የጥናት ርዕስ 37
መዝሙር 114 “በትዕግሥት ጠብቁ”
ለፍትሕ መጓደል ልንሰጥ የሚገባው ምላሽ
“ፍትሕን ሲጠብቅ እነሆ፣ ግፍ ይፈጸማል።”—ኢሳ. 5:7
ዓላማ
የኢየሱስ ምሳሌ ለፍትሕ መጓደል ይሖዋን የሚያስደስት ምላሽ እንድንሰጥ የሚረዳን እንዴት ነው?
1-2. ብዙ ሰዎች ለፍትሕ መጓደል ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣሉ? እኛስ ምን ብለን እንጠይቅ ይሆናል?
የምንኖረው ፍትሕ በጠፋበት ዓለም ውስጥ ነው። ሰዎች በኑሮ ደረጃቸው፣ በፆታቸው፣ በዘራቸው፣ በጎሳቸው ወይም በሌሎች በርካታ ምክንያቶች የተነሳ ግፍ ይፈጸምባቸዋል። ስግብግብ ነጋዴዎችና በሙስና የተዘፈቁ ባለሥልጣናት በሚያደርጉት ነገር የተነሳ ለሥነ ምህዳራዊ ችግሮች ይዳረጋሉ። እነዚህና ሌሎች ኢፍትሐዊ ድርጊቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁላችንንም ይነኩናል።
2 ብዙዎች በዓለም ላይ በሚያዩት ግፍ መበሳጨታቸው ምንም አያስገርምም። ሁላችንም ከስጋት ነፃ በሆነ ዓለም ውስጥ መኖርና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መያዝ እንፈልጋለን። አንዳንዶች ማኅበራዊ ለውጥ ለማምጣት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ይካፈላሉ። የፍትሕ መጓደልን እንታገላለን ለሚሉ ሰዎች በፊርማቸው ድጋፍ ይሰጣሉ፤ ሰልፍ ይወጣሉ፤ እንዲሁም ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን እናስወግዳለን ለሚሉ ፖለቲከኞች ድምፅ ይሰጣሉ። እኛ ግን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ‘የዓለም ክፍል መሆን’ እንደሌለብን እንዲሁም ሁሉንም ኢፍትሐዊ ድርጊቶች የሚያስወግደውን የአምላክን መንግሥት መጠበቅ እንዳለብን ተምረናል። (ዮሐ. 17:16) ያም ቢሆን፣ አንድ ሰው ግፍ ሲፈጸምበት ስናይ ልናዝን አልፎ ተርፎም ልንቆጣ እንችላለን። እንዲህ ብለን እናስብ ይሆናል፦ ‘በዚህ ጊዜ ምን ዓይነት ምላሽ ልሰጥ ይገባል? የፍትሕ መጓደልን ለመቀነስ በአሁኑ ወቅት ማድረግ የምችለው ነገር አለ?’ እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለሳችን በፊት ይሖዋና ኢየሱስ ለፍትሕ መጓደል ምን ዓይነት አመለካከት እንዳላቸው እንመልከት።
ይሖዋና ኢየሱስ የፍትሕ መጓደልን ይጠላሉ
3. ግፍ ሲፈጸም የምንበሳጨው ለምንድን ነው? (ኢሳይያስ 5:7)
3 መጽሐፍ ቅዱስ የፍትሕ መጓደል ሲፈጸም የምንበሳጨው ለምን እንደሆነ ይነግረናል። የአምላክ ቃል፣ ይሖዋ የፈጠረን በራሱ መልክ እንደሆነና እሱ ደግሞ ‘ጽድቅንና ፍትሕን እንደሚወድ’ ይገልጻል። (መዝ. 33:5፤ ዘፍ. 1:26) ይሖዋ ፈጽሞ ፍትሕ የጎደለው ነገር አያደርግም፤ ሌሎችም እንዲህ ዓይነት ነገር እንዲያደርጉ አይፈልግም። (ዘዳ. 32:3, 4፤ ሚክ. 6:8፤ ዘካ. 7:9) ለምሳሌ በነቢዩ ኢሳይያስ ዘመን ይሖዋ በወገኖቻቸው ግፍ የተፈጸመባቸው በርካታ እስራኤላውያን የሚያሰሙትን “የጭንቅ ጩኸት” ሰምቶ ነበር። (ኢሳይያስ 5:7ን አንብብ።) ይሖዋ ሕጉን በተደጋጋሚ የጣሱትንና በሌሎች ላይ ግፍ የፈጸሙትን ሰዎች በመቅጣት እርምጃ ወስዷል።—ኢሳ. 5:5, 13
4. በወንጌሎች ውስጥ የሚገኝ አንድ ዘገባ ኢየሱስ ለፍትሕ መጓደል ስላለው አመለካከት ምን ያስተምረናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
4 ኢየሱስም ልክ እንደ ይሖዋ ፍትሕን ይወዳል፤ የፍትሕ መጓደልን ደግሞ ይጠላል። ምድራዊ አገልግሎቱን እያከናወነ ሳለ አንድ ቀን እጁ የሰለለ ሰው አየ። ኢየሱስ ሰውየውን ለመርዳት ተነሳሳ። ርኅራኄ የሌላቸው የሃይማኖት መሪዎች ግን እንደዚያ አልተሰማቸውም። ይህን ምስኪን ሰው ከመርዳት ይበልጥ ያሳሰባቸው ከሰንበት ሕግ ጋር በተያያዘ ያወጡት የማያፈናፍን ድንጋጌ መከበሩ ነበር። ኢየሱስ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች የሰጡትን ምላሽ ሲመለከት ምን ተሰማው? ‘በልባቸው ደንዳናነት በጣም አዘነ።’—ማር. 3:1-6
የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ለተቸገሩ ሰዎች ርኅራኄ አልነበራቸውም፤ ኢየሱስ ግን ሩኅሩኅ ነበር (አንቀጽ 4ን ተመልከት)
5. ፍትሕ ሲጓደል የሚሰማንን ቁጣ በተመለከተ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?
