የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ጥቅምት ገጽ 18-23
  • የጸሎትህን ይዘት ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የጸሎትህን ይዘት ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በነፃነት ወደ ይሖዋ ጸልይ
  • ጸሎትህ ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
  • በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመዘገቡ ልባዊ ጸሎቶች ላይ አሰላስል
  • በጸሎት አማካኝነት ወደ ይሖዋ መቅረብህን ቀጥል
  • ለሌሎች መጸለይህን አትርሳ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • በጸሎት አማካኝነት ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና አጠናክር
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የጸሎትህን ይዘት አሻሽል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • በጸሎት አማካኝነት ወደ አምላክ ቅረብ
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ጥቅምት ገጽ 18-23

የጥናት ርዕስ 42

መዝሙር 44 የተቸገረ ሰው ጸሎት

የጸሎትህን ይዘት ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው?

“በሙሉ ልቤ እጣራለሁ። ይሖዋ ሆይ፣ መልስልኝ።”—መዝ. 119:145

ዓላማ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተመዘገቡ ጸሎቶች ላይ ማሰላሰላችን የጸሎታችንን ይዘት ለማሻሻል ይረዳናል።

1-2. (ሀ) የልባችንን አውጥተን ወደ ይሖዋ እንዳንጸልይ እንቅፋት ሊሆንብን የሚችለው ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ የምናቀርበውን ጸሎት በጥሞና እንደሚያዳምጥ እንዴት እናውቃለን?

አንዳንድ ጊዜ ጸሎትህ ተደጋጋሚ፣ ጥልቀት የሌለው ወይም የዘልማድ እየሆነ እንደመጣ ይሰማሃል? ከሆነ፣ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ሕይወታችን ሩጫ የበዛበት በመሆኑ የተነሳ በችኮላ የመጸለይ አዝማሚያ ይኖረን ይሆናል። ወይም ደግሞ ወደ ይሖዋ በጸሎት ለመቅረብ ብቁ እንዳልሆንን ስለሚሰማን የልባችንን አውጥተን መጸለይ ሊከብደን ይችላል።

2 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ይሖዋ የሚፈልገው ጸሎታችን የተራቀቀ እንዲሆን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ከትሑት ልብ የመነጨ እንዲሆን ይፈልጋል። እሱ “የዋሆች የሚያቀርቡትን ልመና” ይሰማል። (መዝ. 10:17) የእኛ ጉዳይ በጣም ስለሚያሳስበው ስንጸልይ የምንናገረውን እያንዳንዱን ቃል በጥሞና ያዳምጣል።—መዝ. 139:1-3

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን?

3 እንዲህ ብለን እንጠይቅ ይሆናል፦ በነፃነት ወደ ይሖዋ መጸለይ እንችላለን የምንለው ለምንድን ነው? ጸሎታችን ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተመዘገቡ ልባዊ ጸሎቶች ላይ ማሰላሰላችን የጸሎታችንን ይዘት ለማሻሻል የሚረዳን እንዴት ነው? በተጨማሪም በጭንቀት ከመዋጣችን የተነሳ ስሜታችንን በቃላት መግለጽ ሲያቅተን ምን ማድረግ እንችላለን? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እስቲ እንመልከት።

በነፃነት ወደ ይሖዋ ጸልይ

4. በነፃነት ወደ ይሖዋ በጸሎት ለመቅረብ ምን ሊረዳን ይችላል? (መዝሙር 119:145)

4 ይሖዋ መልካሙን የሚመኝልን ታማኝ ወዳጃችን እንደሆነ ስንረዳ በነፃነት ወደ እሱ በጸሎት መቅረብ እንደምንችል እንገነዘባለን። የመዝሙር 119 ጸሐፊ ከይሖዋ ጋር እንዲህ ያለ የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖረው ይፈልግ ነበር። እርግጥ ሕይወቱ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ክፉ ሰዎች ስሙን አጥፍተዋል። (መዝ. 119:23, 69, 78) በተጨማሪም ከራሱ ድክመት ጋር መታገል ነበረበት። (መዝ. 119:5) ያም ቢሆን የልቡን አውጥቶ ወደ ይሖዋ ለመጸለይ አልፈራም።—መዝሙር 119:145ን አንብብ።

