-
ሰዎች የሚጸልዩት ለምንድን ነው?መጠበቂያ ግንብ—2015 | ጥቅምት 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጸለይ የሚያስገኘው ጥቅም አለ?
ሰዎች የሚጸልዩት ለምንድን ነው?
“ከባድ የቁማር ሱሰኛ ነበርኩ። በጨዋታው አሸንፌ ለመክበር እጸልይ ነበር። ምኞቴ ግን አልተሳካም።”—ሳሙኤል፣a ኬንያ
“ትምህርት ቤት የተማርናቸውን ጸሎቶች በቃላችን ሸምድደን እንድንደግም ይጠበቅብን ነበር።”—ቴሬሳ፣ ፊሊፒንስ
“ችግሮች ሲያጋጥሙኝ እጸልያለሁ። የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘትና ጥሩ ክርስቲያን ለመሆን እጸልያለሁ።”—ማግደሊን፣ ጋና
ሳሙኤል፣ ቴሬሳና ማግደሊን የተናገሯቸው ሐሳቦች ሰዎች የሚጸልዩበት ምክንያት የተለያየ እንደሆነና አንዳንዶቹ ጉዳዮች ከሌሎቹ የበለጠ ትርጉም እንዳላቸው ያሳያሉ። አንዳንድ ሰዎች የሚያቀርቧቸው ጸሎቶች ከልብ የመነጩ ሲሆኑ ሌሎች ጸሎቶች ግን የሚቀርቡት ለወጉ ያህል ነው። ሰዎች የሚጸልዩት የትምህርት ቤት ፈተና ለማለፍ፣ በቤተሰብ ሕይወታቸው ውስጥ የአምላክን አመራር ለማግኘት አሊያም የሚደግፉት የስፖርት ቡድን እንዲያሸንፍም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መጸለይ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንዲያውም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሃይማኖት የሌላቸው አንዳንድ ሰዎች እንኳ አዘውትረው ይጸልያሉ።
አንተስ ትጸልያለህ? ከሆነ የምትጸልየው ስለ ምን ጉዳይ ነው? የመጸለይ ልማድ ኖረህም አልኖረህ፣ ‘ብጸልይ የማገኘው ጥቅም ይኖራል? የሚሰማኝስ አለ?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። አንድ ጸሐፊ፣ ጸሎት “አንድ ዓይነት የሕክምና ዘዴ” ከመሆን ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ተናግረዋል። አንዳንድ የሕክምና ባለሙያዎችም ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ጸሎት “አማራጭ ሕክምና” እንደሆነ ገልጸዋል። ታዲያ ሰዎች በሚጸልዩበት ጊዜ አንድ ትርጉም የሌለው ሥርዓት በዘልማድ እያከናወኑ ነው? ወይስ ቢያንስ ቢያንስ የሆነ የሕክምና ጥቅም ያስገኝላቸዋል?
በሌላ በኩል መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጸሎት ከአንድ ዓይነት ሕክምና እጅግ የበለጠ ነገር እንደሆነ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ በጸሎታችን ላይ ትክክለኛውን ነገር በትክክለኛ መንገድ ከጠየቅን በእርግጥ የሚሰማን አካል እንዳለ ይናገራል። ለመሆኑ ይህ እውነት ነው? እስቲ ማስረጃውን እንመልከት።
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
-
-
ጸሎቴን የሚሰማ አለ?መጠበቂያ ግንብ—2015 | ጥቅምት 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጸለይ የሚያስገኘው ጥቅም አለ?
ጸሎቴን የሚሰማ አለ?
