ማህበራዊ መዝናኛ ጥቅሞቹን አግኙ፣ ወጥመዶቹን ግን ሽሹ
“[ለሰው]ከሚበላና ከሚጠጣ በድካሙም ደስ ከሚለው በቀር የሚሻለው ነገር የለም።”—መክብብ 2:24
1. መዝናኛን በተመለከተ የአምላክ አመራር ሕዝቦቹን የሚረዳቸው እንዴት ነው?
የይሖዋ አመራር ለአገልጋዮቹ ብዙ ጥቅሞችን ያመጣላቸዋል። ይህንንም በመዝናኛው መስክ ልናይ እንችላለን። አመራሩ ክርስቲያኖች መዝናኛን በአንድ በኩል በጣም እንዳይኮንኑ በሌላው በኩል ደግሞ ከልክ እንዳያልፉ ይረዳቸዋል። በአለባበስና በጠባይ አክራሪ የሆኑ አንዳንድ ሃይማኖተኞች ማንኛውንም ዓይነት ተድላ እንደ ኃጢአት ይመለከታሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኞቹ ሰዎች የሚደሰቱበት ነገር ከይሖዋ ሕግና መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚጋጭ ቢሆንም እንኳን ተድላን ያሳድዳሉ።—ሮሜ 1:24-27፤ 13:13, 14፤ ኤፌሶን 4:17-19
2. አምላክ ስለ መዝናኛ ያለውን አመለካከት የሚያሳይ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ነገር ምንድን ነው?
2 ታዲያ የአምላክ ሕዝቦችስ በዚህ ረገድ እንዴት ናቸው? ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምሩ አምላክ ሰዎችን የፈጠረው በሕይወት ከመደሰት ችሎታ ጋር መሆኑን ሲሰሙ በጣም ተደንቀዋል። አምላክ ለመጀመሪያ ወላጆቻችን የሚሠሩት ሥራ ሰጥቷቸው ነበር፤ ነገር ግን በአብዛኞቹ ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች ሕይወት ላይ ጥቁር ነጥብ እንደጣለው አስከፊና የማያስደስት ሥራ አልነበረም። (ዘፍጥረት 1:28-30) በምድራዊ ገነት የሚኖሩ ሁሉ ደስታ ሊያገኙ የሚችሉባቸው ብዛት ያላቸው ጤናማ መንገዶችን አስቡ። ምንም ሥጋት የማያስከትሉ የነበሩትን የዱር አራዊትና የየዕለቱ ሕይወታቸው ክፍል የሆኑትን ልዩ ልዩ የቤት እንስሳት በማየት የሚያገኙትን ደስታ ገምቱት! “ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፣ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ” ሁሉ ምንኛ ይረኩበት ነበር!—ዘፍጥረት 2:9፤ መክብብ 2:24
3-5. (ሀ) መዝናኛ ለምን ዓላማ መዋል ይኖርበታል? (ለ) አምላክ እሥራኤላውያንን ደስታ እንዳያገኙ እንዳልከለከላቸው እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
3 እነዚህ ሁኔታዎች ራሳቸው እንደ መዝናኛ ሊታዩ ይችላሉ። በገነት የተሰናዱበት ምክንያትም ከአሁኑ ጋር አንድ ዓይነት ነበር፤ ይኸውም ለተጨማሪ የማምረት እንቅስቃሴዎች (ሥራ) የአንድን ሰው ሰውነት አዝናንቶ ጥንካሬውን ማደስ ነበር። መዝናኛ ይህን ማከናወን ሲችል ጠቃሚ ነው። ታዲያ ይህ ማለት እውነተኛ አምላኪዎች አሁን የሚኖሩት በምድራዊ ገነት ባይሆንም በሕይወታቸው ውስጥ ለመዝናኛ ቦታ ሊሰጡ ይችላሉ ማለት ነው? አዎ። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ በይሖዋ የጥንት ሕዝቦች መሐል ይደረግ ስለነበረው መዝናኛ እንደሚከተለው ይላል፦