5 ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ የፍትሕ መጓደል የሚያስቆጣቸው ከመሆኑ አንጻር እኛም እንደዚያ ቢሰማን ስህተት አይደለም። (ኤፌ. 4:26) ሆኖም ለመቆጣት ምክንያት እንዳለን ቢሰማንም እንኳ ቁጣችን የፍትሕ መጓደልን ሊያስወግድ እንደማይችል ማስታወስ ይኖርብናል። እንዲያውም ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ወይም ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣ ስሜታዊና አካላዊ ጉዳት ሊያስከትልብን ይችላል። (መዝ. 37:1, 8፤ ያዕ. 1:20) ታዲያ ለፍትሕ መጓደል ምን ዓይነት ምላሽ ልንሰጥ ይገባል? ከኢየሱስ ምሳሌ ትምህርት እናገኛለን።
ኢየሱስ ለፍትሕ መጓደል የሰጠው ምላሽ
6. ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የትኞቹ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ተስፋፍተው ነበር? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
6 ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ በርካታ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ተመልክቷል። ተራው ሕዝብ በሃይማኖት መሪዎች የሚደርስበትን ጭቆና አይቷል። (ማቴ. 23:2-4) የሮም ባለሥልጣናት ሕዝቡን እንዴት በጭካኔ እንደሚይዙም ያውቃል። ብዙዎቹ አይሁዳውያን ከሮም ነፃ ለመውጣት ይመኙ ነበር። ዜለት የሚባለውን ቡድን አባላት ጨምሮ አንዳንዶች ከሮም ጋር እስከመዋጋት ደርሰዋል። ኢየሱስ ግን ማኅበራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረጉ ንቅናቄዎችን አላስጀመረም ወይም አልደገፈም። ሕዝቡ ሊያነግሡት እንደፈለጉ ሲያውቅ ከእነሱ ገለል ብሏል።—ዮሐ. 6:15
ሕዝቡ ኢየሱስን በፖለቲካ ውስጥ ሊያስገቡት ሲሞክሩ ኢየሱስ ትቷቸው ሄዷል (አንቀጽ 6ን ተመልከት)
7-8. ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ የፍትሕ መጓደልን ለማስወገድ ያልሞከረው ለምንድን ነው? (ዮሐንስ 18:36)
7 ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ ብሎ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ እጁን አላስገባም። ለምን? ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብትም ሆነ ችሎታ እንደሌላቸው ያውቅ ነበር። (መዝ. 146:3፤ ኤር. 10:23) በተጨማሪም ሰዎች የፍትሕ መጓደልን ዋነኛ መንስኤዎች ማስወገድ አይችሉም። ዓለምን የሚገዛው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው፤ እሱ ደግሞ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን የሚያስፋፋ ነፍሰ ገዳይ መንፈሳዊ ፍጡር ነው። (ዮሐ. 8:44፤ ኤፌ. 2:2) ከዚህም ሌላ በአለፍጽምና የተነሳ ጥሩ ሰዎችም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ፍትሕ የጎደለው ነገር ማድረጋቸው አይቀርም።—መክ. 7:20
8 ኢየሱስ የፍትሕ መጓደልን ዋነኛ መንስኤዎች የሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ያውቅ ነበር። በመሆኑም ጊዜውንና ጉልበቱን የተጠቀመበት ‘የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክና ለማወጅ’ ነው። (ሉቃስ 8:1) ‘ጽድቅን ለሚራቡና ለሚጠሙ’ ሰዎች ሙስናና ግፍ የሚወገድበት ጊዜ እንደሚመጣ ዋስትና ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 5:6፤ ሉቃስ 18:7, 8) ሆኖም ይህ የሚሆነው በማኅበራዊ ንቅናቄዎች አማካኝነት ሳይሆን በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት አገዛዝ አማካኝነት ነው፤ ይህ መንግሥት ደግሞ “የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም።”—ዮሐንስ 18:36ን አንብብ።
የፍትሕ መጓደል ሲያጋጥማችሁ የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ
9. ሁሉንም ኢፍትሐዊ ድርጊቶች የሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ የሚያሳምንህ ምንድን ነው?
