ቤተሰባችሁ ጥሩ አቋሙን ጠብቆ ወደ አምላክ አዲስ ዓለም እንዲገባ ለማድረግ ጣሩ
“አቤቱ [ይሖዋ አዓት]፣ አንተ ጠብቀን፣ ከዚህችም ትውልድ ለዘላለም ታደገን።”—መዝሙር 12:7
1, 2. (ሀ) አንዳንድ ቤተሰቦች እነዚህ የመጨረሻ ቀኖች በሚያመጧቸው ተፅዕኖዎች ሥር በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? (ለ) ክርስቲያን ቤተሰቦች ከጥፋት ለመትረፍ እንደሚፈልጉ የሚያሳዩት እንዴት ነው?
“ዛሬ ልቤ በደስታ ተሞልቷል!” በማለት ጆን የተባለ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ በደስታ ተናገረ። በደስታ የተሞላበት ምክንያት ምንድን ነው? “የ14 ዓመት ወንድ ልጄና የ12 ዓመት ሴት ልጄ ተጠመቁ” በማለት ሁኔታውን ገለጸ። ይሁን እንጂ ደስታው በዚህ አላበቃም። “ባለፈው ዓመት የ17 ዓመት ወንድ ልጄና የ16 ዓመት ሴት ልጄ ሁለቱም ረዳት አቅኚዎች ነበሩ” በማለት ጨምሮ ተናገረ።
2 በመካከላችን ያሉ ብዙ ቤተሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ በማዋላቸው ይህን የመሰሉ መልካም ውጤቶች እያገኙ ናቸው። አንዳንዶች ግን ችግሮች እያጋጠሟቸው ነው። ክርስቲያን የሆኑ አንድ ባልና ሚስት “አምስት ልጆች አሉን። እነሱን መያዝ አስቸጋሪ እየሆነብን ሄዷል። አንዱ ልጃችን ወደዚህ አሮጌ ሥርዓት ገብቷል። በአሁኑ ጊዜ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ወጣት ልጆቻችን የሰይጣን ዋና የጥቃት መስክ የሆኑ ይመስላል” ብለው ጽፈዋል። እንዲሁም በጋብቻቸው ውስጥ ከባድ ጥል ያጋጠማቸው ባልና ሚስቶችም አሉ። ይህም አንዳንድ ጊዜ ሳይፋቱ ተለያይቶ ወደመኖር ወይም ወደ መፋታት አድርሷቸዋል። የሆነው ሆኖ ክርስቲያናዊ ባሕርዮችን እየኮተኮቱ የሚያዳብሩ ቤተሰቦች “ከታላቁ መከራ” ሊተርፉና መጪው የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመግባት የሚያበቃ ጥሩ አቋም እንደያዙ ሊቀጥሉ ይችላሉ። (ማቴዎስ 24:21፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) ታዲያ የአንተ ቤተሰብ ጥሩ አቋሙን እንደያዘ መቀጠሉን ለማረጋገጥ ምን ልታደርግ ትችላለህ?
የሐሳብ ግንኙነታችሁን ማሻሻል
3, 4. (ሀ) በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ የሐሳብ ግንኙነት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? አብዛኛውን ጊዜ ከዚህ ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚነሱትስ ለምንድን ነው? (ለ) ባሎች ጥሩ አዳማጮች ለመሆን መጣር የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
3 ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት የጤናማ ቤተሰብ ደመ-ሕይወት ነው። የሐሳብ ግንኙነት በማይኖርበት ጊዜ ጭንቀትና ውጥረት ይጨምራል። ምሳሌ 15:22 “ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል” ይላል። አንድ የጋብቻ አማካሪ እንዲህ በማለት ሪፖርት አድርገዋል፦ “ካማከሩኝ ሚስቶች የምሰማው በጣም የተለመደ እሮሮ ‘እሱ አያናግረኝም’ እንዲሁም ‘አይሰማኝም’ የሚል ነው። ይህንን እሮሮ ለባሎቻቸው ስነግራቸው እኔንም አይሰሙኝም።”
