-
ብዙዎች አምላክን መውደድ የሚከብዳቸው ለምንድን ነው?መጠበቂያ ግንብ—2013 | ኅዳር 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክን መውደድ ከባድ እንዲሆን ያደረጉ ውሸቶች
ብዙዎች አምላክን መውደድ የሚከብዳቸው ለምንድን ነው?
“‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’ ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው።”—ኢየሱስ ክርስቶስ፣ 33 ዓ.ም.a
አንዳንዶች አምላክን መውደድ ከባድ ይሆንባቸዋል። እነዚህ ሰዎች፣ አምላክ ሚስጥራዊና ሊቀረብ የማይችል አልፎ ተርፎም ጨካኝ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ቀጥሎ የቀረቡትን አስተያየቶች ተመልከት፦
“አምላክ እንዲረዳኝ ብጸልይም ለእኔ ቅርብ እንደሆነና እንደሚያስብልኝ አይሰማኝም ነበር። አምላክን የምመለከተው እንደ አንድ አካል ሳይሆን ስሜት እንደሌለው ነገር አድርጌ ነበር።”—ማርኮ፣ ጣሊያን
“አምላክን ለማገልገል ከልቤ ብፈልግም ልቀርበው እንደምችል አልተሰማኝም። አምላክ እኛን ለመቅጣት የተቀመጠ ጨካኝ አካል እንደሆነ አስብ ነበር። አፍቃሪና አሳቢ እንደሆነ ተሰምቶኝ አያውቅም ነበር።”—ሮዛ፣ ጓቲማላ
“ልጅ ሳለሁ አምላክ ስህተቶቻችንን እንደሚፈላልግና አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው እኛን ለመቅጣት ተዘጋጅቶ እንደሚጠብቀን አምን ነበር። እያደር ደግሞ አምላክ፣ የማይቀረብ እንደሆነ አድርጌ ማሰብ ጀመርኩ። ስለ አምላክ ሳስብ፣ ሕዝቡን ቢያስተዳድርም ለእነሱ ምንም ግድ እንደሌለው ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሆነ ይሰማኝ ነበር።”—ሬይሞንድ፣ ካናዳ
አንተስ ምን ይመስልሃል? አምላክን መውደድ ከባድ ነው? ክርስቲያኖች፣ ለብዙ ዘመናት ይህን ጥያቄ ሲጠይቁ ኖረዋል። እንዲያውም በመካከለኛው ዘመን፣ የሕዝበ ክርስትና እምነት ተከታይ በሆኑ አገሮች ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ ጸሎት እንኳ አያቀርቡም ነበር። ለምን? በጣም ይፈሩት ስለነበረ ነው። የታሪክ ምሁር የሆኑት ዊል ዱራንት ጉዳዩን እንደሚከተለው በማለት ገልጸውታል፦ “አንድ ኃጢአተኛ ሰው፣ እጅግ አስፈሪ ወደሆነውና ወደማይቀረበው አምላክ ለመጸለይ እንዴት ሊደፍር ይችላል?”
ለመሆኑ ሰዎች፣ አምላክን ‘እጅግ አስፈሪና የማይቀረብ’ እንደሆነ አድርገው እንዲያዩት ያደረጋቸው ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ምን ያስተምራል? ስለ አምላክ እውነቱን መማር እሱን እንድትወደው ሊያነሳሳህ ይችላል?
-
-
ውሸት 1 አምላክ ስም የለውምመጠበቂያ ግንብ—2013 | ኅዳር 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክን መውደድ ከባድ እንዲሆን ያደረጉ ውሸቶች
ውሸት 1 አምላክ ስም የለውም
ብዙዎች ምን ብለው ያምናሉ?
“አምላክ ‘የግል’ ስም አለው ብለን መናገር እንችል እንደሆነ፣ ስም ካለው ደግሞ ያ ስም ማን እንደሆነ ስምምነት ላይ አልደረስንም።”—ፕሮፌሰር ዴቪድ ከኒንግሀም፣ ቲኦሎጂካል ስተዲስ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት
አምላክ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው።” (ኢሳይያስ 42:8)a ይሖዋ ወይም ያህዌ የሚለው የዕብራይስጥ ስም “ይሆናል” የሚል ትርጉም አለው።—ዘፍጥረት 2:4
ይሖዋ በስሙ እንድንጠቀም ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ስሙንም ጥሩ፤ ያደረገውንም በአሕዛብ መካከል አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ከፍ ማለቱንም ዐውጁ።”—ኢሳይያስ 12:4
ኢየሱስ በአምላክ ስም ተጠቅሟል። ኢየሱስ ወደ ይሖዋ ሲጸልይ “ስምህን ለእነሱ [ለደቀ መዛሙርቱ] አሳውቄአለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ” ብሏል። ኢየሱስ መለኮታዊውን ስም ለደቀ መዛሙርቱ ያሳወቀው ለምንድን ነው? ምክንያቱን ሲገልጽ “እኔን የወደድክበትን ፍቅር እነሱም እንዲያንጸባርቁ እንዲሁም እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት እንዲኖረኝ” ብሏል።—ዮሐንስ 17:26
ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?
