ምክንያታዊ የሆነ ጥሎሽ ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል መስማማት
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይደረግ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም በአንዳንድ ባሕሎች አንድ ሰው አንዲትን ሴት ከማግባቱ በፊት ጥሎሽ እንዲሰጥ ይጠየቃል። ያዕቆብ “ስለ ታናሺቱ ልጅህ ስለ ራሔል ሰባት ዓመት እገዛልሃለሁ” በማለት ወደፊት አማቹ ለሚሆነው ለላባ ነገረው። (ዘፍጥረት 29:18) ያዕቆብ ራሔልን ያፈቅራት ስለነበረ ከሰባት ዓመት ደሞዝ ጋር የሚመጣጠን ከፍተኛ ዋጋ ለመክፈል ሐሳብ አቅርቧል! ላባ በሐሳቡ ቢስማማም በመጀመሪያ ታላቅየዋን ልጁን ልያን እንዲያገባ በማድረግ ያዕቆብን አታልሎታል። ላባ በያዕቆብ ላይ ብዙ ተንኮል ሠርቶበታል። (ዘፍጥረት 31:41) ላባ ለቁሳዊ ጥቅም እንደዚያ መስገብገቡ ልጆቹ ለእርሱ የነበራቸውን አክብሮት እንዲያጡ አድርጓቸዋል። “እኛ በእርሱ ዘንድ እንደ ባዕድ የተቆጠርን አይደለንምን? እርሱ እኛን ሸጦ ዋጋችንን በልቶአልና” በማለት ተናግረዋል።—ዘፍጥረት 31:15
የሚያሳዝነው ለቁሳዊ ነገር በሚስገበገበው በዛሬው ዓለም ውስጥ ያሉ ብዙ ወላጆች ልክ እንደ ላባ ናቸው። አንዳንድ ከላባ የባሱም አሉ። አንድ በአፍሪካ የሚታተም ጋዜጣ እንደዘገበው “ስግብግብ የሆኑ አባቶች የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ብቻ” ልጆቻቸውን ይድራሉ። አንዳንድ ወላጆች ከወደቁበት የድህነት አዘቅት መላቀቂያ ዘዴ ሴት ልጆቻቸው እንደሆኑ አድርገው እንዲያስቡ የሚያስገድዳቸው ሌላው ምክንያት የኢኮኖሚው ተጽእኖ ነው።a
አንዳንድ ወላጆች ከፍ ያለ ጥሎሽ ለሚያመጣ ሰው ለመዳር ሲሉ ሴት ልጆቻቸውን እንዳያገቡ እያከላከሉ ያቆዩአቸዋል። ይህም ከባድ ችግር ሊያስከትል ይችላል። በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኝ አንድ የጋዜጣ ዘጋቢ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ወጣቶች አስቸጋሪ የሆኑ አማቶች የሚጠይቁትን ከፍተኛ ጥሎሽ ላለመስጠት ሲሉ እጮኛቸውን ይዘው መኮብለል ይመርጣሉ።” ከፍተኛ ጥሎሽ መጠየቅ ከሚያስከትላቸው መዘዞች መካከል አንዱ የጾታ ብልግና ነው። ከዚህም በላይ አንዳንድ ወጣቶች የተጠየቁትን ከፍለው ሚስት ይገዛሉ፤ ሆኖም ሊወጡት የማይችሉት ዕዳ ውስጥ ይዘፈቃሉ። በደቡብ አፍሪካ የሚገኝ አንድ የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኛ “ወላጆች ምክንያታዊ መሆን ይገባቸዋል” ሲል አጥብቆ አሳስቧል። “ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቅ አይኖርባቸውም። አዲሶቹ ተጋቢዎች የግድ ጎጆ መውጫ ያስፈልጋቸዋል። . . . ታዲያ አግቢው ወጣት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ የሚደረገው ለምንድን ነው?”
