የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ሐምሌ ገጽ 2-7
  • ምክር መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ምክር መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የትኞቹ ባሕርያት ያስፈልጉኛል?
  • ጥሩ ምክር ሊሰጠኝ የሚችለው ማን ነው?
  • አእምሮዬንና ልቤን ክፍት ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?
  • ሌሎች ውሳኔ እንዲያደርጉልኝ ልጠይቅ ይገባል?
  • ምክር መሻታችሁን ቀጥሉ
  • ምክር መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • ታማኝ ሰዎች ከተናገሯቸው የስንብት ቃላት ተማሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ሐምሌ ገጽ 2-7

የጥናት ርዕስ 28

መዝሙር 88 መንገድህን አሳውቀኝ

ምክር መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው?

“ምክር በሚሹ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች።”—ምሳሌ 13:10

ዓላማ

ከሚሰጠን ምክር የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

1. ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ እንዲሁም ዕቅዳችንን ማሳካት የምንችለው እንዴት ነው? (ምሳሌ 13:10፤ 15:22)

ሁላችንም ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ እንፈልጋለን። እንዲሁም ሁላችንም ዕቅዳችን እንዲሳካ እንፈልጋለን። የአምላክ ቃል ሁለቱንም ነገሮች ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይገልጽልናል።—ምሳሌ 13:10፤ 15:22⁠ን አንብብ።

2. ይሖዋ ምን ቃል ገብቶልናል?

2 እርግጥ ነው፣ ከሁሉ የተሻለ ምክርና ጥበብ ሊሰጠን የሚችለው አባታችን ይሖዋ ነው። “ዓይኔን በአንተ ላይ አድርጌ እመክርሃለሁ” በማለት እንደሚረዳን ቃል ገብቶልናል። (መዝ. 32:8) ይህ ጥቅስ፣ ይሖዋ ለእኛ ምክር በመስጠት ብቻ እንደማይወሰን ይገልጽልናል፤ ከዚህ ይልቅ በግለሰብ ደረጃ ትኩረት በመስጠት ምክሩን በሥራ ላይ እንድናውል ይረዳናል።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የአምላክን ቃል ተጠቅመን አራት ጥያቄዎችን እንመልሳለን፦ (1) ከሚሰጠኝ ጥሩ ምክር ጥቅም ለማግኘት የትኞቹ ባሕርያት ያስፈልጉኛል? (2) ጥሩ ምክር ሊሰጠኝ የሚችለው ማን ነው? (3) ምክር ስጠይቅ አእምሮዬንና ልቤን ክፍት ማድረግ የምችለው እንዴት ነው? (4) ሌሎች ውሳኔ እንዲያደርጉልኝ ከመጠየቅ መቆጠብ ያለብኝ ለምንድን ነው?

የትኞቹ ባሕርያት ያስፈልጉኛል?

4. ከምናገኘው ጥሩ ምክር መጠቀም ከፈለግን የትኞቹ ባሕርያት ያስፈልጉናል?

4 ከሚሰጠን ጥሩ ምክር ለመጠቀም ትሑት መሆን እና ልካችንን ማወቅ ያስፈልገናል። በራሳችን ብቻ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ተሞክሮና እውቀት እንደሚጎድለን አምነን መቀበል ይኖርብናል። ትሑቶችና ልካችንን የምናውቅ ካልሆንን የይሖዋን እርዳታ ማግኘት አንችልም። በመሆኑም የአምላክን ቃል በማንበብ የምናገኘው ማንኛውም ምክር ድንጋይ ላይ ውኃ እንደማፍሰስ ይሆናል። (ሚክ. 6:8፤ 1 ጴጥ. 5:5) ትሑትና ልካችንን የምናውቅ ከሆንን ግን የምንሰማውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ለመቀበልና ምክሩን በሥራ ላይ ለማዋል ፈጣን እንሆናለን።

5. ንጉሥ ዳዊት ኩሩ እንዲሆን ሊያደርጉት የሚችሉ ምን ስኬቶች አግኝቷል?

