የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ሐምሌ ገጽ 20-25
  • ባለህ ረክተህ የመኖርን “ሚስጥር” ተምረሃል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ባለህ ረክተህ የመኖርን “ሚስጥር” ተምረሃል?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አመስጋኝነትን አዳብር
  • በይሖዋ ዓላማ ላይ አተኩር፤ እንዲሁም ትሑት ሁን
  • በተስፋህ ላይ አሰላስል
  • “እሱን የሚፈሩ የሚያጡት ነገር የለም”
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ይሖዋ “ሕያው አምላክ” እንደሆነ አስታውስ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • እውነትን ለይተህ ማወቅ ትችላለህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ሐምሌ ገጽ 20-25

የጥናት ርዕስ 31

መዝሙር 111 ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች

ባለህ ረክተህ የመኖርን “ሚስጥር” ተምረሃል?

“በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሆን ባለኝ ረክቼ መኖርን ተምሬአለሁ።”—ፊልጵ. 4:11

ዓላማ

አመስጋኝነትን በማዳበር፣ በይሖዋ ዓላማ ላይ በማተኮርና ትሑት በመሆን እንዲሁም በወደፊቱ ተስፋችን ላይ በማሰላሰል ባለን ነገር መርካትን መማር እንችላለን።

1. ባለን ነገር መርካት ሲባል ምን ማለት ነው? ምን ማለትስ አይደለም?

ባለህ ነገር የምትረካ ሰው ነህ? ባለው ነገር የሚረካ ሰው ባገኛቸው በረከቶች ላይ ስለሚያተኩር ደስታና ሰላም ይኖረዋል። በጎደሉት ነገሮች ምክንያት አይመረርም ወይም አይበሳጭም። ይሁንና ባለን ነገር መርካት ሲባል ግድየለሽ መሆን ማለት አይደለም። ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን አገልግሎቱን ለማስፋት ጥረት ማድረጉ ተገቢ ነው። (ሮም 12:1፤ 1 ጢሞ. 3:1) ያም ቢሆን የአገልግሎት መብቶችን በጠበቀው ጊዜ ባያገኝ ደስታውን አያጣም።

2. ባለን ነገር አለመርካት በጣም አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

2 ባለን ነገር አለመርካት ከባድ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። ባላቸው ነገር መቼም ቢሆን የማይረኩ ሰዎች የማያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ለማግኘት ሲሉ በቀን ውስጥ በጣም ለረጅም ሰዓት ሊሠሩ ይችላሉ። የሚያሳዝነው አንዳንድ ክርስቲያኖች ገንዘብ ወይም ሌላ ነገር እስከመስረቅ ደርሰዋል። እንዲህ ያደረጉት ‘ይህ ነገር ለእኔ ይገባኛል፣’ ‘እስካሁን ረጅም ጊዜ ጠብቄያለሁ’ ወይም ‘ገንዘቡን ወደፊት መልሼ እከፍላለሁ’ ብለው አስበው ይሆናል። ይሁንና ማንኛውም ዓይነት ስርቆት ይሖዋን ያሳዝነዋል እንዲሁም ያሰድበዋል። (ምሳሌ 30:9) ሌሎች ደግሞ የፈለጉትን የአገልግሎት መብት ባለማግኘታቸው በጣም ስላዘኑ ከናካቴው ይሖዋን ማገልገላቸውን አቁመዋል። (ገላ. 6:9) ራሱን የወሰነ አንድ የይሖዋ አገልጋይ እንዲህ የማድረግ ሐሳብ እንኳ እንዴት ወደ አእምሮው ይመጣል? ችግሩ፣ ግለሰቡ ባለው ነገር መርካቱን ማቆሙ ሊሆን ይችላል።

3. በፊልጵስዩስ 4:11, 12 ላይ የትኛውን የሚያበረታታ ትምህርት እናገኛለን?