አንዳንድ ሰዎች ጸሎታቸውን የሚሰማ ስለሌለ መጸለይ ጊዜ ማባከን እንደሆነ ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ የሚጸልዩ ቢሆንም ምንም መልስ እንዳላገኙ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ በአምላክ የማያምን አንድ ሰው፣ አምላክ እንዲህ ይመስላል ብሎ አንድ አካል በምናቡ ከፈጠረ በኋላ “እስቲ በሹክሹክታ እንኳ አናግረኝ” ብሎ ጸለየ። ከዚያ በኋላ ግን ከአምላክ “ምንም መልስ እንዳላገኘ” ተናግሯል።
ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ጸሎት የሚሰማ አንድ አምላክ መኖሩን በማያሻማ መንገድ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ዘመን ለኖረ ሕዝብ የተነገረውን ይህን ሐሳብ ይዟል፦ “እርዳታ ለማግኘት በምትጮኹበት ጊዜ በእርግጥ ሞገስ ያሳያችኋል፤ ጩኸታችሁን እንደሰማም ይመልስላችኋል።” (ኢሳይያስ 30:19) ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ደግሞ ‘የቅኖች ጸሎት ደስ ያሰኘዋል’ ይላል።—ምሳሌ 15:8
ኢየሱስ ወደ አባቱ ያቀረበው ጸሎት “ተሰማለት።”—ዕብራውያን 5:7
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ላቀረቡት ጸሎት መልስ ስላገኙ ሰዎች ይናገራል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ኢየሱስ ‘ከሞት ሊያድነው ለሚችለው ልመና’ እንዳቀረበ ከመግለጹም ሌላ ‘ጸሎቱ እንደተሰማለት’ ይናገራል። (ዕብራውያን 5:7) በዳንኤል 9:21 እና በ2 ዜና መዋዕል 7:1 ላይ ሌሎች ምሳሌዎችን እናገኛለን።
ታዲያ አንዳንድ ሰዎች ጸሎታቸው መልስ እንዳላገኘ የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ጸሎታችን እንዲሰማልን ከፈለግን ወደ ማንኛውም አምላክ ወይም ወደ ቅዱሳን ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ወደሆነው ወደ ይሖዋa ብቻ መጸለይ ይኖርብናል። በተጨማሪም አምላክ፣ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ነገሮች “ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ” እንድንጠይቅ ይፈልጋል። በዚህ መንገድ የምንጸልይ ከሆነ አምላክ ‘እንደሚሰማን’ ተናግሯል። (1 ዮሐንስ 5:14) ስለዚህ ጸሎታችን እንዲሰማልን ከፈለግን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን አምላክ ማወቅና የእሱን ፈቃድ መማር ያስፈልገናል።
ብዙ ሰዎች፣ ጸሎት አንድ ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ብቻ እንዳልሆነና አምላክ ለእሱ የሚቀርበውን ጸሎት ሰምቶ መልስ እንደሚሰጥ ያምናሉ። በኬንያ የሚኖረው አይሳክ እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ እንዲገባኝ እርዳታ ለማግኘት ጸልዬ ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አንድ ሰው ወዳለሁበት መጥቶ ስፈልገው የነበረውን እርዳታ ሰጠኝ።” በፊሊፒንስ የምትኖረው ሂልዳ ሲጋራ ማጨስ ለማቆም ትፈልግ ነበር። ብዙ ጊዜ ሊሳካላት ስላልቻለ ባለቤቷ “አምላክ እንዲረዳሽ ለምን አትጸልይም?” የሚል ሐሳብ አቀረበላት። እሷም ምክሩን በሥራ ላይ ካዋለች በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “አምላክ ያደረገልኝ እርዳታ በጣም አስገርሞኛል። የማጨስ ፍላጎቴ እየጠፋ መጣ። ከዚያም ሙሉ በሙሉ ማጨስ አቆምኩ።”
አምላክ በግል የሚያሳስቡህ ነገሮች ከፈቃዱ ጋር የሚስማሙ እስከሆኑ ድረስ አንተን የመርዳት ፍላጎት አለው?
a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።
-
-
አምላክ እንድንጸልይ የሚያበረታታን ለምንድን ነው?መጠበቂያ ግንብ—2015 | ጥቅምት 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጸለይ የሚያስገኘው ጥቅም አለ?
አምላክ እንድንጸልይ የሚያበረታታን ለምንድን ነው?
