የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 1/15 ገጽ 14-19
  • ይሖዋ በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በፈቃደኛ ልብ መገፋፋት
  • በደስታ እንድንሰጥ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?
  • ስጦታዎችን በጥንቃቄ መያዝ
  • በግድ አይደለም
  • ለአምላክ ስጦታዎች አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ
  • ‘አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳል’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ይሖዋ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳል
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2019
  • የመንግሥቱ ሥራዎች ወጪ የሚሸፈንበት መንገድ
    የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 1/15 ገጽ 14-19

ይሖዋ በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል

“እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ። በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።”—2 ቆሮንቶስ 9:7

1. አምላክና ክርስቶስ ደስተኛ ሰጪዎች የሆኑት እንዴት ነው?

በደስታ ለመስጠት የመጀመሪያ የሆነው ይሖዋ ነው። ለአንድያ ልጁ በደስታ ሕይወት ሰጥቶ መላእክትንና ሰዎችን ወደ ሕልውና እንዲያመጣ ተጠቅሞበታል። (ምሳሌ 8:30, 31፤ ቆላስይስ 1:13-17) አምላክ ከሰማይ ዝናብንና ልባችንን በደስታ ለመሙላት ፍሬ የሚሆንባቸውን ወራት ጨምሮ ሕይወትን እስትንፋስንና ሁሉን ነገር ሰጥቶናል። (ሥራ 14:17፤ 17:25) በእርግጥም አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ደስተኛ ሰጪዎች ናቸው። የሚሰጡትም በደስታና ያለምንም የስስት መንፈስ ነው። ይሖዋ የሰው ልጆችን ዓለም በጣም ከመውደዱ የተነሣ “በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ አንድያ ልጁን አሳልፎ ሰጥቷል።” ኢየሱስም ያለምንም ማጉረምረም “ሕይወቱን ለብዙዎቹ ቤዛ ሰጥቷል።”—ዮሐንስ 3:16፤ ማቴዎስ 20:28

2. ጳውሎስ በተናገረው መሠረት አምላክ የሚወደው እንዴት ያሉ ሰጪዎችን ነው?

2 ስለዚህ የአምላክና የክርስቶስ አገልጋዮች ደስተኛ ሰጪዎች መሆን ይኖርባቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ መስጠት ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በ55 እዘአ ገደማ በጻፈው በሁለተኛው ደብዳቤው ላይ ተብራርቷል። በግልጽ እንደሚታየው ጳውሎስ በተለይ የተቸገሩ ክርስቲያኖችን ለመርዳት ስለሚደረግ የፈቃደኝነትና የግል የገንዘብ መዋጮ ለማመልከት እንዲህ ብሏል፦ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።” (2 ቆሮንቶስ 9:7፤ ሮሜ 15:26፤ 1 ቆሮንቶስ 16:1, 2፤ ገላትያ 2:10) የአምላክ ሕዝቦች የመስጠት አጋጣሚ በሚያገኙበት ጊዜ ምን አድርገዋል? ጳውሎስ ስለ መስጠት ከሰጠው ምክርስ ምን ልንማር እንችላለን?

በፈቃደኛ ልብ መገፋፋት

3. እሥራኤላውያን ለይሖዋ አምልኮ የሚያገለግለው የመገናኛ ድንኳን ሲሠራ ድጋፍ የሰጡት እስከምን ድረስ ነው?

3 የአምላክ ሕዝቦች መለኮታዊውን ዓላማ ለመደገፍ ራሳቸውንና ሀብታቸውን እንዲሰጡ የሚገፋፋቸው ፈቃደኛ ልባቸው ነው። ለምሳሌ ያህል በሙሴ ዘመን ይኖሩ የነበሩት እሥራኤላውያን ለይሖዋ አምልኮ የሚያገለግለው የመገናኛ ድንኳን ሲሠራ በደስታ ረድተዋል። የአንዳንድ ሴቶች ልብ የፍየል ጠጉርን እንዲፈትሉ ሲገፋፋቸው የአንዳንድ ወንዶች ልብ ደግሞ በእጅ ጥበባቸው እንዲያገለግሉ ገፋፍቷቸዋል። ሕዝቡ በደስታ ወርቅ፣ ብር፣ እንጨት፣ ልብስና ሌሎች ነገሮችንም “ለይሖዋ ስጦታ በፈቃዳቸው” ሰጥተዋል። (ዘጸአት 35:4-35) ሕዝቡ በጣም ለጋሶች ከመሆናቸው የተነሣ “ያመጡት ነገር ሥራን ሁሉ ለመፈጸም በቅቶ ገና ይተርፍ ነበር”—ዘፀአት 36:4-7

4. ዳዊትና ሌሎች ሰዎች ለቤተ መቅደሱ መሥሪያ ያዋጡት በምን ዝንባሌ ነበር?

