ተመልሶ በተቋቋመው “ምድር” አንድ ላይ የሚኖሩ ሰዎች
“እናንተ ግን የእግዚአብሔር ካህናት ትባላላችሁ፣ ሰዎቹም የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሩአችኋል።”—ኢሳይያስ 61:6
1, 2. (ሀ) ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች እስራኤል ውስጥ ምን ቦታ ነበራቸው? (ለ) በዘመናቸን ያሉ የ“እጅግ ብዙ ሰዎች” አባላት ምን ዝንባሌ አሳይተዋል?
እስራኤላውያን ታማኝ በነበሩበት በጥንት ዘመን በዓለም መድረክ ላይ ለይሖዋ ክብር ይመሰክሩ ነበር። (ኢሳይያስ 41:8, 9፤ 43:10) ብዙ መጻተኞች አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ይሖዋን ከምርጥ ሕዝቡ ጋር አብረው ለማገልገል መጡ። “ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል” በማለት ሩት ለኑኃሚን የተናገረችውን በተግባር ለእስራኤል ተናግረዋል። (ሩት 1:16) ወንዶቹ በመገረዝ ለሕጉ ቃል ኪዳን ራሳቸውን አስገዝተዋል። (ዘጸአት 12:43–48) አንዳንድ ሴቶች እስራኤላውያንን አግብተዋል። የኢያሪኮዋ ረዓብና ሞዓባዊቷ ሩት የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያቶች ሆነዋል። (ማቴዎስ 1:5) እነዚህ ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች የእስራኤል ጉባኤ ክፍል ነበሩ።—ዘዳግም 23:7, 8
2 በእስራኤል ውስጥ ከነበሩት ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች ጋር በሚመሳሰል መንገድ በአሁኑ ወቅት ያሉት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ቅቡዓን ቀሪዎችን “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ” ብለዋቸዋል። (ራእይ 7:9፤ ዘካርያስ 8:23) እነዚህ ሰዎች ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደሆኑ ያምናሉ፤ ከእነርሱ ጋር በጣም ተቀራርበው ከመሥራታቸውም የተነሣ ቅቡዓንና “ሌሎች በጎች” ‘በአንድ እረኛ’ ሥር ያሉ ‘አንድ መንጋ’ ናቸው። (ማቴዎስ 24:45–47፤ ዮሐንስ 10:16) ቅቡዓን ወንድሞቻቸው በሙሉ ሰማያዊ ሽልማታቸውን ሲያገኙ እጅግ ብዙ ሰዎች ምን ይሆናሉ? መፍራት የለባቸውም። በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ በሙሉ ይሖዋ ለዚህ ጊዜ ሲያዘጋጃቸው ቆይቷል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1
መንፈሳዊ “ምድር”
3. ጴጥሮስ የተነበየው “አዲስ ሰማይ” ምንድን ነው? ይህ “አዲስ ሰማይ” የተመሠረተው መቼ ነው?
3 ሐዋርያው ጴጥሮስ 144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለሚካፈሉበት ሰማያዊ መስተዳድር ተንብዮአል። “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” ብሏል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይህ “አዲስ ሰማይ” ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ በሰማያዊ መንግሥት በዙፋን ላይ በተቀመጠበት በ1914 ተቋቁሟል። ይሁን እንጂ “አዲስ ምድር” የተባለው ምንድን ነው?
4. (ሀ) በ1919 የተከሰተው ያልተጠበቀ ክንውን ምንድን ነው? (ለ) ‘በአንድ ጊዜ የተወለደው’ ሕዝብ የትኛው ሕዝብ ነው? ‘በምጥ የተወለደው ምድር’ ምንድን ነው?