5. አፍራሽ ስሜቶች ከመጸለይ ወደኋላ እንድንል እንዲያደርጉን መፍቀድ የማይኖርብን ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

5 ይሖዋ ከባድ ስህተት የሠሩ ሰዎችንም እንኳ ወደ እሱ እንዲጸልዩ ጋብዟቸዋል። (ኢሳ. 55:6, 7) ስለዚህ አፍራሽ ስሜቶች ከመጸለይ ወደኋላ እንድንል እንዲያደርጉን መፍቀድ አይኖርብንም። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አንድ የአውሮፕላን አብራሪ እርዳታ ካስፈለገው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ማነጋገር እንደሚችል ያውቃል። ታዲያ አቅጣጫው ስለጠፋበት ወይም ስህተት ስለሠራ አፍሮ እነሱን ከማነጋገር ወደኋላ ማለት ይኖርበታል? በጭራሽ! እኛም በተመሳሳይ አልፎ አልፎ ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ ቢገባን ወይም ኃጢአት ብንፈጽምም እንኳ በነፃነት ወደ ይሖዋ በጸሎት መቅረብ እንችላለን።—መዝ. 119:25, 176

ጸሎትህ ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

6-7. በይሖዋ ባሕርያት ላይ ማሰላሰላችን ጸሎታችን ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚረዳን እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ። (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

6 ውስጣዊ ስሜታችንንና የተሰወረ ሐሳባችንን አውጥተን ይሖዋን በግልጽ ስናነጋግረው ጸሎታችን ይበልጥ ትርጉም ያለው ይሆናል። ታዲያ የጸሎታችንን ጥልቀት ለማሻሻል ምን ማድረግ እንችላለን?

7 በይሖዋ ባሕርያት ላይ አሰላስል።a በእሱ ባሕርያት ላይ ባሰላሰልን መጠን ሐሳባችንን ለእሱ በነፃነት መግለጽ ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል። (መዝ. 145:8, 9, 18) የክርስቲንን ምሳሌ እንመልከት፤ አባቷ ቁጡ ሰው ነው። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋን እንደ አባት ቆጥሮ ማነጋገር ለእኔ ቀላል አልነበረም። ባለብኝ ድክመት የተነሳ እንደማይወደኝ ይሰማኝ ነበር።” ታዲያ የረዳት የትኛው የይሖዋ ባሕርይ ነው? እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋ ታማኝ ፍቅር የመተማመን ስሜት እንዲሰማኝ ያደርጋል። መቼም ቢሆን ከጎኔ እንደማይለይ እርግጠኛ ነኝ። ብወድቅም እንኳ ስለሚወደኝ ያነሳኛል። ይህን ማወቄ የሚያስደስቱኝንም ሆነ የሚያሳዝኑኝን ነገሮች እንድነግረው ያነሳሳኛል።”

8-9. ከመጸለያችን በፊት ምን እንደምንል ማሰባችን የትኞቹን ጥቅሞች ያስገኝልናል? ምሳሌ ስጥ።

8 ምን እንደምትል አስብ። ከመጸለይህ በፊት አንዳንድ ጥያቄዎችን ራስህን መጠየቅ ትችላለህ። ለምሳሌ፦ ‘በአሁኑ ወቅት ከየትኞቹ ችግሮች ጋር እየታገልኩ ነው? ይቅር ማለት የሚያስፈልገኝ ሰው አለ? የይሖዋን እርዳታ እንድጠይቅ የሚያነሳሳ አዲስ ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሞኛል?’ (2 ነገ. 19:15-19) በተጨማሪም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ይሖዋን ከስሙ፣ ከመንግሥቱና ከፈቃዱ ጋር በተያያዘ ምን ልንጠይቀው እንደምንችል ማሰብ እንችላለን።—ማቴ. 6:9, 10

