የጥናት ርዕስ 18
መዝሙር 65 ወደፊት ግፋ!
ወጣት ወንድሞች—ማርቆስንና ጢሞቴዎስን ምሰሉ
“ማርቆስ በአገልግሎት ስለሚረዳኝ ከአንተ ጋር ይዘኸው ና።”—2 ጢሞ. 4:11
ዓላማ
የማርቆስና የጢሞቴዎስ ምሳሌ፣ ወጣት ወንድሞች ሌሎችን ይበልጥ እንዲያገለግሉ የሚያስችሏቸውን ባሕርያት እንዲያዳብሩ የሚረዳቸው እንዴት ነው?
1-2. ማርቆስና ጢሞቴዎስ ሌሎችን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ከማገልገል ወደኋላ እንዲሉ ሊያደርጓቸው የሚችሉት የትኞቹ ሁኔታዎች ነበሩ?
ወጣት ወንድሞች፣ በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ተሳትፎ ማድረግና የጉባኤያችሁን ወንድሞች ይበልጥ መርዳት ትፈልጋላችሁ? እንደምትፈልጉ ምንም ጥያቄ የለውም። ሌሎችን ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ በርካታ ወጣት ወንድሞችን ማየት ምንኛ የሚያስደስት ነው! (መዝ. 110:3) ይሁንና እንቅፋት ሊሆኑባችሁ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች አሉ። ወደፊት ሊያጋጥማችሁ የሚችለውን ነገር በመፍራት አገልግሎታችሁን ከማስፋት ወደኋላ ብላችኋል? ‘ብቃት የለኝም’ በሚል ስሜት አንድን ኃላፊነት ሳትቀበሉ ቀርታችሁ ታውቃላችሁ? ከሆነ እንዲህ የተሰማችሁ እናንተ ብቻ አይደላችሁም።
2 ማርቆስና ጢሞቴዎስ የነበሩበት ሁኔታም ከእናንተ ጋር ይመሳሰላል። ሆኖም ወደፊት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ነገር በመፍራት ወይም ‘ብቃት የለኝም’ ብለው በማሰብ ሌሎችን ከማገልገል ወደኋላ አላሉም። ማርቆስ ከሐዋርያው ጳውሎስና ከበርናባስ ጋር በመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዟቸው ላይ እንዲካፈል የተጋበዘው ከእናቱ ጋር በተመቻቸ ቤት ውስጥ ይኖር በነበረበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። (ሥራ 12:12, 13, 25) ማርቆስ አገልግሎቱን ለማስፋት ሲል የለመደውን አካባቢ ትቶ ሄዷል። በመጀመሪያ ወደ አንጾኪያ ሄደ። ከዚያም ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ ሌሎች ሩቅ ቦታዎች ተጓዘ። (ሥራ 13:1-5) ጢሞቴዎስም ጳውሎስ በስብከቱ ሥራ አብሮት እንዲካፈል ሲጋብዘው ከወላጆቹ ጋር ይኖር የነበረ ይመስላል። ጢሞቴዎስ ወጣትና ተሞክሮ የሌለው በመሆኑ ‘ብቃት የለኝም’ በሚል ስሜት ይህን ኃላፊነት ከመቀበል ወደኋላ ሊል ይችል ነበር። (ከ1 ቆሮንቶስ 16:10, 11 እና ከ1 ጢሞቴዎስ 4:12 ጋር አወዳድር።) ሆኖም ጳውሎስ ያቀረበለትን ግብዣ ተቀብሏል፤ በዚህም የተነሳ ብዙ በረከቶችን አግኝቷል።—ሥራ 16:3-5
3. (ሀ) ጳውሎስ ማርቆስንና ጢሞቴዎስን ምን ያህል ያደንቃቸው ነበር? (2 ጢሞቴዎስ 4:6, 9, 11) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።) (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን?
3 ማርቆስና ጢሞቴዎስ ገና በወጣትነታቸው ጠቃሚ ተሞክሮ ማካበትና ከባድ ኃላፊነቶችን መሸከም ችለዋል። ጳውሎስ ለእነዚህ ወጣት ወንድሞች ከፍተኛ አድናቆት ስለነበረው የሕይወቱ ማብቂያ እንደተቃረበ በተገነዘበበት ወቅት ከጎኑ እንዲሆኑ ፈልጎ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 4:6, 9, 11ን አንብብ።) ማርቆስንና ጢሞቴዎስን በጳውሎስ ዘንድ ተወዳጅ ያደረጓቸው የትኞቹ ባሕርያት ናቸው? ወጣት ወንድሞች የእነሱን ባሕርይ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው? በተጨማሪም ወጣት ወንድሞች ከጳውሎስ አባታዊ ምክር ምን ጥቅም ያገኛሉ?
