የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ሐምሌ ገጽ 8-13
  • ምክር መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ምክር መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ምክር ስንጠየቅ
  • ሳንጠየቅ ምክር ስንሰጥ
  • በትክክለኛው ጊዜና በትክክለኛው መንገድ ምክር መስጠት
  • ምክር መስጠትህንና መቀበልህን ቀጥል
  • ምክር መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ‘ሽማግሌዎችን ጥራ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • የምትሰጡት ምክር ‘ልብን ደስ ያሰኛል’?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • ‘የጥበበኞችን ቃል አዳምጥ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ሐምሌ ገጽ 8-13

የጥናት ርዕስ 29

መዝሙር 87 ኑ! እረፍት አግኙ

ምክር መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?

“ዓይኔን በአንተ ላይ አድርጌ እመክርሃለሁ።”—መዝ. 32:8

ዓላማ

ውጤታማ የሆነ ምክር መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?

1. ምክር መስጠት የሚያስፈልገው ማን ነው? አብራራ።

ምክር ስለመስጠት ምን ይሰማሃል? አንዳንዶች ምክር መስጠት ያስደስታቸዋል። ሌሎች ግን ምክር ለመስጠት ያመነታሉ፤ እንዲያውም ምክር በሚሰጡበት ጊዜ በጣም ይጨንቃቸዋል። ያም ሆነ ይህ፣ ሁላችንም አልፎ አልፎ ምክር መስጠት ይጠበቅብናል። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮቹ ተለይተው የሚታወቁት አንዳቸው ለሌላው በሚያሳዩት ፍቅር እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐ. 13:35) ፍቅራችንን ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ደግሞ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምክር ሲያስፈልጋቸው ለእነሱ ምክር በመስጠት ነው። የአምላክ ቃል “ጥሩ ወዳጅነት” የሚመሠረተው “በቀና ምክር ላይ” እንደሆነ ይናገራል።—ምሳሌ 27:9

2. ሽማግሌዎች ምን ማወቅ ይኖርባቸዋል? ለምንስ? (“በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ምክር መስጠት” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

2 በተለይ ሽማግሌዎች ውጤታማ ምክር መስጠት የሚቻልበትን መንገድ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። ይሖዋና ኢየሱስ እነዚህን ወንዶች ጉባኤውን እንደ እረኞች ሆነው እንዲንከባከቡ ሾመዋቸዋል። (1 ጴጥ. 5:2, 3) ይህን የሚያደርጉበት አንዱ መንገድ ለጉባኤው ንግግሮችን ሲያቀርቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር በመስጠት ነው። ከዚህም ሌላ፣ ከመንጋው የራቁ በጎችን ጨምሮ ለወንድሞችና ለእህቶች በግለሰብ ደረጃ ምክር መስጠት ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም ጥሩ ምክር መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?

በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ሊቀ መንበሩ “ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ” የተባለውን ብሮሹር ተጠቅሞ አንድን ተማሪ ሲያመሰግነው እና ምክር ሲሰጠው።

በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ምክር መስጠት

የሳምንቱ መሃል ስብሰባ ሊቀ መንበር የተማሪ ክፍል ለሚያቀርቡ ወንድሞችና እህቶች ጠቃሚ ሐሳቦችን ይሰጣል። ተማሪው ክፍሉን በሚያቀርብበት ጊዜ ሊቀ መንበሩ፣ ተማሪው የተመደበለትን የጥናት ነጥብ ምን ያህል እንደሠራበት ይከታተላል።

ተማሪው ክፍሉን ካቀረበ በኋላ ሊቀ መንበሩ ተማሪው ጥሩ የሠራባቸውን ነጥቦች ጠቅሶ ያመሰግነዋል። አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ፣ ተማሪው የተመደበለትን የጥናት ነጥብ በተሻለ መንገድ ሊሠራበት የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ ቀጥተኛ ምክር በዘዴ ይሰጠዋል። እንዲህ ያለው ምክር ተማሪውን ብቻ ሳይሆን መላውን ጉባኤ ይጠቅማል።—ምሳሌ 27:17