5 ከንጉሥ ዳዊት ምሳሌ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት። ያገኛቸው ስኬቶች ኩሩ እንዲሆን ሊያደርጉት ይችሉ ነበር። ንጉሥ ከመሆኑ ከረጅም ጊዜ በፊት በሙዚቃ ችሎታው ታዋቂ ነበር። እንዲያውም ለንጉሡ ሙዚቃ እንዲጫወት ተጠይቋል። (1 ሳሙ. 16:18, 19) ይሖዋ ዳዊትን ቀጣዩ ንጉሥ እንዲሆን ከቀባው በኋላ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ኃይል ሰጥቶታል። (1 ሳሙ. 16:11-13) ዳዊት ግዙፉን ፍልስጤማዊ ጎልያድን ጨምሮ የእስራኤልን ጠላቶች በመደምሰሱ በሕዝቡ ዘንድ ዝና አትርፎ ነበር። (1 ሳሙ. 17:37, 50፤ 18:7) ዳዊት ኩሩ ቢሆን ኖሮ ካገኛቸው ታላላቅ ስኬቶች አንጻር የሌሎችን ምክር መስማት እንደማያስፈልገው ሊሰማው ይችል ነበር። ዳዊት ግን ትሑት ነበር።

6. ዳዊት ምክር ይሰማ እንደነበር እንዴት እናውቃለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 ዳዊት ንጉሥ ከሆነ በኋላ ምክር ከሚሰጡት ሰዎች ጋር ይቀራረብ ነበር። (1 ዜና 27:32-34) ደግሞም ይህ መሆኑ አያስገርምም፤ ምክንያቱም ዳዊት ቀድሞውንም ቢሆን ምክር የመስማት ልማድ ነበረው። ከወንዶች ብቻ ሳይሆን አቢጋኤል ከተባለች ሴትም ምክር ተቀብሏል። አቢጋኤል አክብሮት የለሽ፣ ምስጋና ቢስና ትዕቢተኛ የሆነው የናባል ሚስት ነበረች። ዳዊት፣ አቢጋኤል የሰጠችውን ጥሩ ምክር በትሕትና ተግባራዊ አድርጓል፤ ይህም ከባድ ስህተት ከመሥራት ጠብቆታል።—1 ሳሙ. 25:2, 3, 21-25, 32-34

ንጉሥ ዳዊት፣ አቢጋኤል መሬት ላይ ተንበርክካ ስትለምነው በጥሞና ሲያዳምጣት።

ዳዊት፣ አቢጋኤል የሰጠችውን ምክር በትሕትና ተቀብሎ ተግባራዊ አድርጓል (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)


7. ከዳዊት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? (መክብብ 4:13) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

7 ከዳዊት አንዳንድ ትምህርቶችን ማግኘት እንችላለን። ለምሳሌ አንድ ዓይነት ችሎታ ወይም ኃላፊነት ሊኖረን ይችላል። ያም ቢሆን ሁሉንም ነገር እንደምናውቅ እንዲሁም ምክር እንደማያስፈልገን ሊሰማን አይገባም። ደግሞም ልክ እንደ ዳዊት፣ አንድ ጥሩ ምክር ከማንም ቢመጣ ለመስማት ፈቃደኛ መሆን አለብን። (መክብብ 4:13⁠ን አንብብ።) እንዲህ ካደረግን እኛንም ሆነ ሌሎችን ለሐዘን ሊዳርጉ የሚችሉ ከባድ ስህተቶችን ከመፈጸም እንጠበቃለን።

ሥዕሎች፦ 1. አራት ሽማግሌዎች አንድ ላይ ተሰብስበዋል። አንደኛው ሽማግሌ በቁጣ እየተናገረ ነው። 2. በስብሰባው ላይ ተገኝቶ የነበረ አንድ ወጣት ሽማግሌ ተቆጥቶ የነበረውን ሽማግሌ በኋላ ላይ መኪና ውስጥ በግል ሲያነጋግረው።

ምክሩን የሰጠን ማንም ይሁን ማን፣ የሚሰጠንን ጥሩ ምክር ለማዳመጥ ፈቃደኞች መሆን አለብን (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)c


ጥሩ ምክር ሊሰጠኝ የሚችለው ማን ነው?

8. ዮናታን ለዳዊት ምክር ለመስጠት ብቃት አለው የምንለው ለምንድን ነው?

8 ከዳዊት የምናገኘውን አንድ ሌላ ትምህርት እንመልከት። ምክር የጠየቃቸው ሰዎች ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ ስላጋጠመው ተፈታታኝ ሁኔታ ጥሩ ግንዛቤ ያላቸውም ነበሩ። ለምሳሌ ከንጉሥ ሳኦል ጋር ያለውን ግንኙነት ከማሻሻል ጋር በተያያዘ ምክር የተቀበለው የሳኦል ልጅ ከሆነው ከዮናታን ነው። ሆኖም ዮናታን ጥሩ ምክር ሊሰጠው የቻለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ዮናታን በአንድ በኩል ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ነበረው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሳኦልን በደንብ ያውቀው ነበር። (1 ሳሙ. 20:9-13) ይህን ትምህርት በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት ነው?

