-
ኤደን ገነት—በእርግጥ የሰው ልጆች የመጀመሪያ መኖሪያ ነበር?መጠበቂያ ግንብ—2011 | ጥር 1
-
-
ኤደን ገነት—በእርግጥ የሰው ልጆች የመጀመሪያ መኖሪያ ነበር?
በአንድ የአትክልት ስፍራ ውስጥ እንዳለህ አድርገህ አስብ። በአካባቢው ምንም የሚረብሽ ነገር የለም፤ ከሩቅ የሚመጣም የከተማ ጫጫታ ባለመኖሩ ስፍራው ሰላማዊ ነው። ይህ የአትክልት ስፍራ በጣም ሰፊ ሲሆን ጸጥታውን የሚያደፈርስ አንዳች ነገር የለም። ከሁሉ በላይ ደግሞ አእምሮህ ከጭንቀት ነፃ ነው፤ በዚያ ላይ አለርጂን ጨምሮ ምንም ዓይነት በሽታ ስለሌለ ምንጊዜም ጤናማ ነህ። በስሜት ሕዋሳትህ ተጠቅመህ የአካባቢህን ውበት እንዳታደንቅ እንቅፋት የሚሆንብህ ምንም ነገር የለም።
ገና እንደገባህ ዓይኖችህ በቀለማት ባሸበረቁት አበቦች ላይ ያርፋሉ፤ ከዚያም ዞር ስትል ኩልል እያሉ የሚፈሱ ጅረቶችን ትመለከታለህ። ወዲያው ደግሞ አረንጓዴ ምንጣፍ የሚመስለው ሣርና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዕፅዋት ቀልብህን ይስቡታል፤ አንዳንዶቹ የፀሐይ ብርሃን ሲያርፍባቸው በሚፈጥሩት ውበት እጅግ ትደመማለህ። መንፈስን የሚያድሰው ነፋሻማ አየር ቆዳህ ላይ ሲያርፍ ይሰማሃል፤ እግረ መንገዱን ይዞት የሚመጣው አስደሳች መዓዛ ደግሞ አፍንጫህን ያውደዋል። ነፋስ የሚያወዛውዛቸው ዛፎችና ከዓለት ጋር እየተላተመ የሚወርደው የወንዝ ውኃ የሚያሰሙት ድምፅ ልዩ ስሜት ይፈጥርብሃል፤ የአእዋፋትን ዝማሬና በሥራ የተጠመዱ ነፍሳትን ድምፅ መስማትም ቢሆን ጆሮህ አይሰለቸውም። ይህን ስፍራ በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ስትሞክር ምን ተሰማህ? ‘ምናለ እንዲህ ባለ ቦታ በኖርኩ’ ብለህ አልተመኘህም?
በመላው ዓለም ያሉ ሕዝቦች የሰው ልጅ መጀመሪያ ላይ እንዲህ ባለ ስፍራ ይኖር እንደነበር ያምናሉ። በአይሁድ፣ በክርስትናና በእስልምና እምነት ውስጥ ያሉ ሰዎች አምላክ አዳምንና ሔዋንን ከፈጠራቸው በኋላ በኤደን የአትክልት ስፍራ እንዳኖራቸው ለብዙ ዘመናት ሲማሩ ኖረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው አዳምና ሔዋን ሰላማዊና አስደሳች ሕይወት ይመሩ ነበር። እርስ በርሳቸውም ሆነ ከእንስሳት ጋር እንዲሁም በዚያ ውብ አካባቢ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ከሰጣቸው ከደጉ አምላካቸው ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ነበራቸው።—ዘፍጥረት 2:15-24
ሂንዱዎችም ቢሆኑ በጥንት ዘመን ስለነበረችው ገነት የራሳቸው የሆነ ግንዛቤ አላቸው። ቡዲስቶች ደግሞ በወርቃማ ዘመናት ላይ ይኸውም ዓለም እንደ ገነት በምትሆንባቸው ጊዜያት ታላላቅ መንፈሳዊ መሪዎች ወይም ቡድሃዎች ይነሳሉ ብለው ያምናሉ። በአፍሪካ ያሉ በርካታ ሃይማኖቶችም ከአዳምና ሔዋን ታሪክ ጋር በሚገርም ሁኔታ የሚመሳሰሉ ታሪኮችን ያስተምራሉ።
እንዲያውም በጥንት ዘመን ስለነበረችው ገነት የሚገልጽ ሐሳብ በሁሉም ሃይማኖትና ባሕል ውስጥ ይገኛል ማለት ይቻላል። አንድ የታሪክ ምሑር እንደገለጹት “በርካታ ማኅበረሰቦች በጥንት ዘመን ፍጽምናን የተላበሰች፣ ነፃነት የነገሠባት፣ ሰላምና ደስታ የሰፈነባት፣ ሁሉ ነገር የተንበሸበሸባት እንዲሁም ከስጋት፣ ከውጥረትና ከግጭት ነፃ የሆነች ገነት እንደነበረች የሚያምኑ መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። . . . ይህ እምነት ብዙኃኑ የጠፋችውን ሆኖም ያልተረሳችውን ገነት በእጅጉ እንዲናፍቅና ይህችን ገነት መልሶ የማግኘት ብርቱ ምኞት እንዲያድርበት አድርጓል።”
እነዚህ ሁሉ ታሪኮችና ባሕሎች አንድ የጋራ መሠረት ይኖራቸው ይሆን? “ብዙኃኑ” እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲይዝ ያደረገ በድሮ ዘመን የተፈጸመ እውነተኛ ታሪክ ይኖር ይሆን? በጥንት ዘመን በእርግጥ የኤደን የአትክልት ስፍራ ነበር? አዳምና ሔዋንስ በገሐዱ ዓለም የኖሩ ሰዎች ነበሩ?
