ፍቅር ተገቢ ያልሆነ ቅናትን ድል ያደርጋል
“ፍቅር አይቀናም።”—1 ቆሮንቶስ 13:4
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ፍቅርን በተመለከተ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ነገር ምንድን ነው? (ለ) አፍቃሪና ቀናተኛ መሆን ይቻላልን? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
ፍቅር እውነተኛ ክርስትና ተለይቶ የሚታወቅበት ምልክት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:35) ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተነሣስቶ ፍቅር ክርስቲያናዊ ግንኙነትን እንዴት ሊነካ እንደሚገባ አብራርቷል። ጳውሎስ ከጻፋቸው ነገሮች መካከል “ፍቅር አይቀናም” የሚለው ይገኝበታል።—1 ቆሮንቶስ 13:4
2 ጳውሎስ እነዚህን ቃላት የጻፈው ተገቢ ያልሆነ ቅናትን ለማመልከት ነበር። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ ለዚሁ ጉባኤ “በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁ” ብሎ ሊጽፍ አይችልም ነበር። (2 ቆሮንቶስ 11:2) ‘አምላካዊ ቅናቱ’ የተነሣሣበት ጉባኤውን በበከሉ ሰዎች ምክንያት ነው። ይህም ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ብዙ ፍቅራዊ ምክር የያዘውን ሁለተኛ መልእክቱን ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንዲጽፍ ገፋፍቶታል።—2 ቆሮንቶስ 11:3–5
ቅናት በክርስቲያኖች መካከል
3. በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መካከል ቅናትን የሚመለከት ችግር የተፈጠረው እንዴት ነበር?
3 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈላቸው የመጀመሪያ መልእክቱ ላይ እነዚህ አዳዲስ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ስምምነት እንዳይኖራቸው ያገዳቸውን ችግር መፍታት ነበረበት። ‘በአንድ ሰው በመመካት ሌላውን ሰው ግን በመናቅ’ አንዳንድ ሰዎችን ከፍ ከፍ ማድረግ ጀምረው ነበር። ይህም ጉባኤው አንዱ “እኔ የጳውሎስ ነኝ”፣ ሌላው “እኔስ የአጵሎስ ነኝ” ሌላው ደግሞ “እኔ ግን የኬፋ ነኝ” በማለት እንዲከፋፈል አድርጎ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:12፤ 4:6 የ1980 ትርጉም) ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ የችግሩን መንስኤ ሊረዳ ችሏል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንደ “መንፈሳውያን” ሰዎች ሳይሆን ሥጋዊ አስተሳሰብ እንዳደረባቸው ሰዎች ዓይነት ባሕርይ አሳይተው ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ “ገና ሥጋውያን ናችሁ።. . . ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን?” በማለት ጻፈላቸው።—1 ቆሮንቶስ 3:1–3
4. ጳውሎስ እርስ በርሳቸው ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው ወንድሞቹን ለመርዳት ምን ምሳሌ ተጠቅሟል? ከምሳሌው ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?
4 ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጉባኤው ውስጥ ያሉ የተለያዩ ሰዎች ላላቸው ተሰጥኦዎችና ችሎታዎች ትክክለኛ አመለካከት እንዲይዙ ረድቷቸዋል። “አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው?” በማለት ጠየቃቸው። (1 ቆሮንቶስ 4:7) ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 12 ላይ የጉባኤው አባላት ልክ እንደ እጅ፣ ዓይንና ጆሮ ያሉ የተለያዩ የአካል ክፍሎች እንደሆኑ ገለጸ። አምላክ የተለያዩ የአካል ክፍሎችን የሠራቸው እርስ በርስ እንዲደጋገፉ አድርጎ እንደሆነ ጠቆማቸው። በተጨማሪም ጳውሎስ “አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 12:26) በአሁኑ ወቅት ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ማዋል አለባቸው። አንድ ሰው በተሰጠው ሥራ ወይም በአምላክ አገልግሎት ባከናወናቸው ነገሮች ከመቅናት ይልቅ ከዚያ ሰው ጋር መደሰት ይኖርብናል።
5. በያዕቆብ 4:5 [አዓት] ላይ ምን ነገር ተገልጿል? ቅዱሳን ጽሑፎች የእነዚህን ቃላት እውነትነት የሚያጎሉት እንዴት ነው?