4 “የእሥራኤላውያን መደሰቻዎችና የጊዜ ማሳለፊያ ጨዋታዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጎላ ብለው አልተገለጹም። ይሁን እንጂ ከብሔሩ ሃይማኖታዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማሙ ሲሆኑ ተገቢና ተፈላጊም ሆነው እንደሚታዩ ያሳያል። ዋናዎቹ የመዝናኛ ዓይነቶች በሙዚቃ መሣሪያዎች መጫወት፣ መዘመር፣ ዘፈንና ጭፈራ፣ የንግግር ጭውውቶችና እንዲሁም አንዳንድ የግጥሚያ ጨዋታዎች ነበሩ። እንቆቅልሾችና ከባድ ጥያቄዎችን ማቅረብ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ነበሩ።—መሳፍንት 14:12”—ጥራዝ 1 ገጽ 102
5 ዳዊት በድል በተመለሰ ጊዜ ዕብራውያን ሴቶች ሲጫወቱ (ዕብራይስጥ ሳካቅ) በከበሮና በአታሞ ተጠቅመዋል። (1 ሳሙኤል 18:6, 7) የዕብራይስጡ ቃል በመሠረቱ “ሳቅ” ማለት ሲሆን አንዳንድ ትርጉሞች የ“ሴቶች ጭፈራ” ብለውታል። (ባይንግተን፣ ሮዘርሃም፣ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ታቦቱ ወደ ሌላ ቦታ በሚዛወርበት ጊዜም “ዳዊትና የእሥራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆም በከበሮም በነጋሪትና በጸናጽል በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር።” የዳዊት ሚስት ሜልኮል ዳዊት በጭፈራው መካፈሉን ስለተቃወመች ሚዛናዊ ያልሆነ አመለካከት ነበራት። (2 ሳሙኤል 6:5, 14-20) አምላክ ከባቢሎን ምርኮ የሚመለሱ ሰዎችም በተመሳሳይ የደስታ መግለጫዎች እንደሚካፈሉ ትንቢት ተናግሮ ነበር።—ኤርምያስ 30:18, 19፤ 31:4፤ ከመዝሙር 126:2 ጋር አወዳድሩ።
6. የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ መዝናኛ ባለን አመለካከት ረገድ የሚረዱን እንዴት ነው?
6 እኛም ስለ መዝናኛ ሚዛናዊ ለመሆን መፈለግ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ እንደ ባሕታዊ ራሱን የሚጨቁን እንዳልነበረ እንገነዘባለንን? ሌዊ ለክብሩ ያዘጋጀለትን “ታላቅ ግብዣ” በመሳሰሉ አእምሮን የሚያዝናኑ ግብዣዎች ላይ ጊዜውን አሳልፏል። ራሳቸውን የሚያጸድቁ ሰዎች በመብላቱና በመጠጣቱ በነቀፉት ጊዜም ኢየሱስ የእነርሱን አመለካከትና መንገድ አልተቀበለም። (ሉቃስ 5:29-31፤ 7:33-36) በሠርግ ላይ እንደተገኘና ለድግሱም አስተዋጽኦ እንዳበረከተም አስታውሱ። (ዮሐንስ 2:1-10) የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የነበረው ይሁዳ ክርስቲያኖች “የፍቅር ግብዣ” እንደነበራቸው ስለሚገልጽ እነዚህ የፍቅር ግብዣዎች ድሆችም ጭምር በመብል እንደዚሁም በአስደሳችና በወዳጅነት መዝናኛዎች ሊደሰቱ የሚችሉባቸው መሰናዶዎች እንደነበሩ ግልጽ ነው።—ይሁዳ 12
ጊዜውንና ቦታውን የጠበቀ ማኅበራዊ መዝናኛ
7. መዝናኛን በሚመለከት የአምላክ ቃል ሚዛናዊነትን የሚያበረታታው እንዴት ነው?