ክርስቲያን ወላጆች ጥሎሽ መስጠትንም ሆነ መቀበልን በተመለከተ በሚደራደሩበት ጊዜ ምክንያታዊ በመሆን ረገድ ለሌሎች ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ ይታወቅ” በማለት ስለሚያዝ ይህ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።—ፊልጵስዩስ 4:5 NW
ምክንያታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች
ክርስቲያን ወላጆች ጥሎሽን በተመለከተ ለመደራደር ወይም ላለመደራደር የሚያደርጉት ውሳኔ የግላቸው ነው። መደራደሩን የሚመርጡ ከሆነ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መደራደር ይኖርባቸዋል። የአምላክ ቃል “አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን” በማለት ይናገራል። (ዕብራውያን 13:5) ጋብቻን በማስመልከት ድርድር በሚደረግበት ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ መሠረታዊ ሥርዓት ካልተሠራበት አንድ ክርስቲያን ወላጅ ጥሩ ምሳሌ አለመሆኑን በገሃድ እያሳየ ሊሆን ይችላል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚሠሩ ወንዶች “ምክንያታዊ” መሆን አለባቸው፤ እንዲሁም ‘ገንዘብ የሚወዱ’ ወይም ‘አላግባብ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ የሚስገበገቡ’ መሆን የለባቸውም። (1 ጢሞቴዎስ 3:3, 8) በስግብግብነት ተነሳስቶ ያለ ኀፍረት ከፍተኛ ጥሎሽ የሚወስድ አንድ ክርስቲያን ከጉባኤ ሊወገድም ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 5:11, 13፤ 6:9, 10
ስግብግብነት በሚያስከትለው ውዝግብ የተነሳ አንዳንድ መንግሥታት በጥሎሽ ላይ ገደብ የሚያደርግ ሕግ ደንግገዋል። ለምሳሌ ያህል በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በቶጎ የወጣ አንድ ሕግ ጥሎሽ “በዕቃ ወይም በጥሬ ገንዘብ አሊያም ደግሞ በሁለቱም መልክ” ሊሰጥ እንደሚችል ከገለጸ በኋላ “ጥሎሹ በየትኛውም መልክ ይሰጥ ግን ከ10,000 F CFA (US$20.00) መብለጥ አይኖርበትም” ይላል። ክርስቲያኖች ሕግ አክባሪ ዜጎች መሆን እንዳለባቸው መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ይናገራል። (ቲቶ 3:1) መንግሥታት ያወጡትን እንዲህ ያለውን ሕግ ተከታትለው ባያስፈጽሙም እንኳ እውነተኛ ክርስቲያኖች መታዘዛቸውን ይቀጥላሉ። እንዲህ የሚያደርግ ክርስቲያን በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና ሊያተርፍና ሌሎችን ከማደናቀፍ ሊርቅ ይችላል።—ሮሜ 13:1, 5፤ 1 ቆሮንቶስ 10:32, 33
መደራደር ያለበት ማን ነው?
በአንዳንድ ባሕሎች ጥሎሽን በተመለከተ ድርድር የሚደረግበት መንገድ አስፈላጊ ከሆነ ሌላ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ይጋጫል። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የቤተሰብን ጉዳዮች በሚመለከት ኃላፊነት ያለበት አባትየው ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ቆላስይስ 3:18, 20) ስለሆነም በጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ የሚያገለግሉ ሁሉ ‘ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤት በመልካም የሚያስተዳድሩ’ ወንዶች መሆን ይገባቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 3:12 NW