አምላክ ወዳጆቹ እንድንሆን ጋብዞናል።
ሁለት ጓደኛሞች ወዳጅነታቸው እየጠነከረ እንዲሄድ እርስ በርስ መነጋገር አለባቸው። በተመሳሳይም አምላክ እንድናነጋግረው ጋብዞናል፤ በመሆኑም ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድንመሠርት አጋጣሚውን ከፍቶልናል። እንዲህ ብሏል፦ “እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ወደ እኔም ቀርባችሁ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ።” (ኤርምያስ 29:12) በመሆኑም አምላክን በጸሎት ስታናግሩት ‘ወደ እሱ ትቀርባላችሁ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።’ (ያዕቆብ 4:8) መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው” ይላል። (መዝሙር 145:18) ወደ አምላክ በጸለይን መጠን ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት በዚያው ልክ እያደገ ይሄዳል።
“ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።”—መዝሙር 145:18
አምላክ አንተን ለመርዳት ዝግጁ ነው።
ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው አለ? ወይስ ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋል? ታዲያ እናንተ . . . ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካም ነገር እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!” (ማቴዎስ 7:9-11) አዎን፣ አምላክ ወደ እሱ እንድትጸልይ የሚጋብዝህ ‘ስለ አንተ ስለሚያስብና’ አንተን መርዳት ስለሚፈልግ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:7) እንዲያውም ችግሮችህን እንድትነግረው ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ” ይላል።—ፊልጵስዩስ 4:6
ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት አላቸው።
ስለ ሰው ባሕርይ የሚያጠኑ ባለሙያዎች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መጸለይ አስፈላጊ እንደሆነ እንደሚሰማቸው ተገንዝበዋል። ከእነዚህ መካከል በአምላክ መኖር የማያምኑ ወይም መኖሩን የሚጠራጠሩ ሰዎች ይገኙበታል።a ይህም ሰዎች ከተፈጠሩበት ጊዜ አንስቶ መንፈሳዊ ፍላጎት እንዳላቸው የሚናገረውን ሐቅ ያረጋግጣል። ኢየሱስ “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 5:3) ይህን ፍላጎት ማርካት የምንችልበት አንድ መንገድ ዘወትር ከአምላክ ጋር መነጋገር ነው።
አምላክ ወደ እሱ እንድንጸልይ የሰጠንን ማበረታቻ የምንቀበል ከሆነ ምን ጥቅሞች ልናገኝ እንችላለን?
a ፒዩ የምርምር ማዕከል በ2012 ያካሄደው አንድ ጥናት እንዳሳየው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚኖሩ በአምላክ መኖር ከማያምኑ ወይም ከሚጠራጠሩ ሰዎች መካከል 11 በመቶ የሚሆኑት ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ ይጸልያሉ።
-
-
ጸሎት እንዴት ሊጠቅምህ ይችላል?መጠበቂያ ግንብ—2015 | ጥቅምት 1
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጸለይ የሚያስገኘው ጥቅም አለ?
ጸሎት እንዴት ሊጠቅምህ ይችላል?
አንድ አዲስ ሥራ ከመጀመርህ በፊት ‘ምን ጥቅም አገኝበታለሁ?’ ብለህ ማሰብህ ያለ ነገር ነው። ይሁንና ጸሎትን በተመለከተ እንዲህ ብለህ መጠየቅህ ራስ ወዳድነት ይሆናል? በፍጹም። ጸሎት ይጠቅመን እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ መፈለጋችን ምንም ስህተት የለውም። ጥሩ ሰው የነበረው ኢዮብ እንኳ “ብጠራው ይመልስልኛል?” ብሎ የጠየቀበት ወቅት ነበር።—ኢዮብ 9:16