5 እንዲህ ብሎ መናገር በተግባር ከመግለጽ ይልቅ ቀላል እንደሆነ የታወቀ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ በማንኛውም ኃጢአተኛ ሰው ውስጥ ስለሚገኘው “የቅናት ዝንባሌ” ጽፏል። (ያዕቆብ 4:5 አዓት) የመጀመሪያው ሰብዓዊ ሞት የተከሰተው ቃየን ተገቢ ላልሆነው ቅናቱ ስለተንበረከከ ነበር። ፍልስጥኤማውያን ይስሐቅን ያሳደዱት እየጨመረ ይሄድ በነበረው ሀብቱ ቀንተው ነበር። ራሔል እህትዋ ብዙ ልጆችን በመውለዷ ምክንያት ቀንታ ነበር። የያዕቆብ ልጆች ያዕቆብ ለታናሽ ወንድማቸው ለዮሴፍ የተለየ ፍቅር ስለ ነበረው ቀንተው ነበር። ሚርያም እስራኤላዊ ባልሆነችው የወንድሟ ሚስት ሳትቀና አልቀረችም። ቆሬ፣ ዳታንና አቤሮን በቅናት ተገፋፍተው በሙሴና በአሮን ላይ አሢረዋል። ንጉሥ ሳኦል ዳዊት ባገኛቸው ወታደራዊ ድሎች ቀንቶ ነበር። በተጨማሪም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በተደጋጋሚ ጊዜያት ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሚሆን እንዲከራከሩ ያደረጋቸው ቅናት እንደነበር አያጠራጥርም። ፍጹም ያልሆነ ማንኛውም ሰው መጥፎ ከሆነው “የቅናት ዝንባሌ” ነፃ እንዳልሆነ ይህ ሐቅ ያሳያል።—ዘፍጥረት 4:4–8፤ 26:14፤ 30:1፤ 37:11፤ ዘኁልቁ 12:1, 2፤ 16:1–3፤ መዝሙር 106:16፤ 1 ሳሙኤል 18:7–9፤ ማቴዎስ 20:21, 24፤ ማርቆስ 9:33, 34፤ ሉቃስ 22:24
በጉባኤ ውስጥ
6. ሽማግሌዎች የቅናትን ዝንባሌ መቆጣጠር የሚችሉት እንዴት ነው?
6 ሁሉም ክርስቲያኖች ምቀኝነትና ተገቢ ያልሆነ ቅናት እንዳያሳዩ መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል። ይህም የአምላክ ሕዝብ ጉባኤዎችን በእንክብካቤ እንዲይዙ የተሾሙ የሽማግሌዎች አካላትን ይጨምራል። አንድ ሽማግሌ ራሱን ዝቅ የማድረግ መንፈስ ካለው ከሌሎች ሽማግሌዎች ልቆ ለመታየት ጥረት አያደርግም። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሽማግሌ የተለየ የማደራጀት ወይም የሕዝብ ንግግር የመስጠት ችሎታዎች ካሉት ሌሎቹ ሽማግሌዎች ለጉባኤው በረከት እንደሆነ አድርገው በመመልከት በነገሩ ይደሰታሉ። (ሮሜ 12:15, 16) አንድ ወንድም የአምላክ መንፈስ ፍሬዎችን በሕይወቱ ውስጥ እያፈራ መሆኑን በማሳየት ጥሩ እድገት እያደረገ ሊሆን ይችላል። ሽማግሌዎች ብቃቶቹን በሚመለከቱበት ወቅት እሱን ለዲቁና ወይም ለሽምግልና ላለማጨት አንዳንድ ጥቃቅን ጉድለቶችን አጉልተው እንዳይመለከቱ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ይህ ፍቅር ማጣትንና ምክንያታዊ አለመሆንን ያሳያል።
7. አንድ ክርስቲያን አንድ ዓይነት ቲኦክራሲያዊ ሥራ ሲሰጠው ምን ችግር ሊፈጠር ይችላል?