ይሁን እንጂ የማጋባቱን ቅድመ ዝግጅት በአንድ ዘመድ የቤተሰብ ራስ በኩል ማስፈጸሙ በማኅበረሰቡ ዘንድ የተለመደ ነገር ሊሆን ይችላል። እነዚህ ዘመዶች ደግሞ ከጥሎሹ የተወሰነ መጠን እንዲሰጣቸው ይጠይቁ ይሆናል። ይህ በክርስቲያን ቤተሰቦች ላይ ፈተና ሊያስከትል ይችላል። አንዳንድ የቤተሰብ ራሶች ባሕል ነው በሚል የማያምኑ ዘመዶች ከፍተኛ የጥሎሽ ዋጋ አላግባብ እንዲወስዱ ይፈቅዱላቸዋል። ይህም አንዳንድ ጊዜ አንዲት ክርስቲያን የማያምን ሰው እንድታገባ ያደርጋታል። ይህ ደግሞ ክርስቲያኖች ‘በጌታ ብቻ’ ያግቡ ከሚለው ምክር ጋር ይጻረራል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) የማያምኑ ዘመዶች የልጆቹን መንፈሳዊ ደህንነት ጉዳት ላይ ሊጥል የሚችል ውሳኔ እንዲያደርጉ የሚፈቅድ የቤተሰብ ራስ ‘ቤተሰቡን በመልካም’ ያስተዳድራል ለማለት ያስቸግራል።—1 ጢሞቴዎስ 3:4 NW
ፈሪሃ አምላክ የነበረው የእምነት አባት አብርሃም እንዳደረገው አንድ ክርስቲያን አባት ከልጆቹ መካከል አንዱ ለሚፈጽመው ጋብቻ በሚደረገው ድርድር በቀጥታ ተካፋይ ባይሆንስ? (ዘፍጥረት 24:2–4) ጥሎሽን በሚመለከት ሌላ ሰው እንዲደራደር የተወከለ ከሆነ አንድ ክርስቲያን አባት ይህ የተወከለው ግለሰብ ምክንያታዊ ከሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማሙ መመሪያዎችን እየተከተለ መሆኑንና አለመሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል። ከዚህም በላይ ክርስቲያን ወላጆች ጥሎሽን በሚመለከት ምንም ዓይነት ድርድር ከማድረጋቸው በፊት ጉዳዩን አውጥተው አውርደው ሊያስቡበትና ምክንያታዊ ባልሆኑ ልማዶች ወይም ፍላጎቶች እንዳይሸነፉ ሊጠነቀቁ ይገባቸዋል።—ምሳሌ 22:3
ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ባሕርያትን ማስወገድ
ኩራትና ‘ያለኝ ይታይልኝ የሚል መንፈስ’ በመጽሐፍ ቅዱስ የተወገዘ ነው። (1 ዮሐንስ 2:16፤ ምሳሌ 21:4) ሆኖም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች ጋብቻን በማስመልከት በሚደረጉ ድርድሮች ረገድ እንደዚህ ዓይነት ባሕርያት አሳይተዋል። አንዳንዶች የሰጡት ወይም የተቀበሉት ከፍተኛ የጥሎሽ መጠን አጉል ይታይልን በማለት የዓለምን መንፈስ አንጸባርቀዋል። በሌላው በኩል ደግሞ በአፍሪካ የሚገኝ አንድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ሪፖርት እንዳደረገው “ቤተሰቦች አነስተኛ መጠን ያለው ዋጋ በሚጠይቁበት ጊዜ አንዳንድ ባሎች ሚስቶቻቸውን ‘በዶሮ’ ዋጋ የገዟቸው ያክል አድርገው በመመልከት አክብሮት ሳያሳዩ ቀርተዋል።”
አንዳንድ ክርስቲያኖች ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሎሽ ለማግኘት መስገብገባቸው አሳዛኝ ለሆነ ውድቀት ዳርጓቸዋል። ለምሳሌ ያህል ከሌላ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የተላከውን የሚከተለውን ሪፖርት ተመልከት:- “በአጠቃላይ ሲታይ ነጠላ ወንድሞች ትዳር መመሥረት በጣም ከባድ ሲሆንባቸው ነጠላ እኅቶች ደግሞ ለጋብቻ የሚጠይቃቸው የትዳር ጓደኛ አያገኙም። በዚህም ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ወንድሞችና እኅቶች የፆታ ብልግና በመፈጸም ከጉባኤ ይወገዳሉ። አንዳንድ ወንድሞች ወርቅ ወይም አልማዝ ሸጠው ትዳር ለመመሥረት የሚሆናቸውን በቂ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ማዕድን ወደሚወጣባቸው አካባቢዎች ይሄዳሉ። ይህ ደግሞ አንድ ወይም ሁለት ወይም ከዚያ የሚበልጡ ዓመታት ሊወስድባቸው ይችላል። በዚህ ጊዜ ከወንድሞችና ከጉባኤ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ስለሚቋረጥ ብዙውን ጊዜ በመንፈሳዊ የነበራቸው ጥንካሬ ይዳከማል።”