3. (ሀ) ጥሩ ምክር መስጠት የሚቻልበትን መንገድ መማር የምንችለው እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 9:6፤ “ምክር ስትሰጥ የኢየሱስን ምሳሌ ተከተል” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።) (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮችን በተለይም የኢየሱስን ምሳሌ በመመርመር ጥሩ ምክር መስጠት ስለሚቻልበት መንገድ ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ለኢየሱስ ከተሰጡት የማዕረግ ስሞች አንዱ “ድንቅ መካሪ” የሚል ነው። (ኢሳይያስ 9:6⁠ን አንብብ።) በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ምክር ስንጠየቅ ምን ማድረግ እንደምንችል እንዲሁም ሳንጠየቅ ምክር መስጠት ሲኖርብን ምን ማድረግ እንደምንችል እንመለከታለን። በተጨማሪም በትክክለኛው ጊዜና በትክክለኛው መንገድ ምክር መስጠት ስላለው አስፈላጊነት እንመረምራለን።

ምክር ስትሰጥ የኢየሱስን ምሳሌ ተከተል

ኢየሱስን “ድንቅ መካሪ” እንዲሆን ያደረጉት አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለውስ እንዴት ነው?

  • ኢየሱስ ምን መናገር እንዳለበት ያውቅ ነበር። ምክሩ የተመሠረተው በራሱ ሳይሆን በይሖዋ ጥበብ ላይ ስለሆነ ምንጊዜም የሚናገረው ትክክለኛውን ነገር ነበር። “የምነግራችሁን ነገር የምናገረው ከራሴ አመንጭቼ አይደለም” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል።—ዮሐ. 14:10

    የምናገኘው ትምህርት፦ ብዙ ተሞክሮና ጥበብ ያካበትን ሰዎች ብንሆንም እንኳ የምንሰጠው ምክር ምንጊዜም በራሳችን አመለካከት ላይ ሳይሆን በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት።

  • ኢየሱስ መቼ ምክር መስጠት እንዳለበት ያውቅ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ማወቅ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በሙሉ በአንድ ጊዜ አልነገራቸውም። ከዚህ ይልቅ ደቀ መዛሙርቱን የመከራቸው ትክክለኛውን ጊዜ ጠብቆ ነው፤ ደግሞም የነገራቸው መሸከም የሚችሉትን ያህል ብቻ ነው።—ዮሐ. 16:12

    የምናገኘው ትምህርት፦ አንድን ሰው ስንመክር “ለመናገር [ትክክለኛው] ጊዜ” እስኪደርስ መጠበቅ ይኖርብናል። (መክ. 3:7) መረጃ ካዥጎደጎድንበት ግራ ሊጋባና ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል። በመሆኑም ልንሰጠው የሚገባው፣ ያጋጠመውን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስፈልገውን ያህል መረጃ ብቻ ነው።

  • ኢየሱስ በዘዴ ምክር መስጠት የሚቻልበትን መንገድ ያውቅ ነበር። ትሕትናን በተመለከተ ለደቀ መዛሙርቱ በተደጋጋሚ ምክር መስጠት አስፈልጎታል። ሆኖም ሁሌም ምክር ይሰጣቸው የነበረው በገርነትና በአክብሮት ነው።—ማቴ. 18:1-5

    የምናገኘው ትምህርት፦ ለአንድ ሰው በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ምክር መስጠት ቢያስፈልገንም እንኳ ይበልጥ ውጤታማ የምንሆነው በገርነትና በአክብሮት ከተናገርን ነው።

ምክር ስንጠየቅ

4-5. አንድ ሰው ምክር ሲጠይቀን በመጀመሪያ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል? በምሳሌ አስረዳ።

4 አንድ ሰው ምክር ሲጠይቀን የመጀመሪያ ምላሻችን ምን ሊሆን ይገባል? ግለሰቡ አክብሮ ምክር ስለጠየቀን ልንደሰትና ወዲያውኑ እርዳታ ለማበርከት ልንነሳሳ እንችላለን። ይሁንና በመጀመሪያ ‘ስለዚህ ጉዳይ ምክር ለመስጠት ብቃቱ አለኝ ወይ?’ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። አንዳንድ ጊዜ ግለሰቡን መርዳት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምክር መስጠት ሳይሆን ስለዚያ ጉዳይ ምክር ለመስጠት ብቃቱ ወዳለው ሰው ግለሰቡን መምራት ሊሆን ይችላል።

5 አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ የቅርብ ጓደኛህ ከባድ ሕመም አጋጥሞታል እንበል። ስላሉት የሕክምና አማራጮች ምርምር እያደረገ እንደሆነ ይነግርህና የትኛው የተሻለ እንደሆነ ይጠይቅሃል። አንተ የተሻለ ነው ብለህ የምታስበው የሕክምና አማራጭ ቢኖርም ከዚያ ሕመም ጋር በተያያዘ የሕክምና እውቀት የለህም፤ ሥልጠናም አልወሰድክም። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ፣ ለጓደኛህ ማድረግ የምትችለው ከሁሉ የተሻለው ነገር እሱን ለመርዳት ብቃቱ ወዳለው ሰው መምራት ነው።

6. ምክር ከመስጠታችን በፊት ጥቂት ጊዜ መቆየታችን ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው?