7 መክብብ 10:19 “በምግብና በወይን ጠጅ ተድላ ደስታ ይገኛል” በማለት በመደገፍ ይናገራል። ይህም መዝናኛ በተፈጥሮ ስህተት እንደሆነ አያመለክትም፣ ያመለክታል እንዴ? ሆኖም ይኸው መጽሐፍ “ለሁሉ ዘመን (ጊዜ) አለው፣ . . . ለማልቀስ ጊዜ አለው፣ ለመዝፈንም ጊዜ አለው” በማለት ይናገራል። (መክብብ 3:1, 4) አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ተገቢ መዝናኛን የማይከለክል ሲሆን ማስጠንቀቂያም ይሰጠናል። ይህም ማስጠንቀቂያ ጊዜያችንንና የመዝናኛውን መጠን በተመለከተ ማኅበራዊ መዝናኛዎችን በቦታቸው መጠበቅን ይጨምራል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ መዝናኛዎቹ ብዙ ሰው የሚመጣባቸው በሚሆኑበት ጊዜ በጣም ስለተለመዱት አደጋዎች ያስጠነቅቀናል።—2 ጢሞቴዎስ 3:4
8, 9. የምንኖርበት ዘመንና ከአምላክ የተሰጠን ሥራ መዝናኛችንን የሚነካው ለምንድን ነው?
8 ከባቢሎን የሚመለሱ አይሁድ ብዙ ከባድ ሥራ ቢኖርባቸውም ደስታ በተሞላበት መዝናኛ እንደተካፈሉ ተመልክተናል። ሆኖም ኤርምያስ ቀደም ሲል “በዋዘኞችና በደስተኞች ጉባኤ አልተቀመጥሁም” ብሎ ነበር። (ኤርምያስ 15:17) ቅጣት መቅረቡን የሚገልጽ መልእክት እንዲያደርስ በአምላክ ተልኮ ስለነበር ደስታ የሚያደርግበት ጊዜ አልደረሰም ነበር።
9 በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች የአምላክን የተስፋ መልእክት እንዲያውጁና በሰይጣን ዓለም ላይ የሚያመጣውን የፍርድ መልእክት እንዲያስታውቁ ተልከዋል። (ኢሳይያስ 61:1-3፤ ሥራ 17:30, 31) ስለዚህ መዝናኛ በሕይወታችን ውስጥ ዋናውን ቦታ እንዲይዝ መፍቀድ እንደሌለብን ግልጽ ነው። ሁኔታውን ምግብን ለማጣፈጥ በሚጨመር ትንሽ ጨው ወይም በአንድ ዓይነት ልዩ ቅመም ልናስረዳ እንችላለን። ማጣፈጫውን በምግቡ ላይ የምትነሰንሱት የምግቡን ጣዕም እስኪያጠፋው ድረስ በብዛት ነውን? በእርግጥ አይደለም። ኢየሱስ በዮሐንስ 4:34 እና በማቴዎስ 6:33 ላይ ከተናገራቸው ቃላት ጋር በመስማማት ዋናው የሚያሳስበን ነገር ምግባችን የሆነው የአምላክን ፈቃድ መፈጸም መሆን ይኖርበታል። ስለዚህ መዝናኛ እንደማጣፈጫው ጨው ወይም ቅመም ይሆንልናል። መዝናኛ ማደስና ማጎልበት እንጂ ማድከምና ኃይላችንን ማሟጠጥ የለበትም።
10. ከጊዜ አንፃር ሁላችንም መዝናኛዎቻችንን እንደገና መመርመር የሚኖርብን ለምንድን ነው?