9. ምክር ሲያስፈልገን ማንን መጠየቅ ይኖርብናል? አብራራ። (ምሳሌ 13:20)

9 ምክር የምንጠይቀው ሰው ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ያለው ብቻ ሳይሆን እርዳታ ስለሚያስፈልገን ጉዳይ ጥሩ ግንዛቤ ያለው ሊሆን ይገባል።a (ምሳሌ 13:20⁠ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል አንድ ወጣት ወንድም ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት ፈልጓል እንበል። ጥሩ ምክር ሊሰጠው የሚችለው ማን ነው? ባለትዳር ያልሆነ ጓደኛው በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተ ጥሩ ምክር ሊሰጠው ይችል ይሆናል። ሆኖም ይህ ወጣት ወንድም እሱን በደንብ የሚያውቁትና ረዘም ላለ ጊዜ አስደሳች የትዳር ሕይወት ያሳለፉ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ባልና ሚስት ቢያማክር ለእሱ የሚሆን ቀጥተኛና ተግባራዊ ምክር ማግኘት ይችላል።

10. ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመለከታለን?

10 እስካሁን፣ ሊኖሩን የሚገቡ ሁለት ባሕርያትንና ጥሩ ምክር ሊሰጠን የሚችለው ማን እንደሆነ ተመልክተናል። ከዚህ በመቀጠል፣ ምክር ስንጠይቅ አእምሯችንንና ልባችንን ክፍት ማድረግ ያለብን ለምን እንደሆነ እንዲሁም ሌሎች ውሳኔ እንዲያደርጉልን መጠየቅ የሌለብን ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

አእምሮዬንና ልቤን ክፍት ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

11-12. (ሀ) አንዳንድ ጊዜ ምን ልናደርግ እንችላለን? (ለ) ንጉሥ ሮብዓም ከባድ ውሳኔ ማድረግ ባስፈለገው ጊዜ ምን አደረገ?

11 አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው ምክር ሊጠይቅ ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የሚፈልገው ላደረገው ውሳኔ ማረጋገጫ ማግኘት ነው። እንዲህ ያለው ግለሰብ አእምሮውንና ልቡን ክፍት አድርጓል ማለት አይቻልም። የንጉሥ ሮብዓም ታሪክ ማስጠንቀቂያ ሊሆንለት ይገባል።

12 ሮብዓም ንጉሥ ሰለሞንን ተክቶ በእስራኤል ላይ ነገሠ። ሮብዓም የተረከበው ብሔር ባለጸጋ ነበር፤ ሆኖም ሕዝቡ ሰለሞን ሸክም እንዳበዛባቸው ተሰምቷቸው ነበር። በመሆኑም ሕዝቡ ወደ ሮብዓም መጥተው ሸክማቸውን እንዲያቀልላቸው ለመኑት። ሮብዓም ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ለማሰብ ጊዜ እንዲሰጡት ጠየቃቸው። መጀመሪያ ላይ ያደረገው ነገር ጥሩ ነበር፤ ሰለሞንን ይረዱት የነበሩትን ሽማግሌዎች ምክር ጠየቀ። (1 ነገ. 12:2-7) ነገር ግን እነዚህ ሽማግሌዎች የሰጡትን ምክር አልተቀበለም። እንዲህ ያደረገው ለምን ይሆን? ሮብዓም ምን እንደሚያደርግ አስቀድሞ ከወሰነ በኋላ ውሳኔውን የሚደግፍለት ሰው እየፈለገ ይሆን? እንደዚያ ከሆነ፣ አብሮ አደጎቹ ከሰጡት ምክር የሚፈልገውን ማረጋገጫ አግኝቷል። (1 ነገ. 12:8-14) ሮብዓም በዚህ ምክር ላይ ተመሥርቶ ለሕዝቡ መልስ ሰጣቸው። በዚህም የተነሳ ብሔሩ ለሁለት ተከፈለ፤ ከዚያ በኋላ ሮብዓም ችግር አልተለየውም።—1 ነገ. 12:16-19