እንደዚህ ያሉ አሳዛኝ ሁኔታዎች እንዳይደርሱ ለመከላከል ክርስቲያን ወላጆች በጉባኤዎቻቸው ውስጥ ያሉ የጎለመሱ ሰዎችን ምሳሌ መከተል ይኖርባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ምንም እንኳ ወላጅ የነበረ ባይሆንም ከመሰል አማኞች ጋር የነበረው ግንኙነት ምክንያታዊ ነበር። በማንም ላይ ከባድ ሸክም ለመጫን አይፈልግም ነበር። (ሥራ 20:33) በእርግጥም ክርስቲያን ወላጆች ጥሎሽ መስጠትንም ሆነ መቀበልን በሚመለከት በሚደራደሩበት ጊዜ ጳውሎስ ያሳየውን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ምሳሌ መኮረጅ ይኖርባቸዋል። እንዲያውም ጳውሎስ የሚከተለውን እንዲጽፍ በመንፈስ ተገፋፍቶ ነበር:- “ወንድሞች ሆይ፣ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፣ እኛም እንደ ምሳሌ እንደምንሆንላችሁ፣ እንዲሁ የሚመላለሱትን ተመልከቱ።”—ፊልጵስዩስ 3:17
ምክንያታዊነትን በማሳየት በኩል የቀረቡ ምሳሌዎች
በርካታ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ለመዳር በሚደራደሩበት ጊዜ ምክንያታዊ በመሆን ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትተዋል። የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን የሆኑት ጆሴፍ እና ሚስቱ ማኢ ያደረጉትን ተመልከቱ።b የሚኖሩት ከሰሎሞን ደሴቶች በአንዷ ላይ ሲሆን በዚህች ደሴት የጥሎሽ ጉዳይ አንዳንድ ጊዜ አለመግባባት እንዲፈጠር ያደርጋል። እንዲህ ያለው ችግር እንዳይከሰት ለማድረግ ሲሉ ጆሴፍ እና ማኢ ሴት ልጃቸው ሄለን በጎረቤት ደሴት የሚኖር አንድ ሰው እንድታገባ ዝግጅት አደረጉ። ለሌላኛዋ ሴት ልጃቸው ለአስቴርም ያደረጉት ልክ እንደዚሁ ነበር። ጆሴፍ አማቹ ፒተር የከፈለውን መጠነኛ ከሚባለው በጣም ያነሰ ጥሎሽ ለመቀበል ፈቃደኛ ነበር። ጆሴፍ ለምን እንዲህ እንዳደረገ ተጠይቆ ሲመልስ “አቅኚ በሆነው በልጄ ባል ላይ ሸክም ልጭንበት ስላልፈለኩ ነው” በማለት አብራርቷል።
በአፍሪካ የሚኖሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችም ምክንያታዊ በመሆን ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። በዚያ አካባቢ የዋናውን ጥሎሽ መጠን ለመወሰን ድርድር ከመደረጉ በፊት አብዛኛውን ጊዜ ቤተ ዘመዶች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በቅድሚያ እንዲከፈላቸው ይጠይቃሉ። እንዲሁም ሙሽራዋን የማግኘቱን ሁኔታ አስተማማኝ ለማድረግ ሙሽራው የእጮኛው ታናሽ ወንድም ወደፊት ለማግባት ሲፈልግ የሚጠየቀውን ጥሎሽ እርሱ እንደሚሸፍንለት ቃል መግባት ይጠበቅበታል።
ኮሲ እና ሚስቱ ማራ ግን ምን እንዳደረጉ ተመልከቱ። በቅርቡ ሴት ልጃቸው ቤቦኮ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች አገባች። ጋብቻው ከመፈጸሙ በፊት ቤተ ዘመዶቻቸው ወላጆቿ ከሚያገኙት ጥሎሽ ድርሻችን ካልተሰጠን ብለው በጣም አስቸግረው ነበር። ሆኖም ወላጆቿ በአቋማቸው በመጽናት ጥያቄውን ሳይቀበሉ ቀሩ። ከዚያ ይልቅ የወደፊት አማቻቸውን በቀጥታ በማነጋገር ለሴት ልጃቸው አነስተኛ ጥሎሽ እንዲሰጥ ጠየቁት። ከዚያም ሙሽሮቹ ለሠርጋቸው ዝግጅት እንዲጠቀሙበት ግማሹን መልሰው ሰጧቸው።