10 እስቲ ቆም በሉና አስቡት፦ አብዛኞቹ ሰዎች ለመዝናኛ የሚሰጡት ጊዜና ትኩረት ልከኛ እንደሆነ ይናገሩ የለምን? ከልክ ያለፈ እንደሆነ ቢሰማቸው ኖሮ መስተካከል ያደርጉ ነበር። ታዲያ ይህ እያንዳንዳችን መዝናኛ በሕይወታችን ውስጥ በእርግጥ ምን ያህል ቦታ እንደያዘ ቆም ብለን በጥሞናና በግልጽ መመርመር እንዳለብን አያመለክትምን? ቀስ ብሎ አድብቶ ዋና ነገር ይሆንብን ይሆንን? ለምሳሌ ያህል ወደ ቤት ወዲያው እንደተመለስን ቴሌቪዥን እንከፍታለንን? በየሳምንቱ ለምሳሌም ሁልጊዜ ዐርብ ወይም ቅዳሜ ማታ ለመዝናኛ ከፍተኛ ጊዜ መመደብ ለምዶብናልን? ያ ሰዓት ደርሶና እኛም እቤት ተገኝተን የታሰበው መዝናኛ ባይኖር ቅር እንሰኛለንን? ሁለት ተጨማሪ ጥያቄዎች፦ ከማኅበራዊው መዝናኛ ማግስት በጣም በማምሸታችን ወይም ብዙ ርቀት በመጓዛችን ምክንያት እንደ ደከመን፣ ምናልባትም በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ለመካፈል ወይም ለአሠሪያችን ተገቢውን ጥሩ አገልግሎት ለመስጠት እስከማንችል ድረስ ኃይላችን የተሟጠጠ ሆኖ ይሰማናልን? አልፎ አልፎ የምናደርገውም ይሁን አዘውትረን፣ መዝናኛችን ይህ ውጤት ካለው በእርግጥ ተገቢና ሚዛናዊ መደሰቻ ነውን?—ከምሳሌ 26:17-19 ጋር አወዳድሩ።
11. የመዝናኛችንን ዓይነት መመርመር ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
11 በተጨማሪም የመዝናኛችንን ዓይነት ብንመረምር ጥሩ ሊሆን ይችላል። የአምላክ አገልጋዮች መሆናችን መዝናኛችን ትክክል እንደሚሆን ዋስትና አይሆንም። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ቀጥሎ የጻፈላቸውን አስቡ፦ “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትም በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።” (1 ጴጥሮስ 4:3) እዚህ ላይ ጴጥሮስ ወንድሞቹ ዓለማውያን የሚያደርጉትን ነገር በመከተላቸው እነርሱን ለመውቀስ ጣቱን እየቀሰረባቸው አልነበረም። ሆኖም አንድ ሰው በቀላሉ ወደ ጎጂ መዝናኛ ላይ ሊወድቅ ስለሚችል ክርስቲያኖች (ያኔ የነበሩትም ሆኑ የዛሬዎቹ) ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል።—1 ጴጥሮስ 1:2፤ 2:1፤ 4:7፤ 2 ጴጥሮስ 2:13
ከወጥመዶች ተጠንቀቁ
12. 1 ጴጥሮስ 4:3 ጎላ አድርጎ የሚገልጸው ምን ዓይነት ወጥመድን ነው?
12 መጠንቀቅ ያለብን ከምን ዓይነት ወጥመዶች ነው? ጴጥሮስ “ስካርን፣ ዘፈንን [ፈንጠዝያ አዓት] ያለ ልክ መጠጣትን” ጠቅሷል። አንድ ጀርመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ እዚህ ላይ የተሠራባቸው የግሪክኛ ቃላት “በአብዛኛው ይሠሩ የነበሩት በማህበራዊ ግብዣ ላይ መጠጣትን” እንደነበረ ይገልጻሉ። አንድ የስዊስ ፕሮፌሰር “መግለጫው ከተደራጁ ስብሰባዎች ወይም የተገለጹት አሳፋሪ ድርጊቶች ከሚካሄዱባቸው የዘወትር ክለቦች ጋር የተያያዘ መሆን አለበት” በማለት እነዚህ ተግባሮች በዚያን ጊዜ የተለመዱ እንደነበሩ ጽፈዋል።
13. በግብዣዎች ስብሰባዎች ላይ መጠጥ ማቅረብ ወጥመድ ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 5:11, 12)
13 በትላልቅ ማኅበራዊ ግብዣዎች ላይ የአልኮል መጠጦችን መውሰድ ብዙዎችን አጥምዷቸዋል። በመጠኑ መጠጣትን መጽሐፍ ቅዱስ ስለማይከለክል ወጥመድ የሆነባቸው የአልኮል መጠጦችን በመጠኑ መጠጣታቸው አይደለም። ለዚህም ማስረጃ ካስፈለገን ኢየሱስ በቃና የሠርግ ድግስ ላይ ውኃውን ወደ ወይን ለውጧል። አምላክ ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ ጋር ከመሆን ስለመራቅ የሰጠውን ምክር ኢየሱስ ያከብር ስለነበረ በሠርጉ ላይ ከልክ ያለፈ ያልጠጣ መሆን ይኖርበታል። (ምሳሌ 23:20, 21) ይሁን እንጂ ይህን ዝርዝር ተመልከቱ፦ የድግሱ አሳላፊም በሌላ ድግስ ላይ መጀመሪያ መልካሙ የወይን ጠጅ ይቀርብና ‘ሰዎቹ ከሰከሩ በኋላ ግን መናኛውን’ እንደሚያቀርብ ተናግሯል። (ዮሐንስ 2:10) ስለዚህ በአይሁድ ሠርግ ላይ ለሁሉም የሚበቃ ወይን ስለሚኖር መስከር የተለመደ ነበር።
14. ክርስቲያን ጋባዦች የአልኮል መጠጦች ሊያመጡ የሚችሉትን ወጥመድ ሊቋቋሙት የሚችሉት እንዴት ነው?