4 ይሖዋ በ1919 ቅቡዓን ቀሪዎችን ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ነፃ አውጥቷቸዋል። (ራእይ 18:4) የሕዝበ ክርስትና መሪዎች ይህን አስደናቂ ክንውን ጨርሶ አልጠበቁትም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሁኔታ በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “ከቶ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? እንዲህስ ያለ ነገር ማን አይቶአል? በውኑ አገር [“ምድር” አዓት] በአንድ ቀን ታምጣለችን? ወይስ በአንድ ጊዜ ሕዝብ ይወለዳልን?” (ኢሳይያስ 66:8) የቅቡዓን ጉባኤ ነፃ የወጣ ሕዝብ ሆኖ በብሔራት ፊት በድንገት ብቅ ሲል በእርግጥም አንድ ሕዝብ ‘በአንድ ጊዜ የተወለደ’ ያህል ነበር። ታዲያ “ምድር” የተባለው ምን ነበር? በአንድ በኩል ሲታይ ከጥንት እስራኤል ምድር ጋር መንፈሳዊ ተመሳሳይነት ያለው ነገር ነው። በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ገነትን በተመለከተ የተነገሩት ትንቢቶች በመንፈሳዊ ረገድ ዘመናዊ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙበት ቦታ ማለትም አዲስ የተወለደው “ሕዝብ” እንቅስቃሴ እንዲያደርግበት የተሰጠው ክልል ነው። (ኢሳይያስ 32:16–20፤ 35:1–7፤ ከዕብራውያን 12:12–14 ጋር አወዳድር።) አንድ ክርስቲያን በአካል የትም ቦታ ቢኖርም በዚያ “ምድር” ውስጥ ነው።
5. በ1919 ወደ ሕልውና የመጣው የአዲሱ ምድር ቆርቋሪ የትኛው ነው? አብራራ።
5 ይህ ጴጥሮስ ከተነበየው “አዲስ ምድር” ጋር ምን ግንኙነት አለው? ተመልሶ በተቋቋመው “ምድር” ውስጥ በ1919 የተወለደው አዲስ “ሕዝብ” ቅቡዓንና ቅቡዓን ያልሆኑ የይሖዋ አወዳሾችን ያቀፈ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት መሆን ነበረበት። ይህ ድርጅት ከአርማጌዶን ተርፎ ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ይገባል። በዚህ መንገድ ይህ ሕዝብ የጻድቅ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ማለትም የሰይጣን ዓለም ከጠፋ በኋላ የሚኖረው የአዲሱ ምድር ቆርቋሪ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል።a በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ ቅቡዓን በቡድን ደረጃ ተመልሶ ወደ ተቋቋመው ምድር ተሰብስበው ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአሁኑ ወቅት ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉትን የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች ለመሰብሰቡ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል። (ራእይ 14:15, 16) ይህ “ምድር” በሕዝብ ብዛት የተጨናነቀ ነውን? አይደለም፣ የምድሩ ወሰን እንደ አስፈላጊነቱ ሊሰፋ ይችላል። (ኢሳይያስ 26:15) እርግጥ፣ ቅቡዓን ቀሪዎች ይህን “ምድር” ‘በፍሬ’ ማለትም ጤናማ በሆነ ኃይል ሰጪ መንፈሳዊ ምግብ ሲሞሉት፣ የሕዝብ ቁጥሩ እየጨመረ መምጣቱን ማየት በጣም ያስደስታል። (ኢሳይያስ 27:6) ይሁን እንጂ እነዚህ ሌሎች በጎች መልሶ በተቋቋመው “ምድር” ውስጥ ያላቸው ቦታ ምንድን ነው?
በዚህ “ምድር” ውስጥ በትጋት የሚሠሩ መጻተኞች
6. መጻተኞች በአምላክ ሕዝቦች “ምድር” ትጋት የተሞላበት ተሳትፎ የሚያደርጉት እንዴት ነው?
6 በእስራኤል ምድር የነበሩ ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች ራሳቸውን ለሙሴ ሕግ ያስገዙ እንደነበር ሁሉ በአሁኑ ወቅት ተመልሶ በተቋቋመው “ምድር” ውስጥ ያሉት እጅግ ብዙ ሰዎችም የይሖዋን ትእዛዛት ያከብራሉ። ከቅቡዓን ወንድሞቻቸው ስለተማሩ ሙሉ በሙሉ ከሐሰት ሃይማኖት ይርቃሉ፤ በተጨማሪም ደምን እንደ ቅዱስ ነገር አድርገው ይመለከቱታል። (ሥራ 15:19, 20፤ ገላትያ 5:19, 20፤ ቆላስይስ 3:5) ይሖዋን በፍጹም ልባቸው፣ አሳባቸው፣ ነፍሳቸውና ኃይላቸው ይወዳሉ፤ በተጨማሪም ሰዎችን እንደ ራሳቸው አድርገው ይወዳሉ። (ማቴዎስ 22:37፤ ያዕቆብ 2:8) በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ሲገነባ ረድተዋል፤ እውነተኛ አምልኮ ተመልሶ ሲቋቋምም ድጋፍ ሰጥተዋል። (1 ዜና መዋዕል 22:2፤ 2 ዜና መዋዕል 15:8–14፤ 30:25) በአሁኑ ወቅት ያሉት እጅግ ብዙ ሰዎችም በግንባታ ፕሮጄክቶች ይሳተፋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ጉባኤዎችንና ወረዳዎችን በማቋቋሙ ሥራ ከመርዳታቸውም በላይ እንደ መንግሥት አዳራሾች፣ የትልልቅ ስብሰባ አዳራሾችና የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃ ባሉት የግንባታ ፕሮጄክቶች ድጋፍ ይሰጣሉ።
7. ከምርኮ በኋላ በኢየሩሳሌም ውስጥ የቤተ መቅደስ አገልግሎቶችን የሚያከናውኑ በቂ ሌዋውያን ሲታጡ ምን ተደረገ?
7 እስራኤላውያን በ537 ከዘአበ ከባቢሎን ምርኮ በተመለሱበት ወቅት እንደገና በተገነባው ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚከናወኑ አገልግሎቶችን ማደራጀት ጀመሩ። ሆኖም ከምርኮ የተመለሱት ሌዋውያን ብዛት አልነበራቸውም። ስለዚህ ቀደም ሲል የሌዋውያን ረዳቶች የነበሩት የተገረዙ መጻተኞች ማለትም ናታኒም ቤተ መቅደስ ውስጥ ተጨማሪ መብቶች ተሰጧቸው። ሆኖም የአሮን ዘር ከሆኑት ቅቡዓን ካህናት ጋር የሚተካከል መብት አላገኙም።b—ዕዝራ 7:24፤ 8:15–20፤ ነህምያ 3:22–26
8, 9. ሌሎች በጎች በመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ ረገድ ያላቸውን ተሳትፎ ከፍ ያደረጉት እንዴት ነው?
8 በአሁኑ ወቅት ያሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይህንን ምሳሌ እየተከተሉ ነው። ‘የፍጻሜው ዘመን’ እየገፋ በሄደ መጠን በአምላክ ሕዝቦች “ምድር” ውስጥ ያሉት የቅቡዓን ቀሪዎች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል። (ዳንኤል 12:9፤ ራእይ 12:17) በዚህ ምክንያት በአሁኑ ወቅት እጅግ ብዙ ሰዎች አብዛኛውን ‘ቅዱስ አገልግሎት’ የማቅረብ ተግባር ያከናውናሉ። (ራእይ 7:15) የቅቡዓን ወንድሞቻቸውን አመራር በመከተል “ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ” ያቀርባሉ። ‘እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን እንደሚያስደስተው’ አውቀው ‘መልካም ማድረግንና ለሌሎች ማካፈልን’ አይረሱም።—ዕብራውያን 13:15, 16
9 ከዚህም በላይ እጅግ ብዙ ሰዎች በየዓመቱ በብዙ መቶ ሺህ እየጨመሩ በመጡ ቁጥር ተጨማሪ የበላይ ተመልካቾች ያስፈልጋሉ። በአንድ ወቅት ይህን ሥራ የያዙት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ነበሩ። አሁን አብዛኞቹን የጉባኤዎች፣ የወረዳዎች፣ የአውራጃዎችና የቅርንጫፎች የበላይ ጥበቃ ለሌሎች በጎች መስጠቱ አስፈላጊ ሆኗል። በ1992 ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ የአስተዳደር አካል ኮሚቴዎች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች የመገኘትና በውይይቶቹ የመካፈል መብት አግኝተዋል፤ ሆኖም የአስተዳደር አካል በሚያደርጋቸው የመጨረሻ ውሳኔዎች አይሳተፉም። ይሁን እንጂ ሌሎች በጎች እንደ እነርሱ ክርስቲያኖች ለሆኑት ቅቡዓን ታማኝ ይሆናሉ፤ የይሖዋ ታማኝና ልባም ባሪያ እንደ መሆናቸው መጠንም እነሱን ማገልገሉን እንደ መብት አድርገው ይቆጥሩታል።—ማቴዎስ 25:34–40
“እንደ አለቃ”
10, 11. አንዳንድ ፍልስጤማውያን እንዳደረጉት ሁሉ ቀደም ሲል የአምላክ ሕዝቦች ጠላቶች የነበሩ አንዳንድ ሰዎች አስተሳሰባቸውን የለወጡት እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስከተለ?
10 ታማኝና ልባም ባሪያ ሌሎች በጎችን በኃላፊነት ቦታዎች እየተጠቀመባቸው ያለው መንገድ በዘካርያስ 9:6, 7 ላይ ተተንብዮአል። እዚህ ጥቅስ ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “የፍልስጥኤማውያንንም ትዕቢት አጠፋለሁ። ደሙንም ከአፉ ውስጥ ርኩሱንም ነገር ከጥርሱ መካከል አስወግዳለሁ፤ እርሱም ደግሞ ለአምላካችን ቅሬታ ይሆናል፤ በይሁዳም እንደ አለቃ ይሆናል፣ አቃሮንም እንደ ኢያቡሳዊ ይሆናል።”c በአሁኑ ወቅት እንዳለው የሰይጣን ዓለም ሁሉ ፍልስጤማውያን የይሖዋ ሕዝቦች ዋነኛ ጠላቶች ነበሩ። (1 ዮሐንስ 5:19) ፍልስጤማውያን በመጨረሻ በሕዝብ ደረጃ እንደጠፉ ሁሉ ይህ ዓለምም ከሃይማኖታዊ፣ ከፖለቲካዊና ከንግድ መዋቅሮቹ ጋር በቅርቡ ጥፋት የሚያስከትለው የይሖዋ ቁጣ ይወርድበታል።—ራእይ 18:21፤ 19:19–21
11 ሆኖም ዘካርያስ በተናገራቸው ቃላት መሠረት አንዳንድ ፍልስጤማውያን አስተሳሰባቸውን ለውጠዋል፤ ይህም በዘመናችን አንዳንድ ዓለማውያን የይሖዋ ጠላት ሆነው እንደማይቀሩ ጥላ ይሆናል። ከአስጸያፊ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችና ከረከሱ መሥዋዕቶች ጋር ሃይማኖታዊ ምንዝር መፈጸማቸውን እርግፍ አድርገው ይተዉና በይሖዋ ዓይን ንጹሕ ይሆናሉ። በዘመናችን እንደነዚህ ያሉ አስተሳሰባቸውን የለወጡ “ፍልስጤማውያን” በእጅግ ብዙ ሰዎች መካከል ይገኛሉ።
12. በዘመናችን “አቃርናውያን” “እንደ ኢያቡሳውያን” የሆኑት በምን መንገድ ነው?
12 በትንቢቱ መሠረት የፍልስጤማውያን ዋና ከተማ የነበረው አቃሮን “እንደ ኢያቡሳዊ ይሆናል።” ኢያቡሳውያንም በአንድ ወቅት የእስራኤል ጠላቶች ነበሩ። ዳዊት ድል አድርጎ እስኪይዛት ድረስ ኢየሩሳሌም በእነሱ እጅ ነበረች። ሆኖም ከእስራኤል ጋር ከተደረገው ጦርነት የተረፉ አንዳንድ ኢያቡሳውያን ወደ አይሁድ እምነት እንደተለወጡ ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል። በእስራኤል ምድር እንደ ባሪያዎች ሆነው ከማገልገላቸውም በላይ ቤተ መቅደሱን የመገንባት መብት አግኝተዋል። (2 ሳሙኤል 5:4–9፤ 2 ዜና መዋዕል 8:1–18) በአሁኑ ወቅት ይሖዋን ወደ ማምለክ ዘወር ያሉት “አቃሮናውያን” ጭምር በታማኝና ልባም ባሪያ የበላይ ጥበቃ ሥር በዚህ “ምድር” ውስጥ የማገልገል መብት አላቸው።
13. በጥንቱ ዓለም የነበሩት አለቆች ምን ቦታ ነበራቸው?
13 ዘካርያስ ፍልስጤማዊው በይሁዳ እንደ አለቃ ይሆናል ብሏል። “አለቃ” የሚል ትርጉም የተሰጠው አሉፍ የተባለው የዕብራይስጥ ቃል “የሺህ አለቃ” (ወይም ኪሊአርክ) ማለት ነው። ይህ ከፍተኛ ሥልጣን ነበር። የጥንቱ የኤዶም ሕዝብ 13 አለቆች ብቻ የነበሩት ይመስላል። (ዘፍጥረት 36:15–19) ብዙውን ጊዜ “አለቃ” የተባለው ቃል ለእስራኤል ባይሠራበትም “የሺህ ራስ (አለቃ)” የተባለው ሐረግ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። ሙሴ የእስራኤል ሕዝብ ወኪሎችን ሲያዝ ‘የእስራኤል አእላፍ ታላላቅ አለቆች’ በማለት ጠርቷቸዋል።d እነዚህ 12ቱ ከሙሴ በታች ሆነው ይሠሩ እንደ ነበር ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል። (ዘኁልቁ 1:4–16) በተመሳሳይም በሠራዊቱ ሥርዓት ሻለቆች ከጄኔራሉ ወይም ከንጉሡ በቀር የበላይ አልነበራቸውም።—2 ሳሙኤል 18:1, 2፤ 2 ዜና መዋዕል 25:5
14. በዘመናችን ‘ፍልስጤማዊው’ እንደ አለቃ የሆነው በምን መንገድ ነው?
14 ዘካርያስ ንስሐ የገባው ፍልስጤማዊ በእስራኤል ውስጥ በቀጥታ አለቃ ይሆናል ማለቱ አልነበረም። ሥጋዊ እስራኤላዊ ስላልሆነ ይህ ተገቢ ሊሆን አይችልም። ይሁን እንጂ አለቃ እንደሚይዘው ያለ ቦታ ስለሚኖረው እንደ አለቃ ይሆናል። ይህ ሁኔታም ተፈጽሟል። የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቀሪዎች ቁጥር እየቀነሰ ሲሄድና በሕይወት ያሉት ዕድሜያቸው እየገፋ ሲመጣ በደንብ የሠለጠኑ ሌሎች በጎች በሚፈለጉበት ቦታ በመርዳት ላይ ናቸው። የቅቡዓን ወንድሞቻቸውን ቦታ ለመያዝ አይፈልጉም። ይሁን እንጂ የአምላክ ድርጅት በተደራጀ መልኩ ወደፊት መራመዱን እንዲቀጥል ታማኝና ልባም ባሪያ በዚህ “ምድር” ውስጥ እንደ አስፈላጊነቱ ሥልጣን ይሰጣቸዋል። ይህ ዓይነቱ የእድገት ሂደት በሌላ ትንቢት ላይም ተገልጿል።
ካህናትና አራሾች
15. (ሀ) በኢሳይያስ 61:5, 6 ላይ ባለው ትንቢት ፍጻሜ መሠረት “የእግዚአብሔር ካህናት” ሆነው የሚያገለግሉት እነማን ናቸው? በተሟላ መንገድ በዚህ ሥልጣን ቦታ የሚያገለግሉት መቼ ነው? (ለ) የእስራኤልን የእርሻ ሥራ የሚያከናውኑት “መጻተኞች” እነማን ናቸው? ይህ ሥራ በመንፈሳዊ ረገድ ምን ነገሮችን ያካትታል?
15 ኢሳይያስ 61:5, 6 እንዲህ ይነበባል፦ “መጻተኞችም ቆመው በጎቻችሁን ያሰማራሉ፣ ሌሎች ወገኖችም አራሾችና ወይን ጠባቂዎች ይሆኑላችኋል። እናንት ግን የእግዚአብሔር ካህናት ትባላላችሁ፣ ሰዎቹም የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሩአችኋል፤ የአሕዛብን ሀብት ትበላላችሁ፣ በክብራቸውም ትመካላችሁ።” በአሁኑ ወቅት “የእግዚአብሔር ካህናት” የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው። በመጨረሻ በሰማያዊ መንግሥት ውስጥ በተሟላ መንገድ “የእግዚአብሔር ካህናት . . . የአምላካችን አገልጋዮች” ሆነው ያገለግላሉ። (ራእይ 4:9–11) የእርሻውን ሥራ በኃላፊነት የያዙት “መጻተኞች” እነማን ናቸው? እነዚህ መጻተኞች በአምላክ እስራኤል “ምድር” ውስጥ የሚኖሩት ሌሎች በጎች ናቸው። ለእነሱ የተሰጣቸው የእረኝነት፣ የእርሻና የወይን ጥበቃ ኃላፊነት ምንድን ነው? እነዚህ ሥራዎች ሰዎችን በመንፈሳዊ ከመርዳት፣ ከመንከባከብና ከመሰብሰብ ጋር ግንኙነት አላቸው።—ኢሳይያስ 5:7፤ ማቴዎስ 9:37, 38፤ 1 ቆሮንቶስ 3:9፤ 1 ጴጥሮስ 5:2
16. ከጊዜ በኋላ በአምላክ ሕዝቦች “ምድር” ያለውን ሥራ ሙሉ በሙሉ የሚረከቡት እነማን ናቸው?
16 በአሁኑ ወቅት በምድር ላይ በመንፈሳዊ እረኝነት፣ የግብርና ሥራና በወይን ተክል አልሚነት ሥራ በመካፈል ላይ ያሉ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መንፈሳዊ እስራኤላውያን ይገኛሉ። በመጨረሻ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ባጠቃላይ ከክርስቶስ ጋር ሲሆኑ ይህ ሥራ በሙሉ ለሌሎች በጎች ይሰጣል። ሌላው ቀርቶ የዚህን “ምድር” ሰብዓዊ የበላይ ጥበቃ እንኳ የሕዝቅኤል መጽሐፍ አለቆች ብሎ የሚጠራቸው ብቃት ያላቸው ሌሎች በጎች ይረከቡታል።—ሕዝቅኤል ምዕራፍ 45 እና 46e
ይህ “ምድር” ከጥፋት ይተርፋል
17. ይሖዋ በእነዚህ መጨረሻ ዘመናት በሙሉ ምን ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቷል?
17 አዎን፣ እጅግ ብዙ ሰዎች መፍራት የለባቸውም! ይሖዋ በቂ ዝግጅቶች አድርጎላቸዋል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በምድር ላይ ከተደረጉት ክንውኖች ሁሉ የላቀው የቅቡዓን መሰብሰብና መታተም ነው። (ራእይ 7:3) ሆኖም ይህ በሚከናወንበት ወቅት ይሖዋ ተመልሶ በተቋቋመው መንፈሳዊ ምድር ውስጥ ከእነርሱ ጋር እንዲተባበሩ ሌሎች በጎችን አምጥቷቸዋል። እዚህ ምድር ውስጥ በመንፈሳዊ ተመግበዋል፤ በተጨማሪም በክርስቲያናዊ አኗኗር ረገድ ሥልጠና አግኝተዋል። ከዚህም በላይ የበላይ ጥበቃን ጨምሮ ቅዱስ አገልግሎት እንዴት እንደሚያቀርቡ በቂ ትምህርት አግኝተዋል። ይህን ሥልጠና በማግኘታቸውም ይሖዋንና ቅቡዓን ወንድሞቻቸውን ያመሰግናሉ።
18. ሌሎች በጎች በመንፈሳዊ እስራኤል “ምድር” በታማኝነት የሚቆዩት በምን ሁኔታዎች ሥር ነው?
18 የማጎጉ ጎግ በአምላክ ሕዝቦች ላይ የመጨረሻውን ጥቃት ሲሰነዝር ሌሎች በጎች ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር ‘ቅጥር በሌላቸው መንደሮች’ ውስጥ ሆነው ፍጹም አቋማቸውን ይጠብቃሉ። ሌሎች በጎች በብሔራት ላይ ከሚደርሰው ጥፋት ተርፈው ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ከገቡም በኋላ ቢሆን በዚህ “ምድር” ውስጥ ይሆናሉ። (ሕዝቅኤል 38:11፤ 39:12, 13፤ ዳንኤል 12:1፤ ራእይ 7:9, 14) በታማኝነታቸው ከጸኑ ከዚህ አስደሳች ቦታ በጭራሽ አይወጡም።—ኢሳይያስ 11:9
19, 20. (ሀ) የዚህ “ምድር” ነዋሪዎች በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚያገኙት ታላቅ የበላይ ጥበቃ ምንድን ነው? (ለ) ወደፊት በታላቅ ጉጉት የምንጠብቀው ምንድን ነው?
19 የጥንቷ እስራኤል በሰብዓዊ ነገሥታት ትመራ ነበር፤ ሌዋውያን ካህናትም ነበሯት። ክርስቲያኖች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ከዚህ የላቀ የበላይ ጥበቃ ይኖራቸዋል፦ ይኸውም ሉዓላዊ ጌታ በሆነው በይሖዋ ሥር ሆነው ለታላቁ ሊቀ ካህንና ንጉሥ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም ለ144,000ዎቹ ተባባሪ ነገሥታትና ካህናት ይገዛሉ፤ ከእነዚህም አንዳንዶቹ በምድር ላይ ሳሉ ክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው እንደነበሩ የሚያውቋቸው ናቸው። (ራእይ 21:1) ታማኝ የሆኑ የዚህ መንፈሳዊ ምድር ነዋሪዎች በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አማካኝነት በሚዘንቡት ፈዋሽ በረከቶች እየተደሰቱ ቃል በቃል ወደ ገነትነት በምትለወጠው ምድር ውስጥ ይኖራሉ።—ኢሳይያስ 32:1፤ ራእይ 21:2፤ 22:1, 2
20 የይሖዋ ታላቅ ሰማያዊ ሠረገላ አንዳች የሚበግረው ኃይል ሳይኖር ወደ ግቡ ሲያመራ ሁላችንም የተሰጠንን ድርሻ ለመፈጸም በጉጉት እንጠባበቃለን። (ሕዝቅኤል 1:1–28) መጨረሻ ላይ እነዚህ ዓላማዎች ሲፈጸሙ ይሖዋ በድል አድራጊነት ያገኘው ቅድስና እንዴት ባለ ደስታ እንደሚከበር አስብ! በዚያን ጊዜ ፍጥረታት በሙሉ በራእይ 5:13 ላይ የተመዘገበውን የሚከተለውን የሚመስጥ የውዳሴ መዝሙር ይዘምራሉ፦ “በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፣ ለበጉ ይሁን”! ቦታችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ ከዚህ ውዳሴ ከሚያቀርብ ታላቅ የመዘምራን ሠራዊት ጋር ለመተባበር እዚያ ለመገኘት አንጓጓምን?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በ1953 በኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” የተባለ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገጽ 322–3 ተመልከት።
b ስለዚህ ጉዳይ የተሟላ ማብራሪያ ለማግኘት በሚያዝያ 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ “‘የተሰጡ ሰዎች’ የይሖዋ ዝግጅት ክፍል ናቸው” በሚል ርዕስ የወጣውን ትምህርት ተመልከት።
c ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በ1972 የታተመውን በቲኦክራሲያዊ አገዛዝ ለሰው ልጆች የተመለሰችላቸው ገነት! የተባለ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገጽ 264–9 ተመልከት።
d በዕብራይስጥ ራሼህ አልፍ ይስራኤል የተባለው ቃል በሴፕቱጀንት ትርጉም ኪሊ አርኪኦ እስራኤል “ኪላአርክስ ኦቭ እስራኤል” ተብሎ ተተርጉሟል።
e ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በ1971 የታተመውን “አሕዛብ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ”—እንዴት? የተባለ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገጽ 401–7 ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በ1919 እንደገና የተቋቋመው “ምድር” ምንድን ነው? ይህ “ምድር” በነዋሪዎች የተሞላው እንዴት ነው?
◻ ሌሎች በጎች እንደገና በተቋቋመው የአምላክ ሕዝቦች “ምድር” ተጨማሪ ኃላፊነቶች የተሰጧቸው እንዴት ነው?
◻ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ‘እንደ እያቡሳውያን’ የሆኑት በምን መንገድ ነው? የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ‘በይሁዳ ውስጥ እንደ አለቃ’ የሆኑትስ በምን መንገድ ነው?
◻ ታማኝ የሆኑ ሌሎች በጎች በዚህ “ምድር” የሚቆዩት ለምን ያህል ጊዜ ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዘመናዊ ፍልስጤማዊ ‘በይሁዳ እንደ አለቃ ይሆናል’
[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ቅቡዓንና ሌሎች በጎች በመንፈሳዊ ምድር ውስጥ አንድ ላይ ሆነው ያገለግላሉ