4 የሐሳብ ግንኙነት እንዳይኖር የሚያደርገው ምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ወንዶችና ሴቶች የተለያዩ መሆናቸው ነው። አብዛኛውን ጊዜም ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን ለሌላ በሚያስተላልፉበት መንገድ ላይ ጎላ ያለ ልዩነት ይኖራቸዋል። አንድ ጽሑፍ እንደዘገበው ባል በንግግሮቹ “ቀጥተኛና ተግባራዊ የሆነ ሐሳብ ወደ መግለጽ ሲያዘነብል” “[ሚስት] ደግሞ ከምንም ነገር ይበልጥ የምትፈልገው ነገሮችን በእርሷ ቦታ ሆኖ እየተመለከተ የሚሰማትን ነው።” በትዳራችሁ ውስጥ ችግር ያመጣው ይህ ከሆነ ሁኔታውን ለማሻሻል ጣሩ። ምናልባት አንድ ክርስቲያን ባል የተሻለ አዳማጭ ለመሆን ጠንክሮ መጣር ይኖርበት ይሆናል። “ሰው ሁሉ” አለ ያዕቆብ “ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ . . . ይሁን።” (ያዕቆብ 1:19) ሚስትህ የምትፈልገው ስለ ስሜቷ እንድታስብላት ብቻ ሆኖ ሳለ እርሷን ከማዘዝ፣ በቁጣ ከመናገርና ከማነብነብ ተቆጠብ። (1 ጴጥሮስ 3:8) ምሳሌ 17:27 “ጥቂት ቃልን የሚናገር ሰው አዋቂ ነው” በማለት ይናገራል።
5. ባሎች ሐሳቦቻቸውንና ስሜቶቻቸውን በመግለጽ በኩል ሊያሻሽሉ የሚችሉባቸው አንዳንድ መንገዶች ምን ምን ናቸው?
5 በሌላው በኩል ደግሞ “ለመናገርም ጊዜ አለውና” ሐሳቦችህንና ስሜቶችህን የበለጠ መግለጽ መቻልን መማር ይኖርብህ ይሆናል። (መክብብ 3:7) ለምሳሌ ያህል ሚስትህ ላከናወነቻቸው ነገሮች የምስጋና ቃል ትለግሳለህን? (ምሳሌ 31:28) አንተን ለመደገፍና ቤተሰቡን ለመንከባከብ በርትታ ለሠራችው ሥራ አመስጋኝነትህን ታሳያለህን? (ከቆላስይስ 3:15 ጋር አወዳድር።) ወይም ምናልባት “የፍቅር መግለጫ” የሆኑ ቃላትን በመናገር በኩል ማሻሻል ይኖርብህ ይሆናል። (መኃልየ መኃልይ 1:2 አዓት) እንዲህ ማድረግ በመጀመሪያ ላይ የሚያሳፍር ሊመስልህ ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ሚስትህ ለሷ ስላለህ ፍቅር እርግጠኝነት እንዲሰማት ሊያደርግ ይችላል።
6. የቤተሰቡን የሐሳብ ግንኙነት ለማሻሻል ሚስቶች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
6 ክርስቲያን ሚስቶችስ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? አንዲት ሚስት ባሏ እሱን እንደምታደንቀው ስለሚያውቅ ለሱ መንገሩ ምንም አስፈላጊ አይደለም ብላ እንደተናገረች ተጠቅሷል። ይሁን እንጂ ወንዶችም ቢሆኑ አድናቆት፣ ምስጋናና ውዳሴ ሲያገኙ ደስ ይላቸዋል። (ምሳሌ 12:8) በዚህ ረገድ ስሜትሽን የበለጠ ግልጽ ማድረግ ያስፈልግሽ ይሆን? በሌላው በኩል ደግሞ እንዴት እንደምትሰሚ ይበልጥ መጠንቀቅ ያስፈልግሽ ይሆናል። ባልሽ ችግሮቹን፣ ፍርሃቶቹን ወይም ስጋት ያሳደሩበትን ነገሮች በግልጽ ለመወያየት አስቸጋሪ ሆኖ ካገኘው በደግነትና በዘዴ እንዲያወጣው ለማድረግ እንዴት እንደምትችይ ተምረሻልን?
7. በጋብቻ ውስጥ ጥል እንዲፈነዳ ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው? እንዴትስ ለመከላከል ይቻላል?
