚስማማ ያሳየው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ ነገሩን ያሰበበት መንገድ ከሰማያዊ አባቱ አስተሳሰብ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ነበር። ኢየሱስ ለጴጥሮስ “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ ሰይጣን! የሰውን እንጂ የአምላክን ሐሳብ ስለማታስብ እንቅፋት ሆነህብኛል” ብሎታል። (ማቴ. 16:23) የጴጥሮስ ምክር ከቅንነት የመነጨ ቢሆንም ኢየሱስ አልተቀበለውም። ምክንያቱም ይሖዋ ለኢየሱስ ያሰበው ሕይወት መሥዋዕትነት የሚያስከፍል ነው። ይህ አጋጣሚ ጴጥሮስ አስተሳሰቡን በአምላክ አስተሳሰብ መቃኘት እንዳለበት ትልቅ ቁም ነገር አስተምሮታል። ይህ እኛም ልንማረው የሚገባ ቁም ነገር ነው።
7. ከጊዜ በኋላ ጴጥሮስ አስተሳሰቡን በይሖዋ አስተሳሰብ ለመቃኘት ንቁ እንደነበር ያሳየው እንዴት ነው? (ሥዕሉን ተመልከት።)
7 በኋላ ላይ ጴጥሮስ አስተሳሰቡ በይሖዋ አስተሳሰብ እንደተቃኘ አሳይቷል። ይሖዋ ያልተገረዙ አሕዛብ፣ ሕዝቦቹን ያቀፈው ጉባኤ ውስጥ እንዲጠቃለሉ የወሰነው ጊዜ ደርሶ ነበር። መጀመሪያ ላይ ጉባኤውን ከተቀላቀሉት ከአሕዛብ ወገን የመጡ ክርስቲያኖች አንዱ ቆርኔሌዎስ ነው። ለእሱ እንዲሰብክ የተላከው ደግሞ ጴጥሮስ ነበር። አይሁዳውያን ከአሕዛብ ጋር መቀራረብ አይፈልጉም ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋ ጴጥሮስን ከመላኩ በፊት አስቀድሞ ያዘጋጀው ለምን እንደሆነ መረዳት አይከብድም። ጴጥሮስ አምላክ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ሲረዳ የራሱን አመለካከት አስተካከለ። በመሆኑም ቆርኔሌዎስ መልእክት ሲልክበት ‘ምንም ሳያንገራግር’ ሄደ። (ሥራ 10:28, 29) ለቆርኔሌዎስና ለቤተሰቡ ሰበከ፤ እነሱም ተጠመቁ።—ሥራ 10:21-23, 34, 35, 44-48
ጴጥሮስ ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ሲገባ (አንቀጽ 7ን ተመልከት)
8. አስተሳሰባችን ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር የሚስማማ እንደሆነ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (1 ጴጥሮስ 3:8 እና የግርጌ ማስታወሻ)
8 ከዓመታት በኋላ ጴጥሮስ “የሐሳብ ስምምነት” እንዲኖራቸው የእምነት ባልንጀሮቹን አበረታቷል። (1 ጴጥሮስ 3:8ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።) እኛ የይሖዋ ሕዝቦች ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የገለጠልንን አስተሳሰቡን የምናንጸባርቅ ከሆነ የሐሳብ ስምምነት ሊኖረን ይችላል። አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ኢየሱስ ተከታዮቹን በሕይወታቸው ውስጥ ለመንግሥቱ ቅድሚያ እንዲሰጡ አበረታቷቸዋል። (ማቴ. 6:33) በጉባኤያችሁ ያለ አንድ አስፋፊ ይህን ምክር በመከተል በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ለመግባት ወሰነ እንበል። በዚህ ጊዜ በራሱ ላይ እንዳይጨክን መምከር አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ የሚክስ ስለሆነው ስለዚህ አገልግሎት በጎ በጎውን ልንነግረው እንዲሁም በሚያስፈልገው ነገር ልንደግፈው ዝግጁ መሆናችንን ልንገልጽለት ይገባል።
ትሑት ሁኑ
9-10. ኢየሱስ ታላቅ ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው?