9 ከኢየሱስ ዘመን ይበልጥ በዛሬው ጊዜ ብዙ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን እናያለን። ሆኖም በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናትም’ ቢሆን የፍትሕ መጓደል ዋነኛ መንስኤዎች ሰይጣንና በእሱ ተጽዕኖ ሥር ያሉት ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ናቸው። (2 ጢሞ. 3:1-5, 13፤ ራእይ 12:12) እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም የፍትሕ መጓደልን ዋነኛ መንስኤዎች የሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ እናውቃለን። ይህን መንግሥት ሙሉ በሙሉ ስለምንደግፍ በዓለም ላይ በሚካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎችና ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ለመዋጋት በሚደረጉ ሌሎች እንቅስቃሴዎች አንካፈልም። ስቴሲa የተባለችን አንዲት እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ስቴሲ እውነትን ከመስማቷ በፊት በማኅበራዊ ንቅናቄዎች አዘውትራ ትካፈል ነበር። ሆኖም እያደረገች ያለችውን ነገር በተመለከተ ጥርጣሬ አደረባት። እንዲህ ብላለች፦ “በተቃውሞ ሰልፎች ላይ በምካፈልበት ጊዜ ‘በእርግጥ የተሰለፍኩት በትክክለኛው ወገን ነው?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስበኝ ነበር። አሁን ግን የአምላክን መንግሥት ስለምደግፍ የተሰለፍኩት በትክክለኛው ወገን እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ። ይሖዋ ጭቆና ለደረሰበት ለእያንዳንዱ ሰው ከእኔ እጅግ የተሻለ መፍትሔ እንደሚሰጠው አውቃለሁ።”—መዝ. 72:1, 4
10. ማኅበራዊ ንቅናቄዎች ኢየሱስ በማቴዎስ 5:43-48 ላይ ከሰጠው ምክር ጋር የሚጋጩት እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
10 በዚህ ዓለም ላይ የሚካሄዱት ብዙዎቹ ማኅበራዊ ንቅናቄዎች ዓመፀኝነትና ጥላቻ የሚንጸባረቅባቸው ናቸው፤ እነዚህ ባሕርያት ደግሞ ኢየሱስ ከተወው ምሳሌና ካስተማራቸው ትምህርቶች ጋር ይጋጫሉ። (ኤፌ. 4:31) ጄፍሪ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ሰላማዊ የሚመስሉ ሰልፎች እንኳ በሴኮንዶች ውስጥ ተቀይረው ወደ ዓመፅና ወደ ዝርፊያ ሊያመሩ እንደሚችሉ አውቃለሁ።” ሆኖም ኢየሱስ ከእኛ ጋር የማይስማሙትንና የሚያሳድዱንን ሰዎች ጨምሮ ሁሉንም ሰው በፍቅር እንድንይዝ አስተምሮናል። (ማቴዎስ 5:43-48ን አንብብ።) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን፣ ኢየሱስ ከተወልን አርዓያ ጋር የሚጋጭ ምንም ነገር ላለማድረግ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን።
በፖለቲካዊና በማኅበራዊ ጉዳዮች ረገድ የገለልተኝነት አቋማችንን ለመጠበቅ ቁርጠኝነት ያስፈልገናል (አንቀጽ 10ን ተመልከት)
11. ማኅበራዊ ንቅናቄዎችን ላለመደገፍ ያለንን ቁርጠኝነት እንድናላላ ሊፈትነን የሚችለው ምንድን ነው?
