የጥናት ርዕስ 43
መዝሙር 41 እባክህ ጸሎቴን ስማ
ለሌሎች መጸለይህን አትርሳ
“አንዳችሁ ለሌላው ጸልዩ። ጻድቅ ሰው የሚያቀርበው ምልጃ ታላቅ ኃይል አለው።”—ያዕ. 5:16
ዓላማ
ለሌሎች መጸለይ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነና ይህን ለማድረግ የሚረዱንን አንዳንድ ሐሳቦች እንመለከታለን።
1. ይሖዋ ለጸሎታችን ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ እንዴት እናውቃለን?
ጸሎት ልዩ መብት ነው። እስቲ አስበው፦ ይሖዋ አንዳንድ ሥራዎችን ለመላእክት ሰጥቷል። (መዝ. 91:11) ለልጁም ከባድ ኃላፊነቶችን ሰጥቶታል። (ማቴ. 28:18) ይሁንና ጸሎታችንን እንዲሰማ የመደበው አካል አለ? በፍጹም! ይህን የሚያደርገው ይሖዋ ብቻ ነው። “ጸሎት ሰሚ” የሆነው ይሖዋ ራሱ ጸሎታችንን ይሰማናል።—መዝ. 65:2
2. ለሌሎች በመጸለይ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ምሳሌ ትቷል?
2 የሚያሳስቡንን ነገሮች አስመልክቶ ወደ ይሖዋ በነፃነት መጸለይ ብንችልም ስለ ሌሎች መጸለያችንም አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አድርጓል። ለምሳሌ ለኤፌሶን ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ስለ እናንተ መጸለዬን እቀጥላለሁ” ብሏል። (ኤፌ. 1:16) ጳውሎስ ለግለሰቦችም ይጸልይ ነበር። ለምሳሌ ጢሞቴዎስን “[አምላክን] አመሰግናለሁ፤ ደግሞም ሌት ተቀን አንተን ዘወትር በምልጃዬ አስታውሳለሁ” ብሎታል። (2 ጢሞ. 1:3) ጳውሎስ የሚጸልይባቸው የራሱ ችግሮች ነበሩት። (2 ቆሮ. 11:23፤ 12:7, 8) ቢሆንም ለሌሎች ለመጸለይ ጊዜ መድቧል።
3. ለሌሎች መጸለይ ልንረሳ የምንችለው ለምንድን ነው?
3 ለሌሎች መጸለይ የምንረሳበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ለምን? ሰብሪናa የተባለች እህት አንዱን ምክንያት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሕይወት በሩጫ የተሞላ ነው። በሚያጋጥሙን ችግሮች ትኩረታችን ከመወሰዱ የተነሳ ስለ ራሳችን ጉዳይ ብቻ ልንጸልይ እንችላለን።” አንተስ እንዲህ ያለ ሁኔታ ገጥሞህ ያውቃል? ከሆነ ይህ የጥናት ርዕስ ሊረዳህ ይችላል። (1) ለሌሎች መጸለይ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንዲሁም (2) እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።
ለሌሎች መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?