ተጠራጣሪዎች ይህን ሐሳብ ያጣጥሉታል። ሳይንስ በተራቀቀበት በዚህ ዘመን ብዙ ሰዎች ስለ ኤደን ገነት የሚናገሩት ዘገባዎች ከፈጠራ ታሪክና ከተረት ያለፉ እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል። ከእነዚህ ተጠራጣሪዎች መሃል ብዙ የሃይማኖት መሪዎች የሚገኙበት መሆኑ የሚያስገርም ነው። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ኤደን ገነት የሚባል ስፍራ ኖሮ አያውቅም ብለው ይናገራሉ። ስለ ኤደን ገነት የሚናገረው ዘገባ ተምሳሌትነት ያለው፣ ተረት፣ የፈጠራ ታሪክ ወይም ተራ ምሳሌ እንጂ እውነተኛ ታሪክ አይደለም ይላሉ።
እርግጥ ነው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ ምሳሌ የተነገሩ ታሪኮች አሉ። እንዲያውም በጣም ታዋቂ የሆኑትን ምሳሌዎች የተናገረው ኢየሱስ ነው። ይሁን እንጂ ስለ ኤደን የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በምሳሌ መልክ የቀረበ ሳይሆን ግልጽና ምንም ያልተወሳሰበ እውነተኛ ታሪክ መሆኑን ከተጻፈበት መንገድ መረዳት ይቻላል። ሆኖም ስለ ኤደን ገነት የሚናገረው ዘገባ ጨርሶ ያልተፈጸመ ታሪክ ከሆነ በተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ እንዴት እምነት መጣል እንችላለን? እስቲ አንዳንዶች ስለ ኤደን ገነት የሚገልጸውን ዘገባ የሚጠራጠሩት ለምን እንደሆነ እንመርምር፤ ከዚያም የሚያቀርቡት ምክንያት አጥጋቢ መሆን አለመሆኑን እናያለን። በተጨማሪም ዘገባው የእያንዳንዳችንን ሕይወት ይነካል የምንልበትን ምክንያት እንመለከታለን።
-
-
ኤደን ገነት በእውን የነበረ ቦታ ነው?መጠበቂያ ግንብ—2011 | ጥር 1
-
-
ኤደን ገነት በእውን የነበረ ቦታ ነው?
ስለ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ስለ ኤደን የአትክልት ስፍራ የሚናገረውን ታሪክ ታውቀዋለህ? በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙ ሰዎች ያውቁታል። ለምን መጽሐፍ ቅዱስህን ገልጠህ ታሪኩን አታነበውም? ዘገባው የሚገኘው ከዘፍጥረት 1:26 እስከ 3:24 ላይ ነው። ታሪኩ ባጭሩ ይህን ይመስላል፦
ይሖዋ አምላክa ሰውን ከምድር አፈር ከሠራው በኋላ ስሙን አዳም ብሎ ጠራው፤ ከዚያም ኤደን ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ባለ የአትክልት ስፍራ ውስጥ እንዲኖር አደረገ። ይህን የአትክልት ስፍራ ያዘጋጀው አምላክ ራሱ ነው። ስፍራው እንደ ልብ ውኃ የሚያገኝ ከመሆኑም ሌላ ፍሬ የሚሰጡ የሚያማምሩ ዛፎች የሞሉበት ነበር። በመካከሉም “መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ” ይገኝ ነበር። አምላክ፣ ሰዎች ከዚህ ዛፍ እንዳይበሉ አዘዛቸው፤ ታዛዥ ሳይሆኑ ቀርተው ቢበሉ ግን እንደሚሞቱ ነገራቸው። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ፣ ከአዳም የጎድን አጥንቶች አንዱን ወስዶ አጋር የምትሆነውን ሴት ማለትም ሔዋንን ፈጠረለት። አምላክ ለአዳምና ሔዋን የአትክልት ስፍራውን የመንከባከብ ሥራ የሰጣቸው ሲሆን እየተባዙ ምድርን እንዲሞሏትም ነገራቸው።
ሔዋን ብቻዋን ሳለች አንድ እባብ አነጋገራት፤ እባቡ አምላክ እንደዋሻትና አንድ መልካም ነገር ማለትም እንደ አምላክ እንድትሆን ሊያደርጋት የሚችል ነገር እንደነፈጋት በመናገር ከተከለከለው ፍሬ እንድትበላ አግባባት። እሷም በማባበያው ተታልላ ከተከለከለው ፍሬ በላች። በኋላም አዳም ከእሷ ጋር በመተባበር የአምላክን ትእዛዝ ጣሰ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ በአዳም፣ በሔዋንና በእባቡ ላይ የፍርድ ብይን አስተላለፈ። ከዚያም ሰዎቹን ከኤደን የአትክልት ስፍራ ያባረራቸው ሲሆን ወደ ገነት የሚያስገባውን በር ለመጠበቅም መላእክት አቆመ።
ምሑራን፣ ጠበብትና የታሪክ ባለሙያዎች በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን ክንውን በመመርመር እውነተኛና በእርግጥ የተፈጸመ ታሪክ ስለመሆኑ የምሥክርነት ቃል መስጠታቸው የተለመደ ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን እንዲህ ስላሉት ጉዳዮች ተጠራጣሪ መሆን ፋሽን እየሆነ መጥቷል። ይሁን እንጂ ስለ አዳም፣ ስለ ሔዋንና ስለ ኤደን የአትክልት ስፍራ የሚተርከውን የዘፍጥረት ዘገባ ለመጠራጠር ምክንያት የሆናቸው ምንድን ነው? እስቲ ብዙ ጊዜ የሚጠቅሷቸውን አራት ምክንያቶች እንመርምር።
1. የኤደን የአትክልት ስፍራ በእውን የነበረ ቦታ ነው?