11 የአምላክ መንግሥት የፍትሕ መጓደልን በዘላቂነት እንደሚያስወግድ ብናውቅም ፍትሕ የጎደለው ነገር ሲፈጸምብን የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ሊከብደን ይችላል። ጃናያ መድልዎ በተፈጸመባት ወቅት ምን እንደተሰማት እንመልከት። እንዲህ ስትል በሐቀኝነት ተናግራለች፦ “በጣም ተበሳጨሁ። ስሜቴ የተጎዳ ከመሆኑም ሌላ መድልዎ የፈጸሙብኝ ሰዎች እንዲቀጡ ፈልጌ ነበር። ከዚያም ዘረኝነትንና መድልዎን የሚቃወምን አንድ ንቅናቄ ለመደገፍ ተነሳሳሁ። እንዲህ ማድረግ ብስጭቴን መግለጽ የምችልበት ጥሩ መንገድ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር።” ውሎ አድሮ ግን ጃናያ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልጋት ተገነዘበች። እንዲህ ብላለች፦ “ሌሎች አስተሳሰቤን እንዲያዛቡት እየፈቀድኩ ነበር። በይሖዋ ላይ ሳይሆን በሰው ላይ እንድታመን ተጽዕኖ እያደረጉብኝ ነበር። ከዚያ ንቅናቄ ጋር ያለኝን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ለማቋረጥ ወሰንኩ።” የሚሰማን የጽድቅ ቁጣ በዚህ ዓለም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ረገድ ያለንን የገለልተኝነት አቋም እንድናላላ እንዳያደርገን መጠንቀቅ ይኖርብናል።—ዮሐ. 15:19
12. በምናስገባው መረጃ ረገድ መራጮች መሆናችን ጥበብ የሆነው ለምንድን ነው?
12 በኢፍትሐዊ ድርጊቶች የተነሳ የሚሰማንን ቁጣ ለመቆጣጠር ምን ሊረዳን ይችላል? ብዙዎች በሚያነቡት፣ በሚያዳምጡትና በሚመለከቱት ነገር ረገድ መራጮች መሆናቸው ጠቅሟቸዋል። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚወጡ በርካታ መረጃዎች ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን አጋንነው ያቀርባሉ፤ እንዲሁም ሰዎች ማኅበራዊ ንቅናቄዎችን እንዲቀላቀሉ ያበረታታሉ። ብዙውን ጊዜ የዜና አውታሮች አንድን መረጃ የሚዘግቡት ወገንተኝነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው። ስለደረሰው የፍትሕ መጓደል የሰማነው መረጃ ትክክል ቢሆንም እንኳ በዚህ ሐሳብ ላይ ማውጠንጠናችን በእርግጥ ይጠቅመናል? እንዲህ ያለውን መረጃ በማንበብና በመስማት ብዙ ጊዜ የምናጠፋ ከሆነ ሳያስፈልግ ለብስጭትና ለተስፋ መቁረጥ ልንዳረግ እንችላለን። (ምሳሌ 24:10) ከዚህም የከፋው ደግሞ፣ ለሁሉም ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ዘላቂ መፍትሔ ከሚሰጠው ከአምላክ መንግሥት ትኩረታችን ሊወሰድ ይችላል።
13. አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን የፍትሕ መጓደልን በተመለከተ ተገቢውን አመለካከት ለመያዝ የሚረዳን እንዴት ነው?
13 አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችንና ማሰላሰላችን ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ለመቋቋም ይረዳናል። አሊያ የተባለች እህት በአካባቢዋ ያሉ ሰዎች የሚፈጸምባቸው ግፍ በጣም ይረብሻት ነበር። ግፍ የሚፈጽሙት ሰዎች ደግሞ ለጥፋታቸው እንዳልተቀጡ ተሰማት። እንዲህ ብላለች፦ “ቁጭ ብዬ ‘ይሖዋ እነዚህን ችግሮች እንደሚያስተካክል በእርግጥ አምናለሁ?’ በማለት ራሴን መጠየቅ ነበረብኝ። በዚያ ወቅት ኢዮብ 34:22-29ን አነበብኩ። ይህ ጥቅስ ማንም ሰው ከይሖዋ ሊደበቅ እንደማይችል አስታወሰኝ። ፍጹም የሆነ የፍትሕ መሥፈርት ያለው እሱ ብቻ ነው፤ ነገሮችን ሙሉ በሙሉ ማስተካከል የሚችለውም እሱ ብቻ ነው።” ይሁንና የአምላክ መንግሥት እውነተኛ ፍትሕ እስኪያሰፍን በምንጠባበቅበት ወቅት የፍትሕ መጓደልን በተመለከተ ማድረግ የምንችለው ነገር አለ። ይህ ነገር ምንድን ነው?
በአሁኑ ወቅት ምን ማድረግ እንችላለን?