9 አሊስካ የተባለች እህት ባለቤቷ የማይድን የአንጎል ካንሰር እንዳለበት ባወቀችበት ወቅት መጸለይ ከብዷት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “በጭንቀት ከመዋጤ የተነሳ ምን ብዬ እንደምጸልይ ግራ ገብቶኝ ነበር።” ታዲያ የረዳት ምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “ከመጸለዬ በፊት ጥቂት ጊዜ ወስጄ ሐሳቤን አደራጃለሁ። ይህም የማቀርበው ጸሎት በራሴ ላይ ብቻ ያተኮረ እንዳይሆን ለማድረግ ረድቶኛል። እንዲህ ማድረጌ በምጸልይበት ወቅት እንድረጋጋና ትኩረቴን እንድሰበስብ አግዞኛል።”

10. ረዘም ያለ ጸሎት ለማቅረብ ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

10 ረዘም ያለ ጸሎት አቅርብ። አጭር ጸሎቶችም እንኳ ትርጉም ያላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ የታወቀ ነው። ሆኖም ረዘም ያለ ጸሎት ስናቀርብ ውስጣዊ ሐሳባችንን መግለጽ ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል።b የአሊስካ ባል የሆነው ኢላይጃ እንዲህ ብሏል፦ “በቀን ውስጥ ብዙ ጊዜ ለመጸለይ እሞክራለሁ። ጊዜ ወስጄ ረዘም ያለ ጸሎት ማቅረቤ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ረድቶኛል። ይሖዋ ቶሎ ብዬ ጸሎቴን እንድጨርስ አያስቸኩለኝም፤ ስለዚህ ረዘም ላለ ሰዓት መጸለይ እችላለሁ።” እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ትኩረትህ ሳይከፋፈል፣ ምናልባትም ድምፅህን አውጥተህ መጸለይ የምትችልበት ጊዜና ቦታ ፈልግ፤ ከዚያም ረዘም ያለ ጸሎት የማቅረብ ልማድ አዳብር።

ሥዕሎች፦ 1. አንድ ወንድም ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት ዴስኩ ጋ ተቀምጦ የተገለጠ መጽሐፍ ቅዱስና ቡና ይዞ ሲያሰላስል። 2. ፀሐይ ከወጣች በኋላ እዚያው ዴስኩ ጋ ተቀምጦ ረዘም ላለ ሰዓት ሲጸልይ።

ረዘም ያለ ጸሎት ማቅረብ የምትችልበት ጊዜና ቦታ ምረጥ (አንቀጽ 10ን ተመልከት)


በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመዘገቡ ልባዊ ጸሎቶች ላይ አሰላስል

11. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተመዘገቡ ልባዊ ጸሎቶች ላይ ማሰላሰላችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? (“ስሜታቸውን ትጋራለህ?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

11 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተመዘገቡ ልባዊ ጸሎቶችና የውዳሴ መዝሙሮች ላይ ማሰላሰልህ ሊጠቅምህ ይችላል። የአምላክ አገልጋዮች ውስጣዊ ሐሳባቸውን የገለጹት እንዴት እንደሆነ ስትመረምር አንተም ልብህን በይሖዋ ፊት ለማፍሰስ ትነሳሳለህ። በጸሎትህ ላይ ልታካትት የምትችላቸውን ይሖዋን ለማወደስ የሚያስችሉ አዳዲስ አገላለጾችም ልታገኝ ትችላለህ። በተጨማሪም ከአንተ ሁኔታ ጋር የሚሄዱ ጸሎቶችን ማግኘትህ አይቀርም።

ስሜታቸውን ትጋራለህ?

የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ልባቸውን በይሖዋ ፊት አፍስሰዋል። አንተስ ስሜታቸውን ትጋራለህ?