በዚህ ጉዳይ ላይ ጥርጣሬ የተፈጠረው ለምንድን ነው? ፍልስፍና የራሱ ድርሻ ሳይኖረው አይቀርም። ለብዙ መቶ ዓመታት የሃይማኖት ምሑራን አምላክ የተከላት ገነት የሆነ ቦታ ላይ ትገኛለች የሚል ግምት ነበራቸው። ይሁን እንጂ፣ ‘ሰማይ ላይ ካልሆነ በስተቀር በምድር ላይ ፍጹም የሆነ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም’ የሚል አመለካከት የነበራቸው እንደ ፕላቶና አርስቶትል ያሉ የግሪክ ፈላስፎች በቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽዕኖ አሳድረው ነበር። በመሆኑም የሃይማኖት ምሑራን፣ የመጀመሪያዋ ገነት ለሰማይ ቀረብ ብላ የምትገኝ መሆን አለባት ብለው አሰቡ።b አንዳንዶች ገነትን የሚያስቧት ከዚህች የረከሰች ምድር ጋር እንዳትነካካ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ተራራ አናት ላይ እንደተቀመጠች አድርገው ነው፤ ሌሎች በሰሜን ወይም በደቡብ ዋልታ ላይ እንደምትገኝ ሲያስቡ አንዳንዶች ደግሞ ጨረቃ ላይ ወይም ለጨረቃ ቅርብ በሆነ አካባቢ እንደምትገኝ ይሰማቸዋል። ከዚህ አንጻር ስለ ኤደን የሚናገረው ታሪክ ቅዠት መስሎ መታየቱ ምንም አያስገርምም። አንዳንድ የዘመናችን ምሑራን ኤደን የሚባል ስፍራ ኖሮ አያውቅም የሚል ጠንካራ እምነት ስላላቸው ኤደንን ከካርታ ላይ ለማግኘት መሞከር ሞኝነት እንደሆነ ይሰማቸዋል።
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አዳምና ሔዋን ስለኖሩበት የአትክልት ስፍራ የሚሰጠው መግለጫ ከዚህ ፍጹም የተለየ ነው። በዘፍጥረት 2:8-14 ላይ ስለዚህ ስፍራ በርካታ ዝርዝር ነገሮች ተገልጸው እናገኛለን። ይህ ስፍራ የሚገኘው ኤደን በሚባል ቦታ ምሥራቃዊ ክፍል ነበር። መነሻው ኤደን ከሆነ አንድ ትልቅ ወንዝ ተከፍለው የሚወጡ አራት ወንዞች የአትክልት ስፍራውን ያጠጡ ነበር። የአራቱም ወንዞች ስም የተጠቀሰ ከመሆኑም በላይ ወዴት አቅጣጫ እንደሚፈሱም በአጭሩ ተገልጿል። እነዚህ ዝርዝር መረጃዎች፣ ምሑራን ይህን ስፍራ ለማግኘት ጉጉት እንዲያድርባቸው አድርገዋል፤ አብዛኞቹ ምሑራንም ይህ ጥንታዊ ስፍራ በአሁኑ ጊዜ የት እንደሚገኝ የሚጠቁም ፍንጭ ለማግኘት በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ጥልቀት ያለው ምርምር ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይሁንና የምርምራቸውን ውጤት አስመልክተው የሰጧቸው አያሌ አስተያየቶች እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ናቸው። ይህ መሆኑ ታዲያ ስለ ኤደን፣ በዚያ ስለነበረው የአትክልት ስፍራና ስለ ወንዞቿ የተሰጠው መግለጫ ሐሰት ወይም ተረት ነው ለማለት ያስችላል?
እስቲ አስበው፦ በኤደን የአትክልት ስፍራ የተከናወኑት ነገሮች የተፈጸሙት ከ6,000 ዓመታት በፊት ነው። እነዚህን ክንውኖች በጽሑፍ እንዳሰፈረ የሚገመተው ሙሴ ሲሆን ዘገባዎቹን ያጠናቀረው በቃል የተላለፉ ታሪኮችን ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል የተጻፉ ሰነዶችን በመጠቀም ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ሙሴ ዘገባውን የጻፈው በኤደን ገነት የተከናወኑት ነገሮች ከተፈጸሙ ከ2,500 ዓመታት ገደማ በኋላ ነበር። ስለ ኤደን ገነት የሚገልጸው ታሪክ ሙሴ ለኖረበት ዘመን ጭምር ጥንታዊ ነበር። ታዲያ ወንዞችን ጨምሮ የኤደን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በበርካታ መቶ ዘመናት ውስጥ ሊለወጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ይሆን? የመሬት ገጽ ባለበት የማይቀጥልና ምንጊዜም የሚለዋወጥ ነው። ኤደን የምትገኝበት ስፍራ እንደነበር የሚገመተው አካባቢ የመሬት መናወጥ የሚያጠቃው ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ከደረሱት ታላላቅ የመሬት ነውጦች ውስጥ 17 በመቶ የሚሆኑት የተከሰቱት በዚህ ቦታ ነው። እንዲህ ባሉ አካባቢዎች ለውጥ መከሰቱ የማይቀር ነገር ነው። ሌላስ ምክንያት ይኖር ይሆን? የኖኅ የጥፋት ውኃ የመሬትን ገጽ በዛሬው ጊዜ ፈጽሞ ልናውቀው በማንችል ሁኔታ ለውጦት ሊሆን ይችላል።c
ይሁንና ስለ ኤደን ገነት የምናውቃቸው ጥቂት እውነታዎች አሉ፦ የዘፍጥረት ዘገባ ስለዚህ ስፍራ የሚናገረው በእውን የነበረ ቦታ እንደሆነ አድርጎ ነው። በዘገባው ላይ ከተጠቀሱት አራት ወንዞች ውስጥ ሁለቱ ማለትም ኤፍራጥስና ጤግሮስ ወይም ሂዲኬል ዛሬም ድረስ እየፈሰሱ ሲሆን የእነዚህ ወንዞች መነሻ ከሆኑት የውኃ አካላት አንዳንዶቹ የሚገኙት ቅርብ ለቅርብ ነው። ሌላው ቀርቶ ዘገባው አራቱ ወንዞች አቋርጠው የሚያልፉባቸውን አገሮች ስም ጭምር የሚጠቅስ ሲሆን በአካባቢው የሚታወቁትን የተፈጥሮ ሀብቶች ለይቶ ይጠቅሳል። ስለ ኤደን በሚገልጸው ዘገባ ውስጥ የቀረቡት ዝርዝር ጉዳዮች የዘፍጥረትን መጽሐፍ ለማንበብ የመጀመሪያ ለሆኑት የጥንቶቹ እስራኤላውያን በቂ መረጃ የሚሰጡ ነበሩ።
ዘገባው የፈጠራ ታሪክ ወይም ተረት ቢሆን ኖሮ በዚህ መልክ ይቀርብ ነበር? እውነት መሆን አለመሆናቸው በቀላሉ ሊረጋገጡ የሚችሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ተረቶች ውስጥ ማግኘት እንችላለን? ተረቶች የሚጀምሩት “ከዕለታት አንድ ቀን በጣም ሩቅ በሆነ አገር” በማለት ነው። እውነተኛ ታሪክ ግን ስለ ኤደን በሚገልጸው ዘገባ ላይ እንዳሉት ያሉ አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር መረጃዎችን አካቶ ይይዛል።
2. አምላክ አዳምን ከምድር አፈር እንደሠራውና ሔዋንን ደግሞ ከአዳም የጎድን አጥንቶች አንዱን ወስዶ እንደሠራት የሚናገረው ታሪክ በእርግጥ ተአማኒ ነው?