7 አንድ ሰው ቲኦክራሲያዊ ሥራ ወይም መንፈሳዊ በረከት ሲያገኝ ሌሎች በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሰዎች እንዳይቀኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ብቃት ያላት እህት ከሌሎች ይበልጥ ብዙ ጊዜ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሠርቶ ማሳያዎችን እንድታቀርብ ትፈለግ ይሆናል። ይህ ነገር አንዳንድ እህቶችን ሊያስቀናቸው ይችላል። በፊልጵስዩስ ጉባኤ ውስጥ በነበሩት በኤዎድያን እና በሲንጤኪ መካከል የነበረው ችግር ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሊሆን ይችላል። በዘመናችን የሚገኙት እንደነዚህ ያሉት ሴቶች ትሑት እንዲሆኑና “በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ” ሽማግሌዎች በደግነት ማበረታቻ እንዲሰጧቸው ያስፈልግ ይሆናል።—ፊልጵስዩስ 2:2, 3፤ 4:2, 3
8. ቅናት ወደ የትኞቹ የኃጢአተኝነት ተግባራት ሊመራ ይችላል?
8 አንድ ክርስቲያን በአሁኑ ወቅት በጉባኤ ውስጥ መንፈሳዊ መብቶች በማግኘት የተባረከ ሰው ቀደም ሲል ስሕተት እንደሠራ ሊያውቅ ይችላል። (ያዕቆብ 3:2) በቅናት ተነሣስቶ ስለዚህ ጉዳይ ለሌሎች ሊናገርና ይህ ሰው በጉባኤ ውስጥ የተሰጠውን ሥራ አጠያያቂ ሊያደርገው ይችላል። ይህ “የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል” ከተባለለት ፍቅር ጋር ይቃረናል። (1 ጴጥሮስ 4:8) የቅናት ወሬ የጉባኤውን ሰላም ሊያውክ ይችላል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል፦ “መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፣ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፣ የሥጋ ነው፣ የአጋንንትም ነው።”—ያዕቆብ 3:14, 15
በቤተሰብህ ውስጥ
9. የትዳር ጓደኛሞች የቅናት ስሜቶችን መቆጣጠር የሚችሉት እንዴት ነው?
9 ብዙ ጋብቻዎች የሚፈርሱት ተገቢ ባልሆነ ቅናት ምክንያት ነው። የትዳር ጓደኛን አለማመን ፍቅር አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 13:7) በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የትዳር ጓደኛ ሌላው የተሰማውን ቅናት ላይረዳ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ሚስት ባሏ ለሌላ ሴት የሚሰጠው ትኩረት ሊያስቀናት ይችላል። ወይም ደግሞ አንድ ባል ሚስቱ የተቸገሩ ዘመዶቿን ለመንከባከብ የምታጠፋው ጊዜ ሊያስቀናው ይችል ይሆናል። የትዳር ጓደኛሞች በእንደነዚህ ዓይነቶቹ ስሜቶች ቅር ተሰኝተው ዝም ዝም ሊባባሉና ችግሩን በሚያባብስ መንገድ ብስጭታቸውን ሊገልጹ ይችላሉ። ከዚህ ይልቅ ቅናት ያደረበት የትዳር ጓደኛ የሐሳብ ግንኙነት መስመሩን ክፍት ማድረግና የሚሰማውን ስሜት በግልጽ መናገር ያስፈልገዋል። ሌላው የትዳር ጓደኛም በአጸፋው ችግሩን እንደተረዳ ማሳየትና ፍቅሩን ማረጋገጥ ይኖርበታል። (ኤፌሶን 5:28, 29) ሁለቱም ቅናት ከሚፈጥሩ ሁኔታዎች በመራቅ የቅናት ስሜቶችን መቀነስ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ አንድ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች የአምላክን መንጋ በእረኝነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን ለመወጣት የጉባኤው አባላት ለሆኑ ሴቶች የተወሰነና ተገቢ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ሚስቱ እንድትገነዘብ መርዳት ያስፈልገው ይሆናል። (ኢሳይያስ 32:2) እርግጥ አንድ ሽማግሌ ለቅናት ምክንያት የሚሆን ምንም ነገር እንዳያደርግ መጠንቀቅ አለበት። ይህን ማድረግ ከትዳር ጓደኛው ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠንከር ከእርሷ ጋር የተወሰነ ጊዜ በማሳለፍ ሚዛናዊ መሆንን ይጠይቅበታል።—1 ጢሞቴዎስ 3:5፤ 5:1, 2
10. ወላጆች የቅናት ስሜቶችን እንዲቋቋሙ ልጆቻቸውን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?