4-5. ለሌሎች የምናቀርበው ጸሎት ‘ታላቅ ኃይል ያለው’ እንዴት ነው? (ያዕቆብ 5:16)
4 ለሌሎች የምናቀርበው ጸሎት “ታላቅ ኃይል አለው።” (ያዕቆብ 5:16ን አንብብ።) ለሌሎች መጸለያችን በእርግጥ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? አዎ፣ ይችላል። ኢየሱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚክደው እያወቀም እንዲህ ብሎታል፦ “እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ምልጃ አቀረብኩ።” (ሉቃስ 22:32) ጳውሎስም ጸሎት ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ያውቅ ነበር። ሮም ውስጥ በግፍ በታሰረበት ወቅት ለፊልሞና እንዲህ ሲል ጽፎለታል፦ “ጸሎታችሁ ተሰምቶ ወደ እናንተ እንደምመለስ ተስፋ [አደርጋለሁ]።” (ፊልሞና 22) ደግሞም ጳውሎስ ብዙም ሳይቆይ ነፃ ወጥቶ መስበኩን መቀጠል ችሏል።
5 እርግጥ ይህ ሲባል፣ በመጸለይ ይሖዋ አንድ ነገር እንዲያደርግ ጫና እናሳድርበታለን ማለት አይደለም። ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያሳስባቸውን ነገር ያስተውላል፤ እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ የጠየቁትን ነገር ለመፈጸም ሊመርጥ ይችላል። ይህን ማወቃችን አንድን ጉዳይ አስመልክቶ ወደ ይሖዋ አጥብቀን እንድንጸልይ፣ ከዚያም በእሱ ተማምነን ጉዳዩን ለእሱ እንድንተወው ይረዳናል።—መዝ. 37:5፤ 2 ቆሮ. 1:11
6. ለሌሎች መጸለያችን ስለ እነሱ ባለን ስሜት ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? (1 ጴጥሮስ 3:8)
6 ለሌሎች መጸለያችን ‘ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን’ ለማዳበር ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 3:8ን አንብብ።) ርኅራኄ አንድ ሰው ያለበትን መከራ መረዳትንና ችግሩን ለማቅለል መፈለግን ያመለክታል። (ማር. 1:40, 41) ማይክል የተባለ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞቼ ስለሚያስፈልጋቸው ነገር መጸለዬ የሚጋፈጡትን ችግር የበለጠ እንድረዳ ያስችለኛል፤ ይህ ደግሞ ለእነሱ ያለኝ ፍቅር እንዲጨምር ያደርጋል። እነሱ ባያውቁትም ይበልጥ እንደቀረብኳቸው ይሰማኛል።” ሪቻርድ የተባለ ሽማግሌ ደግሞ ለሌሎች መጸለይ ያለውን ሌላ ጥቅም ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ለአንድ ሰው ስንጸልይ በሆነ መንገድ ግለሰቡን ለመርዳት እንነሳሳለን። ለጸለይንለት ሰው ተግባራዊ እርዳታ ስናደርግ ስለ እሱ ያቀረብነው ጸሎት መልስ እንዲያገኝ አስተዋጽኦ እያበረከትን ነው ሊባል ይችላል።”
7. ለሌሎች መጸለያችን ስለ ራሳችን ችግር ሚዛናዊ አመለካከት እንድንይዝ የሚረዳን እንዴት ነው? (ፊልጵስዩስ 2:3, 4) (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
7 ለሌሎች መጸለያችን ለራሳችን ችግሮች ሚዛናዊ አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል። (ፊልጵስዩስ 2:3, 4ን አንብብ።) ሁላችንም በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም ውስጥ መኖር ከሚያስከትላቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ጋር እንታገላለን። (1 ዮሐ. 5:19፤ ራእይ 12:12) አዘውትረን ስለ ሌሎች መጸለያችን “በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያሉት [ወንድሞቻችን] ተመሳሳይ መከራ እየደረሰባቸው እንዳለ” እንድናስታውስ ያደርገናል። (1 ጴጥ. 5:9) ካትሪን የተባለች አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “ለሌሎች መጸለዬ ሌሎች ሰዎችም ተፈታታኝ ችግሮች እያጋጠሟቸው እንዳለ እንዳስታውስ ያደርገኛል። ይህን ማስታወሴ በችግሮቼ ላይ ከልክ በላይ እንዳላተኩር ይረዳኛል።”
ለሌሎች መጸለያችን ለራሳችን ችግሮች ሚዛናዊ አመለካከት እንድናዳብር ይረዳናል (አንቀጽ 7ን ተመልከት)d
ጸሎታችን ያስፈልጋቸዋል
8. በጸሎታችን ላይ ማንን ልናካትት እንችላለን?