9 ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት ለጴጥሮስና ለሌሎቹ ሐዋርያት ስለ ትሕትና ትልቅ ቁም ነገር አስተምሯቸዋል። ከዚህ ትንሽ ቀደም ብሎ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ፋሲካን እንዲያዘጋጁ ልኳቸው ነበር። ይህ ፋሲካ፣ ሰው ሆኖ ከእነሱ ጋር የሚጋራው የመጨረሻው ማዕድ ነው። ለፋሲካ ዝግጅት ሲያደርጉ ማስታጠቢያና ፎጣ መኖሩን ማረጋገጥ ነበረባቸው፤ ምክንያቱም እንግዶች ማዕድ ፊት ከመቅረባቸው በፊት እግራቸውን ይታጠባሉ። ይሁንና ሰዓቱ ሲደርስ፣ ዝቅ ተደርጎ የሚታየውን ይህን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ የሚሆነው ማን ይሆን?
10 ታላቅ ትሕትና የሚጠይቀውን ይህን ሥራ ለማከናወን ያለምንም ማንገራገር ፈቃደኛ የሆነው ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ያደረገው ነገር ሐዋርያቱን በጣም አስገርሟቸው መሆን አለበት። በአብዛኛው አንድ አገልጋይ የሚያከናውነውን ሥራ ለመሥራት ተነሳ፤ መደረቢያውን አውልቆ አስቀመጠ፣ ወገቡ ላይ ፎጣ አሸረጠ እንዲሁም መታጠቢያ ዕቃ ውስጥ ውኃ አድርጎ እግራቸውን ማጠብ ጀመረ። (ዮሐ. 13:4, 5) የ12ቱን ሐዋርያት እግር አጥቦ እስኪጨርስ የተወሰነ ጊዜ ወስዶ መሆን አለበት፤ ከእነዚህ አንዱ ደግሞ በኋላ ላይ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ ነው። ያም ቢሆን ኢየሱስ በትሕትና ሥራውን አጠናቀቀ። ከዚያም እንዲህ ሲል በትዕግሥት አስረዳቸው፦ “ምን እንዳደረግኩላችሁ አስተዋላችሁ? እናንተ ‘መምህር’ እና ‘ጌታ’ ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ፤ እንደዚያ ስለሆንኩም እንዲህ ብላችሁ መጥራታችሁ ትክክል ነው። ስለዚህ እኔ ጌታና መምህር ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብኩ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል።”—ዮሐ. 13:12-14
እውነተኛ ትሕትና . . . አስተሳሰባችንን የሚያካትት ነው
11. ጴጥሮስ ትሕትናን እንደተማረ ያሳየው እንዴት ነው? (1 ጴጥሮስ 5:5) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
11 ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ካሳየው ትሕትና ትምህርት ወስዷል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ ጴጥሮስ አንድ ተአምር ፈጽሞ ነበር፤ ይህም ሲወለድ ጀምሮ ሽባ የነበረን ሰው መፈወስ ነው። (ሥራ 1:8, 9፤ 3:2, 6-8) እንደሚጠበቀው ይህ አስደናቂ ክስተት የብዙኃኑን ትኩረት ሳበ። (ሥራ 3:11) ከበሬታና ተደማጭነት ትልቅ ቦታ በሚሰጠው ማኅበረሰብ ውስጥ ያደገው ጴጥሮስ ምን ያደርግ ይሆን? ሰዎቹ የሚሰጡትን ክብር ይቀበል ይሆን? በፍጹም። ጴጥሮስ የሕዝቡ ትኩረት በእሱ ላይ እንዲያርፍ አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ ለይሖዋና ለኢየሱስ በትሕትና እውቅና ሰጠ። “የኢየሱስ ስምና እኛ በስሙ ላይ ያለን እምነት ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን ሰው አጠነከረው” አለ። (ሥራ 3:12-16) ጴጥሮስ ትሕትናን እንዲለብሱ ለክርስቲያኖች ሲጽፍ የተጠቀመበት ቃል፣ ኢየሱስ ወገቡ ላይ ፎጣ አሸርጦ የሐዋርያቱን እግር ያጠበበትን ጊዜ ያስታውሰናል።—1 ጴጥሮስ 5:5ን አንብብ።