  • ያዕቆብ በጣም በተጨነቀበት ወቅት ባቀረበው ጸሎት ላይ አመስጋኝነቱንና እምነቱን ገልጿል።—ዘፍ. 32:9-12

  • ወጣቱ ንጉሥ ሰለሞን አምላክ የሰጠው ኃላፊነት ከአቅሙ በላይ እንደሆነ በተሰማው ወቅት ይሖዋ እንዲረዳው ለምኗል።—1 ነገ. 3:7-9

  • ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ ይሖዋ በውስጡ “ንጹሕ ልብ” እንዲፈጥርለት ተማጽኗል።—መዝ. 51:9-12

  • ማርያም አዲስ የአገልግሎት መብት ባገኘችበት ወቅት ይሖዋን አወድሳለች።—ሉቃስ 1:46-49

የጥናት ፕሮጀክት፦ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪክ ያቀረበውን ጸሎት በጥልቀት መርምር። ከዚያም ይሖዋ የአገልጋዩን ልመና የመለሰለት እንዴት እንደሆነ ልብ በል። ለአንተ ሁኔታ የሚስማማ ሆኖ ያገኘኸውን ትምህርት በሥራ ላይ አውል።

12. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኝ አንድ ጸሎት ላይ በምናሰላስልበት ወቅት የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን?

12 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተመዘገበ አንድ ጸሎት ላይ በምታሰላስልበት ወቅት እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘እነዚህን ቃላት የተናገረው ማን ነው? ይህን ያለውስ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው? እኔስ በጸሎቱ ውስጥ የተጠቀሰው ዓይነት ስሜት ተሰምቶኝ ያውቃል? ከዚህ ጸሎት ምን ትምህርት ማግኘት እችላለሁ?’ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ተጨማሪ ምርምር ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል፤ ሆኖም ጥረት ማድረግህ አያስቆጭም። አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

13. ጸሎትን በተመለከተ ከሐና ምን ትምህርት እናገኛለን? (1 ሳሙኤል 1:10, 11) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

13 አንደኛ ሳሙኤል 1:10, 11ን አንብብ። ሐና ይህን ጸሎት ባቀረበችበት ወቅት ሁለት ትላልቅ ችግሮች አጋጥመዋት ነበር። መሃን ነበረች፤ ጣውንቷ ደግሞ ሕይወቷን መራራ አድርጋባት ነበር። (1 ሳሙ. 1:4-7) አንተስ በቀላሉ የማይፈታ ችግር አጋጥሞህ ከሆነ ሐና ካቀረበችው ጸሎት ምን ትማራለህ? ሐና ረዘም ያለ ጸሎት በማቅረቧና የልቧን ሸክም በአምላክ ላይ በመጣሏ እፎይታ አግኝታለች። (1 ሳሙ. 1:12, 18) እኛም ያጋጠመንን ችግርና ችግሩ ያሳደረብንን ስሜት ለይሖዋ በመግለጽ ‘ሸክማችንን በእሱ ላይ ስንጥል’ እፎይታ እናገኛለን።—መዝ. 55:22

ሥዕሎች፦ 1. ሕልቃና ከሁለት ልጆቹ ጋር ሲጫወት ሐና በሐዘን ተውጣ ፊቷን ታዞራለች። 2. ፍናና ሕፃን ልጇን ታቅፋ ፈገግ ስትል። 3. ሐና እያለቀሰች አጥብቃ ስትጸልይ። 4. ሊቀ ካህናቱ ኤሊ እጁን አጣምሮ ተቀምጦ ሐናን ትኩር ብሎ ያያታል።

ሐና መሃን በመሆኗ እንዲሁም ጣውንቷ በምትሰነዝርባት የማያባራ ፌዝ በተጨነቀችበት ወቅት የልቧን ሸክም በይሖዋ ላይ ጥላለች (አንቀጽ 13ን ተመልከት)


14. (ሀ) ከሐና ምሳሌ ሌላስ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ማሰላሰላችን የጸሎታችንን ይዘት ለማሻሻል የሚረዳን እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