ማርቆስና ጢሞቴዎስ በወጣትነታቸው ኃላፊነት መሸከማቸው በጳውሎስ ዘንድ ተወዳጅ አድርጓቸዋል (አንቀጽ 3ን ተመልከት)b
ማርቆስን ምሰሉ—ለማገልገል ፈቃደኞች ሁኑ
4-5. ማርቆስ ሌሎችን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
4 አንድ ማመሣከሪያ እንደገለጸው “ሌሎችን ማገልገል” የሚለው አገላለጽ “በትጋትና ባለመታከት” እነሱን ለመርዳት ጥረት ማድረግን ያመለክታል። በዚህ ረገድ ማርቆስ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ጳውሎስ በሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት እሱን ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ማርቆስ አዝኖና ስሜቱ ተጎድቶ መሆን አለበት። (ሥራ 15:37, 38) ሆኖም ይህ ሁኔታ፣ ተስፋ ቆርጦ ወንድሞቹንና እህቶቹን ከማገልገል ወደኋላ እንዲል አላደረገውም።
5 ማርቆስ ከዘመዱ ከበርናባስ ጋር ሌላ የአገልግሎት ምድብ ተቀበለ። ከ11 ዓመት ገደማ በኋላ ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ በሮም በታሰረበት ወቅት ከደገፉት ሰዎች መካከል ማርቆስ ይገኝበታል። (ፊልሞና 23, 24) እንዲያውም ጳውሎስ፣ ማርቆስ ላደረገለት ድጋፍ ከፍተኛ አድናቆት ስለነበረው “የብርታት ምንጭ” እንደሆነለት ገልጿል።—ቆላ. 4:10, 11
6. ማርቆስ ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር ተቀራርቦ መሥራቱ የጠቀመው እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
6 ማርቆስ ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር ተቀራርቦ መሥራቱ ጠቅሞታል። በሮም ከጳውሎስ ጋር የተወሰነ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ በባቢሎን ከሐዋርያው ጴጥሮስ ጋር ማገልገል ጀመረ። ከጴጥሮስ ጋር በጣም ከመቀራረባቸው የተነሳ “ልጄ ማርቆስ” በማለት ጠርቶታል። (1 ጴጥ. 5:13) ማርቆስና ጴጥሮስ አብረው በሚያገለግሉበት ወቅት ጴጥሮስ የኢየሱስን ሕይወትና አገልግሎት አስመልክቶ ብዙ አስገራሚ ነገሮችን እንደነገረው ምንም ጥያቄ የለውም፤ ማርቆስም እነዚህን መረጃዎች በወንጌል ዘገባው ላይ አስፍሯቸዋል።a
7. አንድ ወጣት ወንድም የማርቆስን ምሳሌ የተከተለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
7 ማርቆስ በአገልግሎት መጠመዱንና ከጎለመሱ ወንድሞች ጋር መቀራረቡን ቀጥሏል። እናንተስ ማርቆስን መምሰል የምትችሉት እንዴት ነው? አንድ የአገልግሎት መብት ሳታገኙ ከቀራችሁ በራሳችሁ ተስፋ አትቁረጡ፤ እንዲሁም ይሖዋንና ጉባኤውን ማገልገል የምትችሉባቸውን ሌሎች መንገዶች መፈለጋችሁን ቀጥሉ። በአሁኑ ወቅት በጉባኤ ሽማግሌነት የሚያገለግለውን ስንግኡ የተባለ ወንድም እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ወጣት ሳለ ራሱን ከሌሎች ወጣት ወንድሞች ጋር ያወዳድር ነበር። አንዳንዶቹ ከእሱ ቀድመው የአገልግሎት