ዘመናዊው ሳይንስ የሰው አካል እንደ ሃይድሮጅን፣ ኦክሲጅንና ካርቦን ካሉት የተለያዩ ንጥረ ነገሮች እንደተሠራ ያረጋገጠ ሲሆን እነዚህ ንጥረ ነገሮች በሙሉ የሚገኙት በምድር አፈር ውስጥ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ንጥረ ነገሮች ተሰባስበው አንድ ሕያው ፍጡር ያስገኙት እንዴት ነው?
ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት ሕይወት ያላቸው ነገሮች የመጡት በራሳቸው ነው የሚል መላ ምት አላቸው፤ እንደነሱ አነጋገር ሕይወት የጀመረው ውስብስብ ካልሆነ የሴል ዓይነት ሲሆን በሚሊዮን በሚቆጠሩ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ቀስ በቀስ ይበልጥ ውስብስብ ወደሆኑ ሕያዋን ነገሮች ተለውጧል። ይሁን እንጂ “ውስብስብ ያልሆነ” የሚለው አገላለጽ አሳሳች ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም በዓይን የማይታዩ ረቂቅ ሴሎችን ጨምሮ ሕያዋን ነገሮች በሙሉ እጅግ ውስብስብ ናቸው። የትኛውም ዓይነት ሕይወት በአጋጣሚ እንደተገኘ ወይም ሊገኝ እንደሚችል የሚያረጋግጥ ምንም ማስረጃ የለም። ከዚህ ይልቅ በሁሉም ሕያዋን ነገሮች ላይ የሚታየው ንድፍ ከእኛ እጅግ የላቀ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ለመኖሩ የማያሻማ ማስረጃ ይሰጣል።d—ሮም 1:20
በኦርኬስትራ የተቀነባበረ ልዩ ሙዚቃ እያዳመጥክ ወይም አስደናቂ የሥዕል ሥራ እያደነቅህ አሊያም ደግሞ በአንድ የቴክኖሎጂ ግኝት እየተደመምክ ነው እንበል፤ እነዚህ ነገሮች ሠሪ የላቸውም ብለህ ድርቅ ትላለህ? እንደማትል ግልጽ ነው! ነገር ግን እነዚህ ድንቅ የፈጠራ ሥራዎች በሰው አካል ንድፍ አወጣጥ ላይ ከተንጸባረቀው ውስብስብነት፣ ውበት ወይም የፈጠራ ችሎታ ጋር ሲወዳደሩ እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም። ታዲያ የሰው አካል ፈጣሪ የለውም ብለን ማሰብ የምንችለው እንዴት ነው? ከዚህም በላይ የዘፍጥረት ዘገባ በምድር ላይ ካሉት ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ በአምላክ መልክ የተሠሩት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:26) ከዚህ አንጻር በዚህች ምድር ላይ የአምላክን የመፍጠር ፍላጎት የወረሱት ሰዎች ብቻ መሆናቸው ምንም አያስደንቅም፤ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች አስደናቂ የሆኑ የሙዚቃ፣ የሥነ ጥበብና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መፈልሰፋቸው ለዚህ ማስረጃ ይሆናል። ታዲያ አምላክ በመፍጠር ችሎታው ከእኛ እጅግ የሚበልጥ መሆኑ ሊያስገርመን ይገባል?
አምላክ ከአዳም የጎድን አጥንቶች አንዱን ወስዶ ሴትን መፍጠሩስ ያን ያህል ለማመን አስቸጋሪ ነው?e እርግጥ ነው፣ አምላክ ሌላ ዘዴ ሊጠቀም ይችል ነበር፤ ሆኖም ሴትን በዚህ መንገድ መፍጠሩ ጥልቅ ትርጉም አለው። አዳምና ሔዋን እንዲጋቡና “አንድ ሥጋ” የሆኑ ያህል የተሳሰሩ እንዲሆኑ ፈልጎ ነበር። (ዘፍጥረት 2:24) አንድ ወንድና አንዲት ሴት ዘላቂና ለሁለቱም የሚጠቅም ትስስር በመፍጠር አንዳቸው የሌላው ማሟያ መሆን መቻላቸው ጥበበኛና አፍቃሪ ፈጣሪ ለመኖሩ ጠንካራ ማስረጃ አይሆንም?
