የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • yp2 ምዕ. 38 ገጽ 311-317
  • ሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል?
  • ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “ፈጣሪህን አስብ”
  • እቅድ ማውጣት
  • ምክር ጠይቅ
  • ሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል?
    ንቁ!—2006
  • የሰዶምና የገሞራ ጥፋት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ኢየሱስ ተአምራዊ ፈውሶችን አከናውኗል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ኢየሱስ ፈተናን ተቋቁሟል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
ለተጨማሪ መረጃ
ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
yp2 ምዕ. 38 ገጽ 311-317

ምዕራፍ 38

ሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል?

“ከዚህ ቀደም ስለ ወደፊት ሕይወቴ አልጨነቅም ነበር። ትምህርቴን የምጨርስበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ ግን የራሴን ሕይወት መምራት ይኸውም ሥራ መያዝና ወጪዎቼን መሸፈን እንደሚኖርብኝ ተገነዘብኩ።”​—አሌክስ

ከምትኖርበት አካባቢ በጣም ርቆ ወደሚገኝ ቦታ ለመሄድ እቅድ አውጥተሃል እንበል። የተሻለውን አቅጣጫ ለመምረጥ በመጀመሪያ ካርታ ትመለከት ይሆናል። ለወደፊት ሕይወትህ እቅድ ስታወጣም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በአሁኑ ጊዜ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚያገለግል ማይክል የተባለ ወጣት “በጣም ብዙ አማራጮች አሏችሁ” በማለት ተናግሯል። ከእነዚህ ሁሉ አማራጮች ለአንተ የሚሆነውን መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው? ማይክል “የምታደርጉትን ምርጫ የሚወስነው ግባችሁ ነው” ብሏል።

ግብን ልትሄድበት ከፈለግከው አንድ ቦታ ጋር ልታመሳስለው ትችላለህ። የምትሄድበትን አቅጣጫ ሳትመርጥ እንዲሁ የምትባዝን ከሆነ የፈለግክበት ቦታ ላይ መድረስ አትችልም። ከዚህ ይልቅ ካርታ በመመልከት የምትከተለውን ጎዳና መምረጥህ በሌላ አባባል እቅድ ማውጣትህ እጅግ የተሻለ ነው። እንዲህ ካደረግህ በምሳሌ 4:26 ላይ ያለውን “የእግርህን ጐዳና አስተካክል” የሚለውን ምክር ተከትለሃል ማለት ነው። የ1980 ትርጉም ይህንን ሐሳብ “ለምታደርገው ነገር ሁሉ ዕቅድ ይኑርህ” በማለት ይገልጸዋል።

በመጪዎቹ ዓመታት አምልኮን፣ ሥራን፣ ትዳርን፣ ቤተሰብንና ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮችን በተመለከተ አስፈላጊ የሆኑ ብዙ ውሳኔዎችን ታደርጋለህ። ግብ ካለህ ጥበብ የተንጸባረቀበት ምርጫ ማድረግ ቀላል ይሆንልሃል። ሆኖም በሕይወትህ ውስጥ እቅድ ስታወጣ ችላ ማለት የሌለብህ አንድ ነገር አለ።

“ፈጣሪህን አስብ”

እውነተኛ ደስታ ማግኘት ከፈለግህ ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ” በማለት የሰጠውን ምክር መከተል አለብህ። (መክብብ 12:1) በሌላ አባባል በሕይወትህ ውስጥ የምትመርጠው ጎዳና አምላክን ለማስደሰት ያለህን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት።

ለዚህ ጉዳይ ቅድሚያ መስጠትህ ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በራእይ 4:11 ላይ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ እንዲሁም ያሉትም ሆነ የተፈጠሩት በአንተ ፈቃድ ስለሆነ ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።” በሰማይም ሆነ በምድር የሚገኙት ሁሉም ፍጥረታት ፈጣሪያቸውን ለማመስገን የሚያነሳሳ ብዙ ምክንያት አላቸው። አምላክ “ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር” ስለሰጠህ አመስጋኝ ነህ? (የሐዋርያት ሥራ 17:25) ይሖዋ አምላክ ለሰጠህ ነገሮች ያለህ አድናቆት አንተም በበኩልህ አንድ ነገር እንድትሰጠው አይገፋፋህም?

የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ብዙ ወጣቶች ፈጣሪያቸውን በማሰብ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመሳተፍ መርጠዋል። አንተም ልትካፈልባቸው ከምትችላቸው አስደሳች የአገልግሎት መስኮች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

አቅኚ መሆን። የዘወትር አቅኚዎች በአገልግሎት ረዘም ያለ ሰዓት ያሳልፋሉ። አቅኚዎች የሚያገኙት ሥልጠና እና በአገልግሎት የሚያካብቱት ተሞክሮ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።

ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ ማገልገል። አንዳንዶች የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው እያገለገሉ ነው። ሌሎች ደግሞ አዲስ ቋንቋ በመማር በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ በውጭ አገር ቋንቋ የሚመራ ጉባኤ ተዛውረዋል፤ አሊያም ወደ ሌሎች አገሮች ሄደው ማገልገል ችለዋል።a

የሚስዮናዊነት አገልግሎት። ጥሩ ጤንነት እንዲሁም የአካልም ሆነ የመንፈስ ጥንካሬ ያላቸው ብቁ አቅኚዎች በባዕድ አገር ለማገልገል ሥልጠና ይሰጣቸዋል። የሚስዮናዊነት ሕይወት አስደሳችና የሚያረካ ነው።

የቤቴል አገልግሎት። የቤቴል ቤተሰብ አባላት በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ሲሆን በአንዳንድ አገሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማዘጋጀቱ፣ በማተሙና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመላኩ ሥራ ይካፈላሉ።

ዓለም አቀፍ አገልግሎት። ዓለም አቀፍ አገልጋዮች የመንግሥት አዳራሾችን፣ ትላልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾችንና ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመገንባቱ ሥራ እገዛ ለማድረግ ወደ ሌሎች አገሮች ይሄዳሉ።

የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት። በዚህ ትምህርት ቤት ለመካፈል ብቃቱን ያሟሉ ያላገቡ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ድርጅታዊ አሠራርንና በሕዝብ ፊት ንግግር ማቅረብን አስመልክቶ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። አንዳንዶቹ በሌላ አገር እንዲያገለግሉ ሊመደቡ ይችላሉ።

እቅድ ማውጣት

የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከሁሉ የላቀ ግብ ከመሆኑም በላይ ስፍር ቁጥር የሌለው በረከት ያስገኛል። ሆኖም እቅድ ማውጣት አለብህ። ለምሳሌ ‘ራሴን ለማስተዳደር የሚያስችለኝ ምን ችሎታና ሙያ አለኝ?’ በማለት ራስህን ጠይቅ።

ኬሊ አቅኚ የመሆን ግብ ስለነበራት ሥራን በተመለከተ ምን እንደምታደርግ እቅድ አወጣች። “በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድካፈል የሚያስችለኝን የሥራ ዓይነት መምረጥ ነበረብኝ” ብላለች።

ኬሊ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለች በአንድ ሙያ ሠለጠነች። ይህም ዋነኛ ግቧ ላይ እንድትደርስ ረድቷታል። እንዲህ ትላለች፦ “እኔ የምፈልገው የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መሆን ነው፤ የተቀሩት ነገሮች ሁሉ በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጡ ናቸው።” ኬሊ ባደረገችው ምርጫ ደስተኛ ናት። “ከዚህ የተሻለ ውሳኔ ላደርግ እንደማልችል ይሰማኛል” በማለት ትናገራለች።

ምክር ጠይቅ

በማታውቀው አካባቢ እየተጓዝክ ከሆነ አንድ ቦታ ላይ ስትደርስ አቅጣጫ መጠየቅህ አይቀርም። ስለ ወደፊት ሕይወትህ እቅድ በምታወጣበት ጊዜም የሌሎችን ምክር መጠየቅ ትችላለህ። ምሳሌ 20:18 “ምክር ጠይቀህ ዕቅድ አውጣ” ይላል።

ወላጆችህ ጠቃሚ ምክር ሊሰጡህ እንደሚችሉ የታወቀ ነው። በተጨማሪም የአምላክን ምክር በሕይወታቸው ተግባራዊ በማድረግ ጥበበኞች መሆናቸውን ያሳዩ የጎለመሱ ክርስቲያኖችን ምክር መጠየቅ ትችላለህ። በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘውና የቤቴል ቤተሰብ አባል የሆነው ሮቤርቶ “በጉባኤያችሁ ውስጥ ወይም በአቅራቢያችሁ የሚገኙ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ አዋቂዎችን ምክር መጠየቅ ትችላላችሁ” በማለት ይናገራል።