14 በዚህም መሠረት አንዳንድ ክርስቲያኖች ሰዎችን ሲጋብዙ ወይን ጠጅ፣ ቢራና ሌሎችንም የአልኮል መጠጦች የሚያቀርቡት ከእንግዶቻቸው ጋር ሆነው ተጋባዦቹ የሚቀርብላቸውን ወይም የሚወስዱትን መጠን መቆጣጠር የሚችሉ ከሆነ ብቻ እንዲሆን ወስነዋል። የተጋባዦች ቁጥር እንደተጠቀሱት የአይሁድ ሠርጎች ጋባዡ ሊቆጣጠረው ከሚችለው በላይ ብዙ ከሆነ አልኮል በብዛት ማቅረብ አደገኛ ወጥመድ ሊሆን ይችላል። መጠጣትን ለማቆም ታግሎ ያሸነፈ ሰው በግብዣው ላይ ይገኝ ይሆናል። አልኮሉን ያለቁጥጥር ማግኘት መቻሉ ከልክ ያለፈ እንዲጠጣ ሊፈትነውና የመዝናኛውን ወቅት ለሁሉም ሊያበላሽባቸው እንደሚችል ልትገነዘቡ ትችላላችሁ። አንድ በጀርመን የሚኖር የበላይ ተመልካችና የልጆች አባት የሆነ ወንድም ቤተሰቡ በማኅበራዊ ግብዣ ላይ በመገኘት ከመሰል አማኞች ጋር አብረው በመሆናቸው እንደሚጠቀሙ አስተያየቱን ሰጠ። ይሁንና ቢራ በቀላሉ ማግኘት በሚቻልበት ጊዜ ችግር የማድረስ ከፍተኛ አጋጣሚ እንዳለው ጨምሮ ተናግሯል።
15. ማኅበራዊ ግብዣዎችን በሚመለከት ተገቢ አመራር ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው?
15 የቃናው ሠርግ “አሳዳሪ” (የግብዣ ኃላፊ የ1980 ትርጉም) ነበረው። (ዮሐንስ 2:8) ይህ ማለት ግን በቤታቸው ውስጥ ለምግብ ወይም አብረው ጊዜ ለማሳለፍ አንድን ቡድን የጋበዙ ሰዎች ኃላፊ መሾም አለባቸው ማለት አይደለም። ባልየው ሁኔታውን የመቆጣጠር ኃላፊነት ይኖርበታል። ይሁን እንጂ ተጋባዡ ቡድን ሁለት ቤተሰቦችን የያዘም ይሁን ወይም ከዚያ በላይ የሚካሄደውን ሁኔታ የሚታዘብ አንድ ሰው መኖር እንዳለበት ግልጽ መሆን ይኖርበታል። ብዙ ወላጆች ወንድ ልጃቸው ወይም ሴት ልጃቸው ለማኅበራዊ ግብዣ በሚጋበዙበት ጊዜ በግብዣው ላይ ኃላፊነት ወስዶ እንዲቆጣጠር የተመደበ ሰው መኖሩን ያረጋግጣሉ። መላውን ግብዣ ማን እንደሚቆጣጠርና በግብዣው ቦታ እስከመጨረሻ የሚገኝ መሆን አለመሆኑን ለማጣራት በመጀመሪያ ጋባዡን ያነጋግራሉ። አዋቂዎችም ሆኑ ወጣቶች አብረው በመሆን መደሰት ይችሉ ዘንድ ክርስቲያን ወላጆች በግብዣው ላይ ለመገኘት ፕሮግራማቸውን አስተካክለዋል።
16. የተጋበዙትን ቁጥር በተመለከተ ሊታሰብባቸው የሚገቡት ተገቢ ነገሮች ምንድን ናቸው?