10 በተጨማሪም ወላጆች ተገቢ ያልሆነ ቅናት ምን እንደሆነ እንዲገነዘቡ ልጆቻቸውን መርዳት ያስፈልጋቸዋል። ልጆች ብዙውን ጊዜ ወደ ድብድብ የሚያመሩ ንትርኮች ውስጥ ይገባሉ። አብዛኛውን ጊዜ የዚህ መንስኤ ቅናት ነው። እያንዳንዱ ልጅ የተለያዩ ፍላጎቶች ስላሉት ልጆች በአንድ ዓይነት መንገድ ሊያዙ አይችሉም። ከዚህም በላይ ልጆች እያንዳንዳቸው የተለያየ ጠንካራና ደካማ ጎን እንዳላቸው መረዳት ያስፈልጋቸዋል። አንድ ልጅ ሁልጊዜ እንደ ሌላው ልጅ አድርጎ እንዲሠራ ማበረታቻ የሚሰጠው ከሆነ ይህ ሁኔታ በአንዱ ውስጥ ምቀኝነት በሌላው ውስጥ ደግሞ ኩራት ሊያሳድርበት ይችላል። ስለዚህ ወላጆች እርስ በርሳቸው በመፎካከር ሳይሆን በአምላክ ቃል ውስጥ የሰፈሩትን ምሳሌዎች በመመልከት እድገታቸውን እንዲለኩ ልጆቻቸውን ማሠልጠን አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ” ይላል። ከዚህ ይልቅ “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፣ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል።” (ገላትያ 5:26፤ 6:4) ከሁሉም በላይ ደግሞ ክርስቲያን ወላጆች ዘወትር በሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ጥሩና መጥፎ ምሳሌዎች በማጉላት ልጆቻቸውን መርዳት ያስፈልጋቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:15
ቅናትን በቁጥጥራቸው ሥር ያዋሉ ምሳሌዎች
11. ሙሴ ቅናትን በመቆጣጠር ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሆነው እንዴት ነው?
11 የሥልጣን ጥመኞች ከሆኑት የዚህ ዓለም መሪዎች ጋር በሚጻረር መንገድ ‘ሙሴ በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ።’ (ዘኁልቁ 12:3) ሙሴ እስራኤላውያንን ብቻውን መምራት ሲያቅተው ይሖዋ ሙሴን ለመርዳት እንዲችሉ ኃይል በመስጠት በ70 ሌሎች እስራኤላውያን ላይ መንፈሱ እንዲሠራ አደረገ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ሁለቱ እንደ ነቢያት ትንቢት ሲናገሩ ኢያሱ ይህ ነገር ለሙሴ አመራር የሚሰጠውን ትኩረት የሚቀንስ ሆኖ ተሰማው። ኢያሱ ሰዎቹን ሊከለክላቸው ፈለገ፤ ይሁን እንጂ ሙሴ በትሕትና “የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፣ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያወርድ፤ አንተ ስለ እኔ ትቀናለህን?” አለው። (ዘኁልቁ 11:29) አዎን፣ ሙሴ ሌሎች ሰዎች የአገልግሎት መብቶችን ሲቀበሉ ይደሰት ነበር። በቅናት ራሱ ብቻ እንዲከበር አልፈለገም።
12. ዮናታንን ከቅናት እንዲርቅ ያስቻለው ነገር ምንድን ነው?
12 ፍቅር ሊፈጠር የሚችለውን ተገቢ ያልሆነ የቅናት ስሜት በማሸነፍ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የእስራኤላዊው ንጉሥ የሳኦል ልጅ የነበረው ዮናታን ነው። ዮናታን ከአባቱ ቀጥሎ ዙፋኑን መውረስ የሚችልበት መስመር ላይ ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ የእሴይ ልጅ ዳዊትን የሚቀጥለው ንጉሥ እንዲሆን መርጦት ነበር። ብዙዎች በዮናታን ቦታ ቢሆኑ ኖሮ እንደ ተቀናቃኛቸው አድርገው በመመልከት በዳዊት ላይ ይቀኑበት ነበር። ይሁንና ዮናታን ለዳዊት የነበረው ፍቅር እንደዚህ ዓይነቱ ቅናት እንዳይቆጣጠረው ጠበቀው። ዳዊት የዮናታንን ሞት ሲሰማ “ወንድሜ ዮናታን ሆይ፣ እኔ ስለ አንተ እጨነቃለሁ፤ በእኔ ዘንድ ውድህ እጅግ የተለየ ነበር፤ ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ግሩም ነበረ” ሊል ችሎ ነበር።—2 ሳሙኤል 1:26
ከሁሉ የላቁ ምሳሌዎች
13. በቅናት ረገድ ከሁሉ የተሻለ ምሳሌ የሆነው ማን ነው? ለምን?