መብቶችን አግኝተው ነበር። ስንግኡ በዚህ ስሜቱ ተጎዳ። ከጊዜ በኋላ ስሜቱን አውጥቶ ለጎለመሱ ወንድሞች ነገራቸው። በዚህ ጊዜ አንድ ሽማግሌ ጥሩ ምክር ሰጠው፤ አንዳንድ ጊዜ መልካም ሥራውን ሌሎች ላያስተውሉ ቢችሉም እንኳ ሌሎችን ለመርዳት አቅሙ የፈቀደውን እንዲያደርግ ሐሳብ ሰጠው። ይህ ምክር፣ አረጋውያንንና ወደ ስብሰባ ለመምጣት የትራንስፖርት ዝግጅት የሚያስፈልጋቸውን ወንድሞች ለመርዳት ራሱን እንዲያቀርብ አነሳሳው። ያን ጊዜ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ሌሎችን ማገልገል ማለት ምን ማለት እንደሆነ በደንብ ገባኝ። ለሌሎች ተግባራዊ እርዳታ መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ ማጣጣም ቻልኩ።”
ወጣት ወንድሞች ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር አዘውትረው ጊዜ ማሳለፋቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው? (አንቀጽ 7ን ተመልከት)
ጢሞቴዎስን ምሰሉ—ለሌሎች ፍቅራዊ አሳቢነት አሳዩ
8. ጳውሎስ ጢሞቴዎስን የጉዞ አጋሩ አድርጎ የመረጠው ለምንድን ነው? (ፊልጵስዩስ 2:19-22)
8 ጳውሎስ ከዚህ ቀደም ተቃውሞ አጋጥሞት ወደነበረባቸው ከተሞች ተመልሶ በሄደበት ወቅት ደፋር የጉዞ አጋሮች ያስፈልጉት ነበር። በመጀመሪያ አብሮት እንዲጓዝ ሲላስ የተባለን ተሞክሮ ያለው ክርስቲያን መረጠ። (ሥራ 15:22, 40) ከጊዜ በኋላም ጢሞቴዎስን የጉዞ አጋሩ አድርጎ መርጦታል። ጢሞቴዎስን የመረጠው ለምንድን ነው? አንደኛ፣ ጢሞቴዎስ ጥሩ ስም አትርፎ ነበር። (ሥራ 16:1, 2) በተጨማሪም ለሌሎች ከልቡ ያስብ ነበር።—ፊልጵስዩስ 2:19-22ን አንብብ።
9. ጢሞቴዎስ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ ከልቡ እንደሚያስብ ያሳየው እንዴት ነው?
9 ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ጋር ማገልገል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከራሱ ይልቅ ለሌሎች እንደሚያስብ አሳይቷል። በዚህም የተነሳ ጳውሎስ በጢሞቴዎስ ስለተማመነበት በቤርያ የነበሩትን አዳዲስ ደቀ መዛሙርት እንዲያበረታታ እዚያ ትቶት ሄዷል። (ሥራ 17:13, 14) ሲላስም በቤርያ ቀርቶ ስለነበር ጢሞቴዎስ ከእሱ ምሳሌ እንደተጠቀመ ምንም ጥያቄ የለውም። ከጊዜ በኋላ ግን ጳውሎስ በተሰሎንቄ ያሉትን ክርስቲያኖች እንዲያበረታታ ጢሞቴዎስን ብቻውን ወደዚያ ልኮታል። (1 ተሰ. 3:2 ግርጌ) ለቀጣዮቹ 15 ዓመታት ገደማ ጢሞቴዎስ ‘ከሚያለቅሱ ጋር ማልቀስን’ ተምሯል፤ መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች ከልቡ ያዝን ነበር። (ሮም 12:15፤ 2 ጢሞ. 1:4) ወጣት ወንድሞች የጢሞቴዎስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?
10. ኡጄ የተባለ ወንድም ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት የሚችልበትን መንገድ የተማረው እንዴት ነው?