14 ሐና ልጇ ሳሙኤል ከተወለደ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ወደ ሊቀ ካህናቱ ኤሊ አመጣችው። (1 ሳሙ. 1:24-28) ከዚያ በኋላ ባቀረበችው ልባዊ ጸሎት ላይ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚጠብቃቸውና እንደሚንከባከባቸው ያላትን እምነት ገልጻለች።c (1 ሳሙ. 2:1, 8, 9) በሕይወቷ ውስጥ የሚያጋጥማት ችግር ሙሉ በሙሉ አልተቀረፈም፤ ሆኖም ሐና ከይሖዋ ባገኘችው በረከት ላይ አተኩራለች። እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? እስካሁን ድረስ ከይሖዋ ባገኘነው ድጋፍ ላይ ካተኮርን በአሁኑ ወቅት የሚያጋጥሙንን ችግሮች በተሻለ ሁኔታ መቋቋም እንችላለን።

15. የፍትሕ መጓደል ሲያጋጥመን ነቢዩ ኤርምያስ ካቀረበው ልመና ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? (ኤርምያስ 12:1)

15 ኤርምያስ 12:1ን አንብብ። በአንድ ወቅት ነቢዩ ኤርምያስ ክፉዎች ሲሳካላቸው በማየቱ ተረብሾ ነበር። እስራኤላውያን ወገኖቹ የሰነዘሩበት ፌዝም ቅስሙን ሰብሮታል። (ኤር. 20:7, 8) እኛም ክፉ ሰዎች ሲሳካላቸው ስናይ ወይም ፌዝ ሲሰነዘርብን የእሱ ዓይነት ስሜት ሊሰማን ይችላል። ኤርምያስ የተሰማውን ቅሬታ ቢገልጽም በአምላክ ፍትሕ ላይ ጥያቄ አላነሳም። ኤርምያስ፣ ይሖዋ ለዓመፀኛ ሕዝቦቹ የሰጣቸውን ተግሣጽ ሲመለከት በአምላክ ፍትሕ ላይ ያለው እምነት ተጠናክሮ መሆን አለበት። (ኤር. 32:19) እኛም በአሁኑ ወቅት የሚያጋጥመንን ማንኛውንም የፍትሕ መጓደል ይሖዋ በተገቢው ጊዜ እንደሚያስተካክልልን በመተማመን የሚሰማንን ቅሬታ በጸሎታችን ላይ በነፃነት መግለጽ እንችላለን።

16. ያለንበት ሁኔታ አምልኳችንን እንደገደበብን የሚሰማን ከሆነ በግዞት ከተወሰደው ሌዋዊ ምን ትምህርት እናገኛለን? (መዝሙር 42:1-4) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

16 መዝሙር 42:1-4ን አንብብ። ይህን መዝሙር የጻፈው ከእምነት አጋሮቹ ጋር አምልኮ ማቅረብ ያልቻለ በግዞት የተወሰደ ሌዋዊ ነው። የዘመረው መዝሙር የተሰማውን ስሜት ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። እኛም በተለያዩ ምክንያቶች ከቤታችን መውጣት የማንችል ከሆነ ወይም በእምነታችን ምክንያት ከታሰርን የእሱ ዓይነት ስሜት ይሰማን ይሆናል። ስሜታችን ሊቀያየር ይችላል፤ ሆኖም የተሰማንን ማንኛውንም ስሜት በጸሎት መግለጻችን ጠቃሚ ነው። እንዲህ ማድረጋችን ሐሳባችንን ለመገምገምና ያለንበትን ሁኔታ በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ ይረዳናል። ለምሳሌ ሌዋዊው ወደፊት ይሖዋን ማወደስ የሚችልባቸው አዳዲስ አጋጣሚዎች እንደሚያገኝ ተገንዝቧል። (መዝ. 42:5) በተጨማሪም ይሖዋ እያደረገለት ባለው እንክብካቤ ላይ አሰላስሏል። (መዝ. 42:8) አጥብቀን ወደ አምላክ መጸለያችን ስሜታችንን ለመገምገም፣ ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ እንዲሁም ለመጽናት የሚያስችል ብርታት ለማግኘት ይረዳናል።