13. አእምሯችንና ልባችን ክፍት መሆኑን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

13 ከሮብዓም ታሪክ ምን እንማራለን? ምክር ስንጠይቅ አእምሯችንንና ልባችንን ክፍት ማድረግ ይኖርብናል። ይሁንና አእምሯችንና ልባችን ክፍት መሆኑን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ምክር ከጠየቅኩ በኋላ መስማት የምፈልገው ነገር ካልተነገረኝ ምክሩን ወዲያውኑ ችላ እለዋለሁ?’ እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።

14. ምክር ሲሰጠን ምን ማስታወስ ይኖርብናል? በምሳሌ አስረዳ። (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 አንድ ወንድም ጥሩ ገንዘብ የሚያስገኝ ሥራ አግኝቷል እንበል። ሥራውን ከመቀበሉ በፊት አንድ ሽማግሌ ምክር እንዲሰጠው ጠየቀ። ወንድም ሥራው ረዘም ላለ ጊዜ ከቤተሰቡ ተለይቶ እንዲቆይ እንደሚያደርገው ተናገረ። ሽማግሌውም የወንድም ዋነኛ ኃላፊነት የቤተሰቡን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት እንደሆነ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት አስታወሰው። (ኤፌ. 6:4፤ 1 ጢሞ. 5:8) ወንድም፣ ሽማግሌው የሰጠው ምክር ስላልጣመው እሱ መስማት የሚፈልገውን ነገር የሚነግረው ሰው እስኪያገኝ ድረስ ሌሎች ወንድሞችን ምክር ቢጠይቅስ? ወንድም በእርግጥ ምክር እየፈለገ ነው ሊባል ይችላል? ወይስ ያደረገውን ውሳኔ የሚደግፍለት ሰው እየፈለገ ነው? ልባችን ከዳተኛ እንደሆነ ማስታወስ አለብን። (ኤር. 17:9) አንዳንድ ጊዜ በጣም የሚያስፈልገን ምክር መስማት የማንፈልገው ምክር ነው።

አንዲት እህት የተለያዩ ወንድሞችና እህቶችን ምክር ስትጠይቅ። ሁሉም የሰጧት ምክር ስላላረካት ከአንዱ ወደ ሌላው ትሄዳለች።

የምንፈልገው ጥሩ ምክር ነው ወይስ ውሳኔያችንን የሚደግፍልን ሰው? (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)


ሌሎች ውሳኔ እንዲያደርጉልኝ ልጠይቅ ይገባል?

15. ምን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብናል? ለምንስ?

15 እያንዳንዳችን የራሳችንን ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት አለብን። (ገላ. 6:4, 5) እስካሁን እንደተመለከትነው፣ ጥበበኛ ሰው ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ከአምላክ ቃልና ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ምክር ይፈልጋል። ሆኖም ሌሎች ውሳኔ እንዲያደርጉልን ከመጠየቅ መቆጠብ ይኖርብናል። አንዳንዶች “በእኔ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?” ብለው አንድ የሚያከብሩትን ሰው በቀጥታ ይጠይቃሉ። ሌሎች ደግሞ ስለ ጉዳዩ ብዙም ሳያስቡበት ሌላ ሰው ያደረገውን ውሳኔ ይኮርጃሉ።

16. በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ ለጣዖት ከተሠዋ ሥጋ ጋር በተያያዘ ምን ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር? እንዲህ ያለውን ሥጋ ስለመብላት ውሳኔ ማድረግ የማን ኃላፊነት ነው? (1 ቆሮንቶስ 8:7፤ 10:25, 26)

16 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ፣ ለጣዖት መሥዋዕት ተደርጎ ሊሆን ከሚችል ሥጋ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጳውሎስ ለእነዚህ ክርስቲያኖች “በዓለም ላይ ጣዖት ከንቱ እንደሆነና ከአንዱ በቀር አምላክ እንደሌለ እናውቃለን” በማለት ጽፎላቸዋል። (1 ቆሮ. 8:4) አንዳንድ የጉባኤው አባላት ይህን በማሰብ፣ ለጣዖት ተሠውቶ የነበረ ሥጋ በኋላ ላይ በሥጋ ገበያ ሲሸጥ መብላት እንደሚችሉ ተሰምቷቸው ነበር። ሌሎች ግን እንዲህ ያለውን ሥጋ ለመብላት ሕሊናቸው አልፈቀደላቸውም። (1 ቆሮንቶስ 8:7፤ 10:25, 26⁠ን አንብብ።) ይህ የግል ውሳኔ ነው። ጳውሎስ፣ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለሌሎች ውሳኔ እንዲያደርጉ ወይም ሌሎች ያደረጉትን ነገር እንዲኮርጁ አልነገራቸውም። ‘እያንዳንዳቸው ስለ ራሳቸው ለአምላክ መልስ ይሰጣሉ።’—ሮም 14:10-12