4 በመቶ የሚቆጠሩ ዓመታት ካለፉ በኋላ ንጉሥ ዳዊት በልጁ በሰለሞን ለሚሠራው የይሖዋ ቤተመቅደስ ብዙ ስጦታ አዘጋጅቶ ነበር። “የአምላክን ቤት ስለወደደ የግል ገንዘቡ” የነበረውን ወርቅና ብር ሰጠ። መሳፍንት፣ አለቆችና ሌሎችም “ለይሖዋ ፈቅደው ሰጡ።” ውጤቱስ ምን ነበር? “ሕዝቡም ፈቅደው ሰጥተዋልና በፍጹም ልባቸውም ለይሖዋ በፈቃዳቸው አቅርበዋልና ደስ ብሏቸው ነበር።” (1 ዜና 29:3-9) ደስተኛ ሰጪዎች ነበሩ።

5. እሥራኤላውያን ለብዙ መቶ ዓመታት እውነተኛ አምልኮን የደገፉት እንዴት ነው?

5 እሥራኤላውያን በመቶ ለሚቆጠሩ ዘመናት የመገናኛውን ድንኳን፣ በኋላም ቤተ መቅደሱ ሲሠራና በዚያ የሚከናወኑትን ክህነታዊና ሌዋዊ አገልግሎቶች ለመደገፍ ታድለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በነህምያ ዘመን አይሁድ የአምላክን ቤት ችላ ማለት እንደሌለባቸው በመገንዘብ ንጹሕ አምልኮን ለመንከባከብ ስጦታ ለመስጠት ቆርጠው ነበር። (ነህምያ 10:32-39) በተመሳሳይ ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ ቦታዎችን በጥሩ ሁኔታ ለመያዝና እውነተኛ አምልኮን ለመደገፍ በደስታ የፈቃደኛነት ዕርዳታ ያደርጋሉ።

6. ክርስቲያኖች በደስተኝነት የሰጡባቸውን ምሳሌዎች ግለጽ?

6 የቀድሞ ክርስቲያኖችም ደስተኛ ሰጪዎች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ምሥክሮች ዛሬ በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትናንሽ ጽሑፎች ማህበር ለሚላኩት ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የእንግድነት አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው ሁሉ ጋይዮስ ለመንግሥቱ ፍላጎት ሲሉ ለሚጓዙት “የታመነ ሥራ” ይሠራ ነበር። (3 ዮሐንስ 5-8) እነዚህ ወንድሞች ከጉባኤ ወደ ጉባኤ እንዲዘዋወሩ ለማድረግና ለእነሱ የእንግድነት አቀባበል ለማድረግ አንዳንድ ወጪ ይጠይቃል። ይህም ጉዞአቸው በመንፈሳዊ ረገድ ጠቃሚ ነው።—ሮሜ 1:11, 12

7. የፊልጵስዩስ ሰዎች ቁሳዊ ሀብታቸውን የተጠቀሙበት እንዴት ነበር?

7 ጉባኤዎች በአጠቃላይ ሲታይ ሥጋዊ ሀብታቸውን የመንግሥቱን ፍላጎት ለማስፋፋት ይጠቀሙበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ የነበሩትን አማኞች እንዲህ በማለት ነግሮአቸዋል፦ “በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ያስፈለገኝን ሰዳችሁልኝ ነበርና። በስሌታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታውን ፈላጊ አይደለሁም።” (ፊልጵስዩስ 4:15-17) የፊልጵስዩስ ሰዎች በደስታ ሰጥተዋል። ነገር ግን በዚህ መንገድ በደስታ እንድንሰጥ የሚያነሣሱን ነገሮች ምንድን ናቸው?

በደስታ እንድንሰጥ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

8. የአምላክ መንፈስ ሕዝቡ ደስተኛ ሰጪዎች እንዲሆኑ እንደሚቀሰቅሳቸው እንዴት ልታረጋግጥ ትችላለህ?