ሥዕሎች፦ 1. አንድ ሌዋዊ ምድረ በዳ ውስጥ ሆኖ አጥብቆ ሲጸልይ። 2. አንድ ወንድም የሆስፒታል አልጋ ላይ ተቀምጦ ይጸልያል፤ እግሩ ላይ የተገለጠ መጽሐፍ ቅዱስ አለ።

መዝሙር 42ን የጻፈው ሌዋዊ በአምላክ ፊት ልቡን አፍስሷል። እኛም ስሜታችንን በጸሎት መግለጻችን ያለንበትን ሁኔታ በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ ሊረዳን ይችላል (አንቀጽ 16ን ተመልከት)


17. (ሀ) ከነቢዩ ዮናስ ጸሎት ምን እንማራለን? (ዮናስ 2:1, 2) (ለ) በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ሐሳቦችን ማስታወሳችን አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን የሚረዳን እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

17 ዮናስ 2:1, 2ን አንብብ። ነቢዩ ዮናስ ይህን ጸሎት ያቀረበው በአንድ ትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ሆኖ ነው። ዮናስ ይሖዋን ያልታዘዘ ቢሆንም አምላክ ድምፁን እንደሚሰማ እርግጠኛ ነበር። ዮናስ በጸሎቱ ላይ በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ በርካታ አገላለጾችን ተጠቅሟል።d እነዚህን ጥቅሶች በደንብ እንደሚያውቃቸው ምንም ጥያቄ የለውም። በእነሱ ላይ ማሰላሰሉ ይሖዋ እንደሚረዳው እንዲተማመን ረድቶታል። እኛም በተመሳሳይ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃላችን ለመያዝ ጥረት ካደረግን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወደ ይሖዋ ስንጸልይ እነዚህ ጥቅሶች ወደ አእምሯችን ሊመጡና ሊያጽናኑን ይችላሉ።

በጸሎት አማካኝነት ወደ ይሖዋ መቅረብህን ቀጥል

18-19. አንዳንድ ጊዜ በምንጸልይበት ወቅት ስሜታችንን በቃላት መግለጽ ከከበደን ሮም 8:26, 27 ምን ዋስትና ይሰጠናል? ምሳሌ ስጥ።

18 ሮም 8:26, 27ን አንብብ። አንዳንድ ጊዜ በጭንቀት ከመዋጣችን የተነሳ ስሜታችንን በቃላት መግለጽ ሊያቅተን ይችላል። ሆኖም በዚህ ጊዜ የሚረዳን ነገር አለ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ስለ እኛ “ይማልዳል።” እንዴት? ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት በቃሉ ውስጥ በርካታ ጸሎቶች እንዲመዘገቡ አድርጓል። ሐሳባችንን በቃላት መግለጽ ሲከብደን ይሖዋ በእነዚህ ጸሎቶች ውስጥ ያሉ አንዳንድ አገላለጾችን እኛ እንዳቀረብነው ልመና አድርጎ በመቁጠር ሊመልስልን ይችላል።

19 በሩሲያ የምትኖር ዬልዬና የተባለች እህት ይህን ማሰቧ ረድቷታል። ዬልዬና በመጸለይዋና መጽሐፍ ቅዱስን በማንበቧ የተነሳ ታስራ ነበር። ዬልዬና በጭንቀት ከመዋጧ የተነሳ መጸለይ ከብዷት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ነገር አስታወስኩ፤ ነገሮች ከአቅሜ በላይ ሲሆኑብኝና ምን ብዬ እንደምጸልይ ግራ ሲገባኝ . . . በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን የአምላክ አገልጋዮች ጸሎቶች ይሖዋ እንደ እኔ ጸሎቶች አድርጎ ይቀበላቸዋል። . . . በጣም ከባድ ሁኔታ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት ይህ ሐሳብ አጽናንቶኛል።”

20. ውጥረት ውስጥ ስንሆን ለጸሎት አእምሯችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?