3 ሁላችንም ባለን ነገር የመርካት ዝንባሌን ማዳበር እንችላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሆን ባለኝ ረክቼ መኖርን ተምሬአለሁ” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:11, 12⁠ን አንብብ።) እነዚህን ቃላት የጻፈው በእስር ላይ ሆኖ ነው። ያም ቢሆን ደስታውን አላጣም። ባለው ነገር የመርካትን ‘ሚስጥር ተምሯል።’ ባለን ነገር መርካት የሚከብደን ከሆነ ጳውሎስ የተናገራቸው ቃላትና የእሱ ተሞክሮ ይህን ዝንባሌ ማዳበር እንደምንችል ያረጋግጡልናል። ባለን ነገር የመርካት ዝንባሌ በራሱ የሚመጣ ነገር እንደሆነ ማሰብ የለብንም። ከዚህ ይልቅ ልንማረው የሚገባ ነገር ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ባለን ነገር የመርካትን ሚስጥር ለመማር የሚረዱንን ሦስት ባሕርያት እስቲ እንመልከት።

አመስጋኝነትን አዳብር

4. አመስጋኝ መሆናችን ባለን ነገር እንድንረካ የሚረዳን እንዴት ነው? (1 ተሰሎንቄ 5:18)

4 አመስጋኝ መሆናችን ባለን ነገር ለመርካት ይረዳናል። (1 ተሰሎንቄ 5:18⁠ን አንብብ።) ለምሳሌ ለሕይወት የሚያስፈልጉን ነገሮች ስላሉን ከልባችን አመስጋኝ ከሆንን ስለምንፈልጋቸው ሆኖም ስላላገኘናቸው ነገሮች ከመጠን በላይ አንብሰለሰልም። አሁን ላሉን የአገልግሎት መብቶች አድናቆት ካለን አዲስ መብት ስለማግኘት ከመጠን በላይ ከማውጠንጠን ይልቅ አሁን ያለንን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ላይ እናተኩራለን። ቅዱሳን መጻሕፍት በጸሎታችን ውስጥ ምስጋና እንድናካትት የሚመክሩን መሆኑ አያስገርምም። አመስጋኝ መሆናችን ‘ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክ ሰላም’ ለማጣጣም ይረዳናል።—ፊልጵ. 4:6, 7

5. እስራኤላውያን አመስጋኝ ለመሆን የሚያነሳሳ ምን ምክንያት ነበራቸው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

5 እስራኤላውያን ምን እንዳጋጠማቸው እንመልከት። በግብፅ ይመገቧቸው የነበሩትን ምግቦች ባለማግኘታቸው የተነሳ በተደጋጋሚ በይሖዋ ላይ አጉረምርመዋል። (ዘኁ. 11:4-6) እርግጥ ነው፣ በምድረ በዳ ውስጥ የነበራቸው ሕይወት ቀላል አልነበረም። ሆኖም ባላቸው ነገር እንዲረኩ ምን ሊረዳቸው ይችል ነበር? ይሖዋ ባደረገላቸው ነገሮች ላይ በአመስጋኝነት ማሰላሰል ነበረባቸው። በግብፅ ባሪያዎች በነበሩበት ወቅት ይሖዋ በጭካኔ በሚያሠቃዩአቸው ሰዎች ላይ አሥር መቅሰፍቶች አምጥቶባቸዋል። እስራኤላውያን ነፃ ከወጡ በኋላ ብር፣ ወርቅና ልብስ በመውሰድ ‘ግብፃውያኑን በዘበዟቸው።’ (ዘፀ. 12:35, 36) እስራኤላውያን ግብፃውያኑ እያሳደዷቸው ቀይ ባሕር ዳርቻ ሲደርሱ ይሖዋ በተአምራዊ መንገድ ውኃውን ለሁለት ከፈለው። ከዚያም በምድረ በዳ ውስጥ ሲጓዙ በየዕለቱ መና በመስጠት መግቧቸዋል። ታዲያ ችግራቸው ምን ነበር? እስራኤላውያን ባላቸው ነገር ያልረኩት የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ስላላገኙ ሳይሆን ለተደረገላቸው ነገር አመስጋኝ ስላልነበሩ ነው።

አንዳንድ እስራኤላውያን የሚሰበስቡትን መና አስመልክቶ ለሙሴ ሲያጉረመርሙ ሌሎች ደግሞ በአቅራቢያቸው መና እየሰበሰቡ ይመለከቷቸዋል።

እስራኤላውያን ባላቸው ነገር ያልረኩት ለምንድን ነው? (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት)