8 የይሖዋ ሕዝቦች በደስታ እንዲሰጡ የሚያነሳሳቸው የይሖዋ ፈጣን ኃይል ወይም የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ነው። የይሁዳ ክርስቲያኖች በተቸገሩ ጊዜ ሌሎች አማኞች በሥጋዊ እንዲረዱአቸው የአምላክ መንፈስ አነሣስቷቸዋል። ጳውሎስ በቆሮንቶስ የነበሩ ክርስቲያኖች ይህን ዓይነቱን ዕርዳታ ለማድረግ የሚቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ለማበረታታት በመቄዶንያ የነበሩትን ጉባኤዎች ምሳሌ ጠቅሶላቸዋል። የመቄዶንያ ክርስቲያኖች ስደትና ድህነት ያጋጥማቸው የነበሩ ቢሆንም ከችሎታቸው በላይ በመስጠት የወንድማማች ፍቅር አሳይተዋል። እንዲያውም የመስጠት መብት እንዲያገኙ እስከ መለመን ደርሰዋል! (2 ቆሮንቶስ 8:1-5) የአምላክ ሥራ በሀብታሞች እርዳታ ላይ ብቻ የተመካ አይደለም። (ያዕቆብ 2:5) በሥጋዊ ድሆች የሆኑ ውስን አገልጋዮቹም የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ወጪ በመሸፈን ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ አበርክተዋል። (ማቴዎስ 24:14) ሆኖም በለጋሥነታቸው ምክንያት ጉዳት አልደረሰባቸውም። ይህም የሆነው አምላክ ሕዝቡ ለዚህ ሥራ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ሁልጊዜ ስለሚያቀርብላቸውና በሥራው መቀጠልና መጨመር በስተጀርባ ያለው የአምላክ መንፈስ ስለሆነ ነው።

9. እምነት እውቀትና ፍቅር ደስተኛ ሰጪዎች እንዲሆኑ እንደሚቀሰቅሳቸው እንዴት እናውቃለን?

9 እምነት፣ እውቀትና ፍቅር በደስታ እንድንሰጥ ያነሳሳናል። ጳውሎስ “(እናንተ የቆሮንቶስ ሰዎች) በነገር ሁሉ በእምነትና በቃል፣ በዕውቀትም፣ በትጋትም ሁሉ ለእኛም በፍቅራችሁ እንደተረፋችሁ በዚህ ቸር ሥራ ደግሞ ትረፉ። ትዕዛዝ እንደምሰጥ አልልም። ነገር ግን በሌሎች ትጋት በኩል የፍቅራችሁን እውነተኛነት ደግሞ ልመረምር እላለሁ” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 8:7, 8) በተለይ ሰጪው ያለው መተዳደሪያ ውስን በሚሆንበት ጊዜ ለይሖዋ ሥራ መስጠት በአምላክ የወደፊት ዝግጅቶች መተማመንን ይጠይቃል። በዕውቀት የተትረፈረፉ ክርስቲያኖች የይሖዋን ዓላማ ማገልገል ይፈልጋሉ። ለእሱና ለሕዝቡ ባላቸው ፍቅር የተትረፈረፉ ሰዎችም በሀብታቸው የሱን ዓላማ ለማራመድ በደስታ ይጠቀሙበታል።

10. የኢየሱስ ምሳሌነት ክርስቲያኖች በደስታ እንዲሰጡ ይገፋፋቸዋል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

10 የኢየሱስ ምሳሌነት ክርስቲያኖች በደስታ እንዲሰጡ ይገፋፋቸዋል። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች በፍቅር ተገፋፍተው እንዲሰጡ ካሳሰባቸው በኋላ እንዲህ አለ፦ “የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ቸር ስጦታ (የማይገባ ደግነት) አውቃችኋልና። ሀብታም ሲሆን እናንተ በእሱ ድህነት ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሃ ሆነ።” (2 ቆሮንቶስ 8:9) በሰማይ ሳለ ከማንኛውም የአምላክ ልጅ ይበልጥ ባለጠጋ የነበረው ኢየሱስ ራሱን አራቁቶ ሰው ሆነ። (ፊልጵስዩስ 2:5-8) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በዚህ ስስት በሌለበት መንገድ ድሀ በመሆን ለይሖዋ ስም መቀደስ ምክንያት ሆኗል። ቤዛውን ለሚቀበሉ የሰው ልጆች ጥቅም ሲል ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ከፍሏል። እኛም ከኢየሱስ ምሳሌነት ጋር በመስማማት ሌሎችን ለመርዳትና ለይሖዋ ስም መቀደስ ምክንያት ለመሆን በደስታ መስጠት አይኖርብንምን?