17. ሌሎች ያደረጉትን ውሳኔ ዝም ብለን ከኮረጅን ምን ሊፈጠር ይችላል? ምሳሌ ስጥ። (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

17 በዛሬው ጊዜስ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችለው እንዴት ነው? የንዑሳን የደም ክፍልፋዮችን ጉዳይ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እያንዳንዱ ክርስቲያን ንዑሳን ክፍልፋዮችን ለመቀበል ወይም ላለመቀበል የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል።b ይህን ጉዳይ ሙሉ በሙሉ መረዳት ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ሆኖም እንዲህ ያለው ውሳኔ እያንዳንዳችን ልንሸከመው ከሚገባው ሸክም ውስጥ ይካተታል። (ሮም 14:4) ሌላ ሰው ያደረገውን ውሳኔ ዝም ብለን ብንኮርጅ ሕሊናችንን ልናዳክመው እንችላለን። ሕሊናችን የሚሠለጥነውና የሚሻሻለው ስናሠራው ብቻ ነው። (ዕብ. 5:14) ታዲያ የጎለመሱ ክርስቲያኖችን ምክር መጠየቅ የሚኖርብን መቼ ነው? በራሳችን በቂ ምርምር ካደረግን በኋላም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለእኛ ሁኔታ የሚሠሩት እንዴት እንደሆነ ለመረዳት ተጨማሪ እገዛ ካስፈለገን ነው።

ሥዕሎች፦ 1. አንድ ወንድም መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ለዘላለም በደስታ ኑር!” የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 39 እንዲሁም “ደምን በመጠቀም ከሚሰጡ ሕክምናዎች ጋር በተያያዘ ውሳኔ ማድረግ” የተባለውን ቪዲዮ ተጠቅሞ የሕክምና መመሪያ ካርድ ሲሞላ። 2. በኋላ ላይ አንድ የጎለመሰ ወንድም አንድ ጥቅስ አውጥቶ ሲያወያየው በጥሞና ያዳምጣል።

ምክር መጠየቅ ያለብን የራሳችንን ምርምር ካደረግን በኋላ ብቻ ነው (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)


ምክር መሻታችሁን ቀጥሉ

18. ይሖዋ ምን አድርጎልናል?

18 ይሖዋ የራሳችንን ውሳኔ እንድናደርግ በመፍቀድ በጣም እንደሚተማመንብን አሳይቶናል። ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ እንድናመዛዝን የሚረዱ ጥበበኛ ወዳጆች ሰጥቶናል። በዚህ መንገድ የአባትነት ኃላፊነቱን ተወጥቷል። (ምሳሌ 3:21-23) ታዲያ እኛ አመስጋኝነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

19. ይሖዋን ምንጊዜም ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው?

19 ወላጆች ልጆቻቸው አድገው አሳቢ፣ ጥበበኛ እንዲሁም ሌሎችን የሚረዱ ጎልማሳ የይሖዋ አገልጋዮች ሲሆኑ በጣም ይደሰታሉ። በተመሳሳይም ይሖዋ በመንፈሳዊ ስንጎለምስ፣ ምክር ስንጠይቅ እንዲሁም እሱን የሚያስከብር ውሳኔ ስናደርግ ይደሰታል።

ከሚሰጥህ ጥሩ ምክር ለመጠቀም የሚከተሉት ነገሮች የሚያስፈልጉህ ለምንድን ነው?

  • ትሑት መሆንና ልክህን ማወቅ

  • አእምሮህንና ልብህን ክፍት ማድረግ

  • የራስህን ውሳኔ ማድረግ

መዝሙር 127 ምን ዓይነት ሰው መሆን አለብኝ?

a ክርስቲያኖች አንዳንድ ጊዜ ከገንዘብ፣ ከሕክምና ወይም ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ይሖዋን የማያመልኩ ሰዎችን ማማከራቸው ጥበብ ሊሆን ይችላል።

b ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 39 ነጥብ 5⁠ን እና “ምርምር አድርግ” የሚለውን ክፍል ተመልከት።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ሽማግሌ አብሮት ለሚያገለግል ሌላ ሽማግሌ፣ በሽማግሌዎች ስብሰባ ላይ የተናገረበትን መንገድ አስመልክቶ ምክር ይሰጠዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