ጴጥሮስ ተአምር ከፈጸመ በኋላ በትሕትና ለይሖዋና ለኢየሱስ እውቅና ሰጥቷል። እኛም ውዳሴ ወይም ወሮታ ሳንጠብቅ ለሌሎች መልካም በማድረግ ትሕትና ማሳየት እንችላለን (ከአንቀጽ 11-12ን ተመልከት)
12. እንደ ጴጥሮስ ትሕትናን መማራችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
12 ትሕትና በማዳበር ረገድ የጴጥሮስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። እውነተኛ ትሕትና በንግግራችን ብቻ የሚገለጽ ነገር እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። “ትሕትና” ተብሎ የተተረጎመው ጴጥሮስ የተጠቀመበት ቃል፣ አስተሳሰባችንን ይኸውም ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ያለንን አመለካከት የሚያካትት ነው። ለሌሎች መልካም የምናደርገው ይሖዋንና ሰዎችን ስለምንወድ እንጂ አድናቆት ለማትረፍ ብለን አይደለም። ትሑቶች ከሆንን የምናከናውነውን ተግባር ሌሎች አዩትም አላዩት ይሖዋንና ወንድሞቻችንን ለማገልገል በደስታ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።—ማቴ. 6:1-4
“ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ”
13. “ጤናማ አስተሳሰብ” ማዳበር ሲባል ምን ማለት ነው?
13 “ጤናማ አስተሳሰብ” ማዳበር ሲባል ምን ማለት ነው? (1 ጴጥ. 4:7) ጤናማ አስተሳሰብ ያለው አንድ ክርስቲያን ውሳኔ ሲያደርግ የይሖዋን አስተሳሰብ ለማንጸባረቅ ይጥራል። በሕይወቱ ውስጥ ከይሖዋ ጋር ካለው ዝምድና በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር እንደሌለ ይገነዘባል። ስለ ራሱ ሚዛናዊ አመለካከት አለው፤ የማያውቃቸው ነገሮች እንዳሉም ይረዳል። ደግሞም ምንጊዜም የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገው በትሕትና ስለሚገነዘብ አዘውትሮ ይጸልያል።a
14. ጴጥሮስ በአምላክ እርዳታ ሳይታመን የቀረው እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ደቀ መዛሙርቱን “በዚህች ሌሊት ሁላችሁም በእኔ ላይ በሚደርሰው ነገር የተነሳ ትሰናከላላችሁ” በማለት አስጠንቅቋቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በልበ ሙሉነት “ሌሎቹ ሁሉ በአንተ ምክንያት ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልሰናከልም!” አለው። በዚያ ምሽት ኢየሱስ አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱን “ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሳታሰልሱም ጸልዩ” በማለት መክሯቸው ነበር። (ማቴ. 26:31, 33, 41) ጴጥሮስ ይህን ምክር ሰምቶ ቢሆን ኖሮ ከኢየሱስ ጋር ያለውን ዝምድና በይፋ ለማመን ድፍረት ይኖረው ነበር። እሱ ግን ጌታውን በመካድ በጣም የሚቆጨውን ውሳኔ አደረገ።—ማቴ. 26:69-75
15. ኢየሱስ ሰው ሆኖ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?