11, 12. ጥሩ ዕቅድ ማውጣት ደስተኛ ሰጪዎች እንድንሆን የሚያስችለን እንዴት ነው?

11 ጥሩ ዕቅድ ማውጣት በደስታ ለመስጠት ያስችላል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ” ብሏቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 16:1, 2) በዛሬው ጊዜ የመንግሥቱን ሥራ ለማራመድ እርዳታ ለማድረግ የሚፈልጉ ሁሉ ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ በግልና በፈቃደኛነት ከገቢያቸው ጥቂቱን ለዚህ ዓላማ ቢያስቀምጡ መልካም ያደርጋሉ። ግለሰብ ምሥክሮች፣ ቤተሰቦችና ጉባኤዎችም ይህን የመሰለ ጥሩ ዕቅድ በማውጣት እውነተኛ አምልኮን ለማሳደግ ዕርዳታ ሊያደርጉ ይችላሉ።

12 መዋጮ ለማድረግ ያወጣነውን ዕቅድ በሥራ ላይ ማዋል ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል። ኢየሱስ እንዳለው “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ደስተኛ ነው።” (ሥራ 20:35) ስለዚህ የቆሮንቶስ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም መዋጮአቸውን ለመላክ ያወጡትን የአንድ ዓመት እቅድ ለመፈጸም የጳውሎስን ምክር በመከተል ደስታቸውን ሊጨምሩ ይችሉ ነበር። “እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም” ብሏል። አንድ ሰው ባለው መጠን የሰጠው መዋጮ ከፍ ያለ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል። በአምላክ ካመንን ብዙ ያላቸው አባካኞች ሳይሆኑ ለጋሶች እንዲሆኑ ጥቂት ያላቸው እጦት እንዳያጋጥማቸው በማድረግ ነገሮችን ሊያስተካክልልን ይችላል።—2 ቆሮንቶስ 8:10-15

ስጦታዎችን በጥንቃቄ መያዝ

13. የቆሮንቶስ ሰዎች በዕርዳታ ያዋጡትን ገንዘብ ጳውሎስ በሚገባ እንደሚቆጣጠር እምነት ሊኖራቸው ይችል የነበረው ለምን ነበር?

13 ጳውሎስ የተቸገሩ አማኞች ቁሳዊ እርዳታ እንዲያገኙና በስብከቱ ሥራ ይበልጥ በታታሪነት እንዲጠመዱ የእርዳታ ዝግጅቱን በበላይነት ቢቆጣጠርም እሱም ሆነ ሌሎቹ ከተዋጣው ገንዘብ ለራሳቸው ጉዳይ አይወስዱም ነበር። (2 ቆሮንቶስ 8:16-24፤ 12:17, 18) ጳውሎስ በማንኛውም ጉባኤ ላይ ገንዘብ ነክ ሸክም በመጫን ፈንታ የራስን ቁሳዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ይሠራ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 4:12፤ 2 ተሰሎንቄ 3:8) ስለዚህ የቆሮንቶስ ሰዎች መዋጮዋቸውን ለጳውሎስ ሊያስረክቡ ለአንድ ታማኝና ታታሪ ለሆነ የአምላክ አገልጋይ በአደራ መስጠታቸው እንደነበረ ይረዱ ነበር።

14. በእርዳታ መዋጮዎች አጠቃቀም ረገድ የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ምን አድርጓል?