በዚሁ አገር የምትኖረው ኢቶጎ የተባለች ወጣት ምሥክርም በምሳሌነት የምትጠቀስ ናት። ገና ከመጀመሪያው ወላጆቿ ምክንያታዊ የሆነ ጥሎሽ እንዲሰጣቸው ጠየቁ። ይሁን እንጂ ቤተ ዘመዶቻቸው ጥሎሹ በጣም አንሷል በማለት ተሟገቱ። ክርክሩ በጣም ተባባሰና እነዚህ ቤተ ዘመዶች ወደ ማሳመኑ ተቃረቡ። ምንም እንኳ ኢቶጎ በተፈጥሮዋ ዓይነ አፋር ብትሆንም ከተቀመጠችበት ብድግ አለችና ቀደም ሲል በተደረገው ስምምነት መሠረት ሳዛ የተባለውን ቀናተኛ ክርስቲያን ለማግባት የወሰነች መሆኗን በአክብሮት ገለጸች። ከዚያም በድፍረት “እምቤኬ” (ማለትም “በቃ አለቀ”) አለችና ተመልሳ ቁጭ አለች። ሳምቤኮ የተባለችው ክርስቲያን እናቷም ከእርሷ ጎን የቆመች መሆኗን አረጋገጠች። ከዚያ በኋላ ተጨማሪ ውይይት ሳይደረግ ቀደም ሲል በተደረገው ስምምነት መሠረት እጮኛማቾቹ ተጋቡ።
አፍቃሪ ክርስቲያን ወላጆች በጥሎሽ ከሚያገኙት የግል ጥቅም ይልቅ የሚያሳስቧቸው ሌሎች ነገሮች አሉ። በካሜሩን የሚኖር አንድ ባል እንዲህ በማለት ያብራራል:- “ለመስጠት ያሰብኩት ጥሎሽ ምንም ይሁን ምን አማቴ ልጅዋን ለመንከባከብ እንድጠቀምበት ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ትነግረኝ ነበር።” አፍቃሪ ወላጆች ሌላ የሚያሳስባቸው ነገር የልጆቻቸው መንፈሳዊ ደህንነት ነው። ለምሳሌ ያህል በዚምባብዌ የሚኖሩትንና አብዛኛውን ጊዜያቸውን የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ የሚያሳልፉትን ፍሪን እና ሩዶን እንውሰድ። ደሞዝተኞች ባይሆኑም እንኳ ሁለት ሴት ልጆቻቸውን የዳሩት ብዙውን ጊዜ ከሚጠየቀው በጣም ባነሰ ዋጋ ነው። እንዲህ ያደረጉበት ምክንያት ምንድን ነው? ሴት ልጆቻቸው ይሖዋን ከልባቸው የሚወዱ ወንዶችን በማግባት እንዲጠቀሙ ስለፈለጉ ነው። “ከሁሉም ይበልጥ ከፍ አድርገን የምንመለከተው የልጆቻችንና የልጆቻችን ባሎች መንፈሳዊነት ነው” በማለት ተናግረዋል። እንዴት ደስ የሚል ነው! ትዳር ለያዙ ልጆቻቸው መንፈሳዊና ሥጋዊ ደህንነት የሚጨነቁ ወላጆች በጣም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።
ምክንያታዊ መሆን የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
በሰሎሞን ደሴት የሚኖሩት ጆሴፍ እና ማኢ የሴት ልጆቻቸውን ጋብቻ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ማስፈጸማቸው በረከት አስገኝቶላቸዋል። በዚህም የተነሳ አማቾቻቸውን በዕዳ ከመዘፈቅ አድነዋል። እንዲያውም ሁለቱም ባለ ትዳሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በመሆን የመንግሥቱን መልእክት በማሰራጨቱ ሥራ በርካታ ዓመታት ለማሳለፍ ችለዋል። ጆሴፍ የሆነውን ነገር በማስታወስ እንዲህ ይላል:- “እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ ያደረግነው ውሳኔ ከፍተኛ በረከት አስገኝቶልናል። ሁኔታውን ያልተረዱ ሰዎች አልፎ አልፎ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድሩብን እንደነበረ እሙን ነው፤ ሆኖም ልጆቼ በይሖዋ አገልግሎት ተጠምደው ጠንክረው ሲሠሩ በመመልከቴ ጥሩ ሕሊናና የመንፈስ እርካታ አስገኝቶልኛል። እኛም ሆንን እነርሱ በጣም ደስተኞች ነን።”
