የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • mrt ርዕስ 72
  • እውነት ጊዜ ያለፈበት ነገር ሆኗል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እውነት ጊዜ ያለፈበት ነገር ሆኗል?
  • ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በእርግጥ እውነት የሚባል ነገር አለ?
  • እውነትን ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?
  • ውሸት የመጣው ከየት ነው?
  • በዛሬው ጊዜ ውሸት እንዲህ የተስፋፋው ለምንድን ነው?
  • እውነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
  • አምላክ እውነትን እንዳውቅ የሚፈልገው ለምንድን ነው?
  • አምላክ ውሸትን የሚያስወግድበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
  • የእውነትን አምላክ መምሰል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ክርስቲያኖች አምላክን በመንፈስና በእውነት ያመልካሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • እውነትን መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
ለተጨማሪ መረጃ
ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
mrt ርዕስ 72
አንድ ፖለቲከኛ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ብዙ ሰዎች ፊት ንግግር ሲያቀርብ።

እውነት ጊዜ ያለፈበት ነገር ሆኗል?

እውነቱን ከሐሰት መለየት ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም ከባድ እየሆነ እንደመጣ ይሰማሃል? በዛሬው ጊዜ ሰዎች ከእውነታው ይልቅ በስሜት ወይም ራሳቸው በሚያምኑበት ነገር ለመመራት የመረጡ ይመስላል። ይህን ሁኔታ ለመግለጽ ተብሎ የተፈጠረው “ድህረ-እውነት (post-truth)” የሚለው ቃል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑ ይህን ያሳያል።a ይህ ቃል ብዙዎች ‘እውነት የሚባል ነገር የለም’ ብለው የሚያምኑበትን የዛሬውን ጊዜ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል።

ይህ አመለካከት አዲስ አይደለም። ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ሮማዊው አገረ ገዢ ጳንጥዮስ ጲላጦስ “እውነት ምንድን ነው?” በማለት ኢየሱስን በምጸት ጠይቆታል። (ዮሐንስ 18:38) ጲላጦስ፣ ኢየሱስ መልስ እስኪሰጠው ባይጠብቅም ያነሳው ጥያቄ ግን በጣም ወሳኝ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ አጥጋቢ ከመሆኑም በላይ ብዙዎች ግራ በተጋቡበት በዚህ ዓለም ውስጥ እውነቱን ከሐሰት መለየት እንድትችል ይረዳሃል።

በእርግጥ እውነት የሚባል ነገር አለ?

አዎ። መጽሐፍ ቅዱስ “እውነት” የሚለውን ቃል ግልጽ በሆነ ማስረጃ የተደገፈን እንዲሁም ከሥነ ምግባር አንጻር ትክክል የሆነን ነገር ለማመልከት ይጠቀምበታል። የአምላክ ቃል፣ ይሖዋb አምላክ የፍጹም እውነት ምንጭ እንደሆነ ያስተምራል፤ እንዲያውም “የእውነት አምላክ” በማለት ይጠራዋል። (መዝሙር 31:5) በተጨማሪም ቃሉ ከአምላክ የተገኘውን እውነት የያዘ ሲሆን ይህን እውነት ከብርሃን ጋር ያመሳስለዋል፤ ምክንያቱም ይህ እውነት፣ በዚህ ግራ የተጋባ ዓለም ውስጥ መንገድ ይመራናል።—መዝሙር 43:3፤ ዮሐንስ 17:17

እውነትን ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን እውነት በጭፍን እንድንቀበል አይፈልግም። ከዚህ ይልቅ በስሜት ተመርተን ሳይሆን የማሰብ ችሎታችንን ተጠቅመን እውነትን እንድንመረምር ግብዣ አቅርቦልናል። (ሮም 12:1) ‘ሙሉ አእምሯችንን’ ተጠቅመን እንድናውቀውና እንድንወደው ይፈልጋል፤ እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ የምንማረው ነገር እውነት መሆኑን እንድናረጋግጥ ያበረታታናል።—ማቴዎስ 22:37, 38፤ የሐዋርያት ሥራ 17:11

ውሸት የመጣው ከየት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያውን ውሸት የተናገረው የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ይናገራል፤ የአምላክ ቃል ሰይጣንን “የውሸት አባት” በማለት ይጠራዋል። (ዮሐንስ 8:44) ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች አምላክን በተመለከተ ውሸት ነግሯቸዋል። (ዘፍጥረት 3:1-6, 13, 17-19፤ 5:5) ከዚያን ጊዜ አንስቶ ስለ አምላክ ውሸት ማናፈሱንና እውነቱን መደበቁን ቀጥሏል።—ራእይ 12:9