ከዚህም በላይ በዘመናችን ያሉ የጄኔቲክ ተመራማሪዎች፣ የሰው ዘር በሙሉ የመጣው ከአንድ ወንድና ከአንዲት ሴት ሳይሆን እንደማይቀር አምነው ተቀብለዋል። እንዲህ ከሆነ ታዲያ የዘፍጥረት ዘገባ ሊታመን የማይችልበት ምን ምክንያት አለ?
3. ስለ እውቀት ዛፍና ስለ ሕይወት ዛፍ የሚገልጸው ታሪክ ልብ ወለድ ይመስላል።
እንደ እውነቱ ከሆነ የዘፍጥረት ዘገባ እነዚህ ዛፎች በራሳቸው አንዳች የተለየ ባሕርይ ወይም ኃይል እንዳላቸው አያስተምርም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ምሳሌያዊ ትርጉም እንዲኖራቸው አድርጎ ያበቀላቸው እውነተኛ ዛፎች ነበሩ።
ሰዎችስ አንዳንድ ጊዜ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር ያደርጉ የለም? ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ዳኛ ፍርድ ቤቱን መዳፈር ወንጀል እንደሆነ በመናገር ሊያስጠነቅቅ ይችላል። ዳኛው ይህን ሲል የፍርድ ሂደት የሚካሄድበት ሕንፃ ወይም በውስጡ ያሉት ቁሳቁሶች አክብሮት ሊሰጣቸው ይገባል ማለቱ ሳይሆን በፍርድ ቤቱ የሚወከለው የፍትሕ ሥርዓት ሊከበር እንደሚገባ መናገሩ ነው። የተለያዩ ነገሥታትም በትረ መንግሥታቸውንና ዘውዳቸውን የሉዓላዊ ሥልጣናቸው መገለጫ እንደሆኑ አድርገው ሲጠቀሙባቸው ኖረዋል።
ታዲያ እነዚያ ሁለት ዛፎች የያዙት ምሳሌያዊ ትርጉም ምንድን ነው? ይህን በተመለከተ ውስብስብ የሆኑ ብዙ መላ ምቶች ቢሰነዘሩም ትክክለኛው መልስ ቀላል ሆኖም ጥልቅ ትርጉም ያለው ነው። መልካምና ክፉን የሚያሳውቀው ዛፍ ለአምላክ ብቻ የሚገባውን መብት ይኸውም መልካም ወይም ክፉ የሚባለው ምን እንደሆነ የመወሰን መብቱን የሚወክል ነው። (ኤርምያስ 10:23) በመሆኑም ከዛፉ ላይ መስረቅ ወንጀል መሆኑ ምንም አያስደንቅም! በሌላ በኩል ደግሞ የሕይወት ዛፍ አምላክ ብቻ ሊሰጥ የሚችለውን ስጦታ ማለትም የዘላለም ሕይወትን ይወክላል።—ሮም 6:23
4. ስለሚናገር እባብ የሚገልጸው ታሪክ ተረት ተረት ይመስላል።
በተለይ ቀሪውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከግምት ካላስገባን ስለ እባቡ የሚተርከው የዘፍጥረት ዘገባ እንቆቅልሽ ሊሆንብን እንደሚችል ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ቅዱሳን መጻሕፍት ይህን ትኩረት የሚስብ ሚስጥር ደረጃ በደረጃ ይፈቱልናል።
እባቡን የሚናገር እንዲመስል ያደረገው ማን ነበር? የጥንቶቹ እስራኤላውያን እባቡ የነበረውን ሚና ለመረዳት የሚያስችል ፍንጭ የሚሰጡ አንዳንድ ነገሮችን ያውቁ ነበር። ለምሳሌ እንስሳት ሊናገሩ እንደማይችሉ ቢረዱም አንድ መንፈሳዊ አካል ግን አንድን እንስሳ የሚናገር እንዲመስል ሊያደርግ እንደሚችል ያውቁ ነበር። ሙሴ ስለ በለዓም የሚናገረውንም ዘገባ በጽሑፍ አስፍሯል፤ አምላክ የላከው አንድ መልአክ የበለዓም አህያ ልክ እንደ ሰው እንድትናገር ማድረጉን ዘገባው ይናገራል።—ዘኍልቍ 22:26-31፤ 2 ጴጥሮስ 2:15, 16
ታዲያ የአምላክ ጠላት የሆኑትን ጨምሮ ሌሎች መናፍስት ተአምር መሥራት ይችላሉ? ሙሴ አስማት የሚሠሩ የግብፅ ካህናት አምላክ የፈጸማቸውን አንዳንድ ተአምራትን አስመስለው ሲሠሩ ተመልክቷል፤ ለምሳሌ በትራቸውን በመለወጥ እባብ እንዲመስል ማድረግ ችለው ነበር። የግብፅ ካህናት እንዲህ ያሉ አስደናቂ ነገሮችን የማከናወን ኃይል ያገኙት በመንፈሳዊው ዓለም ከሚኖሩ የአምላክ ጠላቶች እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።—ዘፀአት 7:8-12
የኢዮብንም መጽሐፍ የጻፈው ሙሴ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህ መጽሐፍ የይሖዋ አገልጋዮች ለአምላካቸው ያላቸውን ታማኝነት መጠበቅ አይችሉም የሚል የሐሰት ክስ ስላቀረበውና የአምላክ ቀንደኛ ጠላት ስለሆነው ስለ ሰይጣን ብዙ ነገር ያስተምራል። (ኢዮብ 1:6-11፤ 2:4, 5) ታዲያ የጥንቶቹ እስራኤላውያን በኤደን የነበረውን እባብ የሚናገር በማስመሰል ሔዋን ለአምላክ ያላትን ታማኝነት እንድታጓድል ያሳሳታት ሰይጣን ነው ብለው አስበው ይሆን? ሳይሆን አይቀርም።
በእርግጥ ከእባቡ በስተጀርባ የነበረው ሰይጣን ነው? ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ፣ ሰይጣን “ውሸታምና የውሸት አባት” እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:44) በዚህች ምድር ላይ የተነገረውን የመጀመሪያውን ውሸት ያመነጨው ይኸው “የውሸት አባት” ነው ቢባል አትስማማም? የመጀመሪያውን ውሸት ለማወቅ እባቡ ለሔዋን የተናገራትን ነገር እንመልከት። እባቡ፣ ከተከለከለው ፍሬ መብላት ሞት እንደሚያስከትል አምላክ የተናገረውን ማስጠንቀቂያ በመቃረን “መሞት እንኳ አትሞቱም” አለ። (ዘፍጥረት 3:4) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ እባቡን መጠቀሚያ ያደረገው ሰይጣን እንደሆነ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ለሐዋርያው ዮሐንስ በሰጠው ራእይ ላይ ሰይጣን “የመጀመሪያው እባብ” ተብሎ መጠራቱ ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ ያደርግልናል።—ራእይ 1:1፤ 12:9
አንድ ኃያል መንፈሳዊ አካል እባብን የሚናገር እንዲመስል ማድረግ መቻሉ በእርግጥ ሊታመን የማይችል ነገር ነው? ከመንፈሳዊ አካላት እጅግ ያነሰ ኃይል ያላቸው ሰዎችም እንኳ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው አንድን ነገር የሚናገር እንዲመስል ማድረግ ይችላሉ።