10 ኡጄ የተባለ ወንድም ለሌሎች ይበልጥ አሳቢነት ማሳየት የሚችለው እንዴት እንደሆነ ተምሯል። ኡጄ ወጣት ሳለ በዕድሜ ከገፉ ወንድሞችና እህቶች ጋር ማውራት ይከብደው ነበር። በመሆኑም በስብሰባ አዳራሽ ሲያገኛቸው አጭር ሰላምታ ሰጥቷቸው ይሄዳል። አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ኡጄ ለእምነት አጋሮቹ አንድ የሚያደንቅላቸውን ነገር በመጥቀስ ጭውውት እንዲጀምር አበረታታው። በተጨማሪም የእነሱን ትኩረት የሚስበው ነገር ምን ሊሆን እንደሚችል እንዲያስብ መከረው። ኡጄ ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ይህን ምክር በሥራ ላይ አዋለ። በአሁኑ ወቅት ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ኡጄ እንዲህ ብሏል፦ “አሁን የተለያየ ዕድሜ ካላቸው ሰዎች ጋር ትርጉም ያለው ጭውውት ማድረግ ቀላል ሆኖልኛል። የሌሎችን ችግር በተሻለ ሁኔታ መረዳት በመቻሌ ደስ ይለኛል። ይህን ችሎታ ማዳበሬ የእምነት አጋሮቼን ለመርዳት በእጅጉ አግዞኛል።”
11. ወጣት ወንድሞች ለሌሎች በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
11 ወጣት ወንድሞች፣ እናንተም ለሌሎች በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ማሳየት የምትችሉበትን መንገድ መማር ትችላላችሁ። በስብሰባዎች ላይ ስትገኙ የተለያየ ዕድሜና ባሕል ላላቸው ሰዎች ትኩረት ስጡ። ስለ ደህንነታቸው ጠይቋቸው፤ እንዲሁም አዳምጧቸው። ውሎ አድሮ እነሱን መርዳት የምትችሉበትን መንገድ ትገነዘቡ ይሆናል። ለምሳሌ አረጋዊ የሆኑ አንድ ባልና ሚስት በJWJW ላይብረሪ አፕሊኬሽን አጠቃቀም ረገድ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ትገነዘቡ ይሆናል። ወይም ደግሞ አብሯቸው የሚያገለግል ሰው እንዳጡ ልትገነዘቡ ትችላላችሁ። እንዲህ ያሉትን ክርስቲያኖች በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ አጠቃቀም ረገድ ልታግዟቸው ወይም አብራችኋቸው ልታገለግሉ ትችሉ ይሆን? ቅድሚያውን ወስዳችሁ ሌሎችን ለመርዳት ጥረት ስታደርጉ ለሁሉም ጥሩ ምሳሌ ትሆናላችሁ።
ወጣት ወንድሞች በተለያዩ ተግባራዊ መንገዶች ጉባኤውን መርዳት ይችላሉ (አንቀጽ 11ን ተመልከት)
ከጳውሎስ አባታዊ ምክር ተጠቀሙ
12. ወጣት ወንድሞች ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ከሰጠው ምክር መጠቀም የሚችሉት እንዴት ነው?
12 ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በግል ሕይወቱና በአገልግሎቱ ስኬታማ ለመሆን የሚረዱትን ምክሮች ሰጥቶታል። (1 ጢሞ. 1:18፤ 2 ጢሞ. 4:5) እናንተ ወጣት ወንድሞችም ከጳውሎስ አባታዊ ምክር መጠቀም ትችላላችሁ። እንዴት? ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፋቸውን ሁለት ደብዳቤዎች ለእናንተ እንደተጻፉ አድርጋችሁ በመቁጠር አንብቧቸው። ከዚያም በሕይወታችሁ ውስጥ የትኛውን ምክር በሥራ ላይ ልታውሉ እንደምትችሉ አስቡ። አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።
13. ከይሖዋ ጋር በግለሰብ ደረጃ ወዳጅነት ለመመሥረት ምን ያስፈልጋል?
