የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ijwyp ርዕስ 15
  • ስለ መልኬ ከልክ በላይ እየተጨነቅሁ ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ስለ መልኬ ከልክ በላይ እየተጨነቅሁ ነው?
  • የወጣቶች ጥያቄ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጥያቄዎች፦ ከልክ በላይ እየተጨነቅሁ ነው?
  • ‘መልኬን የማልወደው ለምንድን ነው?’
  • ‘መልኬን ለማሻሻል ብሞክር ይሻል ይሆን?’
  • ከሁሉ የላቀው ማሻሻያ!
  • መልክና ቁመናዬን ባልወደውስ?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
  • ውፍረት መቀነስ የምችለው እንዴት ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • የርዕስ ማውጫ
    ንቁ!—2013
  • ስለ ጤንነቴ ያን ያህል ማሰብ ይኖርብኛል?
    ንቁ!—2010
ለተጨማሪ መረጃ
የወጣቶች ጥያቄ
ijwyp ርዕስ 15

የወጣቶች ጥያቄ

ስለ መልኬ ከልክ በላይ እየተጨነቅሁ ነው?

  • ጥያቄዎች፦ ከልክ በላይ እየተጨነቅሁ ነው?

  • መልኬን የማልወደው ለምንድን ነው?

  • መልኬን ለማሻሻል ብሞክር ይሻል ይሆን?

  • ከሁሉ የላቀው ማሻሻያ!

  • የጁሊያ ታሪክ

ጥያቄዎች፦ ከልክ በላይ እየተጨነቅሁ ነው?

  1. ስሜትሽን ጥሩ አድርጎ የሚገልጸው የትኛው ዓረፍተ ነገር ነው?a

    • መልኬን ጨርሶ አልወደውም።

    • መልኬን አንዳንድ ጊዜ እወደዋለሁ።

    • በመልኬ ሁልጊዜም ደስተኛ ነኝ።

  2. ከመልክና ቁመናሽ ጋር በተያያዘ ለመለወጥ በጣም የምትፈልጊው የትኛውን ነው?

    • ቁመት

    • ክብደት

    • የሰውነት ቅርጽ

    • ፀጉር

    • የቆዳ ቀለም

    • ጡንቻ

    • ሌላ

  3. የሚከተለውን ዓረፍተ ነገር አሟዪ።

    በቁመናዬ የማልደሰተው . . .

    • ክብደቴን ስመዘን ነው።

    • በመስታወት ራሴን ስመለከት ነው።

    • ራሴን ከሌሎች (ከጓደኞቼ፣ ከሞዴሎች፣ ከፊልም ተዋንያን) ጋር ሳወዳድር ነው።

  4. የሚከተለውን ዓረፍተ ነገር አሟዪ።

    ክብደቴን የምመዘነው . . .

    • በየቀኑ ነው።

    • በየሳምንቱ ነው።

    • አልፎ አልፎ ነው።

  5. ስሜትሽን ጥሩ አድርጎ የሚገልጸው የትኛው ሐሳብ ነው?

    • መልክና ቁመናዬን አልወደውም። (ምሳሌ፦ “በመስተዋት ራሴን በተመለከትሁ ቁጥር በጣም ወፍራም እና አስቀያሚ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ክብደት ለመቀነስ ስል ራሴን በረሃብ የቀጣሁባቸው ጊዜያት አሉ።”​—ሰሪና)

    • ሚዛናዊ አመለካከት አለኝ። (ምሳሌ፦ “ከመልክና ቁመናችን ጋር በተያያዘ የማንወደው ነገር መኖሩ አይቀርም፤ ይሁንና አንዳንድ ነገሮችን ልንቀበላቸው ይገባል። ልንለውጠው ስለማንችለው ነገር መጨነቅ ምንም ጥቅም የለውም።”​—ናታንያ)