7 እርግጥ በደንብ የሚግባቡ ባልና ሚስትም እንኳን አንዳንድ ጊዜ የሐሳብ ግንኙነት መቋረጥ ያጋጥማቸው ይሆናል። ስሜት ምክንያታዊ አስተሳሰብን ሊያጨልም ይችላል፤ ወይም ረጋ ያለው ውይይት በፍጥነት ወደተጋጋለ ጭቅጭቅ ይለወጥ ይሆናል። (ምሳሌ 15:1) “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለን።” ይሁን እንጂ የጋብቻ ግጭት ትዳሩ ያለቀለት መሆኑን አያሳይም። (ያዕቆብ 3:2) ነገር ግን “ጩኸትም መሳደብም” ተገቢ አይደሉም፤ ማንኛውንም ግንኙነት የሚያበላሹ ነገሮች ናቸው። (ኤፌሶን 4:31) የጎጂ ቃላት ልውውጥ ካለ ሰላምን ለማምጣት ፈጣን ሁን። (ማቴዎስ 5:23, 24) ሁለታችሁም በመጀመሪያ ደረጃ በኤፌሶን 4:26 ላይ ያሉትን “በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ” የሚሉትን የጳውሎስን ቃላት በሥራ ላይ ብታውሉ አብዛኛውን ጊዜ ጥልን ለመከላከል ትችላላችሁ። አዎን፣ ችግሮች ትንሽ ሳሉና በቁጥጥር ሥር ሊደረጉ በሚችሉበት ጊዜ ተነጋገሩባቸው። ስሜታችሁ ፈንድቶ እስኪወጣ ድረስ አትጠብቁ። በየቀኑ ስለሚያሳስቧችሁ ጉዳዮች በመወያየት ጥቂት ጥቂት ደቂቃዎችን ማሳለፍ የሐሳብ ግንኙነታችሁ እንዲያድግ ለማድረግና አለመግባባትን ለመከላከል ብዙ ሊጠቅም ይችላል።
‘የይሖዋ ምክር’
8. አንዳንድ ወጣቶች ከእውነት የሚወጡት ለምንድን ነው?
8 አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው እንዲሁ አብረዋቸው ስለተጓዙ ብቻ የረኩ ይመስላል። ልጆቹ ስብሰባ ላይ ይገኛሉ፤ በመስክ አገልግሎትም በትንሹ ይካፈላሉ፤ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ከአምላክ ጋር የራሳቸውን ዝምድና አልገነቡም። ከጊዜ በኋላ “የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት” ብዙዎቹን እንዲህ ያሉ ወጣቶች ከእውነት ሊያስወጧቸው ይችላሉ። (1 ዮሐንስ 2:16) ወላጆች ልጆቻቸውን በራሳቸው ቸልተኝነት ምክንያት ልጆቻቸው ጠፍተው እነርሱ ግን አርማጌዶንን በሕይወት ቢያልፉ ምንኛ የሚያሳዝን ይሆንባቸው!
9, 10. (ሀ) ልጆችን “በጌታ [በይሖዋ አዓት] ምክርና በተግሣጽ” ማሳደግ ምንን ይጨምራል? (ለ) ልጆች ስሜቶቻቸውን በነፃነት እንዲገልጹ መፍቀድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
9 ስለዚህ ጳውሎስ “እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በጌታ [በይሖዋ አዓት] ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” ሲል ጽፏል። (ኤፌሶን 6:4) እንዲህ ለማድረግ እናንተ ራሳችሁ ከይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ጋር ሙሉ በሙሉ መተዋወቅ አለባችሁ። የመዝናኛ ምርጫን፣ የግል ጥናትን፣ በስብሰባ መገኘትንና የመስክ አገልግሎትን በሚመለከቱ ነገሮች እናንተ ራሳችሁ ተገቢውን ምሳሌ ማሳየት አለባችሁ። የጳውሎስ ቃላት አንድ ወላጅ (1) ልጆቹን በብልሃት የሚከታተል መሆን እንዳለበትና (2) ከእነሱ ጋር ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ሊኖረው እንደሚገባ ያመለክታሉ። የት ላይ “ምክር” እንደሚያስፈልጋቸው ልታውቁ የምትችሉት እንዲህ ካደረጋችሁ ብቻ ነው።