14 የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና የትናንሽ ጽሑፎች ማህበር በ1884 በሕግ ከተቋቋመ ጀምሮ እርዳታ ሰጪዎች ማህበሩ ለይሖዋ መንግሥት ሥራ ተብሎ በአደራ የሚቀበለውን ሁሉ በታማኝነት እንደሚቆጣጠር እርግጠኛ የሚሆኑበት ማስረጃ አላቸው። ማኅበሩ በማኅበሩ ቻርተር መሠረትም ከሁሉም የበለጠውን የሕዝቦች ፍላጎት ማለትም የመንፈሳዊ ነገሮችን ፍላጎት ለማሟላት ይጥራል። ይህም የሚደረገው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አዘጋጅቶ በማሰራጨትና ደህንነት እንዴት እንደሚገኝ በማስተማር ነው። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በግ መሰል ሰዎችን እየሰፋ ወደሚሄደው ድርጅቱ ማሰባሰቡን እያፋጠነ ነው። ለመንግሥቱ ስብከት ሥራ የተዋጡትን እርዳታዎች በጥበብ በመጠቀም ረገድ የተደረገውን ጥረት ይሖዋ የባረከው መሆኑም የመለኮታዊ ድጋፍ ግልጽ ማስረጃ ነው። (ኢሳይያስ 60:8, 22) በደስታ የሚሰጡ ሰዎችን ልብ መቀስቀሱን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን።

15. ይህ መጽሔት አልፎ አልፎ እርዳታ ስለመስጠት ማሳሰቢያ የሚሰጠው ለምንድን ነው?

15 ማህበሩ አልፎ አልፎ አንባቢዎችን ለዓለም አቀፉ የመንግሥት ስብከት ሥራ በፈቃደኛነት ዕርዳታ በመስጠት መብታቸው እንዲጠቀሙ ለማነቃቃት በዚህ መጽሔት አምዶች ይጠቀማል። ይህም የገንዘብ ልመና ሳይሆን አምላክ ባበለጸጋቸው መጠን የምሥራቹን ሥራ ለመደገፍ የሚፈልጉ ሰዎችን ለማሳሰብ ብቻ የሚደረግ ነው። (ሮሜ 15:16፤ 3 ዮሐንስ 2) ማህበሩ በእርዳታ የተሰጠውን ገንዘብ ሁሉ የይሖዋን ስምና መንግሥት ለማሳወቅ ቁጠባ በተሞላበት አያያዝ ይጠቀምበታል። ሁሉንም የእርዳታ መዋጮ በምስጋና እንቀበላለን ምስጋናችንንም እንገልጽላቸዋለን። ገንዘቡ የሚውለው የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማሠራጨት ነው። ለምሳሌ ያህል በብዙ አገሮች ያሉ ሚስዮናዊ ሥራዎችና የመጽሐፍ ቅዱስን ዕውቀት ለማዳረስ አስፈላጊ የሆኑት የሕትመት ግልጋሎቶች የሚተዳደሩትና የሚስፋፉት በዚሁ ገንዘብ ነው። በተጨማሪም ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረጉት መዋጮዎች ዋጋቸው እያሻቀበ ያለውን መጽሐፍ ቅዱሶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ድምፅ የተቀዳባቸውን የቴፕ ክሮችና ቪዲዮ ካሴቶችን ለማዘጋጀትና ለማቅረብ ያገለግላሉ። በዚህ መንገድም የመንግሥቱ ፍላጎቶች በደስተኛ ሰጪዎች ልግስና ይስፋፋል።

በግድ አይደለም

16. በሥጋ ሀብታሞች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ጥቂት ቢሆኑም ስጦታቸው የሚደነቀው ለምንድን ነው?

16 ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች በቁሳዊ ረገድ ሀብታሞች ናቸው። የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማራመድ የሚሰጡት ገንዘብ መጠነኛ ቢሆንም ዕርዳታቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ኢየሱስ አንዲት ድሃ መበለት ሁለት ሳንቲም በቤተ መቅደሱ መዝገብ ስትጥል ባየ ጊዜ እንዲህ አለ፦ “ይህች መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች። እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጉድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች።” (ሉቃስ 21:1-4) ስጦታዋ አነስተኛ ቢሆንም ደስተኛ ሰጪ ነበረች። ስጦታዋም ተደንቋል።

17, 18. ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 9:7 ላይ የተናገራቸው ቃላት ፍሬ ነገር ምንድን ነው? “ደስተኛ” ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል ምን ያመለክታል?