ከሁሉ የላቀው አሳማኝ ማስረጃ
ሰዎች በዘፍጥረት ዘገባ ላይ ያላቸው ጥርጣሬ መሠረተ ቢስ ነው ቢባል አትስማማም? በሌላ በኩል ደግሞ ዘገባው እውነተኛ ታሪክ ለመሆኑ ጠንካራ ማስረጃ አለ።
ለምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ “የታመነውና እውነተኛው ምሥክር” ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 3:14) ኢየሱስ ፍጹም ሰው የነበረ እንደመሆኑ መጠን ፈጽሞ ዋሽቶም ሆነ በምንም መንገድ እውነትን አዛብቶ አያውቅም። ከዚህም በላይ በምድር ላይ ሰው ሆኖ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት እንዲያውም “ዓለም ከመመሥረቱ” አስቀድሞ ከአባቱ ከይሖዋ ጋር እንደኖረ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:5) በመሆኑም ሕይወት በምድር ላይ ሲጀምር ኢየሱስም ነበረ። ታዲያ ከሁሉ የላቀውና አስተማማኝ የሆነው ይህ ምሥክር ምን ብሎ ይሆን?
ኢየሱስ ስለ አዳምና ሔዋን የተናገረው በእውን የነበሩ ሰዎች አድርጎ ነው። ኢየሱስ ጋብቻን በተመለከተ የይሖዋ መሥፈርት አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት መሆኑን በገለጸበት ጊዜ የአዳምና የሔዋንን ጋብቻ ጠቅሷል። (ማቴዎስ 19:3-6) አዳምና ሔዋን በሕይወት ኖረው የማያውቁ ሰዎች ከሆኑ ብሎም የኖሩበት የአትክልት ስፍራ ተረት ከሆነ አንድም ኢየሱስ ተታልሏል አለዚያም ዋሽቷል ማለት ነው። ሁለቱም ቢሆን አያስኬድም! በኤደን ገነት የተፈጸመው አሳዛኝ ሁኔታ ሲከሰት ኢየሱስ በሰማይ ሆኖ እየተመለከተ ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ከሰጠው ምሥክርነት የበለጠ አሳማኝ ማስረጃ ማግኘት ይቻላል?
እውነቱን ለመናገር አንድ ሰው በዘፍጥረት ዘገባ ላይ እምነት ማጣቱ በኢየሱስ ላይ ያለውን እምነት ያዳክምበታል። በተጨማሪም ስለ ዋና ዋናዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችና እጅግ አጽናኝ ስለሆኑት ተስፋዎች መረዳት አዳጋች እንዲሆንበት ያደርገዋል። እንዲህ የምንልበትን ምክንያት እስቲ እንመልከት።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የአምላክ የግል ስም ይሖዋ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።
b ይህ ዓይነቱ አመለካከት የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ሥራ በሙሉ ፍጹም እንደሆነና ለነገሮች መበላሸት መንስኤው እሱ እንዳልሆነ ያስተምራል። (ዘዳግም 32:4, 5) ይሖዋ በምድር ላይ ያሉ ነገሮችን ፈጥሮ ሲያጠናቅቅ የሠራቸው ነገሮች በሙሉ “እጅግ መልካም” እንደሆኑ ገልጿል።—ዘፍጥረት 1:31
c ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው አምላክ ያመጣው የጥፋት ውኃ ኤደን ገነትን ደብዛዋ እስኪጠፋ ድረስ ጠራርጎ አጥፍቷታል። ሕዝቅኤል 31:18 እንደሚጠቁመው ‘የኤደን ዛፎች’ ሕዝቅኤል በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. መጽሐፉን ከመጻፉ ከረጅም ዘመናት በፊት ጠፍተዋል። ስለዚህ ከዚያ ወዲህ ባሉት ዘመናት የኤደንን የአትክልት ስፍራ ለማግኘት ፍለጋ ያካሄዱ ሁሉ ጥረታቸው ከንቱ ሆኖባቸዋል።
d በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።
e የሚገርመው፣ የጎድን አጥንት ከደረሰበት ጉዳት የማገገም ልዩ ችሎታ እንዳለው ዘመናዊው የሕክምና ሳይንስ ደርሶበታል። ከሌሎች አጥንቶች በተለየ መልኩ አያያዥ ሕብረ ሕዋሶቹ እስካልተነኩ ድረስ መልሶ ሊያድግ ይችላል።
-
-
የኤደን ገነት ጉዳይ አንተንም ይነካልመጠበቂያ ግንብ—2011 | ጥር 1
-
-
የኤደን ገነት ጉዳይ አንተንም ይነካል
አንዳንድ ምሑራን ስለ ኤደን በሚናገረው ዘገባ ላይ ካነሷቸው በጣም አስገራሚ ተቃውሞዎች መካከል አንዱ በሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ አልተጠቀሰም የሚል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የሃይማኖታዊ ጥናቶች ፕሮፌሰር የሆኑት ፖል ሞሪስ “የኤደን ገነት ታሪክ በኋላ ላይ በተጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ በቀጥታ አልተጠቀሰም” በማለት ጽፈዋል። የእሳቸው የግምገማ ውጤት በተለያዩ “ምሑራን” ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኝ ቢችልም ከእውነታው ግን በቀጥታ የሚቃረን ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች ላይ ስለ ኤደን የአትክልት ስፍራ፣ ስለ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ስለ እባቡ ይናገራል።a ይሁንና ጥቂት ምሑራን የሚሠሩት ስህተት የሃይማኖት መሪዎች ከሚፈጽሙት መጠነ ሰፊ ስህተት ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የሃይማኖት መሪዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ስለ ኤደን የአትክልት ስፍራ የሚናገረውን የዘፍጥረት ዘገባ ሲያጣጥሉ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የጥቃት ዘመቻ መክፈታቸው ነው። እንዴት?