6 ስለ አንድ ጉዳይ ምክር ለመስጠት ብቃቱ እንዳለን ቢሰማንም እንኳ ምክር ለጠየቀን ሰው መልስ ከመስጠታችን በፊት የተወሰነ ጊዜ ለመቆየት ልንመርጥ እንችላለን። ለምን? ምሳሌ 15:28 “ጻድቅ . . . መልስ ከመስጠቱ በፊት ያሰላስላል” ይላል። ይሁንና መልሱን እንደምናውቀው ቢሰማንስ? እንደዚያም ቢሆን ጥቂት ጊዜ ወስደን ምርምር ማድረግ፣ መጸለይና ማሰላሰል እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ካለው አመለካከት ጋር ይበልጥ የሚስማማ ምክር መስጠት እንችላለን። የነቢዩ ናታንን ምሳሌ እንመልከት።

7. ከነቢዩ ናታን ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

7 ንጉሥ ዳዊት ለይሖዋ ቤተ መቅደስ የመገንባት ፍላጎት እንዳለው ለነቢዩ ናታን ነገረው። ናታንም ወዲያውኑ በሐሳቡ እንዲገፋበት መከረው። ሆኖም ናታን በመጀመሪያ ይሖዋን ቢጠይቅ ጥሩ ነበር። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ፣ ዳዊት ቤተ መቅደስ እንዲገነባለት አልፈለገም። (1 ዜና 17:1-4) ይህ ታሪክ እንደሚያሳየው ምክር ስንጠየቅ ‘ለመናገር የዘገየን’ መሆናችን ጥበብ ነው።—ያዕ. 1:19

8. ምክር ስንሰጥ እንድንጠነቀቅ የሚያነሳሳን ሌላው ምክንያት ምንድን ነው?

8 ምክር በምንሰጥበት ጊዜ እንድንጠነቀቅ የሚያነሳሳን ሌላም ምክንያት አለ፦ ግለሰቡ እኛ በሰጠነው ምክር ላይ ተመሥርቶ የሚያደርገው ውሳኔ መጥፎ ውጤት ካስከተለበት እኛም በተወሰነ መጠን ተጠያቂ ልንሆን እንችላለን። በእርግጥም፣ ምክር ከመስጠታችን በፊት በጥንቃቄ ማሰባችን በጣም አስፈላጊ ነው።

ሳንጠየቅ ምክር ስንሰጥ

9. ሽማግሌዎች ምክር ከመስጠታቸው በፊት ስለ ምን ጉዳይ እርግጠኞች መሆን ይኖርባቸዋል? (ገላትያ 6:1)

9 አልፎ አልፎ ሽማግሌዎች “የተሳሳተ ጎዳና” መከተል ለጀመረ ክርስቲያን ቅድሚያውን ወስደው ምክር መስጠት ይጠበቅባቸዋል። (ገላትያ 6:1⁠ን አንብብ።) እንዲህ ያለው ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት ወደመፈጸም ሊመሩት የሚችሉ መጥፎ ውሳኔዎችን እያደረገ ይሆናል። የሽማግሌዎቹ ግብ ግለሰቡ ወደ ዘላለም ሕይወት ከሚመራው ጎዳና እንዳይወጣ መርዳት ነው። (ያዕ. 5:19, 20) ይሁንና ምክራቸው ውጤታማ እንዲሆን ከፈለጉ በመጀመሪያ ግለሰቡ በእርግጥ የተሳሳተ ጎዳና መከተሉን እርግጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል። ይሖዋ ሁላችንም በራሳችን ሕሊና ተመሥርተን ውሳኔ እንድናደርግ ፈቅዶልናል። (ሮም 14:1-4) ይሁንና ግለሰቡ በእርግጥ የተሳሳተ ጎዳና ተከትሎ ቢሆንና ሽማግሌዎች ቅድሚያውን ወስደው ምክር ሊሰጡት እንደሚገባ ቢወስኑስ?