14. የፍትሕ መጓደልን ለመቀነስ በአሁኑ ወቅት ምን ማድረግ እንችላለን? (ቆላስይስ 3:10, 11)
14 ሌሎች የሚፈጽሙትን ኢፍትሐዊ ድርጊት መቆጣጠር አንችልም፤ የራሳችንን ድርጊት ግን መቆጣጠር እንችላለን። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፣ ፍቅር በማሳየት የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን። እንዲህ ያለው ፍቅር፣ ኢፍትሐዊ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን ጨምሮ ሌሎችን በአክብሮት እንድንይዝ ያነሳሳናል። (ማቴ. 7:12፤ ሮም 12:17) ሁሉንም ሰው በደግነትና በፍትሕ ስንይዝ ይሖዋ ይደሰታል።—ቆላስይስ 3:10, 11ን አንብብ።
15. የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ማካፈላችን የፍትሕ መጓደልን ለመቀነስ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው እንዴት ነው?
15 ለፍትሕ መጓደል ምላሽ መስጠት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሌሎች ማካፈል ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ‘የይሖዋ እውቀት’ ብስጩና ዓመፀኛ የነበረ ሰው ተለውጦ ደግና ሰላም ወዳድ ሰው እንዲሆን ሊረዳው ይችላል። (ኢሳ. 11:6, 7, 9) ጀማል የተባለ ሰው እውነትን ከመስማቱ በፊት፣ ጨቋኝ እንደሆነ የሚያስበውን የፖለቲካ ሥርዓት ለመዋጋት አንድን ዓማፂ ቡድን ተቀላቅሎ ነበር። ጀማል እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎችን በጉልበት መለወጥ አይቻልም። እኔም በጉልበት አልተለወጥኩም፤ የተማርኩት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ግን ለውጦኛል።” ጀማል የተማረው ነገር መዋጋቱን እንዲያቆም አነሳሳው። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ተምረው የሚለወጡ ሰዎች ብዛት በጨመረ ቁጥር ለፍትሕ መጓደል አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሰዎች ብዛት ይቀንሳል።
16. የመንግሥቱን ተስፋ ለሰዎች ለማካፈል የምትጓጓው ለምንድን ነው?
16 እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም የአምላክ መንግሥት የፍትሕ መጓደልን በዘላቂነት እንደሚያስወግድ ለሰዎች ለመንገር እንጓጓለን። ይህ ተስፋ ግፍ የተፈጸመባቸውን ሰዎች ሊያጽናናቸው ይችላል። (ኤር. 29:11) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ስቴሲ እንዲህ ብላለች፦ “እውነትን ማወቄ በእኔም ሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ የሚደርሱትን ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ለመቋቋም ረድቶኛል። ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ተጠቅሞ ሰዎችን ያጽናናል።” አንተም የፍትሕ መጓደል ስለሚወገድበት ጊዜ የሚገልጸውን አጽናኝ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለሰዎች ለማካፈል በደንብ መዘጋጀት ይኖርብሃል። በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች እውነት መሆናቸውን እርግጠኛ ከሆንክ ይህ ርዕሰ ጉዳይ በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ ሲነሳ በዘዴ ጥሩ ማብራሪያ ለመስጠት ዝግጁ ትሆናለህ።b
17. ይሖዋ የፍትሕ መጓደልን እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?
17 ሰይጣን “የዚህ ዓለም ገዢ” ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ የፍትሕ መጓደል እንደሚያጋጥመን እናውቃለን። ሆኖም እሱ ‘የሚባረርበትን’ ጊዜ በምንጠባበቅበት ወቅት አቅመ ቢስም ሆነ ተስፋ ቢስ አይደለንም። (ዮሐ. 12:31) ይሖዋ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች በጣም የበዙት ለምን እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነግሮናል፤ እንዲሁም በሚደርስብን የፍትሕ መጓደል የተነሳ የሚሰማንን ጭንቀት ሲያይ እንደሚያዝን ገልጾልናል። (መዝ. 34:17-19) ይሖዋ ለፍትሕ መጓደል ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት እንዳለብን እንዲሁም መንግሥቱ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያስወግድ በልጁ አማካኝነት አስተምሮናል። (2 ጴጥ. 3:13) ምድር “በፍትሕና በጽድቅ” የምትሞላበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቅን ስለዚያ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች በቅንዓት መስበካችንን እንቀጥል።—ኢሳ. 9:7
መዝሙር 158 ‘አይዘገይ ከቶ!’
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
b ሰዎችን ውደዱ—ደቀ መዛሙርት አድርጉ በተባለው ብሮሹር ላይ ተጨማሪ መረጃ ሀ ነጥብ 24-27ንም ተመልከት።