8 በጸሎታችን ላይ ማንን ልናካትት እንችላለን? በቡድን ደረጃ ለተለያዩ ሰዎች መጸለይ እንችላለን። ለምሳሌ የጤና ችግር ላለባቸው ወንድሞች፣ በትምህርት ቤት ፌዝና የእኩዮች ተጽዕኖ ለሚደርስባቸው ወጣቶች ወይም በዕድሜ መግፋት ምክንያት የሚመጡ ችግሮችን ለሚጋፈጡ አረጋውያን መጸለይ እንችላለን። ብዙ የእምነት አጋሮቻችን ከቤተሰባቸው አባላት ወይም ከመንግሥት ተቃውሞ ያጋጥማቸዋል። (ማቴ. 10:18, 36፤ ሥራ 12:5) አንዳንድ ወንድሞቻችን በፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል። ሌሎች ደግሞ የተፈጥሮ አደጋ ደርሶባቸዋል። እነዚህን ወንድሞችና እህቶች በግለሰብ ደረጃ አናውቃቸው ይሆናል። ይሁንና ለእነሱ ስንጸልይ ኢየሱስ ‘እርስ በርሳችን እንድንዋደድ’ የሰጠንን መመሪያ እንደምንከተል እናሳያለን።—ዮሐ. 13:34
9. በይሖዋ ድርጅት ውስጥ አመራር ለሚሰጡ ወንድሞች እንዲሁም ለሚስቶቻቸው መጸለይ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
9 በይሖዋ ድርጅት ውስጥ አመራር ለሚሰጡ ወንድሞችም መጸለይ እንችላለን። ይህም የበላይ አካሉንና ረዳቶቻቸውን፣ የቅርንጫፍ ኮሚቴዎችን፣ በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ያሉ የሥራ የበላይ ተመልካቾችን፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን ያካትታል። እነዚህ ወንድሞች እኛን በትጋት የሚያገለግሉን ከግል ችግሮቻቸው ጋር እየታገሉ ነው። (2 ቆሮ. 12:15) ለምሳሌ ማርክ የተባለ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንዲህ ብሏል፦ “በጣም ከሚያሳስቡኝ ችግሮች አንዱ በዕድሜ ከገፉ ወላጆቼ መራቄ ነው። ሁለቱም ያሉበት የጤንነት ሁኔታ ጥሩ የሚባል አይደለም። እህቴና ባለቤቷ እየተንከባከቧቸው ቢሆንም እኔ በግለሰብ ደረጃ ለእነሱ ብዙ ነገር ማድረግ አለመቻሌ በጣም ያሳዝነኛል።” እነዚህ ታታሪ ወንድሞች እየተጋፈጡ ያሉትን ችግር አወቅንም አላወቅን ለእነሱ መጸለያችን ተገቢ ነው። (1 ተሰ. 5:12, 13) ለእነዚህ ወንድሞች ሚስቶች መጸለይም እንችላለን፤ ምክንያቱም እነዚህ ወንድሞች ያሉባቸውን ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚስቶቻቸው ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።
10-11. ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን በቡድን ደረጃ የምናቀርበው ጸሎት ይሖዋን ያስደስተዋል? አብራራ።
10 ከላይ እንደተመለከትነው፣ ብዙ ጊዜ ለወንድሞችና ለእህቶች በቡድን ደረጃ እንጸልያለን። ለምሳሌ አንድን ግለሰብ በአእምሯችን ሳንይዝ ይሖዋ በእስር ላይ ያሉትን እንዲረዳ ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡትን እንዲያጽናና ልንጠይቀው እንችላለን። ዶናልድ የተባለ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “በመከራ ውስጥ ያሉ ብዙ ወንድሞችና እህቶች አሉ። ስለዚህ ሁሉንም ለማካተት ስንል አንዳንድ ጊዜ በጅምላ ጸሎት እናቀርባለን።”
11 እንዲህ ያሉ ጸሎቶች ይሖዋን ያስደስቱታል? እንዴታ! ደግሞም የእምነት አጋሮቻችን የሚያስፈልጋቸውን እያንዳንዱን ነገር አናውቅም። በመሆኑም ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን በቡድን ደረጃ ጸሎት ማቅረባችን ተገቢ ነው። (ዮሐ. 17:20፤ ኤፌ. 6:18) እንዲህ ያሉ ጸሎቶች “ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር” እንዳለን የሚያሳዩ ናቸው።—1 ጴጥ. 2:17
ለግለሰቦች ስትጸልይ
12. በትኩረት መመልከታችን ለወንድሞቻችን በግለሰብ ደረጃ ጸሎት እንድናቀርብ የሚረዳን እንዴት ነው?