13 “ለአምላክ ማደርን ግብ አድርገህ ራስህን አሠልጥን።” (1 ጢሞ. 4:7ለ) ለአምላክ ማደር ሲባል ምን ማለት ነው? በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረትና እሱን የሚያስደስተውን ነገር ለማድረግ መጓጓት ማለት ነው። ይህን ባሕርይ ይዘን አልተወለድንም፤ ስለዚህ ልናዳብረው ይገባል። ታዲያ እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? “ራስህን አሠልጥን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ለውድድር የሚዘጋጁ አትሌቶች የሚወስዱትን ከባድ ሥልጠና ለማመልከት ይሠራበት ነበር። እነዚህ አትሌቶች ራሳቸውን መገሠጽ ያስፈልጋቸው ነበር። እኛም ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ የሚረዱንን ባሕርያት ለማዳበር ራሳችንን መገሠጽ ያስፈልገናል።
14. መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ ግባችን ምን ሊሆን ይገባል? በምሳሌ አስረዳ።
14 መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ በምታዳብሩበት ጊዜ ግባችሁ ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ መሆኑን አትዘንጉ። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ሀብታሙን ወጣት አለቃ ከያዘበት መንገድ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላላችሁ? (ማር. 10:17-22) ወጣቱ፣ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን አምኖ ነበር፤ ሆኖም እሱን ለመከተል የሚያበቃ እምነት አልነበረውም። ያም ቢሆን ኢየሱስ ‘ወዶታል።’ ኢየሱስ ይህን ወጣት ያነጋገረበት መንገድ ልብ የሚነካ አይደለም? ኢየሱስ ይህ ወጣት ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ እንዲያደርግ እንደፈለገ በግልጽ ማየት ይቻላል። በተጨማሪም ኢየሱስ ወጣቱን የያዘበት መንገድ ይሖዋ ለወጣቱ ያለውን ፍቅር ያንጸባርቃል። (ዮሐ. 14:9) በዚህ ዘገባ ላይ ስታሰላስሉ የራሳችሁን ሁኔታ በአእምሯችሁ ይዛችሁ ‘ወደ ይሖዋ ለመቅረብና ሌሎችን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ለማገልገል ምን ማድረግ ያስፈልገኛል?’ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ።
15. አንድ ወጣት ወንድም ጥሩ ምሳሌ መሆኑ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ። (1 ጢሞቴዎስ 4:12, 13)
15 “ታማኞች ለሆኑት . . . አርዓያ ሁን።” (1 ጢሞቴዎስ 4:12, 13ን አንብብ።) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንደ ማንበብና ማስተማር ያሉትን ክህሎቶች ብቻ ሳይሆን እንደ ፍቅር፣ እምነትና ንጽሕና ያሉትን ባሕርያትም ጭምር እንዲያዳብር አበረታቶታል። ለምን? መልካም ምሳሌነት ከንግግር ይበልጥ ኃይል አለው። ለምሳሌ ለአገልግሎት ያለንን ቅንዓት ማሳደግ ስለምንችልበት መንገድ ንግግር እንድታቀርቡ ተጠየቃችሁ እንበል። እናንተ በአገልግሎት ላይ ምርጣችሁን የምትሰጡ ከሆነ ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ ንግግር ማቅረብ ይበልጥ ይቀላችኋል። መልካም ምሳሌነታችሁ ለንግግራችሁ ክብደት ይጨምርለታል።—1 ጢሞ. 3:13
16. (ሀ) ወጣት ክርስቲያኖች በየትኞቹ አምስት አቅጣጫዎች አርዓያ መሆን ይችላሉ? (ለ) አንድ ወጣት ወንድም “በንግግር” አርዓያ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?
16 በ1 ጢሞቴዎስ 4:12 ላይ ጳውሎስ አንድ ወጣት ወንድም አርዓያ መሆን የሚችልባቸውን አምስት አቅጣጫዎች ጠቅሷል። በግል ጥናታችሁ ላይ እያንዳንዱን አቅጣጫ ለመመርመር ለምን ግብ አታወጡም? ለምሳሌ “በንግግር” አርዓያ ለመሆን አሰባችሁ እንበል። አንደበታችሁን ተጠቅማችሁ ሌሎችን ማነጽ የምትችሉባቸውን የተለያዩ መንገዶች ለማሰብ ሞክሩ። የምትኖሩት ከወላጆቻችሁ ጋር ከሆነ ለሚያደርጉላችሁ ነገር ያላችሁን አድናቆት ለምን አዘውትራችሁ አትገልጹላቸውም? በስብሰባዎች ላይ ክፍል ያቀረቡ ወንድሞችን ከስብሰባው በኋላ ክፍላቸውን የወደዳችሁት ለምን እንደሆነ ልትነግሯቸው ትችላላችሁ። በስብሰባዎች ላይ በራሳችሁ አባባል ሐሳብ ለመስጠትም ልትሞክሩ ትችላላችሁ። በንግግር አርዓያ ለመሆን የምታደርጉት ጥረት መንፈሳዊ እድገት እያደረጋችሁ እንደሆነ ያሳያል።—1 ጢሞ. 4:15