የሥነ መለኮት ምሁር የሆኑት ዎልተር ሎውሪ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “የአምላክን ስም የማያውቅ ሰው፣ የአምላክን ማንነት ያውቃል ማለት አይቻልም፤ ይህ ሰው አምላክን የሚመለከተው፣ የራሱ ማንነት እንደሌለው ኃይል አድርጎ ከሆነ እሱን ሊወደው አይችልም።”
ቪክቶር የሚባል አንድ ሰው በየሳምንቱ ቤተ ክርስቲያን ይሄድ የነበረ ቢሆንም አምላክን እንደሚያውቀው አይሰማውም ነበር። ቪክቶር እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክ ስም፣ ይሖዋ እንደሆነ ስማር ግን ከእሱ ጋር እንደተዋወቅሁ ሆኖ ተሰማኝ። ብዙ ሲወራለት ከሰማሁት አካል ጋር በመጨረሻ የተገናኘሁ ያህል ነበር። አምላክ እውን ሆነልኝ፤ ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረትም ቻልኩ።”
ይሖዋም ስሙን የሚጠቀሙ ሰዎችን ወደ እሱ ያቀርባቸዋል። አምላክ ‘ስሙን የሚያከብሩ’ ሰዎችን በሚመለከት “አባት የሚያገለግለውን ልጁን እንደሚታደግ ሁሉ እኔም እታደጋቸዋለሁ” በማለት ቃል ገብቷል። (ሚልክያስ 3:16, 17) በተጨማሪም አምላክ ስሙን የሚጠሩ ሰዎችን ወሮታ ይከፍላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ይላል።—ሮም 10:13
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የአዲሱ መደበኛ ትርጉም መቅድም፣ “መለኮታዊው ስም” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር እንዲህ ይላል፦ “‘ያህዌ’ [LORD] ለሚለው ስም . . . ‘እግዚአብሔር’ የሚለው መጠሪያ ትክክለኛ ምትክ ሆኖ በመገኘቱ የሆሄያቱ አጣጣል ወይም ቅርጽ ‘እግዚአብሔር’ የሚለውን መልክ እንዲይዝ ተደርጓል።”
-
-
ውሸት 2 ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልምመጠበቂያ ግንብ—2013 | ኅዳር 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክን መውደድ ከባድ እንዲሆን ያደረጉ ውሸቶች
ውሸት 2 ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም
ብዙዎች ምን ብለው ያምናሉ?
የክርስትና ሃይማኖት “ሦስቱ ዋና ዋና ክፍሎች ይኸውም የሮም ካቶሊክ፣ ምሥራቃዊ ኦርቶዶክስ እንዲሁም ፕሮቴስታንት አምላክ አንድም ሦስትም እንደሆነ ያምናሉ፤ በሌላ አባባል አምላክን እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ብለው ይገልጹታል። በክርስትና ሃይማኖታዊ ትምህርት መሠረት፣ ይህ ሦስት አማልክት እንዳሉ የሚገልጽ ሳይሆን ሦስቱም አንድ እንደሆኑ የሚጠቁም ነው።”—ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት
የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ፣ ከአባቱ ጋር እኩል እንደሆነ ወይም በመለኮት አንድ እንደሆኑ በፍጹም ተናግሮ አያውቅም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ብሏል፦ “የምትወዱኝ ቢሆን ኖሮ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ ምክንያቱም አብ ከእኔ ይበልጣል።” (ዮሐንስ 14:28) በተጨማሪም ከተከታዮቹ ለአንዷ “ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ላርግ ነው” ብሎ ነግሯታል።—ዮሐንስ 20:17
መንፈስ ቅዱስ አካል አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የቀድሞ ክርስቲያኖች “በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ” ይላል፤ ይሖዋም “መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4, 17) ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ ክፍል አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሥራ ላይ የዋለ የአምላክ ኃይል ነው።
ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?