ከማንም በበለጠ ደግሞ ይሖዋ አምላክ፣ በሕይወትህ ውስጥ ከሁሉ የላቀ ደስታ የሚያስገኝልህን ምርጫ እንድታደርግ ሊረዳህ ይፈልጋል። ስለዚህ የወደፊት ሕይወትህን በተመለከተ ‘የእሱ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማስተዋል’ እንዲረዳህ ጠይቀው። (ኤፌሶን 5:17) በሁሉም የሕይወትህ ዘርፍ በምሳሌ 3:5, 6 (NW) ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ አድርግ፦ “በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፣ በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፣ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።”

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት “የወጣቶች ጥያቄ​—ሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል?” የተባለውን ዲቪዲ ተመልከት። ይህ ፊልም ከ30 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል (በአማርኛ ግን አይገኝም)

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በገጽ 164 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

ቁልፍ ጥቅስ

‘“የሰማያትን መስኮቶች ከፍቼ ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት ባላፈስላችሁ፣ እስቲ በዚህ ፈትኑኝ” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።’​—ሚልክያስ 3:10 NW

ጠቃሚ ምክር

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ረጅም ዓመት የቆዩ ክርስቲያኖችን አነጋግር። ይህን የአገልግሎት መስክ የመረጡት ለምን እንደሆነና ምን በረከት እንዳገኙ ጠይቃቸው።

ይህን ታውቅ ነበር?

የኤሌክትሪክ ኃይል አንድን መሣሪያ እንዲሠራ እንደሚያደርገው ሁሉ መንፈስ ቅዱስም በአምላክ አገልግሎት ብዙ ነገር እንድታከናውን ሊያንቀሳቅስህ ይችላል።​—የሐዋርያት ሥራ 1:8

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

በአገልግሎት ይበልጥ ደስተኛ ለመሆን እንዲረዳኝ ላናግረው የምችለው ሰው ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ምን ችሎታና ሙያ አለህ?

● ችሎታህን ይሖዋን ለማወደስ ልትጠቀምበት የምትችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

● በዚህ ምዕራፍ ላይ ከተጠቀሱት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች ውስጥ አንተን ይበልጥ የሚማርክህ የትኛው ነው?

[በገጽ 313 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወላጆቼን በጣም አደንቃቸዋለሁ። ለአገልግሎት ያላቸው የማይቀዘቅዝ ቅንዓት፣ የኢኮኖሚ ችግሮችን የተቋቋሙበት መንገድ እንዲሁም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድካፈል የሰጡኝ ማበረታቻ በጎ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል።”​—ጃሮድ

[በገጽ 314 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የመልመጃ ሣጥን

ግቦቼ

ልትደርስባቸው በምትፈልጋቸው ግቦች ላይ ምልክት አድርግ። ከታች የሰፈሩትን ግቦች ከአንተ ሁኔታ ጋር ለማስማማት ወይም አዳዲስ ግቦችን ለመጻፍ በክፍት ቦታዎቹ ተጠቀም።

ከአገልግሎት ጋር የተያያዙ ግቦች

□ በወር ውስጥ በአገልግሎት የማሳልፈውን ሰዓት ወደ ከፍ ማድረግ

□ በየወሩ ጽሑፎችን ማበርከት

□ ስለ እምነቴ ስናገር በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም

□ በየወሩ ያህል ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ

□ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር

ሌሎች ግቦች፦ ․․․․․

ከጥናት ጋር የተያያዙ ግቦች

□ በየቀኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ገጾች ማንበብ

□ በየሳምንቱ ለሚደረጉት ስብሰባዎች መዘጋጀት

□ በሚከተሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሶች ላይ ምርምር ማድረግ

ከጉባኤ ጋር የተያያዙ ግቦች

□ በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ቢያንስ አንድ ጊዜ ሐሳብ መስጠት

□ ይበልጥ ላውቀው ከምፈልገው አንድ ትልቅ ሰው ጋር ጨዋታ መጀመር

□ በዕድሜ የገፉ ወይም የታመሙ የጉባኤ አባላትን መጠየቅ

ሌሎች ግቦች፦ ․․․․․

የዛሬው ቀን ․․․․․

ከስድስት ወር በኋላ እነዚህን ግቦች መለስ ብለህ በመመልከት ምን ያህል እንደተሳካልህ ገምግም። እንዳስፈላጊነቱ ማስተካከያ አድርግባቸው አሊያም ተጨማሪ ግቦች አውጣ።

[በገጽ 312 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ግብ ማውጣት አንድ ቁም ነገር ላይ ሳትደርስ እንዲሁ ጉልበትህን ከማባከን እንድትቆጠብ ይረዳሃል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