13 ይሖዋ ተገቢ የሆነውን ቅናት እንኳ በመቆጣጠር ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ነው። እንደነዚህ ያሉትን ስሜቶች ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር ያውላቸዋል። ማናቸውም ኃይለኛ የሆነ የመለኮታዊ ቅናት መግለጫ ምን ጊዜም ቢሆን ከአምላክ ፍቅር፣ ፍትሕና ጥበብ ጋር የሚስማማ ነው።—ኢሳይያስ 42:13, 14
14. ኢየሱስ ከሰይጣን ጋር በሚጻረር መንገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል?
14 የቅናት ስሜትን በመቆጣጠር ረገድ ሁለተኛው የላቀ ምሳሌ የአምላክ ውድ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ “በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም።” (ፊልጵስዩስ 2:6) ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ የሆነው የሥልጣን ጥማት ያለው መልአክ ከተከተለው መንገድ ጋር ምንኛ ፈጽሞ የሚጻረር ነገር ነው! ሰይጣን ራሱን ይሖዋን የሚቃወም ተቀናቃኝ አምላክ በማድረግ እንደ ‘ባቢሎን ንጉሥ’ ሁሉ በቅናት ‘በልዑል ለመመሰል’ ተመኘ። (ኢሳይያስ 14:4, 14፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4) እንዲያውም ሰይጣን ኢየሱስ ‘ወድቆ እንዲሰግድለት’ ለማድረግ ሞክሮ ነበር። (ማቴዎስ 4:9) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለይሖዋ ሉዓላዊነት ራሱን በትሕትና ከማስገዛት ምንም ነገር ዘወር ሊያደርገው አልቻለም። ከሰይጣን ጋር በሚጻረር መንገድ ኢየሱስ “የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፣ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት [“በመከራ እንጨት ላይ ለመሞት” አዓት] እንኳ የታዘዘ ሆነ።” በመሆኑም ኢየሱስ የዲያብሎስን የኩራትና የቅናት ድርጊት ሙሉ በሙሉ ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ የአባቱን ሕጋዊ የሆነ የመግዛት መብት ደግፏል። ኢየሱስ ታማኝ በመሆኑ ምክንያት “እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፣ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።”—ፊልጵስዩስ 2:7–11
ቅናትህን በቁጥጥር ሥር ማዋል
15. የቅናት ስሜቶችን ለመቆጣጠር ንቁ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
15 ክርስቲያኖች እንደ አምላክና እንደ ክርስቶስ ፍጹማን አይደሉም። ኃጢአተኞች ስለሆኑ አንዳንድ ጊዜ መጥፎ የቅናት ስሜት አንድ ዓይነት እርምጃ እንዲወስዱ ሊገፋፋቸው ይችላል። ስለዚህ በአንድ አነስተኛ ጉድለት ወይም ስሕተት ነው ብለን ባሰብነው ነገር ምክንያት በቅናት ተገፋፍተን የእምነት ወንድማችን የሆነን ሰው ከመተቸት ይልቅ “እጅግ ጻድቅ አትሁን፣ እጅግ ጠቢብም አትሁን፣ እንዳትጠፋ” በሚሉት በመንፈስ አነሣሽነት በተጻፉ ቃላት ላይ ማሰላሰላችን በጣም አስፈላጊ ነው።—መክብብ 7:16
16. በዚህ መጽሔት አንድ የቆየ እትም ላይ ቅናትን በተመለከት ምን ጥሩ ምክር ተሰጥቶ ነበር?