15 ኢየሱስ ምንጊዜም የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ያውቅ ነበር፤ ፍጹም ቢሆንም ደጋግሞ ወደ አባቱ ጸልዮአል። ይሖዋ ለእሱ ካለው ፈቃድ ጋር የሚስማማ ነገር ለማድረግ ድፍረት ያገኘው ለዚህ ነው። (ማቴ. 26:39, 42, 44፤ ዮሐ. 18:4, 5) ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ የአባቱን እርዳታ በጸሎት ሲጠይቅ መመልከቱ ዕድሜውን ሙሉ የማይረሳው ትልቅ ትምህርት አስተምሮት መሆን አለበት።
16. ጴጥሮስ ጤናማ አስተሳሰብ እንዳዳበረ ያሳየው እንዴት ነው? (1 ጴጥሮስ 4:7)
16 በጊዜ ሂደት ጴጥሮስ የይሖዋን እርዳታ ተግቶ በጸሎት መጠየቅን ተማረ። ከሞት የተነሳው ኢየሱስ፣ የስብከት ተልእኳቸውን ለመፈጸም የሚያግዛቸውን መንፈስ ቅዱስ እንደሚቀበሉ ለጴጥሮስና ለሌሎቹ ሐዋርያት አረጋግጦላቸው ነበር። ይህ እስኪሆን ድረስ ግን ኢየሩሳሌም ሆነው እንዲጠብቁ ኢየሱስ ነገራቸው። (ሉቃስ 24:49፤ ሥራ 1:4, 5) ጴጥሮስ በዚህ ወቅት ምን እያደረገ ነበር? እሱና የእምነት ባልንጀሮቹ “ተግተው ይጸልዩ ነበር።” (ሥራ 1:13, 14) በኋላ ላይ ጴጥሮስ በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖራቸውና የይሖዋን እርዳታ በጸሎት እንዲጠይቁ የእምነት ባልንጀሮቹን አበረታቷቸዋል። (1 ጴጥሮስ 4:7ን አንብብ።) ጴጥሮስ በይሖዋ እርዳታ መታመንን ስለተማረ ለጉባኤው ዓምድ መሆን ችሏል።—ገላ. 2:9
17. ምንም ዓይነት ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ ቢኖረን ምንጊዜም ምን ማድረግ አለብን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
17 ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖረን አዘውትረን ወደ ይሖዋ የመጸለይ ልማድ ሊኖረን ይገባል። ምንም ዓይነት ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ ቢኖረን ምንጊዜም የይሖዋን እርዳታ መጠየቅ አስፈላጊ እንደሆነ እንገነዘባለን። በተለይ ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን ከማድረጋችን በፊት ይሖዋ እንዲመራን እንጸልያለን፤ ምክንያቱም ለእኛ የሚበጀውን የሚያውቀው እሱ እንደሆነ እንተማመናለን።
ጴጥሮስ በጸሎት የይሖዋን እርዳታ የመጠየቅን አስፈላጊነት ተምሯል። እኛም በተለይ ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን ከማድረጋችን በፊት የይሖዋን እርዳታ በጸሎት በመጠየቅ ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለን ማሳየት እንችላለን (አንቀጽ 17ን ተመልከት)b
18. አስተሳሰባችን በይሖዋ አስተሳሰብ ይበልጥ እየተቃኘ እንዲሄድ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
18 ይሖዋ የእሱን ባሕርያት ማንጸባረቅ እንድንችል አድርጎ ስለፈጠረን በጣም አመስጋኞች ነን። (ዘፍ. 1:26) ይሖዋን ፍጹም በሆነ መንገድ መምሰል እንደማንችል የታወቀ ነው። (ኢሳ. 55:9) ይሁንና እኛም እንደ ጴጥሮስ አስተሳሰባችን በይሖዋ አስተሳሰብ ይበልጥ እየተቃኘ እንዲሄድ ማድረግ እንችላለን። እንግዲያው ይህ ይሳካልን ዘንድ የአምላክን አስተሳሰብ መኮረጃችንን እንቀጥል፣ ትሑት እንሁን እንዲሁም ጤናማ አስተሳሰብ ይዘን እንኑር።
መዝሙር 30 አባቴ፣ አምላኬና ወዳጄ
a ጤናማ አስተሳሰብ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት jw.org ወይም JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው” በተባለው ዓምድ ሥር “2 ጢሞቴዎስ 1:7—‘አምላክ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንም’” የሚለው ርዕስ ላይ “ጤናማ አእምሮ” የሚለውን ተመልከት።
b የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት የሥራ ቃለ መጠየቅ ለማድረግ እየጠበቀች ሳለ በልቧ ወደ ይሖዋ ትጸልያለች።