6. የአመስጋኝነት መንፈስን ማዳበር የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

6 ታዲያ የአመስጋኝነት መንፈስ ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ በየዕለቱ ስላሉህ መልካም ነገሮች የምታስብበት ጊዜ መድብ። ምናልባትም አመስጋኝ ለመሆን የሚያነሳሱህን ሁለት ወይም ሦስት ነገሮች ልትጽፍ ትችላለህ። (ሰቆ. 3:22, 23) ሁለተኛ፣ አመስጋኝነትህን ግለጽ። ሌሎች መልካም ነገር ሲያደርጉልህ ሳትረሳ አመስግን። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ይሖዋን አዘውትረህ አመስግነው። (መዝ. 75:1) ሦስተኛ፣ አመስጋኝ የሆኑ ሰዎችን የቅርብ ጓደኛ አድርገህ ምረጥ። አመስጋኝነት ወደ ሌሎች የሚጋባ ባሕርይ ነው፤ ምስጋና ቢስነትም እንደዚያው። (ዘዳ. 1:26-28፤ 2 ጢሞ. 3:1, 2, 5) አመስጋኝነታችንን በመግለጽ ላይ ካተኮርን ባለን ነገር ያለመርካታችን አጋጣሚ ይቀንሳል።

7. አቺ የአመስጋኝነት መንፈስ ማዳበር የቻለችው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?

7 በኢንዶኔዥያ የምትኖረው አቺ ምን እንዳጋጠማት እንመልከት። እንዲህ ስትል ሳትሸሽግ ተናግራለች፦ “በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት እኔ ያለሁበትን ሁኔታ የእምነት አጋሮቼ ካሉበት ሁኔታ ጋር ማወዳደር ጀመርኩ። በዚህም የተነሳ ባለኝ ነገር መርካት አቃተኝ።” (ገላ. 6:4) ታዲያ አመለካከቷን እንድታስተካክል የረዳት ምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “በየዕለቱ የማገኛቸውን በረከቶች መቁጠር እንዲሁም የይሖዋ ድርጅት ክፍል በመሆኔ ስላገኘኋቸው በርካታ መልካም ነገሮች ማሰላሰል ጀመርኩ። ከዚያም ይሖዋን አመሰገንኩት። በዚህም የተነሳ እውነተኛ እርካታ አገኘሁ።” አንተም በአፍራሽ ስሜቶች የምትዋጥ ከሆነ እነዚህን እርምጃዎች በመውሰድ የአመስጋኝነት መንፈስ ማዳበር ትችል ይሆን?

በይሖዋ ዓላማ ላይ አተኩር፤ እንዲሁም ትሑት ሁን

8. ባሮክ ምን ዓይነት ወጥመድ ውስጥ ገብቶ ነበር?

8 የነቢዩ ኤርምያስ ጸሐፊ የሆነው ባሮክ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ወጥመድ ውስጥ ገብቶ ነበር። የባሮክ የአገልግሎት ምድብ ከባድ ነበር፤ ኤርምያስ ምስጋና ቢስ ለሆነው ብሔር ኃይለኛ መልእክት በሚያውጅበት ወቅት እሱን መደገፍ ነበረበት። በአንድ ወቅት ባሮክ ትኩረቱ ተከፋፈለ። ይሖዋ በሰጠው ሥራ ላይ ከማተኮር ይልቅ በራሱና እሱ ማድረግ በሚፈልገው ነገር ላይ ከመጠን በላይ ማተኮር ጀመረ። ይሖዋ በኤርምያስ አማካኝነት ባሮክን እንዲህ አለው፦ “አንተ . . . ለራስህ ታላላቅ ነገሮችን ትፈልጋለህ። እንዲህ ያሉ ነገሮችን ፈጽሞ አትፈልግ።” (ኤር. 45:3-5) በሌላ አባባል ይሖዋ “አሁን ባሉህ ነገሮች ረክተህ ኑር” እያለው ነበር። ባሮክ የተሰጠውን እርማት በመቀበሉ የይሖዋን ሞገስ ሳያጣ መኖር ችሏል።

9. በ1 ቆሮንቶስ 4:6, 7 መሠረት ትሕትና ምን አምነን እንድንቀበል ይረዳናል? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

9 አንድ ክርስቲያን አንድን የአገልግሎት መብት ማግኘት እንደሚገባው ይሰማው ይሆናል። ተሰጥኦ እና ተሞክሮ ያለው እንዲሁም ታታሪ ሊሆን ይችላል። ይሁንና እሱ ማግኘት የሚፈልገው መብት ለሌላ ሰው ሊሰጥ ይችላል። በዚህ ጊዜ ምን ብሎ ቢያስብ ይጠቅመዋል? ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 4:6, 7 ላይ በጻፈው ሐሳብ ላይ ሊያሰላስል ይችላል። (ጥቅሱን አንብብ።) የሚሰጠን የትኛውም መብት እንዲሁም ያለን ማንኛውም ችሎታ ከይሖዋ የተገኘ ነው። ይሖዋ እነዚህን ስጦታዎች የሰጠን የሚገባን ሰዎች ስለሆንን አይደለም። ሁሉም የይሖዋ ጸጋ መገለጫዎች ናቸው።—ሮም 12:3, 6፤ ኤፌ. 2:8, 9