በኤደን የተከሰተውን ነገር መረዳት ቀሪውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለመረዳት በጣም ወሳኝ ነው። ለአብነት ያህል፣ የአምላክ ቃል የተዘጋጀው ሰዎች ለሚያነሷቸው እጅግ አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ለመርዳት ታስቦ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ በአብዛኛው በኤደን የአትክልት ስፍራ ከተፈጸሙ ክስተቶች ጋር ተዛማጅነት አለው። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።
● የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው? አዳምና ሔዋን ለአምላክ ታዛዥ ቢሆኑ ኖሮ ለዘላለም ይኖሩ ነበር። የሚሞቱት ካመፁ ብቻ ነበር። ባመፁበት ዕለት ወደ ሞት ማምራት ጀመሩ። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:19) በዚህ ጊዜ ፍጽምናቸውን ያጡ ሲሆን ለዘሮቻቸውም ማውረስ የሚችሉት ኃጢአትንና አለፍጽምናን ነበር። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ” በማለት ሁኔታውን ይገልጻል።—ሮም 5:12
● አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? በኤደን ገነት ሰይጣን፣ አምላክ ለፍጡራኑ መልካም ነገርን የሚነፍግ ውሸታም እንደሆነ በመግለጽ ሰድቦታል። (ዘፍጥረት 3:3-5) በዚህ በመንገድ ሰይጣን የይሖዋ አገዛዝ ትክክለኛ ስለመሆኑ ጥያቄ አስነስቷል። አዳምና ሔዋን ከሰይጣን ጎን ለመሰለፍ በመምረጥ እነሱም የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመቀበል አሻፈረኝ ብለዋል፤ በሌላ አባባል ሰዎች መልካም ወይም ክፉ የሚባለው ምን እንደሆነ በራሳቸው መወሰን ይችላሉ ብለው የተናገሩ ያህል ነበር። ፍጹም ፍትሐዊና ጥበበኛ የሆነው ይሖዋ ለተነሳው ክርክር ተገቢ መልስ ለመስጠት ብቸኛው አማራጭ ሰዎች በፈለጉት መንገድ ራሳቸውን የሚገዙበት አጋጣሚ እንዲያገኙ ጊዜ መስጠት መሆኑን ያውቅ ነበር። ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር መምረጣቸው ያስከተለው ክፋት፣ በከፊል የሰይጣን እጅ ያለበት ሲሆን በጊዜ ሂደት አንድ ትልቅ እውነታ እንዲገለጥ አድርጓል፦ ሰው ከአምላክ ተነጥሎ ራሱን በተሳካ መንገድ ማስተዳደር አይችልም።—ኤርምያስ 10:23
● አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው? ይሖዋ በኤደን የአትክልት ስፍራ በማዘጋጀት ምድር ሊኖራት የሚገባውን ውበት በተመለከተ መሥፈርት አውጥቶ ነበር። አዳምና ሔዋን ምድርን በዘሮቻቸው እንዲሞሉና ‘እንዲገዟት’ ተልእኮ የሰጣቸው ሲሆን ይህም በመላዋ ፕላኔት ወጥነት ያለው ውበት እንዲኖርና ሁሉ ነገር ስምም እንዲሆን ያስችላል። (ዘፍጥረት 1:28) ስለዚህ አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ፍጹም የሆኑና አንድነት ያላቸው የአዳምና ሔዋን ዘሮች የሚኖሩባት ገነት እንድትሆን ነው። አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚያተኩረው አምላክ ይህን የመጀመሪያ ዓላማውን ስለሚፈጽምበት መንገድ ነው።
● ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው ለምን ነበር? በኤደን ገነት የተነሳው ዓመፅ በአዳምና በሔዋን ብሎም በዘሮቻቸው ላይ የሞት ቅጣት ያስከተለ ቢሆንም አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ ተስፋ የሚሰጥ ነገር አዘጋጀ። አምላክ ቤዛ ለማዘጋጀት ልጁን ወደ ምድር ላከ። (ማቴዎስ 20:28) ይህ ምን ማለት ነው? ኢየሱስ “ኋለኛው አዳም” ተብሎ የተጠራ ሲሆን በምድር ላይ በኖረባቸው ዓመታት ሁሉ ለይሖዋ ታዛዥ ሆኖ ፍጽምናውን በመጠበቅ አዳም ያላደረገውን ነገር ፈጽሟል። ከዚያም ሕይወቱን መሥዋዕት ወይም ቤዛ አድርጎ በነፃ በመስጠት ታማኝ የሆኑ ሰዎች በሙሉ ኃጢአታቸው ይቅር እንዲባልላቸውና ወደፊት ደግሞ አስደሳች ሕይወት እንዲመሩ ይኸውም አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት በኤደን ውስጥ የነበራቸውን ዓይነት ሕይወት እንዲያገኙ መንገድ ከፈተላቸው። (1 ቆሮንቶስ 15:22, 45፤ ዮሐንስ 3:16) በዚህም ምክንያት ኢየሱስ፣ ይሖዋ ይህችን ምድር ልክ እንደ ኤደን ገነት የማድረግ ዓላማውን ከግብ እንደሚያደርስ ዋስትና ሰጥቷል።b