20 ውጥረት ውስጥ ስንሆን፣ በምንጸልይበት ወቅት ትኩረታችንን መሰብሰብ ሊከብደን ይችላል። አእምሯችንን ለማዘጋጀት የመዝሙር መጽሐፍን የድምፅ ቅጂ ማዳመጥ እንችላለን። በተጨማሪም ንጉሥ ዳዊት እንዳደረገው ስሜታችንን በጽሑፍ ለማስፈር ልንሞክር እንችላለን። (መዝ. 18፤ 34፤ 142ን እና አናት ላይ ያሉትን መግለጫዎች ተመልከት።) እርግጥ ነው፣ ለጸሎት ራሳችንን ማዘጋጀት የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ ድርቅ ያለ ሕግ ማውጣት አያስፈልግም። (መዝ. 141:2) ለአንተ ተስማሚ የሆነውን ነገር አድርግ።

21. በሙሉ ልባችን መጸለይ የምንችለው ለምንድን ነው?

21 ገና ምንም ነገር ሳንናገር ይሖዋ ስሜታችንን እንደሚረዳልን ማወቅ በጣም የሚያጽናና ነው። (መዝ. 139:4) ያም ቢሆን ይሖዋ ምን እንደሚሰማንና ምን ያህል እንደምንተማመንበት ስንገልጽለት ይደሰታል። እንግዲያው ወደ ሰማዩ አባትህ ከመጸለይ ወደኋላ አትበል። በቃሉ ውስጥ ከተመዘገቡት ጸሎቶች ተማር። በሙሉ ልብህ ጸልይ። የሚያስደስትም ሆነ የሚያሳዝን ነገር ሲያጋጥምህ ንገረው። ይሖዋ እውነተኛ ወዳጅህ ስለሆነ ምንጊዜም ከጎንህ ይሆናል!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • የልብህን አውጥተህ ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ምን ሊረዳህ ይችላል?

  • ጸሎትህ ትርጉም ያለው እንዲሆን የትኞቹን ተግባራዊ እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ?

  • በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተመዘገቡ ልባዊ ጸሎቶች ላይ ማሰላሰልህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

መዝሙር 45 በልቤ የማሰላስለው ነገር

a ጥቅሶች ለክርስቲያናዊ ሕይወት በተባለው መጽሐፍ ላይ “ይሖዋ” በሚለው ርዕስ ሥር የሚገኘውን “ከይሖዋ አስደናቂ ባሕርያት አንዳንዶቹ” የሚለውን ክፍል ተመልከት።

b በጥቅሉ ሲታይ፣ ጉባኤውን ወክለው የሚቀርቡ ጸሎቶች አጭር መሆን አለባቸው።

c ሐና በጸሎቷ ላይ ሙሴ ከጻፋቸው ሐሳቦች ጋር የሚመሳሰሉ አንዳንድ አገላለጾችን ተጠቅማለች። ጊዜ ወስዳ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ታሰላስል እንደነበር በግልጽ ማየት ይቻላል። (ዘዳ. 4:35፤ 8:18፤ 32:4, 39፤ 1 ሳሙ. 2:2, 6, 7) በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ደግሞ የኢየሱስ እናት ማርያም ከሐና ጸሎት ጋር በጣም የሚመሳሰሉ የውዳሴ ቃላትን ተጠቅማለች።—ሉቃስ 1:46-55

d አንዳንድ ምሳሌዎችን ለማየት ዮናስ 2:3-9ን ከመዝሙር 69:1፤ 16:10፤ 30:3፤ 142:2, 3፤ 143:4, 5፤ 18:6 እና 3:8 ጋር አወዳድር። እዚህ ላይ በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ጥቅሶች የተቀመጡት ዮናስ የተጠቀመባቸው አገላለጾች ባሉበት ቅደም ተከተል ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