10-12. ሽማግሌዎች ሳይጠየቁ ምክር በሚሰጡበት ወቅት ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? በምሳሌ አስረዳ። (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

10 ሽማግሌዎች ሳይጠየቁ ምክር መስጠት ሲኖርባቸው ለየት ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። እንዴት? ሐዋርያው ጳውሎስ አንድ ሰው የተሳሳተ ጎዳና መከተሉን እንኳ ላያውቅ እንደሚችል ተናግሯል። በመሆኑም ግለሰቡ ምክሩን እንዲቀበል ሽማግሌዎች በመጀመሪያ ልቡን ሊያዘጋጁት ይገባል።

11 ሳይጠየቁ ምክር መስጠት በደደረ አፈር ላይ ዘር ለመዝራት እንደመሞከር ሊቆጠር ይችላል። አንድ ገበሬ መዝራት ከመጀመሩ በፊት መሬቱን ያርሰዋል። ይህም አፈሩ እንዲለሰልስና ዘሩን ለማብቀል ዝግጁ እንዲሆን ያደርጋል። ከዚያም ገበሬው ዘሩን ይዘራል። በመጨረሻም ዘሩ እንዲያድግ ውኃ ያጠጣዋል። በተመሳሳይም አንድ ሽማግሌ ሳይጠየቅ ምክር ከመስጠቱ በፊት በምሳሌያዊ ሁኔታ አፈሩን ማለስለሱ ጠቃሚ ነው። ወንድምን ማነጋገር የሚችልበት አመቺ ጊዜ ከመረጠ በኋላ ለወንድም በጣም እንደሚያስብለት ያረጋግጥለታል። ሽማግሌው አፍቃሪና ደግ በመሆን ረገድ ጥሩ ስም ካተረፈ ሌሎች የእሱን ምክር መቀበል ቀላል ይሆንላቸዋል።

12 በሚነጋገሩበት ወቅት ሽማግሌው ሁሉም ሰው ስህተት እንደሚሠራና አልፎ አልፎ ምክር እንደሚያስፈልገው በመናገር የግለሰቡን ልብ ማለስለሱን ሊቀጥል ይችላል። (ሮም 3:23) ግለሰቡ የተሳሳተ ጎዳና የተከተለው እንዴት እንደሆነ ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ያሳየዋል፤ ይህን የሚያደርገው በተረጋጋ ድምፅና በጥልቅ አክብሮት ነው። ወንድም ስህተት መሥራቱን አምኖ ከተቀበለ በኋላ ሽማግሌው ግለሰቡ ችግሩን ለማስተካከል ምን ማድረግ እንዳለበት በቀጥታ በመናገር “ዘሩን ይዘራል።” በመጨረሻም ሽማግሌው ወንድምን ከልቡ በማመስገንና አብሮት በመጸለይ ዘሩን “ውኃ ያጠጣል።”—ያዕ. 5:15

አንድ ሽማግሌ ለአንድ ወንድም ምክር የሚሰጥበትን መንገድ አንድ ገበሬ በደደረ አፈር ላይ ዘር ከሚዘራበት መንገድ ጋር የሚያመሳስሉ ሥዕሎች። 1. መሬቱን ማዘጋጀት፦ ገበሬው መሬቱን ያርሰዋል፤ ሽማግሌው ወንድምን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ያነጋግረዋል። 2. መዝራት፦ ገበሬው ዘሩን በታረሰው አፈር ላይ ይዘራዋል፤ ሽማግሌው መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅሞ ወንድምን ይመክረዋል። 3. ማጠጣት፦ ገበሬው ዘሩን ውኃ ያጠጣዋል፤ ሽማግሌው ከወንድም ጋር ይጸልያል።

ሳይጠየቁ ምክር መስጠት ፍቅርና ክህሎት ይጠይቃል (ከአንቀጽ 10-12⁠ን ተመልከት)


13. ሽማግሌዎች ምክር ተቀባዩ ምክሩ በትክክል እንደገባው ማረጋገጥ የሚችሉት እንዴት ነው?

13 አንዳንድ ጊዜ መካሪው የሚናገረው ነገርና ምክር ተቀባዩ የሚያዳምጠው ነገር የተለያየ ሊሆን ይችላል። ሽማግሌዎች ይህ እንዳይሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? በዘዴና በአክብሮት አንዳንድ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ቁልፍ ነጥቦቹን ማጉላት ይችላሉ። (መክ. 12:11) ግለሰቡ የሚሰጠው መልስ ምክሩ በትክክል ገብቶታል ወይ የሚለውን ለማረጋገጥ ያስችላል።