በዛሬው ጊዜ ውሸት እንዲህ የተስፋፋው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ በማለት በሚጠራው በዘመናችን፣ ሰይጣን ከምንጊዜውም ይበልጥ በዓለም ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ሰዎችን እያሳሳተ ይገኛል። ብዙ ጊዜ ሰዎች፣ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማስተላለፍ ሌሎችን መጠቀሚያ ያደርጋሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ ሃይማኖቶችም በውሸት የተሞሉ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ያለንበትን ጊዜ በተመለከተ አስቀድሞ እንደተናገረው፣ ሰዎች ‘ጆሯቸውን እንዲኮረኩሩላቸው በዙሪያቸው አስተማሪዎችን በመሰብሰብ እውነትን ከመስማት ጆሯቸውን ለመመለስ’ መርጠዋል።—2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4

አንድ የሃይማኖት መሪ መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ ንግግር ሲያቀርብ፤ አድማጮቹ እያጨበጨቡለት ነው።

እውነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

በሰዎች መካከል መተማመን እንዲኖር ዋናው መሠረት እውነት ነው። መተማመን ከሌለ ወዳጅነትም ሆነ ጠንካራ ማኅበረሰብ ሊኖር አይችልም። አምላክ፣ አምልኳችን በእውነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እንዲህ ይላል፦ “[አምላክን የሚያመልኩ] በመንፈስና በእውነት ሊያመልኩት ይገባል።” (ዮሐንስ 4:24) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት ሃይማኖታዊ ውሸቶችን ለመለየትና ከዚያ ነፃ ለመውጣት የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ ለማወቅ “አምላክን መውደድ ከባድ እንዲሆን ያደረጉ ውሸቶች” በሚል ርዕስ የወጡትን ተከታታይ ርዕሶች ተመልከት።

አምላክ እውነትን እንዳውቅ የሚፈልገው ለምንድን ነው?

አምላክ እንድትድን ይፈልጋል፤ ለመዳን ደግሞ ስለ እሱ እውነቱን ማወቅ ያስፈልግሃል። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) አምላክ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ ያወጣውን መሥፈርት ከተማርክና በዚያ ከተመራህ ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ትችላለህ። (መዝሙር 15:1, 2) አምላክ ሰዎች እውነትን እንዲማሩ ለመርዳት ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው ሲሆን ኢየሱስ ያስተማራቸውን ትምህርቶች እንድንሰማ ይፈልጋል።—ማቴዎስ 17:5፤ ዮሐንስ 18:37

አምላክ ውሸትን የሚያስወግድበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

አዎ። አምላክ፣ ሰዎች ሌሎችን በማታለል መጠቀሚያ ሲያደርጓቸው ሲያይ ያዝናል። በውሸት ጎዳና መመላለሳቸውን ለማቆም ፈቃደኛ ያልሆኑትን ሁሉ ከምድር ገጽ እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል። (መዝሙር 5:6) በዚያን ጊዜ፣ አምላክ “እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ” በማለት የሰጠው ተስፋም ይፈጸማል።—ምሳሌ 12:19

ስለ እውነትና ስለ ውሸት የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች

ዮሐንስ 8:44፦ “[ዲያብሎስ] ውሸታምና የውሸት አባት [ነው]።”

ትርጉም፦ የመጀመሪያውን ውሸት የተናገረውም ሆነ የውሸት ሁሉ ምንጭ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው።

ምሳሌ 12:22፦ “ይሖዋ ውሸታም ከንፈሮችን ይጸየፋል።”

ትርጉም፦ አምላክን የሚወዱ ሰዎች ልክ እንደ እሱ ውሸትን ሊጠሉ ይገባል።

ዮሐንስ 4:24፦ “[አምላክን የሚያመልኩ] በመንፈስና በእውነት ሊያመልኩት ይገባል።”

ትርጉም፦ አምላክ ለእሱ የምናቀርበው አምልኮ ስለ እሱ ከተገለጸው እውነት ጋር የሚስማማ እንዲሆን ይፈልጋል።

ዮሐንስ 8:32፦ “[እውነት] ነፃ ያወጣችኋል።”

ትርጉም፦ ኢየሱስ ያስተማረው እውነት ከድንቁርና፣ ከአጉል እምነት፣ ከሃይማኖታዊ ውሸቶችና ከሌሎች በርካታ ነገሮች ነፃ ያወጣናል። “‘እውነት ነፃ ያወጣችኋል’—እንዴት?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

1 ጢሞቴዎስ 2:4፦ “[የአምላክ] ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።”

ትርጉም፦ አምላክ ስለ እሱ እውነቱን በመማር መዳን እንድናገኝ ይፈልጋል።

a “ድህረ-እውነት (post-truth)” የሚለው ቃል በ2016 የዓመቱ ቃል እንዲሆን በኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ተመርጧል።

b ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