የአምላክ ዓላማ ለመረዳት የሚያስቸግር ወይም የማይጨበጥ ሃይማኖታዊ ትምህርት አይደለም። ከዚህ ይልቅ እውን የሆነ ነገር ነው። በዚህች ምድር ላይ የነበረችው ኤደን ገነት በእውን የነበሩ እንስሳትና ሰዎች የሚኖሩባት እውን ቦታ እንደሆነች ሁሉ አምላክ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ የገባው ቃልም በቅርቡ የሚፈጸም እውንና የተረጋገጠ ተስፋ ነው። አንተስ ይህን ተስፋ መጨበጥ ትችል ይሆን? ይህ በአብዛኛው የተመካው በአንተ ላይ ነው። አምላክ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ሌላው ቀርቶ በተሳሳተ የሕይወት ጎዳና ላይ የሚገኙትም ጭምር ይህን የወደፊት ተስፋ እንዲያገኙ ይፈልጋል።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4
ኢየሱስ ሊሞት በሚያጣጥርበት ጊዜ መጥፎ የሕይወት ጎዳና ይከተል ከነበረ አንድ ሰው ጋር ተነጋግሮ ነበር። ሰውየው ወንጀለኛ ሲሆን የሞት ቅጣት እንደሚገባውም ያውቅ ነበር። ያም ሆኖ ከኢየሱስ መጽናኛና ተስፋ ለማግኘት ፈልጎ ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ምን ምላሽ ሰጠው? “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” አለው። (ሉቃስ 23:43) ኢየሱስ ይህ ወንጀለኛ ወደፊት ከሞት ተነስቶ ልክ እንደ ኤደን ገነት ውብ በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር መብት ሲያገኝ መመልከት የሚፈልግ ከሆነ ለአንተስ ይህንኑ አይመኝልህም? በእርግጥ ይመኝልሃል! አባቱም ቢሆን የሚመኝልህ ይህንኑ ነው! ይህንን የወደፊት ተስፋ መጨበጥ የምትፈልግ ከሆነ የኤደንን የአትክልት ስፍራ ስላዘጋጀው አምላክ ለማወቅ የተቻለህን ጥረት አድርግ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ለምሳሌ ያህል፣ ዘፍጥረት 13:10ን፤ ዘዳግም 32:8ን የ1954 ትርጉም፤ 2 ሳሙኤል 7:14ን NW፤ 1 ዜና መዋዕል 1:1ን፤ ኢሳይያስ 51:3ን፤ ሕዝቅኤል 28:13ንና 31:8, 9ን፤ ሉቃስ 3:38ን፤ ሮም 5:12-14ን፤ 1 ቆሮንቶስ 15:22, 45ን፤ 2 ቆሮንቶስ 11:3ን፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:13, 14ን፤ ይሁዳ 14ን እና ራእይ 12:9ን ተመልከት።
b ስለ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተሰኘው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 5ን ተመልከት።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተሳስር ትንቢት
“በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።”—ዘፍጥረት 3:15
ይህ ትንቢት፣ አምላክ በኤደን ገነት የተናገረው የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ነው። ለመሆኑ በትንቢቱ ላይ የተጠቀሱት ማለትም ሴቲቱና ዘሯ እንዲሁም እባቡና ዘሩ እነማን ናቸው? በመካከላቸው “ጠላትነት” የተፈጠረውስ እንዴት ነው?
እባቡ
ሰይጣን ዲያብሎስ።—ራእይ 12:9
ሴቲቱ
በሰማይ ያሉ ፍጥረታትን ያቀፈው የይሖዋ ድርጅት። (ገላትያ 4:26, 27) ኢሳይያስ “ሴቲቱ” መንፈሳዊ ሕዝብ እንደምትወልድ ትንቢት ተናግሮ ነበር።—ኢሳይያስ 54:1፤ 66:8
የእባቡ ዘር
የሰይጣንን ፈቃድ ለማድረግ የመረጡ።—ዮሐንስ 8:44
የሴቲቱ ዘር
በዋነኝነት የሚያመለክተው ከይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ወጥቶ የመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የሚገዙት የእሱ መንፈሳዊ ወንድሞችም ‘በዘሩ’ ውስጥ ተካተዋል። እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በአንድነት መንፈሳዊ ብሔር የሚያስገኙ ሲሆን ‘የአምላክ እስራኤል’ ተብለው ተጠርተዋል።—ገላትያ 3:16, 29፤ 6:16፤ ዘፍጥረት 22:18
የተረከዙ መቀጥቀጥ
በመሲሑ ላይ የሚደርስ ዘላቂ ያልሆነ ጉዳት። ሰይጣን ኢየሱስን በምድር ሳለ እንዲገደል በማድረግ ተሳክቶለት የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ከሞት ተነስቷል።
የራሱ መቀጥቀጥ
በሰይጣን ላይ የሚደርስ ዘላቂ ጉዳት። ኢየሱስ ሰይጣንን ለዘላለም ከሕልውና ውጪ ያደርገዋል። ከዚያ በፊትም እንኳ ኢየሱስ፣ ሰይጣን በኤደን የጀመረውን ክፋት ያስወግዳል።—1 ዮሐንስ 3:8፤ ራእይ 20:10
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ዋና ጭብጥ አጭርና ግልጽ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ—የያዘው መልእክት ምንድን ነው? የተሰኘውን ብሮሹር ተመልከት።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዳምና ሔዋን ኃጢአት የሚያስከትለው አስከፊ መዘዝ ደርሶባቸዋል
-