10 ወጣቶች ከፍ ሲሉ በመጠኑ ራሳቸውን ለመቻል መጣራቸው ተፈጥሮአዊ ነው። ይሁን እንጂ በአነጋገራቸው፣ በአስተሳሰባቸው፣ በአለባበሳቸውና በአበጣጠራቸው እንዲሁም በጓደኛ ምርጫቸው ላይ ዓለማዊ ግፊት እያደረባቸው እንደሆነ ለሚያሳዩ ምልክቶች ንቁ መሆን አለባችሁ። አንድ ጥበበኛ አባት በምሳሌ 23:26 ላይ እንደተመዘገበው “ልጄ ሆይ፣ ልብህን ስጠኝ” ብሏል። ልጆቻችሁ ሐሳቦቻቸውንና ስሜቶቻቸውን ለናንተ ለማካፈል ነጻነት ይሰማቸዋልን? ልጆች ወዲያው ቁጣ ይመጣብኛል ብለው የማይፈሩ ከሆኑ ከትምህርት ውጭ ስለሚያደርጓቸው ነገሮች፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ለመጫወት ስለ መቀጣጠር፣ ከፍተኛ ትምህርት ስለመከታተል ወይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ራሱ በእርግጥ ምን እንደሚሰማቸው በግልጽ ለመንገር ዝንባሌ ያድርባቸዋል።
11, 12. (ሀ) የምግብ ጊዜያት የቤተሰብን የሐሳብ ግንኙነት ለማዳበር እንዴት ልንጠቀምባቸው እንችላለን? (ለ) አንድ ወላጅ ከልጆቹ ጋር የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ ከሚያደርገው ያልተቋረጠ ጥረት ምን ውጤት ሊገኝ ይችላል?
11 በብዙ አገሮች ቤተሰቦች አንድ ላይ መብላታቸው የተለመደ ነገር ነው። ስለዚህ የራት ጊዜ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት የሚያንጽ ጭውውት ለማድረግ መልካም አጋጣሚ ሊሆንላቸው ይችላል። የቤተሰቡ የምግብ ጊዜ በአብዛኛው በቴሌቪዥንና ትኩረትን በሚስቡ ሌሎች ነገሮች እየተተካ ነው። ደግሞም ልጆቻችሁ ማለቂያ ለሌላቸው ሰዓታት በትምህርት ቤት ውስጥ ልክ እንደ እሥረኞች ሆነው በመዋል ለዓለማዊ አስተሳሰቦች ይጋለጣሉ። የምግብ ሰዓት ከልጆቻችሁ ጋር የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ጥሩ ጊዜ ነው። አንዲት ወላጅ “በምግብ ጊዜ በቀኑ ውስጥ ስላጋጠሙን ነገሮች እናወራለን” በማለት ተናግራለች። አሁንም ቢሆን የምግብ ጊዜያት ልጆቹን የሚያሳፍር ተግሣጽ የሚሰጥባቸው ወይም በመስቀለኛ ጥያቄዎች ምርመራ የሚካሄድባቸው ጊዜያት እንዲሆኑ አያስፈልግም። ወቅቱን የሚያዝናናና የሚያስደስት አድርጉት።
12 ልጆች በነፃነት ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ማድረግ ተፈታታኝና ምናልባትም መጠን የሌለው ትዕግሥት የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ልብን በደስታ የሚያሞቁ ውጤቶችን ትመለከቱ ይሆናል። “የ14 ዓመት ወንድ ልጃችን ደስታ በማጣት ከሰው ተገልሎ መኖርን ይወድ ነበር” በማለት አንዲት ነገሩ ያሳሰባት እናት ታስታውሳለች። “ባልተቋረጠው ጸሎታችን ምክንያት አሁን ሐሳቡን መግለጽና መናገር እየጀመረ ነው!”
የሚያንጽ የቤተሰብ ጥናት
13. ልጆችን አስቀድሞ ማሰልጠን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህንንስ እንዴት ማከናወን ይቻላል?
13 “ምክር” በአምላክ ቃል ላይ መደበኛ የሆነ መምሪያ መስጠትንም ያጠቃልላል። ይህ ዓይነቱ ሥልጠና እንደ ጢሞቴዎስ “ከሕፃንነት” መጀመር አለበት። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) አስቀድሞ የተጀመረ ሥልጠና ልጆች ትምህርት ቤት ባሉባቸው ዓመታት ለሚመጡባቸው ልደትን፣ ያገር ፍቅር ስሜት ያለባቸውን በዓላት ወይም ሃይማኖታዊ በዓላትን እንደማክበር ላሉ የእምነት ፈተናዎች ያጠነክራቸዋል። እንዲህ ላሉት ፈተናዎች ዝግጅት ካልተደረገ የትንሹ ልጅ እምነት ሊፈረካከስ ይችላል። ስለዚህ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ለትንንሽ ልጆች ያዘጋጃቸውን መሣሪያዎች ማለትም እንደ ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የያዘው መጽሐፌ ያሉትን መጽሐፎች ተጠቀሙባቸው።a
14. የቤተሰብ ጥናት እንዴት ቋሚ ሊደረግ ይችላል? ቋሚ የቤተሰብ ጥናት እንዲኖራችሁ ምን አድርጋችኋል?
14 ሌላው ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ነገር የቤተሰብ ጥናት ሲሆን ብዙ ጊዜ ሊቋረጥ ወይም የሚያሰለች ሊሆን ይችላል። እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ወላጆችንም ሆነ ልጆችን የሚያደክም ሊሆን ይችላል። ሁኔታውን ማሻሻል የምትችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ጊዜያችሁ በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ወይም በሌሎች ጊዜ ማሳለፊያ ጨዋታዎች እንዲጣበብ ባለመፍቀድ ለጥናቱ ‘ጊዜን መዋጀት’ አለባችሁ። (ኤፌሶን 5:15-17) “የቤተሰብ ጥናታችንን ቋሚ የማድረግ ችግር ነበረብን” በማለት አንድ የቤተሰብ ራስ ሳይደብቅ ተናግሯል። “በተለያየ ጊዜያት ልናደርገው ሞከርን። በመጨረሻም ምሽት ላይ ትንሽ ቆየት ብሎ ማድረግን ተስማሚያችን ሆኖ አገኘነው። አሁን የቤተሰብ ጥናታችን ቋሚ ነው።”
15. የቤተሰብ ጥናታችሁን ለቤተሰባችሁ ከሚያስፈልጓችሁ ነገሮች ጋር እንዴት ልታስማሙት ትችላላችሁ?
15 ቀጥሎ በተለይ ለቤተሰባችሁ የሚያስፈልገው ነገር ምን እንደሆነ አስቡበት። ብዙ ቤተሰቦች ሳምንታዊውን የመጠበቂያ ግንብ ጥናት አብሮ መዘጋጀት ደስ ያሰኛቸዋል። ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቤተሰቡ እንዲወያይባቸው የሚያስፈልጉአችሁ ጉዳዮች ይኖሩ ይሆናል። ይህም ልጆች በትምህርት ቤት የሚያጋጥማቸውን ችግሮችም ይጨምራል። የወጣቶች ጥያቄና ሊሠሩ የሚችሉ መልሶቻቸው የተባለው መጽሐፍ እንዲሁም በመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ላይ የወጡ ትምህርቶች ይህን የሚያስፈልጋችሁን ነገር ሊያሟሉ ይችላሉ። “ወንዶች ልጆቻችን ሊታረሙ የሚገባቸው አመለካከቶች እንዳሏቸው ካወቅን የወጣቶች ጥያቄ ከሚለው መጽሐፍ ውስጥ ነገሩን በሚያጠቃልለው አንድ የተለየ ምዕራፍ ላይ እናተኩራለን” በማለት አንድ አባት ተናግሯል። ሚስቱም በመጨመር “የሚጠናውን ነገር እንደ ሁኔታው ለመለዋወጥ እንሞክራለን። ለጥናታችን አንድ ነገር አቅደን ከነበረና ስለ አንድ ሌላ ነገር መወያየት የሚያስፈልገን ከሆነ እንደ አስፈላጊነቱ እንለውጠዋለን” ብላለች።
16. (ሀ) ልጆቻችሁ የሚማሩትን ነገር እንደተረዱት እንዴት እርግጠኞች ልትሆኑ ትችላላችሁ? (ለ) የቤተሰብ ጥናት ሲመራ በአብዛኛው ሊወገድ የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
16 ልጆቻችሁ የሚማሩትን ነገር በእርግጥ እንደተረዱት እንዴት ልታውቁ ትችላላችሁ? ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ “ምን ይመስልሃል?” እንደሚሉት ያሉ የአመለካከት ጥያቄዎችን ይጠይቅ ነበር። (ማቴዎስ 17:25) እናንተም ልክ እንደዚሁ በማድረግ ልጆቻችሁ በእርግጥ የሚያስቡት ምን እንደሆነ ለማወቅ ሞክሩ። እያንዳንዱ ልጅ በራሷ ወይም በራሱ አነጋገር እንዲመልሱ አበረታቷቸው። እርግጥ ሐሳባቸውን ሳይደብቁ በመግለጻቸው ቁጣ ወይም ድንጋጤ በማሳየት ከሚገባው በላይ የስሜት መረበሽ ካሳያችሁ በድጋሚ ከእናንተ ጋር ግልጽ ሆኖ መነጋገርን ይፈራሉ። ስለዚህ ረጋ ብላችሁ ቆዩ። የቤተሰብ ጥናቱን የቁጣ መግለጫ አድርጋችሁ አትጠቀሙበት። የቤተሰብ ጥናት የሚያስደስትና የሚያንጽ መሆን ይኖርበታል። አንድ አባት “ከልጆቼ አንዱ ችግር እንዳለበት ከተረዳሁ ነገሩን በሌላ ጊዜ እንወያይበታለን” ብሏል። እናትየውም ጨምራ “ልጁን ብቻውን ስናወያየው ስለማያፍር በቤተሰብ ጥናት ላይ ቢመከር ከሚያሳየው ስሜት ይልቅ አሁን ዘና ብሎ ይናገራል” ብላለች” ብላለች።
17. የቤተሰብ ጥናቱን አስደሳች ለማድረግ ምን ሊደረግ ይችላል? ለቤተሰባችሁ ተግባራዊ ሆኖ ያገኛችሁት ምንድን ነው?
17 በተለይም ልጆቹ በተለያየ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ከሆነ በቤተሰብ ጥናት ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረግ ተፈታታኝ ሁኔታ ነው። ትንንሾቹ ልጆች ወደ መቁነጥነጥ ሊያዘነብሉና በአንድ ቦታ አርፎ መቀመጥ ያስቸግራቸው ይሆናል። ወይም ትኩረት ሰጥተው ሊከታተሉ የሚችሉበት ጊዜ አጭር እንደሆነ ያሳዩ ይሆናል። ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? የጥናቱን መንፈስ የተዝናና አድርጉት። ልጆቻችሁ ትኩረት ሰጥተው ሊከታተሉ የሚችሉበት ጊዜ አጭር ከሆነ አጫጭር ግን ቶሎ ቶሎ የሚደረጉ ጥናቶችን ሞክሩ። ሞቅ ባለ ስሜት የምትናገሩ መሆናችሁም ሊረዳቸው ይችላል። “የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ።” (ሮሜ 12:8) ሁሉም በውይይቱ እንዲሳተፉ አድርጉ። ትንንሽ ልጆች ስዕሎቹን በተመለከተ ሐሳብ ሊሰጡ ወይም ቀላል ጥያቄዎችን ሊመልሱ ይችላሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ተጨማሪ ምርምር እንዲያደርጉ ወይም የምታጠኑት ነገር ተግባራዊ በሆነ መንገድ እንዴት በሥራ ላይ ለማዋል እንደሚቻል እንዲናገሩ ሊጠየቁ ይችላሉ።
18. ወላጆች የአምላክን ቃል በየአጋጣሚው ሁሉ በልባቸው ውስጥ ለመትከል የሚችሉት እንዴት ነው? ከምንስ ውጤት ጋር?
18 ይሁን እንጂ መንፈሳዊ ትምህርት መስጠቱን በሳምንት አንድ ሰዓት ብቻ በማድረግ አትወስኑት። የአምላክን ቃል በየአጋጣሚው በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ ትከሉ። (ዘዳግም 6:7) ጊዜ ወስዳችሁ ልጆቹ የሚናገሩትን አዳምጡ። አስፈላጊ ሲሆን ምከሩአቸው እንዲሁም አጽናኑአቸው። (ከ1 ተሰሎንቄ 2:11 ጋር አወዳድሩ።) ርኅሩኅና መሐሪ ሁኑ። (መዝሙር 103:13፤ ሚልክያስ 3:17) እንዲህ በማድረግ በልጆቻችሁ ‘ደስ ትሰኛላችሁ’፤ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመግባት አቋማቸውን ጠብቀው እንዲቆዩም ትደግፏቸዋላችሁ።—ምሳሌ 29:17
“ለመሳቅም ጊዜ አለው”
19, 20. (ሀ) መዝናኛ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ምን ሚና አለው? (ለ) ወላጆች ለቤተሰባቸው መዝናኛ የሚያዘጋጁባቸው አንዳንድ መንገዶች ምን ምን ናቸው?
19 “ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ለመዝፈንም [እየዘፈኑ ለመጨፈርም የ1980 ትርጉም] ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:4) “ሳቅ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “መጨፈር፣” “በዓል ማክበር፣” “መጫወት፣” “ማስደሰት፣” “ስፖርት መሥራት፣” ወይም “መዝፈን፣” “ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። (2 ሳሙኤል 6:21፤ ኢዮብ 41:5፤ መሳፍንት 16:25፤ ዘጸአት 32:6፤ ዘፍጥረት 26:8) ጨዋታ ጠቃሚ ለሆነ ዓላማ ሊያገለግል ይችላል። ይህም ለልጆችና ለወጣቶች አስፈላጊ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ወላጆች ለቤተሰባቸው መደሰቻዎችና መዝናኛዎችን ያዘጋጁ ነበር። (ከሉቃስ 15:25 ጋር አወዳድሩ።) እናንተስ እንዲህ ታደርጋላችሁ?
20 አንድ ክርስቲያን ባል “ሕዝባዊ መናፈሻዎችን እንጠቀምባቸዋለን” ብሏል። “አንዳንድ ወጣት ወንድሞችን እንጋብዛቸውና የኳስ ጨዋታና ሽርሽር እናደርጋለን። ጥሩ ጊዜ ያሳልፋሉ። እንዲሁም ጤናማ ጓደኝነት በማግኘታቸው ይደሰታሉ።” አንድ ሌላ ወላጅ እንዲህ በማለት ጨምሯል፦ “ከወንዶች ልጆቻችን ጋር የምናደርጋቸውን ነገሮች ዕቅድ እናወጣለን። ዋና እንሄዳለን፣ ኳስ እንጫወታለን፣ አብረን የዕረፍት ጊዜ እናሳልፋለን። ነገር ግን የመዝናኛን ተገቢ ቦታ እንጠብቃለን። ሚዛናዊ የመሆንን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጌ እገልጻለሁ።” ለምሳሌ አንድ ላይ ተሰብስቦ እንደ መጫወት ወይም እንደ መዋዕለ እንስሳትና ቤተ መዘክሮች ሄዶ እንደ ማየት ያሉ ተገቢ የሆኑ መዝናኛዎች አንድን ልጅ በዓለማዊ መደሰቻዎች ከመሳብ ለመጠበቅ ብዙ ሊረዱ ይችላሉ።
21. ወላጆች ልጆቻቸው ዓለማዊ በዓላትን ባለማክበራቸው ምክንያት አንድ ነገር እንደጎደላቸው ሆኖ እንዳይሰማቸው ለማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
21 ልጆችህ ልደትን ወይም ክርስቲያናዊ ያልሆኑ በዓሎችን ባለማክበራቸው ምክንያት አንድ ነገር እንደቀረባቸው ሆኖ እንዳይሰማቸው ማድረግም አስፈላጊ ነው። በእናንተ በኩል አንዳንድ ነገሮችን ካደራጃችሁ በዓመቱ በሙሉ ያሏችሁን ብዙ ደስ የሚሉ ጊዜያት ሊጠባበቁ ይችላሉ። አንድ ጥሩ ወላጅ ፍቅሩን ቁሳዊ በሆነ ሁኔታ ለመግለጽ ምክንያት እንዲሆኑት አንዳንድ በዓላት አያስፈልጉትም። እንደ ሰማያዊ አባቱ በፈቃደኝነት ‘ለልጆቹ መልካም ስጦታ መስጠትን ያውቃል’።—ማቴዎስ 7:11
የቤተሰብህን ዘላለማዊ ተስፋ አስተማማኝ ማድረግ
22, 23. (ሀ) ታላቁ መከራ እየተቃረበ ሲሄድ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ቤተሰቦች ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን ይችላሉ? (ለ) ቤተሰቦች አቋማቸው እንደተጠበቀ ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ለመግባት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
22 መዝሙራዊው “አቤቱ [ይሖዋ አዓት]፣ አንተ ጠብቀን፣ ከዚህችም ትውልድ ለዘላለም ታደገን” ብሎ ጸልዮአል። (መዝሙር 12:7) ከሰይጣን የሚመጣው ግፊት በተለይም በይሖዋ ምስክሮች ቤተሰቦች ላይ የሚያመጣው ግፊት እየጨመረ እንደሚሄድ የተረጋገጠ ነው። ሆኖም ይህን እየጨመረ የሚሄደውን ጥቃቱን ለመቋቋም ይቻላል። በይሖዋ እርዳታና በከፍተኛ ቆራጥነት እንዲሁም ባሎች፣ ሚስቶችና ልጆች በየበኩላቸው ጠንክረው በመሥራት ቤተሰቦች፣ ያንተንም ቤተሰብ ጨምሮ፤ በታላቁ መከራ ወቅት ሕይወታቸው እንደሚጠበቅላቸው ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ።
23 ባሎችና ሚስቶች በአምላክ የተመደበላችሁን ቦታ በመጠበቅ ለጋብቻችሁ ሰላምና ስምምነት ልታመጡ ትችላላችሁ። ወላጆች ሆይ፣ በጣም የሚያስፈልጋቸውን ሥልጠናና ተግሣጽ ለመስጠት እንድትችሉ ዘመኑን እየዋጃችሁ ለልጆቻችሁ ተገቢውን ምሳሌ መተዋችሁን ቀጥሉ። አወያዩአቸው። አድምጧቸው። ሕይወታቸው አደጋ ላይ ነው! ልጆች ሆይ፣ ወላጆቻችሁን ስሟቸው እንዲሁም ታዘዟቸው። በይሖዋ እርዳታ የተሳካላችሁ ልትሆኑ ትችላላችሁ። በመጪው የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥም ዘላለማዊ ሕይወት ልታገኙ ትችላላችሁ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የካሴት ቅጂዎችም በአንዳንድ ቋንቋዎች ይገኛሉ።
ታስታውሳለህን?
◻ ባሎችና ሚስቶች የሐሳብ ግንኙነታቸውን ሊያሻሽሉ የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ ወላጆች ልጆቻቸውን “በጌታ [በይሖዋ አዓት] ምክርና በተግሣጽ” ሊያሳድጉ የሚችሉት እንዴት ነው? (ኤፌሶን 6:4)
◻ የቤተሰብ ጥናትን የሚያንጽና ይበልጥ የሚማርክ እንዲሆን የሚያደርጉ አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
◻ ወላጆች ለቤተሰባቸው መዝናኛና አስደሳች ጊዜ ለማዘጋጀት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሙዚቃ ኃይለኛ ግፊት አለው
ልጆችን ማሳደግን በተመለከተ የአንድ መጽሐፍ ደራሲ እንዲህ ብለዋል፦ “በአድማጮች ፊት ብቆምና . . . ያለልክ መጠጣትን፣ እንደ ኮኬን፣ ፖት ያሉትንና አእምሮን የሚያደነዝዙ ሌሎች ዕፆችን በጣም እንደምወዳቸው ብናገር ሰዎቹ ደንግጠው በመገረም ይመለከቱኝ ነበር። . . . [ሆኖም] ወላጆች አብዛኛውን ጊዜ ልጆቻቸው እነዚህን ነገሮች በግልጽ የሚደግፉትን የዘፈን ወይም የቪድዮ ካሴቶች እንዲገዙበት ገንዘብ ይሰጧቸዋል።” (ቀና አመለካከት ያላቸውን ልጆች ጠማማ አመለካከት ባለው ዓለም ውስጥ ማሳደግ በዚግ ዚግለር የተጻፈ መጽሐፍ) ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ ብዙ ወጣቶች ስለ ፍትወተ ሥጋ በግልጽ የሚናገሩ ግጥሞች ያላቸው ሙዚቃዎችን እየደጋገሙ ይዘፍኗቸዋል። ልጆቻችሁ እንዲህ ያሉትን አጋንንታዊ ወጥመዶች ማስወገድ ይችሉ ዘንድ በሙዚቃ ምርጫቸው በኩል መራጮች እንዲሆኑ እየረዳችኋቸው ነውን?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምግብ ጊዜያት ቤተሰብን የሚያስተሳስሩና የሚያገናኙ አስደሳች ወቅቶች ሊሆኑ ይችላሉ