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከሚገባው በላይ ስለ ራሳችን ማሰብ’ እንደሌለብን ያሳስበናል። (ሮም 12:3) ከዚህ አንጻር በተወሰነ መጠን ስለ ራስ ማሰብ ተገቢ እንዲያውም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ጥርስሽን መቦረሽሽ ወይም ንጽሕናሽን መጠበቅሽ ተገቢ ነው።

ይሁንና ስለ መልክሽ ባሰብሽ ቁጥር መጥፎ የሚሰማሽ አልፎ ተርፎም ነገሩ ከመጠን በላይ የሚያስጨንቅሽ ቢሆንስ? ይህ ከሆነ እንደሚከተለው ያለ ጥያቄ ሊፈጠርብሽ ይችላል፦

‘መልኬን የማልወደው ለምንድን ነው?’

የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  • የመገናኛ ብዙኃን ተጽዕኖ። “ወጣቶች ነጋ ጠባ የሚያዩት ነገር፣ ሁልጊዜም በጣም ቀጭንና ውብ መሆን እንዳለባቸው እንዲሰማቸው የሚያደርግ ነው። በመሆኑም ልክ እንደሚባለው በጣም ቆንጆ ካልሆንን ስለ ራሳችን መጥፎ ይሰማናል።”​—ኬሊ

  • የወላጆች ተጽዕኖ። “አንዲት እናት የመልኳ ጉዳይ ከመጠን በላይ የሚያሳስባት ከሆነ ብዙውን ጊዜ ልጇም ተመሳሳይ አመለካከት እንደሚኖራት አስተውያለሁ። ከአባቶችና ከወንዶች ልጆች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።”​—ሪታ

  • ራስን ዝቅ አድርጎ መመልከት። “የመልካቸው ጉዳይ ከመጠን በላይ የሚያስጨንቃቸው ሰዎች፣ ሌሎች ሁልጊዜ መልካቸውን እንዲያደንቁላቸው ይፈልጋሉ። ከእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ጋር መሆን ይሰለቻል።”​—ዣን

መልክሽን እንዳትወጂው ያደረገሽ ምክንያት የትኛውም ቢሆን፣ እንደሚከተለው ብለሽ ታስቢ ይሆናል፦

‘መልኬን ለማሻሻል ብሞክር ይሻል ይሆን?’

እስቲ አንዳንድ እኩዮችሽ ምን እንደሚሉ ተመልከቺ።

“ከመልካችን ጋር በተያያዘ የማንወዳቸውን ነገሮች መለወጥ የምንችለው ሁልጊዜ አይደለም፤ ስለዚህ አንዳንድ ጉድለቶቻችንን ተቀብሎ መኖሩ የተሻለ ነው። እኛ እንዲህ ካደረግን ሌሎች ሰዎች ያን ያህል ላያስተውሉት ይችላሉ።”​—ሮሪ

“ጤነኛ ለመሆን የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ። ጤናማ መሆን በራሱ ጥሩ መልክ እንዲኖራችሁ ያደርጋል። ደግሞም አንድ ሰው መልካችሁን እንጂ ማንነታችሁን ማድነቅ ካልቻለ ያ ግለሰብ ጥሩ ጓደኛ አይደለም።”​—ኦሊቪያ

ዋናው ነጥብ፦ ጥሩ አቋም እንዲኖርሽ ማድረግ የምትችዪውን አድርጊ። ስለቀረው ነገር አትጨነቂ። ስለ መልክ ከሚገባው በላይ መጨነቅ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። (“የጁሊያ ታሪክ” የሚለውን ሣጥን ተመልከቺ።)

በሌላ በኩል ግን ኤሪን የተባለች ወጣት እንደተናገረችው ስለ መልክ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት መያዝ ለራስሽ ያልተዛባ አመለካከት እንዲኖርሽ ይረዳሻል። ኤሪን እንዲህ ብላለች፦ “ስለ መልኬ የማልወዳቸው ነገሮች እንዳሉ የታወቀ ነው፤ ያም ቢሆን ስለ ራሴ መጥፎ የሚሰማኝ በእነዚህ ነገሮች ላይ ትኩረት ሳደርግ ብቻ እንደሆነ አስተውያለሁ። አዘውትሬ ስፖርት እሠራለሁ፤ እንዲሁም ጥሩ የአመጋገብ ልማድ እንዲኖረኝ እጥራለሁ። ይህን ሳደርግ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ይስተካከላሉ።”

ከሁሉ የላቀው ማሻሻያ!