12 በትኩረት ተመልከት። ለወንድሞችና ለእህቶች በቡድን ደረጃ ከመጸለይ ባሻገር በግለሰብ ደረጃ ስማቸውን እየጠቀስን መጸለያችን ተገቢ ነው። በጉባኤህ ውስጥ ከከባድ ሕመም ጋር እየታገለ ያለ ሰው አለ? በትምህርት ቤት በሚገጥመው የእኩዮች ተጽዕኖ ምክንያት ተስፋ የቆረጠ ወጣት አለ? ልጆቹን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” ለማሳደግ ደፋ ቀና የሚል ነጠላ ወላጅ አለ? (ኤፌ. 6:4) በትኩረት የምትመለከት ከሆነ የእምነት አጋሮችህን ስሜት በደንብ መረዳት ትችላለህ፤ ይህ ደግሞ ለእነሱ ለመጸለይ ያለህን ፍላጎት ያጠናክርልሃል።b—ሮም 12:15
13. በአካል ለማናውቃቸው ሰዎች መጸለይ የምንችለው እንዴት ነው?
13 የሌሎችን ስም ጠቅሰህ ጸልይ። ለማናውቃቸው ሰዎችም ጭምር ይህን ማድረግ እንችላለን። ለምሳሌ እንደ ክራይሚያ፣ ኤርትራ፣ ሩሲያ እና ሲንጋፖር ባሉ አገሮች የታሰሩ ወንድሞችና እህቶችን ማንሳት ይቻላል። በእስር ላይ ያሉ ወንድሞችንና እህቶችን ስም jw.org ላይ ማግኘት ትችላለህ።c የወረዳ የበላይ ተመልካች የሆነው ብራያን እንዲህ ብሏል፦ “በእስር ላይ የሚገኝን አንድ የእምነት አጋሬን ስም መጻፌና ስሙን ጮክ ብዬ መጥራቴ ግለሰቡን እንዳስታውሰውና በጸሎቴ ላይ እንዳካትተው ረድቶኛል።”
14-15. ወንድሞቻችን የሚያስፈልጋቸውን ነገር በጸሎታችን ላይ ለይተን መጥቀስ የምንችለው እንዴት ነው?
14 የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለይተህ ጥቀስ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ማይክል እንዲህ ብሏል፦ “በእስር ላይ የሚገኙ ወንድሞችን በተመለከተ jw.org ላይ ሳነብ እኔ በእነሱ ቦታ ብሆን ምን እንደሚሰማኝ ለማሰብ እሞክራለሁ። ለምሳሌ በእነሱ ቦታ ብሆን ስለ ባለቤቴ መጨነቄ አይቀርም፤ የሚያስፈልጋት ነገር እንዲሟላላትም እፈልጋለሁ። ይህን ማሰቤ በእስር ላይ የሚገኙ ባለትዳር ወንድሞችን በተመለከተ ስጸልይ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለይቼ እንድጠቅስ ይረዳኛል።”—ዕብ. 13:3 ግርጌ
15 ወንድሞቻችን እስር ቤት ውስጥ የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ምን ሊመስል እንደሚችል ስናስብ በጸሎታችን ላይ ልንጠቅሳቸው የምንችላቸው ሌሎች ነጥቦችም እናገኛለን። ለምሳሌ የእስር ቤት ጠባቂዎቹ ደግነት እንዲያሳዩአቸው እንዲሁም ባለሥልጣናቱ አምልኳቸውን በነፃነት እንዲያከናውኑ እንዲፈቅዱላቸው መጸለይ እንችላለን። (1 ጢሞ. 2:1, 2) በእስር ላይ ያሉት ወንድሞች በሚያሳዩት ታማኝነት ጉባኤው እንዲበረታታ እንዲሁም የማያምኑ ሰዎች የወንድሞቻችንን መልካም ምግባር አይተው መልእክታችንን ለማዳመጥ እንዲነሳሱ መጸለይ እንችላለን። (1 ጴጥ. 2:12) ሌሎች ፈተናዎችን በጽናት እየተቋቋሙ ስላሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስንጸልይም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንችላለን። ሌሎችን በትኩረት በመመልከት፣ ስማቸውን ጠቅሰን በመጸለይ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለይተን በመጥቀስ አንዳችን ለሌላው ያለንን ‘የተትረፈረፈ ፍቅር’ እናሳያለን።—1 ተሰ. 3:12