የካቶሊክ ምሁራን የሆኑት ካርል ራነ እና ኸርበርት ፎርግሪምለ እንደገለጹት የሥላሴን ትምህርት “አንድ ሰው ራእይ ካልተገለጠለት በቀር ሊረዳው አይችልም፤ ራእይ ቢታየውም እንኳ ሙሉ በሙሉ ሊገነዘበው አይችልም።” ታዲያ ልታውቀው የማትችለውን አካል ልትወደው ትችላለህ? ከዚህ አንጻር የሥላሴ መሠረተ ትምህርት አምላክን እንዳናውቀውና እሱን እንዳንወድደው እንቅፋት ይሆንብናል ማለት ይቻላል።
ቀደም ባለ ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ማርኮ፣ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት አምላክን እንዳያውቅ እንቅፋት እንደሆነበት ተሰምቶት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ማንነቱን እንደደበቀኝ ተሰምቶኝ ነበር፤ ይህ ደግሞ ሊቀረብ እንደማይችልና ሚስጥራዊ እንደሆነ እንዳስብ አደረገኝ።” ይሁን እንጂ “አምላክ ግራ የሚያጋባ አምላክ አይደለም።” (1 ቆሮንቶስ 14:33 አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን) አምላክ ማንነቱን አልደበቀንም። እንዲያውም እንድናውቀው ይፈልጋል። ኢየሱስ “የምናውቀውን እናመልካለን” ብሏል።—ዮሐንስ 4:22
ማርኮ “አምላክ ሥላሴ እንዳልሆነ ሳውቅ ከእሱ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት ቻልኩ” ብሏል። ይሖዋን፣ ማንነቱ በግልጽ ሊታወቅ እንደሚችል አካል አድርገን የምንመለከተው ከሆነ እሱን መውደድ ከባድ አይሆንብንም። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር የማያሳይ አምላክን አያውቅም፤ ምክንያቱም አምላክ ፍቅር ነው” ይላል።—1 ዮሐንስ 4:8
-
-
ውሸት 3 አምላክ ጨካኝ ነውመጠበቂያ ግንብ—2013 | ኅዳር 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክን መውደድ ከባድ እንዲሆን ያደረጉ ውሸቶች
ውሸት 3 አምላክ ጨካኝ ነው
ብዙዎች ምን ብለው ያምናሉ?
“ከባድ ኃጢአት የሠሩ ሰዎች፣ ልክ ሲሞቱ ነፍሳቸው ወደ ሲኦል ይወርዳል፤ በዚያም ‘በዘላለማዊ እሳት’ ይሠቃያሉ።” (ካቴኪዝም ኦቭ ዘ ካቶሊክ ቸርች) አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሲኦል ከአምላክ መገለልን ወይም መራቅን እንደሚያመለክት ይናገራሉ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት
“ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች።” (ሕዝቅኤል 18:4) “ሙታን . . . ምንም አያውቁም።” (መክብብ 9:5) ነፍስ የምትሞትና ከሞት በኋላ ምንም የማታውቅ ከሆነ ዘላለማዊ እሳት ወይም ከአምላክ መራቅ የሚያስከትለው ሥቃይ ሊሰማት የሚችለው እንዴት ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙውን ጊዜ “ሲኦል” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት የሚያመለክቱት የሰው ልጆችን መቃብር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ኢዮብ የሚያሠቃይ ሕመም ይዞት ሳለ “በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ!” ብሎ ጸልዮአል። (ኢዮብ 14:13 የ1954 እትም) ኢዮብ የተመኘው፣ በመቃብር ውስጥ እረፍት ማግኘትን እንጂ ወደ ሥቃይ ሥፍራ መግባትን ወይም ከአምላክ መነጠልን አልነበረም።
ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?
ጭካኔ አምላክን እንድንወደውና እንድንቀርበው አያደርገንም፤ ከዚህ ይልቅ ከእሱ እንድንርቅ ያደርገናል። በሜክሲኮ የምትኖረው ሮሲዮ እንዲህ ብላለች፦ “ከሕፃንነቴ ጀምሮ ስለ ገሃነም እሳት እማር ነበር። አምላክን በጣም ከመፍራቴ የተነሳ ምንም ዓይነት ጥሩ ባሕርያት ሊኖሩት እንደሚችሉ ማሰብ አልቻልኩም። ቁጡ እንደሆነና ትዕግሥት እንደሌለው ይሰማኝ ነበር።”
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ስለሚወስዳቸው የፍርድ እርምጃዎችና ሙታን ስላሉበት ሁኔታ የሚናገረው ግልጽ ሐሳብ ሮሲዮ ለአምላክ የነበራትን አመለካከት እንድትለውጥ ረድቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “ነፃ እንደወጣሁ፣ ይኸውም ከባድ ሸክም ከላዬ ላይ እንደወረደልኝ ተሰማኝ። አምላክ ከሁሉ የተሻለውን እንደሚመኝልንና እንደሚወደን መተማመን ቻልኩ፤ እኔም ልወደው እንደምችል ተሰማኝ። አምላክ፣ ልጆቹን እጃቸውን ይዞ እንደሚመራና ለእነሱ ከሁሉ የተሻለውን እንደሚመኝ አባት ነው።”—ኢሳይያስ 41:13
ብዙዎች ገሃነመ እሳትን በመፍራት ሃይማኖተኛ ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ፤ አምላክ ግን እሱን በመፍራት እንድታገለግለው አይፈልግም። ኢየሱስ “አምላክህን ይሖዋን . . . ውደድ” ብሏል። (ማርቆስ 12:29, 30) በተጨማሪም አምላክ በዛሬው ጊዜ ፍትሕ የጎደለው ነገር እንደማያደርግ ስንገነዘብ ወደፊት የሚወስዳቸው የፍርድ እርምጃዎችም ፍትሐዊ እንደሚሆኑ እንተማመናለን። እኛም የኢዮብ ወዳጅ እንደሆነው እንደ ኤሊሁ “ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር ዘንድ፣ በደልንም መፈጸም ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ” ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን።—ኢዮብ 34:10