17 ለይሁዳ ክርስቲያኖች ይደረግ ስለነበረው የእርዳታ መሰብሰብ ሥራ ጳውሎስ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ሐዋርያው እዚህ ላይ እንደ ግሪክ ሰፕቱዋጅንት ትርጉም ምሳሌ 22:8⁠ን በከፊል መጥቀሱ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ይላል፦ “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ይባርካል፤ በሥራው የሚጐድለውንም ሁሉ ያሟላለታል።” (የሰፕቱዋጅንት መጽሐፍ ቅዱስ በቻርለስ ቶምፕሰን የተተረጐመ) ጳውሎስ “ይባርካል” የሚለውን “ይወዳል” በሚል ቃል ተክቶታል። ነገር ግን ከአምላክ ፍቅር የበረከት ምርት ስለሚገኝ በሁለቱ ቃላት መካከል ዝምድና አለ።

18 በደስታ የሚሰጥ ሰው ከልቡ ደስ እያለው ይሰጣል። እንዲያውም በ2 ቆሮንቶስ 9:7 ላይ “በደስታ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “በፍንደቃ” የሚል ትርጉም አለው። ምሁሩ አር ሲ ኤች ሌንስኪ ይህን ካመለከቱ በኋላ እንዲህ አሉ፦ “አምላክ የሚወደው የመስጠት አጋጣሚ ሲያገኝ እምነቱን በፈገግታ አጅቦ ሳይጨናነቅና ሳይጠበብ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ነው።” ይህን የመሰለ ደስተኛ መንፈስ ያለው ሰው በማጉረምረም ወይም ተገድዶ የሚሰጥ ሳይሆን ለመስጠት የሚጓጓ ነው። የመንግሥቱን ፍላጎቶች የሚደግፍ ስጦታ በመስጠት ረገድ ይህን የመሰለ የደስተኝነት መንፈስ ታሳያለህን?

19. የቀድሞ ክርስቲያኖች መዋጮ ያደርጉ የነበሩት እንዴት ነበር?

19 የቀድሞ ክርስቲያኖች የገንዘብ መሰብሰቢያ ሙዳየ ምጽዋት አያዞሩም ነበር። ወይም ደግሞ ለሃይማኖታዊ ዓላማ ከገቢያቸው አንድ አሥረኛውን በእርዳታ በመስጠት አሥራት አይከፍሉም ነበር። ከዚህ ይልቅ ስጦታዎቻቸው ሙሉ በሙሉ በፈቃደኝነት የሚደረጉ ነበሩ። በ190 እዘአ አካባቢ ወደ ክርስትና የተለወጠው ተርቱሊያን “የራሳችን የገንዘብ ካዝና ቢኖረንም ሃይማኖታችንን ለሽያጭ በማቅረብ የተገኘ የሃይማኖት ሽያጭ ገንዘብ የለንም። እያንዳንዱ ሰው ከፈለገ በወር ውስጥ አንዴ አነስተኛ ዕርዳታ ያስቀምጣል። ነገር ግን ይህን የሚያደርገው ደስ ካለውና ከቻለ ብቻ ነው። ምክንያቱም ግዴታ የለም። ሁሉም በፈቃደኝነት የሚደረግ ነው” በማለት ጽፏል።—አፖሎጂ ምዕራፍ 39

20, 21. የዚህ መጽሔት የቀድሞ እትም የአምላክን ዓላማ በገንዘብ ስለመደገፍ መብት ምን ብሏል? ይህስ አሁንም የሚሠራው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋን በሀብታችን ስናከብር ምን ውጤት ይገኛል?

20 በዘመናዊ የይሖዋ አገልጋዮች ዘንድም በፈቃደኛነት መስጠት የዘወትር ልማድ ሆኖ ቆይቷል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ዕርዳታ በማድረግ የአምላክን ዓላማ የመደገፍ መብታቸውን ሙሉ በሙሉ ያልተጠቀሙበት ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል ይህ መጽሔት በየካቲት 1883 እትም ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አንዳንዶች ለሌሎች ጥቅም ሲሉ ከፍተኛ የገንዘብ ሸክም ተሸክመዋል። ከዚህም የተነሣ የገንዘብ አቅማቸው ተሟጥጦ ወደማለቅ ደርሷል። ይህም ብቻ ሳይሆን እነዚህ . . . በዚህ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ የማይካፈሉ ሰዎች በዚህ ረገድ የሚደረገው ልምምድ ስለሚጐድላቸው ትልቅ ኪሣራ እየደረሰባቸው ነው።”