ሥዕሎች፦ የተለያየ የአገልግሎት መብት ያላቸው ወንድሞችና እህቶች። 1. አንድ ወንድም በቲኦክራሲያዊ ሕንፃ ላይ ቧንቧ ሲጠግን። 2. አንዲት እህት በምልክት ቋንቋ በሚካሄድ የወረዳ ስብሰባ ላይ ቃለ መጠይቅ ሲደረግላት። 3. አንድ ወንድም በጉባኤ ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያቀርብ።

ያገኘነው ማንኛውም ስጦታ የይሖዋ ጸጋ መገለጫ ነው (አንቀጽ 9⁠ን ተመልከት)b


10. ትሕትና ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

10 ኢየሱስ በተወልን ምሳሌ ላይ በጥልቀት ማሰላሰላችን ትሕትና ለማዳበር ይረዳናል። ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር ባጠበበት ምሽት ምን እንደተከናወነ እንመልከት። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ኢየሱስ፣ [1] አብ ሁሉን ነገር በእጁ እንደሰጠው እንዲሁም [2] ከአምላክ እንደመጣና [3] ወደ አምላክ እንደሚሄድ ያውቅ ስለነበር . . . የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብ . . . ጀመረ።” (ዮሐ. 13:3-5) ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱ የእሱን እግር ሊያጥቡ እንደሚገባ ሊሰማው ይችል ነበር። ይሁንና ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት በሙሉ፣ የአምላክ ልጅ ስለሆነ ሀብታም መሆንና የተመቻቸ ሕይወት መምራት እንደሚገባው ተሰምቶት አያውቅም። (ሉቃስ 9:58) ኢየሱስ ትሑትና ባለው ነገር የሚረካ ሰው ነበር። ለእኛም ፍጹም አርዓያ ሆኖልናል።—ዮሐ. 13:15

11. ዴኒስ ባለው ነገር እንዲረካ ትሕትና የረዳው እንዴት ነው?

11 በኔዘርላንድስ የሚኖረው ዴኒስ የኢየሱስን የትሕትና አርዓያ ለመከተል ጥረት ያደርጋል፤ ሆኖም እንዲህ ማድረግ ቀላል አልሆነለትም። እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ የኩራት ወይም ባለኝ ያለመርካት ዝንባሌ በውስጤ ሲፈጠር ይሰማኛል። ለምሳሌ ሌሎች የአገልግሎት መብት በሚያገኙበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ስሜት ያድርብኛል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመኝ ስለ ትሕትና አጠናለሁ። በ​JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ስለ ትሕትና የሚናገሩ አንዳንድ ጥቅሶችን በአንድ ፈርጅ መድቤ አስቀምጫለሁ፤ ይህም እነዚህን ጥቅሶች በቀላሉ ለማግኘትና ደጋግሜ ለማንበብ ይረዳኛል። በተጨማሪም ስለ ትሕትና የሚናገሩ አንዳንድ ንግግሮችን በስልኬ ላይ አውርጃለሁ፤ እነዚህን ንግግሮች በተደጋጋሚ አዳምጣቸዋለሁ።a ማንኛውንም ሥራ የምናከናውነው ራሳችንን ሳይሆን ይሖዋን ለማስከበር እንደሆነ ተምሬያለሁ። ይሖዋ በሚያከናውነው ሥራ ውስጥ እያንዳንዳችን አነስተኛ ሚና መጫወት እንችላለን።” አንተም ባለህ ነገር መርካት እያቃተህ ከመጣ ትሕትናን ለማዳበር የሚያስችሉ እርምጃዎችን ውሰድ። ይህም ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት ያጠናክርልሃል፤ እንዲሁም ባለህ ነገር እንድትረካ ይረዳሃል።—ያዕ. 4:6, 8

በተስፋህ ላይ አሰላስል

12. ባለን ነገር እንድንረካ የሚረዳን የትኛው ተስፋ ነው? (ኢሳይያስ 65:21-25)

12 ከፊታችን በሚጠብቀን ግሩም ተስፋ ላይ ማሰላሰላችን ባለን ነገር ለመርካት ይረዳናል። በኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ ይሖዋ ራሱ የተናገራቸው ቃላት በአሁኑ ጊዜ ሕይወት ምን ያህል ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ ይሖዋ እንደሚረዳ ያሳያሉ፤ በተጨማሪም ይሖዋ እነዚህን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች እንደሚያስወግድ ዋስትና ይሰጣሉ። (ኢሳይያስ 65:21-25⁠ን አንብብ።) ደህንነቱ በተጠበቀና ምቹ በሆነ ቤት ውስጥ እንኖራለን። ትርጉም ያለው ሥራ ይኖረናል። ጤናማና ጣፋጭ ምግብ እንመገባለን። በእኛም ሆነ በልጆቻችን ላይ አደጋ ይደርሳል ብለን ፈጽሞ አንሰጋም። (ኢሳ. 32:17, 18፤ ሕዝ. 34:25) በእርግጥም ወደፊት አስደሳች ሕይወት ይጠብቀናል። ደግሞም ይህ ተስፋ አስተማማኝ ነው።

13. በተስፋችን ላይ ትኩረት ማድረግ የሚያስፈልገን በተለይ ምን ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ነው?

13 ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አሁን በተስፋችን ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ እንደመሆኑ መጠን ሁላችንም ‘ለመቋቋም የሚያስቸግሩ’ መከራዎች ያጋጥሙናል። (2 ጢሞ. 3:1) ይሖዋ የሚያስፈልገንን አመራር፣ ብርታትና ድጋፍ በመስጠት በየዕለቱ እንድንጸና ይረዳናል። (መዝ. 145:14) ከዚህም ሌላ፣ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን ክርስቲያናዊ ተስፋችን እንድንጸና ሊረዳን ይችላል። ምናልባትም የቤተሰብህን ቁሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ተቸግረህ ይሆናል። ታዲያ ሁሌም ቤተሰብህን ለማስተዳደር እየተቸገርክ ትኖራለህ ማለት ነው? በፍጹም! ይሖዋ በገነት ውስጥ የሚያስፈልግህን ነገር ብቻ ሳይሆን ከዚያ እጅግ አብልጦ እንደሚሰጥህ ቃል ገብቶልሃል። (መዝ. 9:18፤ 72:12-14) ከማይድን በሽታ፣ ከመንፈስ ጭንቀት ወይም አቅም ከሚያሳጣ ሌላ የጤና ችግር ጋር እየታገልክ ይሆናል። ታዲያ ከሥቃይህ መቼም እፎይታ አታገኝም ማለት ነው? በጭራሽ! በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ በሽታና ሞት ይወገዳል። (ራእይ 21:3, 4) ይህ ተስፋ በአሁኑ ወቅት ከመበሳጨት ወይም ከመማረር ይልቅ ባለን ነገር እንድንረካ ይረዳናል። ግፍ፣ ሐዘን፣ ሕመም ወይም ሌላ ፈተና ቢደርስብንም ባለን ነገር መርካት እንችላለን። ለምን? በአሁኑ ጊዜ ያጋጠመን ፈተና ምንም ያህል ከባድ ቢሆን “የሚደርስብን መከራ ጊዜያዊ” እንደሆነ እንዲሁም በአዲሱ ዓለም ውስጥ ዘላቂ እፎይታ እንደምናገኝ እናውቃለን።—2 ቆሮ. 4:17, 18

14. ተስፋችንን ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

14 ባለን ነገር ለመርካት ተስፋ ወሳኝ ከመሆኑ አንጻር ተስፋችንን ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? አንድ ሰው ሩቅ ቦታ ያሉ ነገሮችን አጥርቶ ለማየት መነጽር ማድረግ ሊያስፈልገው እንደሚችል ሁሉ እኛም ወደፊት የሚመጣው ገነት ይበልጥ እውን ሆኖ እንዲታየን ተስፋችንን ለማጠናከር አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ሊያስፈልገን ይችላል። በኢኮኖሚ ችግር የተነሳ በጭንቀት ስንዋጥ ገንዘብ፣ ዕዳና ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በማይኖርበት ዓለም ውስጥ ሕይወታችን ምን እንደሚመስል መሣል እንችላለን። አንዳንድ የአገልግሎት መብቶችን ማግኘት ባለመቻላችን የተነሳ ስንጨነቅ፣ ፍጽምና ላይ ከደረስንና ይሖዋን በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ካገለገልን በኋላ እንዲህ ያሉ ጭንቀቶች ምን ያህል ተራ ነገር እንደሚሆኑ ማሰብ እንችላለን። (1 ጢሞ. 6:19) አሁን ስላለንበት ሁኔታ መጨነቅ ትተን ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማሰላሰል መጀመሪያ ላይ ሊከብደን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ በሰጠን ተስፋ ላይ ማሰላሰል በጊዜ ሂደት እየቀለለን ይሄዳል።