16 የካናዳው የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ቅርንጫፍ እንደሚከተለው ጽፏል፦ “በማህበራዊ ግብዣ የተጋባዦችን ቁጥር መወሰንን በሚመለከት የተሰጠው ምክር አንዳንድ ሽማግሌዎች በሠርግ ግብዣ ላይ ብዙ ሰው መጥራት ማድረግ ምክሩን መጻረር እንደሆነ አድርገው ተረድተውታል። ሽማግሌዎቹ ማህበራዊ ግብዣዎቻችንን በመጠኑና ልንቆጣጠረው በምንችለው መጠን እንድናደርግ ከተመከርን በሠርግ ግብዣ ላይ 200 ወይም 300 ሰዎች መጥራት ስህተት ነው ብለው ደምድመዋል።”a በተጋባዦቹ ቁጥር ላይ የተወሰነ ገደብ አበጅቶ ከዚህ አትለፉ ከማለት ይልቅ በግብዣው ላይ የተገኙት ምንም ያህል ብዛት ይኑራቸው፣ ዋና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ተገቢ የሆነ ቁጥጥር ወይም ታዛቢነት እንዲኖር ከማድረጉ ላይ መሆን አለበት። ኢየሱስ ያቀረበው የወይን መጠን በቃና በነበረው ሠርግ ላይ በጣም ብዛት ያላቸው ቡድኖች እንደተገኙ ያመለክታል፤ ይሁን እንጂ ግብዣው ተገቢ ቁጥጥር እንደተደረገለት ግልጽ ነው። በዚያ ዘመን ይደረጉ የነበሩ ሌሎች ድግሶች ግን ተገቢ ቁጥጥር አይደረግላቸውም ነበር፤ በቂ ቁጥጥር እንዳይኖራቸው ያደረገው አንዱ ምክንያት የሰዎቹ ብዛት ሊሆን ይችላል። ግብዣው ሠፊ በሆነ መጠን አስቸጋሪነቱም በዚያው ልክ ከፍ ያለ ነው፤ ምክንያቱም ከልክ ማለፍ ለሚቀናቸው ደካማ ሰዎች ዓይን እንዲያወጡ ያመቻልና። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ቁጥጥር በማይደረግባቸው ግብዣዎች ላይ አጠያያቂ ተግባሮችን ሊያስፋፉ ይችላሉ።—1 ቆሮንቶስ 10:6-8
17. አንድ ግብዣ በሚታቀድበት ጊዜ ክርስቲያናዊው ሚዛን ሊገለጽ የሚችለው እንዴት ነው?
17 የማህበራዊ ግብዣ መልካም ቁጥጥር የድግሡን ዕቅድና ዝግጅትንም ያጠቃልላል። ይህም ድግሱን ልዩ ወይም የማይረሳ ለማድረግ ሲባል ባሕላዊ የዳንስ ምሽቶች ወይም ፊት ተሸፋፍኖ የባሕል ልብሶች የሚለበሱባቸው ዓለማዊ ፓርቲዎችን የመሰለ ቅልጥ ያለ ድግስ ማዘጋጀትን አይጠይቅም። ታማኞቹ እሥራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ ሁሉም በግብፅ ወይም በሌላ አገር እንደነበሩት አረማውያን የሚለብሱባቸውን ፓርቲዎች ለማዘጋጀት ሲያቅዱ በዓይነ ሕሊናችሁ ሊታያችሁ ይችላልን? የሥጋ ፍትወትን የሚያነሳሳ ዳንስ ወይም በአረማውያን ዘንድ ተወዳጅ የነበረውን ቅጥ የለሽ ሙዚቃ ያዘጋጁ ነበርን? በሲና ተራራ ሳሉ የተጠመዱት በጊዜው በነበረውና በግብፅ ተወዳጅ በነበረ ሙዚቃና ዳንስ ሊሆን ይችላል። ያንን መዝናኛ አምላክና የእሱ የጎለመሰ አገልጋይ የነበረው ሙሴ እንዴት እንደተመለከቱት እናውቃለን። (ዘጸአት 32:5, 6, 17-19) ስለዚህ የአንድ ማኅበራዊ ድግስ አዘጋጅ ወይም ተቆጣጣሪ ዘፈን ወይም ዳንስ መኖሩ ተገቢ ስለመሆኑ ወይም አለመሆኑ ሊያስብበት ይገባል፤ ከኖረም ከክርስቲያናዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ እንዲሆን ማድረግ አለበት።—2 ቆሮንቶስ 6:3
18, 19. ኢየሱስ ወደ ሠርግ ከመታደሙ ምን ማስተዋል እናገኛለን? ይህንንስ ማስተዋል ልንሠራበት የምንችለው እንዴት ነው?