16 በመጋቢት 15, 1911 የወጣው መጠበቂያ ግንብ ቅናትን በተመለከተ እንዲህ በማለት አስጠንቅቆ ነበር፦ “ለጌታ በጣም ልንቀና ቢገባንም የሌላ ክርስቲያን ድካም ማንም ሰው ጣልቃ ሊገባበት የማይገባ የግል ጉዳይ መሆኑን እርግጠኞች መሆን አለብን፤ በተጨማሪም ‘በሌላ ሰው ጉዳይ’ ውስጥ የማንገባ መሆናችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል። ከዚህም ሌላ ችግሩን ሽማግሌዎች ሊፈቱት የሚገባ መሆኑን ወይም የግድ ወደ ሽማግሌዎች መሄድ እንዳለብን ወይም እንደሌለብን መመርመር ያስፈልገናል። ሁላችንም ለጌታና ለጌታ ሥራ ከፍተኛ ቅናት ሊኖረን ይገባል፤ ይሁን እንጂ መጥፎ ዓይነት ቅናት እንዳናሳይ እጅግ እንጠንቀቅ።. . . በሌላ አነጋገር በሌላ ሰው መቅናት የለብንም፤ ከዚህ ይልቅ ለጥቅሞቹና ለደኅንነቱ በማሰብ ለዚያ ሰው መቅናታችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል።”—1 ጴጥሮስ 4:15
17. ከመጥፎ የቅናት ተግባራት መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?
17 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከኩራት፣ ከቅናትና ከምቀኝነት መራቅ የምንችለው እንዴት ነው? መፍትሔ ልናገኝ የምንችለው የአምላክ መንፈስ በሕይወታችን ውስጥ ምንም ሳያግደው በቀላሉ እንዲፈስስ ስናደርግ ነው። ለምሳሌ ያህል የአምላክን መንፈስ ለማግኘትና መልካም ፍሬዎቹን ለማሳየት እንድንችል እርዳታ ለማግኘት መጸለይ ያስፈልገናል። (ሉቃስ 11:13) በጸሎት በሚከፈቱትና የአምላክ መንፈስና በረከት ባለባቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይኖርብናል። ከዚህም በተጨማሪ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ያስፈልገናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በተጨማሪም በአምላክ መንፈስ ኃይል በሚሠራው በመንግሥቱ ስብከት ሥራ መሳተፍ አለብን። (ሥራ 1:8) በችግር የተደቆሱ መሰል ክርስቲያኖችን መርዳትም ሌላው የአምላክ መንፈስ አስተሳሰባችን እንዲለወጥ የሚያደርግበት መንገድ ነው። (ኢሳይያስ 57:15፤ 1 ዮሐንስ 3:15–17) የአምላክ ቃል “በመንፈስ ተመላለሱ፣ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ” ስለሚል እነዚህን ክርስቲያናዊ ግዴታዎች በሙሉ በቅንዓት መፈጸማችን ከመጥፎ የቅናት ተግባራት ይጠብቀናል።—ገላትያ 5:16
18. ተገቢ ካልሆነ ቅናት ጋር ለዘላለም ስንታገል የማንኖረው ለምንድን ነው?
18 ፍቅር ከአምላክ የመንፈስ ፍሬዎች ውስጥ በአንደኝነት ተጠቅሷል። (ገላትያ 5:22, 23) የፍቅርን ባሕርይ ማዳበራችን በአሁኑ ወቅት ያሉብንን የኃጢአተኝነት ዝንባሌዎች እንድንቆጣጠራቸው ይረዳናል። ይሁን እንጂ የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞልናል? በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ አገልጋዮች ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ለመድረስ የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ በሚችሉባት በመጪዋ ምድራዊት ገነት ውስጥ ሕይወት የማግኘት ተስፋ አላቸው። በዚያች አዲስ ዓለም ውስጥ “ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት” ስለሚደርስ ፍቅር ይሰፍንና ማንኛውም ሰው ተገቢ ላልሆነ የቅናት ስሜቶች መገዛቱ ይቀራል።—ሮሜ 8:21
የምናሰላስልባቸው ነጥቦች
◻ ጳውሎስ ቅናትን ለማዳከም የሚረዳ ምን ምሳሌ ተጠቅሟል?
◻ ቅናት የጉባኤውን ሰላም ሊያደፈርስ የሚችለው እንዴት ነው?
◻ ወላጆች ቅናትን እንዲቋቋሙ ልጆቻቸውን ሊያሠለጥኗቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ ከመጥፎ የቅናት ተግባራት መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቅናት የጉባኤውን ሰላም እንዲያደፈርስ አትፍቀዱ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆች ልጆቻቸው ቅናትን እንዲቋቋሙ ሊያሠለጥኗቸው ይችላሉ