ከዚህ በፊት ባሉት ርዕሶች ላይ ጸሎት አንድ ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ወይም የአእምሮ ሕክምና ከመሆን ያለፈ ጥቅም እንዳለው የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ተመልክተናል። እውነተኛው አምላክ በእርግጥ ጸሎት ሰሚ ነው። ትክክለኛ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት በተገቢው መንገድ የምንጸልይ ከሆነ ትኩረት ሰጥቶ ያዳምጠናል። እንዲያውም ወደ እሱ እንድንቀርብ ያበረታታናል። (ያዕቆብ 4:8) ታዲያ ጸሎት የሕይወታችን ክፍል እንዲሆን ካደረግን ምን ጥቅም ማግኘት እንችላለን? እስቲ አንዳንዶቹን ጥቅሞች እንመልከት።
የአእምሮ ሰላም።
በሕይወትህ ውስጥ ችግሮችና ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙህ በጭንቀት ትዋጣለህ? እንደዚህ ባሉት ጊዜያት ‘ዘወትር እንድንጸልይ’ እና ‘ልመናችንን ለአምላክ እንድናቀርብ’ መጽሐፍ ቅዱስ ያበረታታናል። (1 ተሰሎንቄ 5:17፤ ፊልጵስዩስ 4:6) በጸሎት ወደ አምላክ የምንቀርብ ከሆነ ‘ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም ልባችንንና አእምሯችንን እንደሚጠብቅልን’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ፊልጵስዩስ 4:7) በሰማይ ለሚኖረው አባታችን ያስጨነቁንን ነገሮች በምንገልጽበት ጊዜ በተወሰነ መጠን ስሜታችን ይረጋጋል። እንዲያውም አምላክ በመዝሙር 55:22 ላይ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል” በማለት ማበረታቻ ሰጥቶናል።
“ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል።”—መዝሙር 55:22
በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በጣም ብዙ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሰላም አግኝተዋል። በደቡብ ኮሪያ የምትኖረው ሂ ራን እንዲህ ብላለች፦ “ከባድ ችግሮች ቢኖሩብኝም እንኳ ችግሮቼን ጠቅሼ ከጸለይኩ በኋላ ሸክም እንደቀለለኝ የሚሰማኝ ከመሆኑም ሌላ ለመጽናት የሚያስፈልገኝን አቅም እንዳገኘሁ ይሰማኛል።” በፊሊፒንስ የምትኖረው ሴሲልያ እንዲህ ብላለች፦ “እናት እንደመሆኔ መጠን የሴቶች ልጆቼና የእናቴ ነገር በጣም ያስጨንቀኛል፤ በአሁኑ ሰዓት እናቴ አታውቀኝም። ይሁንና ጸሎት ስለ ብዙ ነገር ሳልጨነቅ የዕለት ተዕለት ሕይወቴን እንድገፋ አስችሎኛል። ይሖዋ እነሱን መንከባከብ እንድችል እንደሚረዳኝ አውቃለሁ።”
በመከራ ጊዜ መጽናኛና ብርታት ማግኘት።
ከባድ ጭንቀት ውስጥ ነህ? አልፎ ተርፎም ለሕይወት የሚያሰጉ ወይም እጅግ አሳዛኝ የሆኑ ሁኔታዎች አጋጥመውሃል? “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ወደሆነው አካል መጸለይህ ትልቅ እፎይታ ሊያመጣልህ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “እሱ በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ኢየሱስ እጅግ ከመጨነቁ የተነሳ “ተንበርክኮ መጸለይ ጀመረ።” ከዚያስ ምን ሆነ? “አንድ መልአክ ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው።” (ሉቃስ 22:41, 43) ሌላው ታማኝ ሰው ደግሞ ነህምያ ነው፤ አምላክ የሰጠውን ሥራ ለማስቆም በክፉ ዓላማ የተነሳሱ ሰዎች ዛቻ ሰንዝረውበት ነበር። ነህምያ “በዚህ ጊዜ እጆቼን አበርታልኝ ብዬ ጸለይኩ” ብሏል። ከዚህ በኋላ የተከናወኑት ነገሮች አምላክ ፍርሃቱን እንዲያሸንፍና ሥራውን ዳር እንዲያደርስ በእርግጥ እንደረዳው ያሳያሉ። (ነህምያ 6:9-16) ጋና ውስጥ የሚኖረው ሬጀነልድ ከጸሎት ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “በተለይ ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች አጋጥመውኝ በምጸልይበት ጊዜ እኔን መርዳት ለሚችልና ያን ያህል የምደናገጥበት ምክንያት እንደሌለ በመግለጽ ለሚያጽናናኝ አካል ችግሬን እንደነገርኩ ሆኖ ይሰማኛል።” አዎን፣ አምላክ ወደ እሱ ከጸለይን ሊያጽናናን ይችላል።