18 በመጨረሻም ‘ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሠርጉ መታደማቸውን’ እናስታውሳለን። (ዮሐንስ 2:2) እርግጥ ነው፣ አንድ ግለሰብ ክርስቲያን ወይም ቤተሰብ ሌሎችን የሚጎበኘው አስደሳችና የሚያንጽ ጊዜ አብሮ ለማሳለፍ ብቻ ብሎ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ቅድመ ዝግጅት ለተደረገባቸው ማህበራዊ ድግሶች በዚያ የሚገኙት እነማን መሆን እንዳለባቸው አስቀድሞ ማወቁ ችግሮች እንዳይደርሱ ለመከላከል እንደሚረዳ የተገኘው ተሞክሮ ያሳያል። የዚህ አስፈላጊነት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በቴኔሲ ከተማ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ የሚገኙ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ባሳደገ አንድ ሽማግሌ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። እሱ ወይም ሚስቱ አንድን ግብዣ ከመቀበላቸው ወይም ልጆቻቸው በግብዣው ላይ እንዲገኙ ከመፍቀዳቸው በፊት ተጋባዦቹ የታወቁና የተወሰኑ መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ጋባዡን ይጠይቁ ነበር። ስለዚህ የዚህ ወንድም ቤተሰብ ለምግብም ይሁን ለሽርሽር ወይም ኳስ ጨዋታ በመሳሰሉ የሰውነት እንቅስቃሴ የሚደረግባቸው ሥፍራዎች ለሁሉም ክፍት በሆኑ ስብሰባዎች በመሄዳቸው ምክንያት በአንዳንዶች ላይ ከደረሱት ወጥመዶች ተጠብቀዋል።
19 ኢየሱስ ዘመዶችን፣ የቆዩ ጓደኞችን፣ ወይም በዕድሜ ወይም በኤኮኖሚያዊ ሁኔታ አቻ የሆኑትን ሰዎች ብቻ ወደ ግብዣ መጥራትን ነቅፏል። (ሉቃስ 14:12-14፤ ከኢዮብ 31:16-19፤ ከሥራ 20:7-9 ጋር አወዳድሩ።) እነማንን ወደ ድግስህ እንደምትጠራ በጥንቃቄ የምትመርጥ ከሆነ በግብዣው ላይ የተለያየ ዕድሜና ሁኔታ ያላቸውን ክርስቲያኖች ከየዓይነቱ ለመጨመር ቀላል ነው። (ሮሜ 12:13፤ ዕብራውያን 13:2) ከተጋባዦችህ መካከል ጥቂቶቹ ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር በመሆን ሊጠቀሙ የሚችሉ በመንፈሳዊ ደካሞች የሆኑ ወይም አዳዲሶች ሊሆኑ ይችላሉ።—ምሳሌ 27:17
መዝናኛን በቦታው
20, 21. መዝናኛ በሕይወታችን ተገቢ ቦታ ሊኖረው የሚችለው ለምንድን ነው?