15. ክሪስታ ከሰጠችው ሐሳብ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

15 ተስፋ ቀደም ሲል የተጠቀሰው የዴኒስ ሚስት የሆነችውን ክሪስታን የረዳት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “ባለብኝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ የጡንቻ ሕመም የተነሳ ዊልቼር ለመጠቀምና አብዛኛውን የቀኑን ክፍል አልጋ ላይ ለማሳለፍ እገደዳለሁ። ሕመሙ በየቀኑ ያሠቃየኛል። በቅርቡ ሐኪሜ ሁኔታዬ እምብዛም ተስፋ እንደሌለው ነገረኝ። እኔ ግን ወዲያውኑ ‘እሱ የወደፊቱን ጊዜ የሚያይበት መንገድ የተለየ ነው’ ብዬ አሰብኩ። እኔ የማተኩረው በተስፋዬ ላይ ነው። ይህም የአእምሮ ሰላም ይሰጠኛል። ዛሬ ብዙ ችግሮችን በጽናት መቋቋም ቢያስፈልገኝም በአዲሱ ዓለም ውስጥ አስደሳች ሕይወት ይጠብቀኛል!”

“እሱን የሚፈሩ የሚያጡት ነገር የለም”

16. ንጉሥ ዳዊት ‘ይሖዋን የሚፈሩ የሚያጡት ነገር የለም’ ብሎ ሊጽፍ የቻለው ለምንድን ነው?

16 ባለው ነገር የሚረካ የይሖዋ አገልጋይ ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት ይመራል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት ቢያንስ ሦስት ልጆቹ ሞተውበታል። በሐሰት ተከሷል፤ ተከድቷል፤ እንዲሁም ለበርካታ ዓመታት በስደት ለመኖር ተገዷል። ይሁንና በከባድ መከራ ውስጥ ቢሆንም ስለ ይሖዋ ሲናገር “እሱን የሚፈሩ የሚያጡት ነገር የለም” ብሏል። (መዝ. 34:9, 10) እንዲህ ሊል የቻለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እኛ የይሖዋ አገልጋዮች ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት እንመራለን ብለን ባንጠብቅም የሚያስፈልገንን ነገር እንደማናጣ እርግጠኞች ነን። (መዝ. 145:16) በተጨማሪም በሚያጋጥመን ፈተና ሁሉ ይሖዋ ለመጽናት እንደሚረዳን መተማመን እንችላለን። ባለን ነገር ረክተን መኖር እንችላለን።

17. ባለህ ነገር ረክቶ የመኖርን ሚስጥር ለመማር ቁርጥ ውሳኔ ያደረግከው ለምንድን ነው?

17 ይሖዋ ባለህ ነገር ረክተህ እንድትኖር ይፈልጋል። (መዝ. 131:1, 2) እንግዲያው ባለህ ነገር ረክቶ የመኖርን ሚስጥር ለመማር ጥረት አድርግ። አመስጋኝነትን ለማዳበር፣ በይሖዋ ዓላማ ላይ ለማተኮርና ትሑት ለመሆን እንዲሁም ተስፋህን ለማጠናከር ጥረት ካደረግክ “አዎ፣ . . . ረክቻለሁ” ማለት ትችላለህ።—መዝ. 16:5, 6

የሚከተሉት ነገሮች ባለህ ነገር ለመርካት የሚረዱህ እንዴት ነው?

  • አመስጋኝነትን ማዳበር

  • በይሖዋ ዓላማ ላይ ማተኮርና ትሑት መሆን

  • በተስፋህ ላይ ማሰላሰል

መዝሙር 118 “እምነት ጨምርልን”

a ለምሳሌ ይሖዋ ለትሑት አገልጋዮቹ ያስባል እና ኩራት ጥፋትን ይቀድማል የሚሉትን የማለዳ አምልኮ ፕሮግራሞች jw.org ላይ ተመልከት።

b የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም በቲኦክራሲያዊ ሕንፃ ላይ የጥገና ሥራ ሲያከናውን፣ ምልክት ቋንቋ የተማረች አንዲት እህት የወረዳ ስብሰባ ላይ ቃለ መጠይቅ ሲደረግላት እንዲሁም አንድ ወንድም የሕዝብ ንግግር ሲያቀርብ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