በትክክለኛው ጊዜና በትክክለኛው መንገድ ምክር መስጠት

14. ተቆጥተን እያለ ምክር ልንሰጥ ይገባል? አብራራ።

14 ሁላችንም ፍጽምና ይጎድለናል፤ በመሆኑም ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ነገር መናገራችን ወይም ማድረጋችን አይቀርም። (ቆላ. 3:13) እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ አንዳችን ሌላውን ልናስቆጣ እንደምንችል የአምላክ ቃል ይናገራል። (ኤፌ. 4:26) ሆኖም ተቆጥተን እያለ ምክር ከመስጠት ልንቆጠብ ይገባል። ለምን? ምክንያቱም “የሰው ቁጣ የአምላክ ጽድቅ እንዲፈጸም አያደርግም።” (ያዕ. 1:20) ተቆጥተን እያለ ምክር ብንሰጥ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ይህ ሲባል ግን ላበሳጨን ሰው ሐሳባችንን ወይም ስሜታችንን ፈጽሞ መግለጽ የለብንም ማለት አይደለም። ሆኖም እስክንረጋጋ ከጠበቅን ሐሳባችንን በተሻለ መንገድ መግለጽ እንችላለን። የኢዮብ ታማኝ መካሪ የሆነው ኤሊሁ የተወውን ምሳሌ እንመልከት።

15. ከኤሊሁ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

15 ኤሊሁ፣ ኢዮብ አጽናኝ ተብዬዎቹ ለሰነዘሩበት ክስ መልስ ሲሰጥ ለቀናት አዳምጧል። ኤሊሁ ለኢዮብ አዝኖለታል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢዮብ ስለ ይሖዋ ትክክል ያልሆነ ነገር በመናገሩ እንዲሁም ከመጠን በላይ በራሱ ላይ ትኩረት በማድረጉ በእሱ ላይ ቁጣው ነዷል። ያም ቢሆን ኤሊሁ ለመናገር ተራው እስኪደርስ ጠብቋል፤ ለኢዮብ ምክር በሰጠበት ጊዜም በገርነትና በጥልቅ አክብሮት አነጋግሮታል። (ኢዮብ 32:2፤ 33:1-7) ኤሊሁ የተወው ምሳሌ ወሳኝ እውነታ ያስተምረናል፦ ምክር ውጤታማ የሚሆነው በትክክለኛው ጊዜና በትክክለኛው መንገድ ማለትም በአክብሮትና በፍቅር ሲሰጥ ነው።—መክ. 3:1, 7

ኤሊሁ በቁስል የተወረሰውን ኢዮብን በርኅራኄ ሲያዳምጠው።

ኤሊሁ ቁጣው ነድዶ የነበረ ቢሆንም ምክር የሰጠው በገርነትና በጥልቅ አክብሮት ነው (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)


ምክር መስጠትህንና መቀበልህን ቀጥል

16. ከመዝሙር 32:8 ምን ትምህርት እናገኛለን?

16 ይህ የጥናት ርዕስ የተመሠረተበት የጭብጥ ጥቅስ ይሖዋ ‘ዓይኑን በእኛ ላይ አድርጎ እንደሚመክረን’ ይናገራል። (መዝሙር 32:8⁠ን አንብብ።) ይህም ይሖዋ በቀጣይነት እንደሚረዳን ያመለክታል። ለእኛ ምክር ከመስጠት ባለፈ ምክሩን በሥራ ላይ እንድናውል ይረዳናል። እኛም የእሱን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ለሌሎች ምክር የመስጠት መብት ስናገኝ ዓይናችንን በእነሱ ላይ አድርገን የሚያስፈልጋቸውን ማንኛውንም እርዳታ በመስጠት የይሖዋን ምሳሌ እንከተል።

17. በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ቀጥተኛ ምክር የሚሰጡ ሽማግሌዎች እንደ ምን ይቆጠራሉ? አብራራ። (ኢሳይያስ 32:1, 2)

17 ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአሁኑ ወቅት ምክር መስጠትና መቀበል ያስፈልገናል። (2 ጢሞ. 3:1) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ቀጥተኛ ምክር የሚሰጡ ሽማግሌዎች “ውኃ በሌለበት ምድር እንደ ጅረት” ናቸው። (ኢሳይያስ 32:1, 2⁠ን አንብብ።) መስማት የምንፈልገውን ነገር እያወቁ መስማት የሚያስፈልገንን ነገር የሚነግሩን ጓደኞች “ከብር በተሠራ ዕቃ ላይ እንዳለ የወርቅ ፖም” ውድ የሆነ ስጦታ ይሰጡናል። (ምሳሌ 25:11) እንግዲያው ሁላችንም ጥሩ ምክር ለመስጠትና ለመቀበል የሚያስፈልገውን ጥበብ ማዳበራችንን እንቀጥል።

ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

  • ምክር ስንጠየቅ

  • ሳንጠየቅ ምክር መስጠት ሲኖርብን

  • ስንቆጣ

መዝሙር 109 አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