17. አንድ ወጣት ወንድም መንፈሳዊ ግቦቹ ላይ እንዲደርስ ምን ይረዳዋል? (2 ጢሞቴዎስ 2:22)
17 “ከወጣትነት ምኞቶች ሽሽ፤ ከዚህ ይልቅ . . . ጽድቅን . . . ለማግኘት ተጣጣር።” (2 ጢሞቴዎስ 2:22ን አንብብ።) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ከመንፈሳዊ ግቦቹ ሊያሰናክሉትና ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ሊያበላሹበት ከሚችሉ ምኞቶች እንዲርቅ አሳስቦታል። እናንተም አንዳንድ ነገሮች በራሳቸው ስህተት ባይሆኑም መንፈሳዊ ግቦችን መከታተል የምትችሉበትን ጊዜ እንደሚሻሙባችሁ አስተውላችሁ ይሆናል። ለምሳሌ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ ኢንተርኔት በመቃኘት ወይም ቪዲዮ ጌሞችን በመጫወት ምን ያህል ጊዜ እንደምታሳልፉ አስቡ። ከዚያ ጊዜ ውስጥ የተወሰነውን ለቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ልታውሉት ትችሉ ይሆን? ምናልባትም የስብሰባ አዳራሻችሁን ለመንከባከብ ወይም ጉባኤያችሁ ባደራጀው የጋሪ ምሥክርነት ለመካፈል ራሳችሁን ማቅረብ ትችሉ ይሆናል። እንዲህ ባሉ እንቅስቃሴዎች ከተካፈላችሁ መንፈሳዊ ግቦችን ለማውጣትና ግቦቻችሁ ላይ ለመድረስ የሚያግዙ አዳዲስ ጓደኞችን ልታፈሩ ትችላላችሁ።
ሌሎችን ማገልገል በረከት ያስገኛል
18. ማርቆስና ጢሞቴዎስ ትርጉም ያለውና አርኪ የሆነ ሕይወት አሳልፈዋል የምንለው ለምንድን ነው?
18 ማርቆስና ጢሞቴዎስ ሌሎችን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ለማገልገል ሲሉ አንዳንድ መሥዋዕቶችን ከፍለዋል። በዚህም የተነሳ ትርጉም ያለውና አርኪ የሆነ ሕይወት ማሳለፍ ችለዋል። (ሥራ 20:35) ማርቆስ የእምነት አጋሮቹን ለማገልገል ሲል ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተጉዟል። በተጨማሪም ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚገልጽ አስገራሚ ዘገባ ጽፏል። ጢሞቴዎስ ደግሞ ጳውሎስ ጉባኤዎችን ሲያቋቁም እንዲሁም ወንድሞችንና እህቶችን ሲያበረታታ ከጎኑ ሆኖ አግዞታል። ማርቆስና ጢሞቴዎስ ባሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ይሖዋ እንደተደሰተ ምንም ጥያቄ የለውም።
19. ወጣት ወንድሞች ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ለሰጠው ምክር ትኩረት መስጠት ያለባቸው ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረጋቸውስ ምን ውጤት ያስገኛል?
19 ጳውሎስ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ የጻፋቸው ደብዳቤዎች ለእሱ ያለውን ፍቅር በግልጽ ያሳያሉ። ወጣት ወንድሞች፣ በመንፈስ መሪነት የተጻፉት እነዚህ ደብዳቤዎች ይሖዋ እናንተንም በጣም እንደሚወዳችሁ ያረጋግጣሉ። ይሖዋ እንዲሳካላችሁ ይፈልጋል። እንግዲያው የጳውሎስን አባታዊ ምክር ተከተሉ፤ እንዲሁም ሌሎችን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ለማገልገል ያላችሁን ፍላጎት አሳድጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ በአሁኑ ወቅት አርኪ የሆነ ሕይወት መምራት፣ ለወደፊቱ ደግሞ ‘እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቃችሁ መያዝ’ ትችላላችሁ።—1 ጢሞ. 6:18, 19
መዝሙር 80 “ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም”
b የሥዕሉ መግለጫ፦ ማርቆስ ጳውሎስንና በርናባስን በሚስዮናዊ ጉዟቸው ላይ ሲያገለግላቸው። ጢሞቴዎስ ወንድሞችን ለማበረታታትና ለማጠናከር ሲል አንድን ጉባኤ በፈቃደኝነት ሲጎበኝ።