21 በአሁኑ ጊዜ ታላቁ ጭፍራ ወደ ይሖዋ ድርጅት ሲጐርፍና የአምላክ ሥራም ወደ ምሥራቅ አውሮፓና ከዚህ በፊት ሥራው ታግዶ ወደነበረባቸው ሌሎች አገሮችም ሲስፋፋ የሕትመት ተቋሞችንና ሌሎችንም ግልጋሎቶች የማስፋፋቱ አስፈላጊነት ጨምሯል። ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሶችንና ሌሎች ጽሑፎችን ማተም አስፈልጓል። ብዙ ቲኦክራቲካዊ ፕሮጀክቶች በመካሄድ ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ በቂ ገንዘብ ቢኖር አንዳንዶቹ ከአሁኑ በበለጠ ፍጥነት ሊራመዱ ይችሉ ነበር። በእርግጥ የሚያስፈልገውን ሁሉ አምላክ እንደሚያቀርብ እምነት አለን። “ይሖዋን በሀብታቸው የሚያከብሩ” ሰዎችም እንደሚባረኩ እናውቃለን። (ምሳሌ 3:9, 10) በእርግጥ “በበረከት የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል።” ይሖዋ “ልግስና ሁሉ እንድናሳይ በነገር ሁሉ ባለጠጎች ያደርገናል።” በደስታ የምንሰጠውም ስጦታ ብዙዎች እሱን እንዲያመሰግኑትና እንዲያወድሱት ያስችላቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 9:6-14

ለአምላክ ስጦታዎች አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ

22, 23. (ሀ) በቃላት ሊገለጽ የማይችለው የአምላክ ነፃ ስጦታ ምንድን ነው? (ለ) የይሖዋን ስጦታ ስለምናደንቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

22 ጳውሎስ ራሱ ጥልቅ በሆነ ምሥጋና ተገፋፍቶ “ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 9:15) ኢየሱስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖችና ለዓለም ሰዎች “የኃጢአት ማስተሠረያ” በመሆኑ በቃላት ሊገለጽ ለማይችለው የይሖዋ ነፃ ስጦታ መሠረትና መተላለፊያ ቦይ ነው። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) ይህም ስጦታ አምላክ በምድር ላይ ላሉ ሕዝቦች በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያሳየው “የላቀ የአምላክ የማይገባ ደግነት” ነው። ለእነዚህም ሕዝቦች መዳንና ለይሖዋ ክብር እንዲሁም ለስሙ ቅድስና ይትረፈረፋል።—2 ቆሮንቶስ 9:14

23 ይሖዋ ለሕዝቡ ላደረገው በቃላት ሊገለጽ የማይችል ነፃ ሥጦታውና ለሌሎች ብዙ መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ስጦታዎቹ ጥልቅ ምስጋናችን ይድረሰው። እንዲያውም ሰማያዊው አባታችን ለእኛ ያሳየው ደግነት በጣም ድንቅ ከመሆኑ የተነሣ ሰዎች በአንደበታቸው ሊገልጹ ከሚችሉት በላይ ነው! በእርግጥም ደስተኛ ሰጪዎች እንድንሆን ሊያነሣሣን ይገባል። እንግዲያውስ ከልብ በመነጨ አድናቆት የመጀመሪያውና ከሁሉ የበለጠ ደስተኛ ሰጪ የሆነውን የለጋሱን አምላካችንን የይሖዋን ዓላማ ለማራመድ የሚቻለንን ሁሉ እናድርግ!

ታስታውሳላችሁን?

◻ ፈቃደኛ ልብ የይሖዋ ሕዝቦች ምን እንዲያደርጉ ገፋፍቷቸዋል?

◻ ሰዎች በደስታ እንዲሰጡ የሚያነሣሣቸው ምንድን ነው?

◻ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሚቀበላቸውን ዕርዳታዎች ሁሉ የሚጠቀምባቸው እንዴት ነው?

◻ አምላክ የሚወደው ምን ዓይነቱን ሰጪ ነው? ለአምላክ ብዙ ስጦታዎች ያለንን አመስጋኝነት ማሳየት የሚኖርብን እንዴት ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመገናኛው ድንኳን ሲሠራ እሥራኤላውያን በታታሪነት ይሠሩና ለይሖዋም የልግስና ስጦታ ይሰጡ ነበር።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የድሃዋን መበለት የመሰሉ የዕርዳታ መዋጮዎች የሚደነቁና ከቁም ነገር የሚገቡ ናቸው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