የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 7/1 ገጽ 26-28
  • ብቸኛ ብሆንም ፈጽሞ አልተተውኩም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ብቸኛ ብሆንም ፈጽሞ አልተተውኩም
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ መተዋወቅ
  • አሁን የባሰ ብቸኛ ሆንኩ
  • ከድርጅቱ ጋር መገናኘት
  • የአውራጃ ስብሰባ፣ በመጨረሻም ጥምቀት
  • ወደ ማውንት ጋምቢየር መመለስ
  • አዲስ የአገልግሎት ምድብ
  • በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቀጠል
  • ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ የዕድሜ ልክ በረከት ያስገኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሀብት አገኘሁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 7/1 ገጽ 26-28

ብቸኛ ብሆንም ፈጽሞ አልተተውኩም

አዳ ሌዊስ እንደተናገረችው

ሁልጊዜ ብቻዬን መሆን እወድ ነበር። በተጨማሪም ሌሎች ሰዎች አንዳንድ ጊዜ እንደ ግትርነት ቢያዩትም እኔ ግን አንዴ ላደርገው ያሰብኩትን ከማድረግ ፍንክች የማልል ሰው ነበርኩ። ፊት ለፊት መናገር ይቀናኝ ነበር። ይህም ባሕርይ ለብዙ ዓመታት ችግር ፈጥሮብኛል።

ይሁን እንጂ በሚነቀፍ ባሕርዬ ምክንያት ይሖዋ ስላልተወኝ አመስጋኝ ነኝ። የእርሱን ቃል በማጥናት ባሕርዬን ለማሻሻልና ለ60 ዓመታት ያህል በመንግሥቱ አገልግሎት ተካፋይ ለመሆን ችያለሁ። ከልጅነቴ ጀምሮ ፈረስ እወድ ስለነበር የግትርነት ባሕርዬን ለመቆጣጠር አምላክ የሚሰጠኝ እርዳታ አንድን ፈረስ በልጓም አማካኝነት እንዴት መግታት እንደሚቻል ያስታውሰኝ ነበር።

በደቡብ አውስትራሊያ ማውንት ጋምቢየር በሚገኝበት ውብ ሰማያዊ ሐይቅ አቅራቢያ በ1908 ተወለድኩ። ወላጆቼ የከብት እርባታ ነበራቸው። ከስምንት ልጆች መካከል ከሴቶቹ እኔ ታላቅ ነበርኩ። አባታችን የሞተው ሁላችንም ገና ትንንሽ ልጆች እያለን ነበር። ሁለቱ ታላቅ ወንድሞቼ ለቤተሰብ የሚሆን ገቢ ለማምጣት ከቤት ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደው መሥራት ስለነበረባቸው የእርሻውን ሥራ ለማካሄድ አብዛኛው ኃላፊነት በእኔ ላይ ተጣለ። የግብርና ኑሮ ጊዜና ጉልበት የሚጨርስ አስቸጋሪ ሥራ ነው።

ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ መተዋወቅ

ቤተሰባችን በፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ይከታተል ስለነበር እኛም አዘውትረን ቤተ ክርስቲያን የመሄድ ልማድ ነበረን። እኔም የሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪ ሆንኩ። በመንፈሳዊም ሆነ በሥነ ምግባር ትክክል ነው ብዬ የማምነውን ነገር ለልጆች በማስተማር ረገድ ያለብኝን ኃላፊነት በቁም ነገር ያዝኩ።

በ1931 ወንድ አያቴ ሲሞት ከነበሩት ንብረቶች መካከል በዚያን ጊዜ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት የነበረው ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ የጻፋቸው በርካታ መጽሐፎች ይገኙበታል። የአምላክ በገና እና ፍጥረት የተባሉትን የእንግሊዝኛ መጽሐፎች ማንበብ ጀመርኩ። ብዙ ባነበብኩ መጠን ብዙ አምንባቸው የነበሩ ነገሮችና ልጆቹን ሳስተምራቸው የቆየሁት ትምህርቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እንደሌላቸው በማወቄ በጣም ተገረምኩ።

ነፍስ እንደምትሞት፣ ሰዎች ሲሞቱ አብዛኞቹ ወደ ሰማይ እንደማይሄዱ፣ ክፉ ሰዎች ለዘላለም የሚሠቃዩበት የሲኦል እሳት እንደሌለ ስገነዘብ በጣም ደነገጥኩ። በየሳምንቱ እሁድ ሰንበትን ማክበር ከአንድ ክርስቲያን የሚፈለግ ብቃት እንዳልሆነ ሳውቅም እንደገና ግራ ተጋባሁ። ስለዚህ አንድ ከባድ ውሳኔ ማድረግ ነበረብኝ፦ በወግ ላይ ከተመሠረተው የሕዝበ ክርስትና ትምህርት ጋር መጣበቅ አለዚያም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር። ወዲያው ከፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበረኝን ጠቅላላ ቁርኝት እርግፍ አድርጌ ለመተው ወሰንኩ።

አሁን የባሰ ብቸኛ ሆንኩ

ቤተ ክርስቲያኑን ትቼ ለመሄድ ያለኝን ሐሳብና ከአሁን በኋላ በሰንበት ትምህርት ቤት እንደማላስተምር በምገልጽበት ጊዜ ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼና ቀድሞ በቤተ ክርስቲያን የተዋወቅኋቸው ሰዎች አልተደሰቱም። የጀጅ ራዘርፎርድ ተከታዮች ተብለው ከሚጠሩት ሰዎች ጋር የበለጠ እየተቀራረብኩ መሄዴን ሲያውቁ ስለ እኔ ይወራ የነበረው ሐሜት የበለጠ እንዲቀጣጠል ምክንያት ሆነ። ቤተሰቦቼና የቀድሞ ጓደኞቼ ሙሉ በሙሉ ባያገሉኝም እንኳን ለእኔ የነበራቸው አመለካከት ቀዝቅዞ ነበር ብዬ ለመናገር እችላለሁ።

አነባቸው በነበሩት መጽሐፎች ላይ የሰፈሩትን ጥቅሶች የበለጠ ባጠናኋቸውና ባገናዘብኳቸው መጠን ለሕዝብ የመስበኩ አስፈላጊነት የበለጠ እየታየኝ መጣ። የይሖዋ ምሥክሮች ለሕዝብ ምሥክርነት ከሚሰጡበት መንገድ አንዱ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መስበክ መሆኑን ተገነዘብኩ። ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ በእኛ አውራጃ የሚኖር ማንም የይሖዋ ምሥክር አልነበረም። በዚህ የተነሳ የአምላክ መንግሥት ምሥራች እንዴት እንደሚሰበክ ያሳየኝ ወይም እንድሰብክ ያበረታታኝ ሰው አልነበረም። (ማቴዎስ 24:14) ብቸኝነት በጣም ተሰማኝ።

ይሁን እንጂ ሌሎች ሰዎች ሊሰበክላቸው እንደሚገባ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ያለማቋረጥ በጆሮዬ ያቃጭል ስለነበረ በዚያም ሆነ በዚህ መስበክ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። ከብዙ ጸሎት በኋላ ከጥናቴ ያገኘኋቸውን ነገሮች በአካባቢዬ ለሚገኙ ሰዎች መንገርና እነዚህንም ነገሮች ከራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ በማሳየት ጎረቤቶቼን ለማነጋገር ወሰንኩ። በመጀመሪያ የሄድኩት የቀድሞ የሰንበት ትምህርት ቤት ተቆጣጣሪዬ ቤት ነበር። ቤተ ክርስቲያኑን ለቅቄ በመውጣቴ ምክንያት ያሳየው ቀዝቃዛ ምላሽና የሰነዘረው አፍራሽ አስተያየት ገና ከመጀመሪያው ተስፋ እንድቆርጥ የሚያደርግ ነበር። ይሁን እንጂ ሌላ ቤት ለማንኳኳት የእርሱን ቤት ትቼ ስሄድ ቅንዓትና ያልተለመደ ውስጣዊ ጥንካሬ ተሰማኝ።

እርግጥ ይህን ያህል ግልጽ ተቃውሞ አልነበረም። ይሁን እንጂ የቀድሞ የቤተ ክርስቲያን ጓደኞቼን ሄጄ ሳነጋግራቸው ሁሉም ግዴለሾች መሆናቸው በጣም ያስደንቀኝ ነበር። ያስገረመኝና ያሳዘነኝ ግን ከታላቅ ወንድሜ የደረሰብኝ ጠንካራ ተቃውሞ ነበር። ይህም “ወላጆችም ስንኳ ወንድሞችም ዘመዶችም ወዳጆችም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፣ . . . በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት አስታወሰኝ።—ሉቃስ 21:16, 17

ገና በልጅነቴ ፈረስ የመጋለብ ልምድ ስለነበረኝ የሰዎችን ቤት በፍጥነት ለማዳረስ በፈረስ መጓዝ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። ይህም በአካባቢው ወደሚገኙ ራቅ ያሉ የገጠር ክልሎች እንድሄድ አስችሎኛል። ይሁን እንጂ አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ፈረሴ አዳለጠውና ወደቀ። እኔም ጭንቅላቴ ላይ ከባድ መፈንከት ደረሰብኝ። እንዲያውም አልድን ይሆናል የሚል ፍርሃት ነበረኝ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንገዱ ርጥብ ወይም የሚያዳልጥ ከሆነ ፈረስ ከመጋለብ ይልቅ በፈረስ በሚጎተት ጋሪ እጓዝ ነበር።a

ከድርጅቱ ጋር መገናኘት

አደጋ ከደረሰብኝ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች አሁን አቅኚዎች የሚባሉት ቡድን ማውንት ጋምቢየርን ጎበኘ። በዚህ የተነሳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመሰል አማኞች ጋር ፊት ለፊት ለመነጋገር ቻልኩ። ከመሄዳቸው በፊት የበለጠ በተደራጀ መንገድ ለሕዝብ በሚሰጠው ስብከት እንዴት መካፈል እንደምችል ለመጠየቅ ለጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ እንድጽፍ አበረታቱኝ።

ለማኅበር ደብዳቤ ከጻፍኩ በኋላ በየበሩ ራሴን ለማስተዋወቅ እንዲረዱኝ መጻሕፍት፣ ቡክሌቶችና የመመሥከሪያ ካርዶች ደረሱኝ። ከቅርንጫፍ ቢሮው ጋር በደብዳቤ አማካኝነት መገናኘቴ ከመንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር በትንሹም ቢሆን የተቀራረብኩ ሆኖ ተሰማኝ። ይሁን እንጂ የአቅኚዎቹ ቡድን ወደሚቀጥለው ከተማ ሲሄዱ ከበፊቱ የባሰ የብቸኝነት ስሜት ተሰማኝ።

በፈረስ በሚጎተተው ጋሪ እየተረዳሁ በከተማው ውስጥ በየቀኑ በማደርገው ምሥክርነት በአውራጃው በደንብ ታወቅሁ። በተመሳሳይም በእርሻ ቦታ ያለውን የዕለት ሥራዬንም በሚገባ አከናውን ነበር። በዚህ ጊዜ ቤተሰቦቼ ሙሉ በሙሉ ተቃውሞአቸውን ትተው ነበር። በዚህ መንገድ ገለልተኛ በሆነ አካባቢ ያልተጠመቅሁ የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪ ሆኜ ለአራት ዓመታት አገልግያለሁ።

የአውራጃ ስብሰባ፣ በመጨረሻም ጥምቀት

በሚያዝያ 1938 ወንድም ራዘርፎርድ አውስትራሊያን ጎበኘ። ቀሳውስት ባስነሱት ኃይለኛ ተቃውሞ ምክንያት በሲድኒ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ሊደረግ የታቀደው የስብሰባ ውል ተሰረዘ። ይሁን እንጂ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ የስፖርት ሜዳውን ለመጠቀም የሚያስችል ፈቃድ ተገኘ። በትልቁ የስፖርት ሜዳ ላይ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለመገኘት በመቻላቸው አስቀድሞ የተያዘው እቅድ መሰናከሉ የተሻለ ጥቅም እንዳስገኘ ጥርጥር የለውም። 12,000 የሚያህሉ ሰዎች ሲገኙ ብዙዎቹ በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ያነሳሳቸው በስብሰባችን ላይ በቀሳውስት ቆስቋሽነት የተነሳው ተቃውሞ ነበር።

ከወንድም ራዘርፎርድ ጉብኝት ጋር በተያያዘ መንገድ በሲድኒ አቅራቢያ ባለ አንድ መንደር የተወሰኑ ቀናት የፈጀ ስብሰባ ተደርጎ ነበር። በመጨረሻም ለይሖዋ ያደረኩትን ውሳኔ በውኃ ጥምቀት ያሳየሁት በዚህ ጊዜ ነበር። በጣም ሰፊ ከሆነው የአውስትራሊያ አህጉር ከመጡ በብዙ መቶ ከሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች ጋር አብሬ በመሰብሰቤ ያገኘሁትን ደስታ ልትገምቱ ትችላላችሁ!

ወደ ማውንት ጋምቢየር መመለስ

ወደምኖርበት ከተማ ስመለስ ኃይለኛ የብቸኝነት ስሜት ቢሰማኝም በመንግሥቱ ሥራ የምችለውን ያህል ለመሥራት ከበፊቱ የበለጠ ቆርጬ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከአግኒው ቤተሰብ ማለትም ከኽዩ እና ከባለቤቱ እንዲሁም ከአራት ልጆቻቸው ጋር ተዋወቅሁ። እነርሱም ከማውንት ጋምቢየር 50 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ሚሊሰንት በሚባል ከተማ ይኖሩ ነበር። ከእነርሱ ጋር ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ 50 ኪሎ ሜትር በፈረስ በሚጎተት ጋሪ እጓዝ ነበር። እውነትን በደስታ ሲቀበሉ የነበረኝ የብቸኝነት ስሜት ለቀቀኝ።

በአጭር ጊዜ ውስጥ በተደራጀ መልክ ምሥክርነት ለመስጠት አንድ ቡድን አቋቋምን። ከዚያም እናቴ ፍላጎት በማሳየቷ አዲስ ከተቋቋመው ቡድን ጋር በሚደረገው ጥናት ለመካፈል አብራኝ ደርሶ መልስ 100 ኪሎ ሜትር ትጓዝ ነበር። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ምንም እንኳ እናቴ የተጠመቀችው ከጥቂት ዓመታት በፊት ቢሆንም ሁልጊዜ ታበረታታኝና ትረዳኝ ነበር። አሁን የብቸኝነት ስሜት ጨርሶ ጠፋ!

ትንሿ ቡድናችን ሦስቱን የአግኒው ሴት ልጆች ክሪስታል፣ ኢስቴል እና ቤቲ እንዲሁም እኔን ጨምሮ አራት አቅኚዎችን አፈራች። ከዚያም በ1950ዎቹ መግቢያ ላይ ሦስቱ እህትማማቾች የመጠበቂያ ግንብ የጊልያድ ትምህርት ቤት ገቡ። ሚስዮናዊ ሆነው ህንድና ስሪላንካ ተመደቡ። በዚሁ ምድባቸው እስከ አሁን ድረስ በታማኝነት እያገለገሉ ነው።

በጥር 1941 በአውስትራሊያ የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ታገደ። እኛም ፈጣን እርምጃ ወሰድን። ለአገልግሎት እንጠቀምባቸው የነበሩትን ጽሑፎች፣ ተንቀሳቃሽ ፊልሞች፣ የተቀዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችንና የመሳሰሉትን በአንድ ትልቅ የብረት ሣጥን ውስጥ ከተትናቸው። ከዚያም ሣጥኑን በአንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ አስቀመጥነውና በላዩ ላይ ድርቆሽ ከመርንበት።

እገዳ ቢኖርም ከቤት ወደ ቤት ማገልገላችንን አላቋረጥንም። ሆኖም እቤት የምናገኛቸውን ሰዎች የምናነጋግረው በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ በመጠቀም ነበር። መጽሔቶችንና ቡክሌቶችን ኮርቻ ሥር እደብቃቸውና ለመንግሥቱ መልእክት እውነተኛ የሆነ ፍላጎት እንዳለ ስመለከት ብቻ አወጣቸው ነበር። በመጨረሻም ሰኔ 1943 እገዳው ስለተነሳ እንደገና ጽሑፎችን በግልጽ ለማበርከት ቻልን።

አዲስ የአገልግሎት ምድብ

በ1943 አቅኚ ሆንኩና በቀጣዩ ዓመት ለሌላ የሥራ ምድብ ማውንት ጋምቢየርን ለቀቅሁ። በመጀመሪያ ስትራትፊልድ በሚገኘው የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ ለአጭር ጊዜ እንዳገለግል ግብዣ ቀረበልኝ። ከዚያም ኒው ሳውዝ ዌልስና ዌስተርን ቪክቶሪያ በተባሉት ትንንሽ ከተሞች እንዳገለግል ተከታታይ የአገልግሎት ምድብ ተቀበልኩ። ይሁን እንጂ ብዙ መንፈሳዊ በረከቶችን ካገኘሁባቸው ምድቦች መካከል አንዱ በሜልቦርን በሚገኝ በአንድ ትልቅ ጉባኤ ያገለገልኩት ነበር። ከአንዲት ትንሽ የገጠር ከተማ የመጣሁ ስለሆነ እዚህ በማገልገሌ ብዙ ትምህርት አግኝቼአለሁ።

የአገልግሎት ምድቤ በሆነው በቪክቶሪያ አውራጃ በሚገኘው በጊብስላንድ አቅኚ ጓደኛዬ ሄለን ክሮፈርድና እኔ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እንመራ ነበር። በጥቂት ጊዜ ውስጥም አንድ ጉባኤ ሲመሠረት አይተናል። ይህ አውራጃ ሰፊ የገጠር ክልሎች ስለነበሩት ለመጓጓዣ የምንጠቀምባት ብዙ ጊዜ የምትበላሽብን መኪና ነበረችን። አንዳንድ ጊዜ ደህና እየነዳናት ብንጓዝም ብዙ ጊዜ ግን ሞተር ስለሚጠፋብን እየገፋን እናስነሳት ነበር። በዚህ ምክንያት ከመኪናው ይልቅ ፈረስ እመኝ ነበር! አንዳንድ ጊዜ “ለፈረስ ስል ማናንኛውንም ነገር (ከመንግሥቱ በስተቀር) እሰጣለሁ!” ብዬ በግልጽ እናገር ነበር። በአሁኑ ጊዜ በዚህ አውራጃ በሚገኙ በአብዛኞቹ ከተሞች ጠንካራ ጉባኤዎችና ጥሩ የመንግሥት አዳራሾች አሉ።

በ1969 የአውስትራሊያ ዋና ከተማ በሆነችው በካንቤራ እንዳገለግል ተመደብኩ። በተለያዩ የውጪ አገር ኤምባሲዎች ከሚሠሩ ሰዎች ጋር አዘውትረን እንገናኝ ስለነበረ በዚህ ቦታ መመሥከር ጥሩ ችሎታ የሚጠይቅና ለመመሥከር የሚያስችሉ የተለያዩ አጋጣሚዎች ያሉበት ነበር። አሁንም በእዚህ ቦታ እያገለገልኩ ነው። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢንዱስትሪ በበዛባቸው የከተማው ክፍሎች በመመሥከር ላይ አተኮርኩ።

በ1973 በዩናይትድ ስቴትስ በተደረጉ ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ የመገኘት መብት አግቼአለሁ። ሌላው በሕይወቴ ውስጥ ጎላ ያለው ነገር በ1979 በተደረገ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ልኡክ መሆኔና እስራኤልንና ዮርዳኖስን መጎብኘቴ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ትክክለኛ ቦታዎች መጎብኘትና በእነዚያ ቦታዎች ላይ ስለ ተከናወኑት ነገሮች ማሰላሰል ስሜት የሚቀሰቅስ ተሞክሮ ነው። ከመጠን በላይ ጨው በበዛበት በሙት ባሕር ላይ መንሳፈፍ ምን ስሜት እንደሚፈጥር ለማየት ችያለሁ፤ እንዲሁም ዮርዳኖስ ውስጥ የሚገኘውን ፔትራን የተባለውን ቦታ በምንጎበኝበት ጊዜ ፈረስ የመጋለብ አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። ይህም የመንግሥቱን መልእክት ለማዳረስ ተበታትነው ወደሚገኙት የገጠር ቦታዎች በፈረስ እጓዝባቸው የነበሩት እነዚያን የቀድሞ ጊዜያት እንዳስታውስ አደረገኝ።

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቀጠል

ምንም እንኳ እድሜዬ እየገፋ ቢሄድም የአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤትና በወረዳ ስብሰባ ላይ የሚደረጉ የአቅኚዎች ስብሰባ ዝግጅቶች እንዲሁም ከተጓዥ የበላይ ተመልካቾች አገኝ የነበረው ያልተቋረጠ ማበረታቻ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመቀጠል ምኞቴ ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል አስችሎኛል። ይሖዋ ሁሉንም ነገር በደግነት ስላስተካከለልኝ በብቸኝነት ያሳለፍኳቸው ጊዜያት ያለፉ ታሪኮች ናቸው ብዬ በእውነት ለመናገር እችላለሁ።

አሁን 87 ዓመት ሆኖኛል፤ ይሖዋን በማገልገል ወደ 60 የሚጠጉ ዓመታት ያሳለፍኩ ሲሆን ፊት ለፊት በመናገር ሌሎችን ለሚጎዱና እኔ ያልኩት ይሁን ለሚሉ ሰዎች የሚያበረታታ ቃል አለኝ። ይህም፦ ሁልጊዜ ለይሖዋ አመራር ራሳችሁን አስገዙ የሚል ነው። እንዳመጣልን ከመናገር እንድንቆጠብና ብዙ ጊዜ ብቸኝነት የሚሰማን ቢሆንም እሱ እንደማይተወን ለማስታወስ እንድንችል ይሖዋ ይርዳን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ጋሪ ቀላልና ባለ ሁለት ጎማ ተሽከርካሪ ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