ከአምላክ የሚገኝ ጥበብ።
በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸው አንዳንድ ውሳኔዎች በእኛም ሆነ በቅርብ የቤተሰባችን አባላት ላይ ዘላቂ ውጤት ሊያስከትሉ ይችላል። ታዲያ ጥበብ የተሞላበት ምርጫ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው [በተለይ ፈተናዎችን ለመወጣት] ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣልና፤ ይህም ሰው ይሰጠዋል።” (ያዕቆብ 1:5) ጥበብ ለማግኘት የምንጸልይ ከሆነ አምላክ በቅዱስ መንፈሱ ተጠቅሞ ጥበብ የታከለባቸው ውሳኔዎች እንድናደርግ ሊመራን ይችላል። እንዲያውም ኢየሱስ “በሰማይ ያለው አባትማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!” ስላለን መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን ለይተን መጠየቅ እንችላለን።—ሉቃስ 11:13
“ይሖዋ ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ እንድችል መመሪያ እንዲሰጠኝ ያለማሰለስ ጸለይኩ።”—ክዋቤና፣ ጋና
ኢየሱስ እንኳ ከባድ ውሳኔዎችን ከማድረጉ በፊት አባቱ እንዲረዳው መጠየቅ እንዳለበት ተሰምቶታል። ኢየሱስ ሐዋርያት ሆነው የሚያገለግሉትን 12 ሰዎች መምረጥ በፈለገ ጊዜ “ሌሊቱንም ሙሉ ወደ አምላክ ሲጸልይ አደረ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ሉቃስ 6:12
እንደ ኢየሱስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎችም ጥበብ ያለባቸው ውሳኔዎች ማድረግ እንዲችሉ ላቀረቧቸው ልመናዎች አምላክ እንዴት መልስ እንደሰጣቸው ሲመለከቱ ተበረታተዋል። በፊሊፒንስ የምትኖረው ሬጂና ልዩ ልዩ ፈተናዎች አጋጥመዋት እንደነበር ተናግራለች፤ ለምሳሌ ባሏ ከሞተ በኋላ ለራሷና ለቤተሰቧ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማሟላት፣ ሥራ ማጣት እንዲሁም ልጆች ማሳደግ ተፈታታኝ ሆኖባት ነበር። ታዲያ ጥበብ የታከለባቸው ውሳኔዎች እንድታደርግ የረዳት ምንድን ነው? “ይሖዋ እንዲረዳኝ ጸለይኩ” ብላለች። በጋና የሚኖረው ክዋቤና ወደ አምላክ የጸለየበትን ምክንያት ሲገልጽ “ጥሩ ደመወዝ የማገኝበትን የግንባታ ሥራዬን አጣሁ” ብሏል። ከፊቱ የተደቀኑትን አማራጮች በተመለከተ “ይሖዋ ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ እንድችል መመሪያ እንዲሰጠኝ ያለማሰለስ ጸለይኩ” ሲል ተናግሯል። አክሎም “ይሖዋ መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍላጎቶቼን እንዳሟላ የሚያስችለኝን ሥራ እንድመርጥ እንደረዳኝ አምናለሁ” ብሏል። አንተም ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና ሊነኩ የሚችሉ ጉዳዮችን በጸሎትህ በመጥቀስ የእሱን አመራር ማግኘት ትችላለህ።
ቀደም ሲል የተጠቀሱት ነጥቦች ጸሎት እንዴት ሊጠቅምህ እንደሚችል የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው። (ተጨማሪ ምሳሌዎችን ለማግኘት “ጸሎት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ይሁንና እነዚህን ጥቅሞች ለማግኘት በመጀመሪያ አምላክን እንዲሁም የእሱን ፈቃድ ማወቅ ያስፈልግሃል። ይህን የምትፈልግ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠኑህ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል።a እንዲህ ማድረግህ “ጸሎት ሰሚ” ወደሆነው አምላክ ለመቅረብ የምትወስደው የመጀመሪያ እርምጃ ሊሆን ይችላል።—መዝሙር 65:2
a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ማናገር ወይም www.jw.org/am የተባለውን ድረ ገጻችንን መመልከት ትችላለህ።
-