የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“ማስተማርንና የምሥራች መናገርን አላቋረጡም ነበር”
ከኢየሱስና ከሐዋርያቱ ዘመን ጀምሮ የሃይማኖት መሪዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ስብከት ለማጨናገፍ በሚያደርጉት ጥረት ማንኛውንም ዘዴ ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ሐዋርያት “በኢየሱስ ስም እንዳይናገሩ” በኢየሩሳሌም ይገኙ በነበሩት የአካባቢው ባለ ሥልጣናት በተደጋጋሚ ‘በጥብቅ ታዘው’ ነበር። (ሥራ 5:27, 28, 40) ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ እንደሚናገረው “የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፣ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቁጥር እጅግ እየበዛ ሄደ።”—ሥራ 6:7
ሁለት ሺህ ዓመታት ካለፉ በኋላ አሁንም በእስራኤል ውስጥ የእውነተኛ ክርስቲያኖችን ሥራ የአካባቢው ባለ ሥልጣናት እንዲያጨናግፉ ተጽእኖ የሚያደርጉ የሃይማኖት መሪዎችን እናገኛለን። ይሁን እንጂ ልክ እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን በእስራኤል የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ማደጉ ቀጥሏል። የሃይማኖታዊ ለውጥ አራማጆች ባደረጉት ግፊት ኅዳር 1987 በቴል አቪቭ እስራኤል የሚገኙ የአካባቢው ባለ ሥልጣናት በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ምሥክሮቹ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ማድረጋቸውን እንዲያቆሙ ትእዛዝ አስተላለፉ። ሕጉ ከጥቅምት 1989 ጀምሮ ተግባራዊ ሆነ። ስለዚህ ምሥክሮቹ የመንግሥት አዳራሻቸው እያለ ሕግ ለማክበር ሲሉ አዳራሾችን እየተከራዩ ለሦስት ዓመት ያክል ስብሰባዎቻቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ጉዳዩ ለእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረበ። የመንግሥት ዐቃቢ ሕግ ጽሕፈት ቤት የምሥክሮቹን የመከላከያ ነጥብ ከተመለከተ በኋላ መሠረተ ቢስ ሃይማኖታዊ ጥላቻ ካልሆነ በስተቀር ይግባኛቸውን ውድቅ የሚያደርግ ምንም ዓይነት የተቃውሞ ሐሳብ መቅረብ አይችልም ብሎ ወሰነ። ስለዚህ የአካባቢው ባለ ሥልጣናት ውሳኔአቸውን ከመለወጥ በስተቀር ምንም አማራጭ አልነበራቸውም። አዳራሹ እንዲዘጋ የተሰጠው ትእዛዝ ተሰረዘ፤ የይሖዋ ምሥክሮችም በደስታ ወደ መንግሥት አዳራሻቸው ተመለሱ።
በእነዚያ ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የመስበኩ ሥራ ቸል ተብሎ ነበርን? በፍጹም! የመንግሥት አዳራሹ በተዘጋበት ጊዜ በቴል አቪቭ ሁለት ጉባኤዎች ሲኖሩ በአካባቢው በምትገኝ ሎድ የተባለች አንድ የገጠር ከተማ ደግሞ አንድ ገለልተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ብቻ ነበር። ከሦስት ዓመት በኋላ የመንግሥት አዳራሹ እንደገና ሲከፈት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ አራት ጉባኤዎች አድገው ነበር፤ እንዲሁም በቤርሳቤህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ይሰበሰብ ነበር።
በእስራኤል ውስጥ ያለው እድገት በዋናዎቹ ቋንቋዎች በዓረብኛና በዕብራይስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት በብዛት የጎረፉ ተፈናቃዮች አሉ፤ ስለዚህ የሩስያ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ለእነዚህ ተፈናቃዮች ምሥራቹን ያለ እረፍት በማካፈል ላይ ናቸው። አንዳንድ ስብሰባዎች በሦስት ጉባኤዎች ውስጥ በሩስያ ቋንቋ በመደረግ ላይ ናቸው። በቅርቡ በሩስያ ቋንቋ በተደረገ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ከመቶ በላይ ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር።
በእስራኤል ያሉት መሠረተ ቢስ ጥላቻ ያላቸው ሃይማኖተኞች ልክ በሌሎቹ የዓለም ክፍሎች እንደሚደረገው ሁሉ በእውነተኛ አምልኮ ላይ የሚያደርጉትን ዘመቻ እንደሚቀጥሉበት ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ልክ በሐዋርያት ዘመን እንደነበረው የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመንግሥት አዳራሾቻቸው ውስጥ መሰብሰባቸውንና ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ሰዎችን ማነጋገራቸውን ቀጥለዋል። ተቃውሞ ቢኖርባቸውም “በየቀኑም በቤተ መቅደስና በየቤቱም ስለ መሲሑ ኢየሱስ ማስተማርንና የምሥራች መናገርን” ያላቋረጡትን የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን አርአያ ይከተላሉ።—ሥራ 5:42 የ1980 ትርጉም