20 ፈሪሃ አምላክ ያለን ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ለመዝናኛችን ትኩረት መስጠትና መዝናኛው ተገቢ ስለመሆኑ እንዲሁም ለእርሱ በምናውለው ጊዜ ረገድ ሚዛናዊ የመሆናችን ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባል። (ኤፌሶን 2:1-4፤ 5:15-20) በመንፈስ የተመራው የመክብብ ጸሐፊም እንዲሁ ተሰምቶታል፦ “ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፤ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል” ብሏል። (መክብብ 8:15) እንዲህ ዓይነቱ ሚዛናዊ የሆነ መዝናኛ ሰውነትን ሊያድስና በአሁኑ ሥርዓት የተለመዱ የሆኑትን ችግሮችና ብስጭቶች ለመቋቋም ሊረዳ ይችላል።
21 ለምሳሌ ያህል አንዲት ኦስትሪያዊት አቅኚ ለቀድሞ ጓደኛዋ እንደሚከተለው ስትል ጻፈችላት፦ “ከትናንት በስቲያ በጣም ጥሩ ሽርሽር ነበረን። 50 የምንሆን በፌርላክ አጠገብ ወደሚገኘው ትንሽ ሐይቅ ሄደን ነበር። በመለስተኛ አውቶቡሱ ሦስት የብረት ምድጃዎችን፣ ታጣፊ ወንበሮችን፣ ጠረጴዛዎችንና የጠረጴዛ ቴኒስ መጫወቻዎችን ሳይቀር ይዞ ጉዞውን የመራው ወንድም ቢ—— ነበር። በሽርሽሩ በጣም ተደስተናል። አንዲት እህት አኮርዲዮን ይዛ መጥታ ነበርና ብዙ የመንግሥት መዝሙሮችን ዘመርን። ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች ወንድሞች ሁሉ በህብረት ጉዞው በጣም ተደስተውበታል።” ይህች እህት ከልክ በላይ እንደመጠጣት ወይም ስድ ጠባይ ከመሳሰሉት ወጥመዶች ነፃ በሆነ ጥሩ ቁጥጥር በተደረገበት መዝናኛ በመካፈሏ አስደሳች ትዝታ አሳድሮባታል።—ያዕቆብ 3:17, 18
22. በማህበራዊ መዝናኛ ስንደሰት አስቀድመን ልናስብበት የሚገባን ምን ማስጠንቀቂያ ነው?
22 ጳውሎስ ፍጹም ላልሆነው ሥጋችን ምኞቶች እንዳንሸነፍ፣ ለፈተና አጋልጠው የሚሰጡን ዕቅዶችን ባለማድረግም እንኳን ሳይቀር እንድንጠነቀቅ አጥብቆ አሳስቦናል። (ሮሜ 13:11-14) ይህም ለማኅበራዊ መዝናኛዎች የምናደርጋቸውን ዕቅዶች ይጨምራል። የጳውሎስን ምክር ለመዝናኛ በምናውልበት ጊዜ አንዳንዶችን ለመንፈሳዊ ውድቀት ያበቋቸውን ሁኔታዎች ለማስወገድ እንችላለን። (ሉቃስ 21:34-36፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:19) በዚህ ፈንታ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ጠብቀን ለመኖር የሚረዳንን ጤናማ መዝናኛ በጥበብ እንመርጣለን። እንዲህ በማድረጋችንም ከአምላክ መልካም ስጦታዎች መካከል እንደ አንዱ ሊቆጠር ከሚችለው ማህበራዊ መዝናኛ ልንጠቀም እንችላለን።—መክብብ 5:18
[የግርጌ ማስታወሻ]
a 4-105 የመጠበቂያ ግንብ እትም ስለ ሠርግና ስለ ሠርግ ድግሦች ሚዛናዊ ምክር ይዞ ነበር። ለመጋባት የተዘጋጁ ወንድና ሴት ሙሽራዎች እንዲህም እነርሱን የሚረዷቸው ሌሎች ሰዎች የሠርግ ድግሱን ፕላን ከማውጣታቸው አስቀድሞ ይህን ርዕሰ ትምህርት ቢመለከቱት ሊጠቅማቸው ይችላል።
ምን ተምረናል?
◻ በማኅበራዊ መዝናኛ ስለመደሰት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ሚዛናዊ አመለካከት እናገኛለን?
◻ ለመዝናኛ ከምናውለው ጊዜ አንፃርና ስለ መዝናኛው ዓይነት ልናስብበት የሚገባን ለምንድን ነው?
◻ አንድ ክርስቲያን ከወጥመዶች ራሱን ለመጠበቅ ሊያደርጋቸው የሚችላቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
◻ መዝናኛ ተገቢና ሚዛናዊ ከሆነ ለክርስቲያኖች ምን ያከናውንላቸዋል?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ግብዣ ላይ አንድ ጋባዥ ወይም አንድ ተቆጣጣሪ ተጋባዦች በወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቁ የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት