የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 1/1 ገጽ 22-24
  • የይሖዋን በረከቶች በእርግጥ ታደንቃለህን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የይሖዋን በረከቶች በእርግጥ ታደንቃለህን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ተወዳዳሪ የሌለው ተንከባካቢ
  • ባለጠጋ የሚያደርጉን በረከቶች
  • ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቅ
  • በረከቶቹን ለማግኘት ተጣጣሩ
  • ‘እያለቀሱ መዝራት እና በዕልልታ ማጨድ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • የይሖዋ በረከት ባለጠጋ ታደርገናለች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ያለ ነቀፋ መኖር የሚያስገኘው ደስታ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • ‘ከሕፃናት አፍ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 1/1 ገጽ 22-24

የይሖዋን በረከቶች በእርግጥ ታደንቃለህን?

ኬኒቺ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው ሰው ሲሆን ለጉንፋን የሚሆን መድኃኒት ፍለጋ ወደ አንድ መድኃኒት ቤት ይሄዳል። የወሰደው መድኃኒት ለሰውነቱ አለርጂ ስለሆነበት የሚያሳክክ ሽፍታና ውኃ የቋጠረ ቁስል መላው አካሉን ወረሰው። ኬኒቺ ፋርማሲስቱ ለችግሩ ተገቢውን ትኩረት መስጠቱን መጠራጠሩ ምንም አያስደንቅም።

አንዳንዶች ስለ ይሖዋ አምላክ ያላቸው አመለካከት ኬኒቺ ለፋርማሲስቱ ከነበረው አመለካከት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ በእርግጥ የሚያስብልን መሆኑን ይጠራጠራሉ። አምላክ ጥሩ መሆኑን ቢቀበሉም ስለ እያንዳንዳችን ያስባል ብለው ግን አያምኑም። በተለይ ነገሮች ሳይሳኩላቸው ሲቀሩ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሙጥኝ በማለታቸው ምክንያት መከራ ሲደርስባቸው እንዲህ ይሰማቸዋል። የማስተዋል ጉድለት ስላለባቸው ለደረሰባቸው መከራ ተጠያቂው አምላክ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። በመሆኑም ችግሮቻቸውን ልክ በኬኒቺ ሰውነት ላይ ድንገት እንደወጣው የሚያሳክክ ሽፍታና ቁስል አድርገው ይመለከቷቸዋል።​—⁠ምሳሌ 19:​3

ይሖዋን ፍጽምና ከሌላቸው ሰዎች ጋር ማወዳደር አይቻልም። የሰው ልጆች ያላቸው እውቀትና ችሎታ ውስን ነው። ፋርማሲስቱ በኬኔቺ እንዳደረገው ሁሉ ሌሎች በትክክል የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ ሙሉ በሙሉ አይገነዘቡም። ከዚህ በተቃራኒ ግን ከይሖዋ ዓይኖች ምንም የሚያመልጥ ነገር የለም። እኛ ሳናስተውለውና ሳንገነዘበው ይሖዋ ብዙ ጊዜ ይረዳናል። በሌሉን ነገሮች ላይ ማትኮር ስለሚቀናን ያሉንን ብዙ በረከቶች ሳናስተውል እንቀራለን። ለሚደርሱብን ችግሮች ይሖዋን ለመውቀስ ከመቸኮል ይልቅ ከይሖዋ ያገኘናቸውን በረከቶች ለማስተዋል መጣር ይኖርብናል።

ዌብስተርስ ናይንዝ ኒው ኮሊጂየት ዲክሽነሪ “ብሌሲንግ” ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የሰጠው ፍቺ “ወደ ደስታ ወይም ወደ ደኅንነት የሚመራ ነገር” የሚል ነው። በተለይ ከይሖዋ የሚገኙ በረከቶች እንዲህ መሆናቸውን ተገንዝበሃልን?

ተወዳዳሪ የሌለው ተንከባካቢ

አንዲት ሚስት ባሏ ጥሩ ተንከባካቢ እንደሆነ በምትገልጽበት ጊዜ በአጠቃላይ በቂ ምግብ፣ መጠለያና ልብስ በማቅረብ ለቤተሰቡ ደስታና ደኅንነት በጥልቅ ያስባል ማለቷ ነው። ይሖዋ እኛን የሚንከባከበን ምን ያህል ነው? የሰው መኖሪያ የሆነችውን ፕላኔቷን ምድር በደንብ ተመልከት። ከፀሐይ በ150,000,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን ይህም ሕይወት በምድር ላይ እንዲኖር የሚያስችል ተስማሚ የአየር ሁኔታን የሚያስገኝ ትክክለኛ ርቀት ነው። ምድራችን በ23.5 ዲግሪ እንድታጋድል ሆና መሠራቷ ወቅቶች እንዲፈራረቁ ስለሚያደርግ የተትረፈረፈ ምርት ያስገኛል። በዚህም ምክንያት ምድር ከአምስት ቢልዮን የሚበልጡ ሰዎችን ትመግባለች። ይሖዋ በእርግጥም ግሩም ተንከባካቢ ነው!

ከዚህም በላይ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለደኅንነታችን በጥልቅ እንደሚያስብ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጣል። እስቲ አስቡት፣ ይሖዋ በቢልዮን የሚቆጠሩ ከዋክብትን በየስማቸው ያውቃቸዋል፤ እንዲሁም አንዲት ድንቢጥ እንኳ ያለ እሱ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። (ኢሳይያስ 40:​26፤ ማቴዎስ 10:​29-31) እርሱን የሚወዱትንና በተወዳጅ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ደም የተገዙትን የሰው ዘሮችማ ምን ያህል አብልጦ ያስብላቸው! (ሥራ 20:​28) ጠቢቡ ሰው እንዲህ ሲል ማወጁ የተገባ ነው:- “የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች፣ ኀዘንንም ከእርስዋ ጋር አይጨምርም።”​—⁠ምሳሌ 10:​22

ባለጠጋ የሚያደርጉን በረከቶች

ከልብ አመስጋኞች እንድንሆን የሚያደርገን ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነገር አለን። ይህ ነገር ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ምንነቱን ሲገልጽ እንደሚከተለው ይላል:- “ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል።” (መዝሙር 119:​72፤ ምሳሌ 8:​10) ወርቅ ዋጋው ከፍተኛ ቢሆንም ከይሖዋ ሕግ ጋር ግን አይተካከልም። የሕጉ ትክክለኛ እውቀትና ይሖዋ ቅን ለሆኑ እውነት ፈላጊዎች የሚሰጠው ጥልቅ ማስተዋልና ግንዛቤ ከፍ አድርገን ልንመለከታቸው የሚገቡ ውድ ሀብት ናቸው። ራሳችንን እንድንጠብቅ፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንድንወጣና ችግሮችን በተሳካ ሁኔታ እንድንፈታ በሚገባ ስለሚያስታጥቁን እንረካለን፤ ደስተኞችም እንሆናለን።

ይህ ሁኔታ በልጅነት ዕድሜ ላይ ባሉት እንኳን ሳይቀር ይሠራል። አንዲት ትንሽ ልጃገረድ ያጋጠሟትን ችግሮች የይሖዋን ሕግ በመከተል እንዴት እንደፈታቻቸው ተመልከት። አኬሚ የምትባለው ይህች ልጃገረድ የምትኖረው በቶኪዮ አቅራቢያ ነው። አባቷና እናቷ በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች አሰልጥነዋታል። ሴት ልጃቸው ለይሖዋና ለሰዎች ፍቅር እንድትኮተኩት በቃልና ምሳሌ በመሆንም ጭምር ረድተዋታል። በትምህርት ቤት ውስጥ ለሚያጋጥሟት ችግሮች ሁሉ ዝግጁ እንድትሆን በተቻላቸው አቅም አስታጥቀዋታል። ይሁን እንጂ አኬሚ ከምግብ በፊት ትጸልይና ቅዱስ ጽሑፋዊ ካልሆኑ አንዳንድ ድርጊቶች ሆን ብላ ትርቅ ስለነበር ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስትገባ አብረዋት የሚማሩ ጥቂት ተማሪዎች “ልዩ” እንደሆነች አድርገው ይመለከቷት ጀመር። ብዙም ሳይቆይ በጉልበት ከእነሱ የሚያንሱትን ልጆች የሚያሠቃዩ ተማሪዎች የጥቃታቸው ዒላማ አደረጓት። ወደ አንድ ጥግ በመውሰድ በጥፊ ይመቷት፣ እጅዋን ይጠመዝዟትና ያሾፉባት ነበር።

ትንሿ አኬሚ አጸፋውን አልመለሰችም፤ የሚያሰቃዩአትንም ልጆች ፈርታ ወደኋላ አላለችም። ከዚህ ይልቅ የተማረችውን በተግባር ላይ ለማዋል ጥረት አደረገች። መልካም ሥነ ምግባሯና ድፍረቷ አብረዋት ከሚማሩ ተማሪዎች ከበሬታን አተረፉላት። ተማሪዎቹ የደረሰባትን ችግር ለመምህራቸው ተናገሩ። ከዚያን ቀን ጀምሮ አኬሚ በትምህርት ቤት ውስጥ አንዳችም ዓይነት ጥቃት አልደረሰባትም።

አኬሚ ይህን አስቸጋሪ ነገር በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት የረዳት ምንድን ነው? ወላጆቿ በውስጧ የተከሏቸው ከይሖዋ የሚገኙት ትክክለኛ እውቀት፣ ጥልቅ ማስተዋልና ጥበብ ናቸው። ኢየሱስ ያሳየው ጽናት በአእምሮዋ በደንብ መቀረጹ የእሱን ምሳሌ እንድትኮርጅ ገፋፍቷታል። መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ሰዎች መጥፎ ነገሮችን የሚያደርጉት ካለማወቅ መሆኑን እንድትገነዘብ የረዳት ከመሆኑም በላይ እነዚያን በዕድሜ የሚያንሷቸውን ልጆች የሚያሠቃዩ ተማሪዎችን ሳይሆን የሚያደርጓቸውን መጥፎ ነገሮች እንድትጠላ አበረታቷታል።​—⁠ሉቃስ 23:​34፤ ሮሜ 12:​9, 17-21

እርግጥ ነው፣ የትኛውም ወላጅ ልጁ መቀለጃ ሲሆንና ጥቃት ሲሰነዘርበት ማየት አይፈልግም። ቢሆንም የአኬሚ ወላጆች የተፈጸመውን ነገር ሲሰሙ የተሰማቸውን ደስታ ልትገምቱት ትችላላችሁ። እነዚህን የመሳሰሉ ልጆች በእርግጥም ከይሖዋ የሚገኙ በረከቶች ናቸው።​—⁠መዝሙር 127:​3፤ 1 ጴጥሮስ 1:​6, 7

ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቅ

ይሁንና አንዳንድ ጊዜ የይሖዋን በረከቶች ለማግኘት ይሖዋ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ መጠበቅ አለብህ። ይሖዋ ያለህበትን ሁኔታ ስለሚያውቅ የሚያስፈልግህን ነገር ይበልጥ በሚጠቅምህ ጊዜ ይሰጥሃል። (መዝሙር 145:​16፤ መክብብ 3:​1፤ ያዕቆብ 1:​17) ፍራፍሬ መብላት በጣም ትወድ ይሆናል። ነገር ግን አንድ ሰው ያልበሰለ ፍሬ እንድትበላ ቢጋብዝህ ምን ይሰማሃል? ፖምም ይሁን ብርቱካን ወይም ሌላ ፍሬ የበሰለ፣ ያልጠወለገና ጣፋጭ ቢሆን ትመርጣለህ። በተመሳሳይም ይሖዋ የሚያስፈልግህን ነገር እጅግም ሳያስቀድም፣ እጅግም ሳያዘገይ በተገቢው ጊዜ ይሰጥሃል።

ዮሴፍ ያጋጠመውን ተሞክሮ አስታውስ። ባልሠራው ጥፋት በግብጽ በሚገኝ በአንድ ጨለማ እስር ቤት ውስጥ ታስሯል። አብሮት ታስሮ የነበረው የፈርዖን ጠጅ አሳላፊ እንደሚፈታ ተስፋ አድርጎ ስለነበር የዮሴፍን ጉዳይ ለፈርዖን ለመንገር ቃል ገባ። ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ግን ዮሴፍን ረሳው። ዮሴፍ ፈጽሞ የተተወ ይመስል ነበር። ይሁን እንጂ ከሁለት ዓመታት በኋላ ከእስር የተፈታ ከመሆኑም በላይ በግብጽ ሁለተኛ ገዥ ለመሆን በቅቷል። ዮሴፍ ትዕግሥቱን ከማጣት ይልቅ ይሖዋ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ ተጠባብቋል። በዚህም ምክንያት የእስራኤላውያንም ሆነ የግብጻውያን ሕይወት ከጥፋት እንዲድን በማስቻል ተባርኳል።​—⁠ዘፍጥረት 39:​1–41:​57

ማሳሺ በሰሜን ጃፓን በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግል ነበር። በጨለማ እስር ቤት ውስጥ የነበረ ባይሆንም እንኳ ይሖዋን መጠበቅ አስፈልጎት ነበር። ለምን? ብቃት ያላቸው ክርስቲያን አገልጋዮችን የሚያሰለጥነው የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በጃፓን ከተቋቋመ ጀምሮ በትምህርት ቤቱ ለመካፈል ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ይህን መብት ለማግኘት አጥብቆ ጸለየ። አብሮት የሚያገለግለው አቅኚ ስልጠናውን እንዲወስድ ሲጋበዝ ማሳሺ ምንም እንኳ ከፍተኛ ጉጉት የነበረው ቢሆንም አልተጋበዘም ነበር። በዚህ በጣም ተበሳጨ።

የሆነ ሆኖ ስሜቱን ለመግታት እርምጃዎችን ወሰደ። ትሑት ስለመሆንና ስሜትን ስለመቆጣጠር በሚናገሩ ርዕሶች ላይ በማትኮር መጽሐፍ ቅዱስንና በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የታተሙ ጽሑፎችን አጠና። አስተሳሰቡን በማስተካከሉ በተሰጠው ኃላፊነት የበለጠ እርካታን አገኘ። ከዚያ በኋላ ጭራሽ ባልጠበቀበት ጊዜ በትምህርት ቤቱ እንዲካፈል ግብዣ ቀረበለት።

ማሳሺ እንደ ትዕግሥትና ትሕትና የመሳሰሉ ባሕርያትን ማዳበሩ በትምህርት ቤቱ ከሚሰጠው ትምህርት ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሎታል። ከጊዜ በኋላ ማሳሺ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ወንድሞቹን የማገልገል መብት አግኝቷል። አዎን፣ ይሖዋ ማሳሺ የሚያስፈልገውን ነገር ያውቅ ነበር፤ ይበልጥ ሊጠቅመው በሚችልበት ወቅት ላይም ሰጥቶታል።

በረከቶቹን ለማግኘት ተጣጣሩ

ስለዚህ ይሖዋ እንደ ፋርማሲስቱ አይደለም። የይሖዋን ጥበቃና አሳቢነት ሳናስተውል ልንቀር ብንችልም እንኳ ይበልጥ በሚጠቅመን ጊዜና ሁኔታ ደግነቱን በተለያዩ መንገዶች ያሳየናል። ስለዚህ በረከቶቹን ለማግኘት መጣጣራችሁን ቀጥሉ። አሁንም እንኳ አመስጋኞች የምትሆኑባቸው ብዙ ነገሮች መኖራቸውን አስታውሱ። በምድር ላይ በሕይወት ለመኖር እንድትቀጥሉ የሚያስችሏችሁ መሠረታዊ ነገሮች በማግኘት ተባርካችኋል። ስለ ይሖዋና ፍጹም ስለሆኑት መንገዶቹ እውቀት አግኝታችኋል። ጥልቅ ማስተዋል ተሰጥቷችኋል። ጥሩ የማመዛዘን ችሎታም አግኝታችኋል። እነዚህ ሁሉ ለደኅንነታችሁና ለደስታችሁ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

እንግዲያው የይሖዋ በረከት ይበልጥ እንዲትረፈረፍላችሁ አዘውትራችሁ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በመንፈሱ ባስጻፈው ቃሉ ውስጥ የሚገኙትን እንቁ መሰል ትምህርቶች ለመረዳትና በተግባር ለመተርጎም እንዲረዳችሁ አጥብቃችሁ ይሖዋን ለምኑ። ባለጠጋ ስለሚያደርጓችሁ ምንም አይጎድልባችሁም። አዎን፣ በአሁኑ ጊዜ ደስታና እርካታ የሚያስገኝላችሁ ከመሆኑም በላይ በሚመጣው አዲስ ዓለም የተሟላ ሕይወት ያስጨብጣችኋል።​—⁠ዮሐንስ 10:​10፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:​8, 9

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ በረከት ከወርቅ ይበልጥ ውድ ነው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