-
-
እውነት ነፃ ያወጣችኋልመጠበቂያ ግንብ—2013 | ኅዳር 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክን መውደድ ከባድ እንዲሆን ያደረጉ ውሸቶች
እውነት ነፃ ያወጣችኋል
አንድ ቀን፣ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም እየሰበከ ነበር፤ በወቅቱ ስለ አባቱ ስለ ይሖዋ ያስተማረ ከመሆኑም ሌላ በዘመኑ የነበሩትን የሐሰት ሃይማኖት መሪዎች አጋልጧል። (ዮሐንስ 8:12-30) ኢየሱስ በዚያ ቀን የተናገረው ነገር፣ በዛሬው ጊዜ ስለ አምላክ የሚነገሩ በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ እምነቶችን መመርመር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል። ኢየሱስ “በቃሌ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ብሏል።—ዮሐንስ 8:31, 32
“በቃሌ ብትኖሩ።” እዚህ ላይ ኢየሱስ፣ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች “እውነት” መሆን አለመሆናቸውን መመዘን የምንችልበትን መሥፈርት ሰጥቶናል። ስለ አምላክ አንድ ትምህርት ስትሰማ፣ ‘ይህ ሐሳብ ኢየሱስ ከተናገራቸውና በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ሐሳቦች ጋር ይስማማል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ጳውሎስ ሲናገር ካዳመጡ በኋላ፣ “የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ [የመረመሩትን]” ሰዎች ምሳሌ ተከተል።—የሐዋርያት ሥራ 17:11
በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች መጀመሪያ ላይ የተጠቀሱት ማርኮ፣ ሮዛ እና ሬይሞንድ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት እምነቶቻቸውን በጥንቃቄ መርምረዋል። ታዲያ ምን ማወቅ ቻሉ?
ማርኮ፦ “እኔና ባለቤቴ ለምንጠይቃቸው ጥያቄዎች በሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪያችን መልስ የሚሰጠን ከመጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ለይሖዋ ያለን ፍቅር ማደግ የጀመረ ሲሆን በእኔና በባለቤቴ መካከል ያለው ዝምድናም እየጠነከረ ሄደ!”
ሮዛ፦ “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሳስብ ሰዎች፣ አምላክን በራሳቸው አመለካከት ለመግለጽ የሞከሩበት የፍልስፍና መጽሐፍ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ቀስ በቀስ ግን ለጥያቄዎቼ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ አገኘሁ። አሁን፣ ይሖዋ ለእኔ እውን ነው። እምነት ልጥልበት እንደምችል ይሰማኛል።”
ሬይሞንድ፦ “ስለ እሱ እንዳውቅ እንዲረዳኝ ወደ አምላክ ጸልዬ ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እኔና ባለቤቴ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርን። በመጨረሻ፣ ስለ ይሖዋ እውነቱን አወቅን! እሱ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ስናውቅ ደስታችን ወሰን አልነበረውም።”
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የተነገሩ ውሸቶችን በማጋለጥ ብቻ ሳይወሰን ማራኪ ስለሆኑት የአምላክ ባሕርያት እውነቱን ይገልጽልናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ያስጻፈው ቃሉ ሲሆን “አምላክ በደግነት የሰጠንን ነገሮች ማወቅ እንችል ዘንድ” ይረዳናል። (1 ቆሮንቶስ 2:12) ስለ አምላክ፣ ስለ ዓላማውና ስለ ወደፊቱ ሕይወታችን ብዙ ጊዜ ለሚነሱ አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስ ምን መልስ እንደሚሰጥ ለምን አትመረምርም? ከእነዚህ ጥያቄዎች ለአንዳንዶቹ የተሰጡትን መልሶች ለማግኘት www.jw.org/am በተሰኘው ድረ ገጻችን ላይ “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው” የሚለውን ክፍል ተመልከት። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከፈለግህ በዚሁ ድረ ገጽ ላይ ያለውን ቅጽ መሙላት ወይም ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱን ማነጋገር ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስን ካጠናህ፣ አምላክን መውደድ ከምታስበው በላይ ቀላል እንደሚሆንልህ እርግጠኞች ነን።
-