ለጸሎታችን ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
16. ለጸሎታችን ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ የምንችለው እንዴት ነው? (ማቴዎስ 6:8)
16 እስካሁን እንደተመለከትነው፣ ጸሎታችን ሁኔታዎች እንዲለወጡ ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። ስንጸልይ ይሖዋ የማያውቀውን ነገር እየነገርነው አይደለም፤ እንዲሁም አንድን ጉዳይ እንዴት መያዝ እንዳለበት ለእሱ ምክር ለመስጠት መሞከር የለብንም። ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እነሱም ሆነ እኛ ሳናውቀው በፊት ያውቀዋል። (ማቴዎስ 6:8ን አንብብ።) እንዲህ ከሆነ ታዲያ ለሌሎች መጸለይ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ባለፈ ለሌሎች መጸለይ አሳቢነታችንን ማሳየት የምንችልበት መንገድ ነው። ፍቅር አንዳችን ለሌላው እንድንጸልይ ያነሳሳናል። ይሖዋም አገልጋዮቹ የእሱን ፍቅር ሲያንጸባርቁ ሲመለከት ይደሰታል።
17-18. ለእምነት አጋሮቻችን መጸለይ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።
17 ጸሎታችን ሁኔታዎች እንዲለወጡ ባያደርግም እንኳ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለንን ፍቅር እናሳይበታለን፤ ይሖዋም ይህን ልብ ብሎ ይመለከታል። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ሁለት ትናንሽ ልጆች ያሉትን አንድ ቤተሰብ ለማሰብ ሞክር። ወንዱ ልጅ ታሞ ተኝቷል። በዚህ ጊዜ ሴቷ ልጅ አባቷን “ለወንድሜ የሆነ ነገር አድርግለት። በጣም ታሟል እኮ!” ብላ ትለምነዋለች። አባትየው ቀድሞውንም ልጁ የሚያስፈልገውን ነገር እያደረገለት ነው። ልጁን ይወደዋል፤ እንዲሁም ይንከባከበዋል። ሆኖም ሴት ልጁ ለወንድሟ በጣም ከማሰቧ የተነሳ እንዲረዳው ስትለምነው ምንኛ ይደሰት ይሆን!
18 ይሖዋም እንድናደርግ የሚፈልገው ይህንኑ ነው፤ እርስ በርሳችን እንድንተሳሰብና አንዳችን ለሌላው እንድንጸልይ ያበረታታናል። እንዲህ ስናደርግ ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችንም እንደምናስብ እናሳያለን፤ ይሖዋ ደግሞ ይህን ልብ ብሎ ይመለከተዋል። (2 ተሰ. 1:3፤ ዕብ. 6:10) በተጨማሪም ቀደም ሲል እንደተወያየነው፣ አንዳንድ ጊዜ ጸሎታችን ሁኔታዎች እንዲለወጡ ሊያደርግ ይችላል። እንግዲያው አንዳችን ለሌላው መጸለያችንን እንቀጥል።
መዝሙር 101 በአንድነት አብሮ መሥራት
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
b ትካሺ ሺሚዙ፦ ይሖዋ “ጸሎት ሰሚ” ነው የሚለውን ቪዲዮ jw.org ላይ ተመልከት።
c በእስር ላይ ያሉ የእምነት አጋሮቻችንን ስም ለማግኘት jw.org ላይ “በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ የይሖዋ ምሥክሮች—በአገር” ብለህ ፈልግ።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ የራሳቸው ችግሮች ያሉባቸው ወንድሞችና እህቶች ለሌሎች ሲጸልዩ።