ስለ መልክሽ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ስታዳብሪ ስለ ራስሽ ጥሩ ስሜት ይኖርሻል፤ ይህ ደግሞ ከውጭ የሚታይ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ሊረዳሽ ይችላል። የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ እንድትሞክሪ ያበረታታሻል፦

  • ባለሽ መርካት። “ትርፍ ነገር ለማግኘት ከመቅበዝበዝ ይልቅ፥ ባለህ ነገር መደሰት የተሻለ ነው።”​—መክብብ 6:9 የ1980 ትርጉም

  • ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ስፖርት መሥራት። “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል።”​—1 ጢሞቴዎስ 4:8

  • ውስጣዊ ውበት ማዳበር። “ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።”​—1 ሳሙኤል 16:7

“ስለ ራሳችን ያለን አመለካከት በፊታችን ላይ ይነበባል። አንድ ሰው ባለው የሚረካ ከሆነ ሌሎች ይህን ማስተዋል የሚችሉ ከመሆኑም ሌላ ወደ እሱ ለመቅረብ ይነሳሳሉ።”​—ዛራ

“ውበት፣ ቶሎ ዓይን ውስጥ እንድንገባ ሊያደርገን ይችላል። ከሰዎች አእምሮ የማይጠፋው ግን ማንነታችን እና መልካም ባሕርያችን ነው።”​—ፊሊስያ

በተጨማሪም ምሳሌ 11:22ን፣ ቆላስይስ 3:10, 12ን እና 1 ጴጥሮስ 3:3, 4ን ተመልከቺ።

የጁሊያ ታሪክ

የ16 ዓመት ልጅ እያለሁ ከክብደቴ ጋር በተያያዘ ትልቅ ችግር ነበረብኝ። ከመጠን በላይ ወፍሬ ባላውቅም በተፈጥሮዬ ቀጭን የምባል አይደለሁም። ሞላ ያልኩ ነበርኩ። በመሆኑም ትንሽ ቀጠን ብል ወንዶች እንደሚወዱኝ ይሰማኝ ነበር። ስለዚህ የምፈልገው ዓይነት ቅርጽ እንዲኖረኝ ስል ምግብ አቁሜ ነበር ማለት ይቻላል።

እንዳሰብኩትም ቀጭን መሆን ቻልኩ፤ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያደረግሁት ነገር ግን የጤና ችግር አስከተለብኝ። አሁን ጤንነቴ ቢስተካከልም በስሜቴ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ አልተወገደም። እስካሁንም ድረስ ከምግብ ጋር በተያያዘ ችግር አለብኝ። ቀስ በቀስ፣ ለሰውነቴ ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር ችያለሁ። ጥሩ የአመጋገብ ልማድ ያለኝ ሲሆን ስፖርትም እሠራለሁ። ያም ቢሆን በሆነ ምክንያት በራሴ ስበሳጭ መጀመሪያ የምወስደው እርምጃ ራሴን በረሃብ መቅጣት ነው።

ለሌሎች ወጣቶች መንገር የምፈልገው ነገር ቢኖር ሁሉም ሰው የተለያየ አመለካከት ያለው መሆኑን ነው። ምንም ዓይነት መልክ ቢኖራችሁ፣ አንዳንዶች ቆንጆ እንደሆናችሁ ሊያስቡ ሌሎች ደግሞ እንደማታምሩ ሊሰማቸው እንደሚችል አትዘንጉ። ዋናው ነገር ጤና ነው። ከልብ የሚወዷችሁ ሰዎች ከሁሉ የበለጠ የሚፈልጉት ይህንን ነው።

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