ሌላው ጥቅም ደግሞ በአማቶች መካከል ጥሩ ግንኙነት እንዲሰፍን ማድረጉ ነው። ለምሳሌ ያህል ዞንዲ እና ሲቡሴሶ በሥጋ እህትማማች ከሆኑ ሚስቶቻቸው ጋር ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው ዚምባብዌ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ያገለግላሉ። የሚስቶቻቸው አባት ዳክሪ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ በመሆኑ ደሞዝ የሚያስገኝለት ሥራ የለውም። ጥሎሽን በሚመለከት ድርድር ሲደረግ ለመስጠት የሚችሉትን ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ገለጸላቸው። “አማቻችንን በጣም እንወደዋለን። በማንኛውም በሚያስፈልገው ነገር ሁሉ እርሱን ለመርዳት የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን” በማለት ዞንዲ እና ሲቡሴሶ ይናገራሉ።
አዎን፣ ጥሎሽን በተመለከተ ድርድር በሚደረግበት ጊዜ ምክንያታዊ መሆን ለቤተሰብ ደስታ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ለምሳሌ ያህል አዲስ ጎጆ ወጪዎቹን በዕዳ ከመዘፈቅ ስለሚያድናቸው ከትዳር ሕይወት ጋር በቀላሉ ይላመዳሉ። ይህም በርካታ ወጣት ባልና ሚስቶች አጣዳፊ በሆነው በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈልን የመሰሉ መንፈሳዊ በረከቶችን እንዲከታተሉ ያስችላቸዋል። ይህ ደግሞ በምላሹም አፍቃሪ የጋብቻ መሥራች ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ክብር ያመጣለታል።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በአንዳንድ ባህሎች ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው። ጥሎሽ የሚሰጡት የሙሽራዋ ወላጆች ናቸው።
b በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን ሰዎች ስሞች ቀይረናቸዋል።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ጥሎሹን እንዳለ መለሱላቸው
በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ጥሎሹ አነስተኛ ከሆነ ሙሽራይቱና የሙሽራይቱ ወላጆች ይናቃሉ። ስለሆነም አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ የጥሎሽ ዋጋ እንዲጠየቅ ምክንያት የሚሆነው ኩራትና የቤተሰብን ትልቅነት የማሳየት ውስጣዊ ምኞት ነው። በሌጎስ ናይጄሪያ የሚኖር አንድ ቤተሰብ ከዚህ በጣም የተለየ ነገር አድርጓል። ደለ የተባለው አማቻቸው እንዲህ በማለት ሁኔታውን ያብራራል:-
የባለቤቴ ቤተሰቦች ውድ ቅያሪ ልብሶችን መግዛትን ከመሳሰሉት ከአካባቢው ባሕል ጋር ከተያያዙ ለጥሎሽ ከሚወጡ ወጪዎች አሳርፈውኛል። ቤተሰቦቼ ጥሎሽ ለመስጠት በሄዱ ጊዜ የሚስቴ ቤተሰቦች የወከሉት ሰው ‘ይህችን ልጅ የምትወስዷት እንደ ሚስት አድርጋችሁ ነው ወይስ እንደ ልጃችሁ?’ በማለት ጠየቀ። ቤተሰቦቼም ‘እንደ ልጃችን አድርገን ልንወስዳት ነው የመጣነው’ በማለት በአንድ ድምፅ መለሱ። ከዚያም ጥሎሹን የወሰድንበትን ፖስታ ሳይከፍቱት እንዳለ መለሱልን።
“አማቾቼ ለሰርጋችን ያደረጉልንን ነገር እስከ ዛሬ ድረስ አልረሳውም። ለእነርሱ ከፍተኛ አክብሮት እንዲኖረኝ አድርጎኛል። ግሩም የሆነው መንፈሳዊ አመለካከታቸው የቅርብ ዘመዶቼ አድርጌ እንድመለከታቸው አድርጎኛል። ለባለቤቴ ልዩ አመለካከት አንዲኖረኝ በማድረግ ረገድ ያሳደረው ተጽዕኖም ቀላል አይደለም። እነሱ ለእኔ ያደረጉልኝ ነገር ለእርሷ ጥልቅ የሆነ አድናቆት እንዲያድርብኝ አድርጓል። በአንዳንድ ጉዳዮች ሳንስማማ ስንቀር ሁኔታው እንዲባባስ አልፈቅድም። ቤተሰቦቿ ትዝ ስለሚሉኝ አለመግባባቱ በቀላሉ ይፈታል።
“የእኔና የእርሷ ቤተሰቦች የጠበቀ ወዳጅነት መሥርተዋል። ይኸው ከተጋባን ከሁለት ዓመት በኋላ እንኳን አባቴ ለሚስቴ ቤተሰቦች ስጦታዎችና እህል ይልካል።”